በኢትዮጵያ የፈርኒቸርና የቤተ ውበት ኢንዱስትሪ መስክ በሚፈለገው ልክ ያልተስፋፋ ከመሆኑም በላይ ዘርፉ ለሆቴሎችና ለመዝናኛ ስፍራዎች ብቻ የተፈቀደ ይመስል ተረስቶ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት በመንግስት እና በግለሰቦች ዘንድ ዘርፉን ለማነቃቃት በተሰሩ የተለያዩ ስራዎች የቤተ ውበት ሙያ ትኩረት እያገኘና ቤትን በደመቀና በተለየ ሁኔታ የማስዋብ ሂደት ልምድ እየሆነ መምጣቱ ግልፅ ነው።
በአሁን ወቅት በአገሪቷ እየታየ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ተከትሎ የማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ወደ ዘመናዊነት እየተሸጋገር መጥቷል። በተለይም በከተሞች የሚስተዋለው ፈጣን የግንባታ እንቅስቃሴ የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበት መገልገያዎችን እና ተያያዥ የግንባታ አጨራረስ ምርቶችን በስፋት የሚጠይቅ በመሆኑ ኢንቨስትመንትና የንግዱ ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተስፋፍቷል። ከዚህም ባለፈ የሆቴል፣ የቢሮ፣ የንግድ ቤቶች ቁሳቁሶችን ከማሟላት በተጨማሪም ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
መንግስት የአገሪቱን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት ለመደገፍ የግሉ ዘርፍ ትልቅ ሚና እንዳለው የገለፁት የፕራናይቬንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መስራችና ባለቤት አቶ ነብዩ ለማ ናቸው። አቶ ነብዩ፤ የተለያዩ ዘርፍ ተኮር የሆኑ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀት የንግድ ትስስርን ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂና ግብዓቶችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም በዘርፉ ተዋንያኖች መካከል የእርስ በእርስ መስተጋብር እንዲፈጠር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።
የአገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራት እንዲችሉ የተለያዩ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት በተለይም በፈርኒቸር ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ድርጅቶች በጋራ መስራት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል የሚሉት አቶ ነብዩ፤ ሌሎች ድርጅቶችም ከዚህ በመማር በጋራ ሰርተው ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ያስረዳሉ። በመሆኑም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች በአገሪቷ መካሄዳቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ከማበርከቱም ባለፈ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የኢኮኖሚ መናሐሪያ ማድረግ እንደሚቻል ይገልጻሉ።
“ሁሉም ዘርፎች ማደግና መለወጥ አለባቸው” የሚሉት አቶ ነብዩ፤ ዘርፎቹን በማሳደግ ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ ቴክኖሎጂ፣ ዕውቀትና ግብዓት ወሳኝ መሆናቸውን ይገልፃሉ። አቅራቢዎችን አምራቾችን እና አጠቃላይ የዘርፉ ባለሙያዎችን ማቀራረብና በአንድ ጣሪያ ሰር ማሰባሰብ የሚቻለው የተለያዩ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት ነው። ስለዚህ የዘርፉን ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲሰሩ በማድረግ ዘርፉን ማሳደግ ይቻላል በማለት ምክረ ሀሳብ ይለግሳሉ።
ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀት ከአስር በላይ የሆኑ ዘርፎችን በማስተዋወቅ የንግድ ትስስሩ ጠንካራ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ነብዩ፤ እንደ አገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ድርጅቱ ትኩረት የተሰጣቸውን ዘርፎች ለማሳደግ ወሳኝ የሆኑትን ቴክኖሎጂ፣ ዕውቀትና ግብዓቶች እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከኤክስፖርቱ በበለጠ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ከቱሪዝም ዘርፉ የተገኘ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በፈርኒቸር ስራ የተሰማራችው የእሌኒ ፈርኒቸር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወጣት እሌኒ ገብረእግዚአብሔር፤ የፈርኒቸር ምርቶችን በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ በማመረት ስራ ላይ ከተሰማራች ሶስት ዓመታትን አስቆጥራለች። እሌኒ ለአራት ቋሚ ሰራተኞች የስራ ዕድል በመፍጠር የምትሰራ ሲሆን፤ የሆቴል ዕቃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ፈርኒቸሮችን ማለትም አልጋ፣ ቁምሳጥን፣ የምግብ ጠረጴዛ፣ መደርደሪያና የመሳሰሉትን አምርታ ለገበያ ታቀርባለች።
በፈርኒቸር ስራ ላይ ለመሰማራት ከመንግስት ብድር ማግኘቷን የምትገልፀው እሌኒ፤ በተለያየ ጊዜ በሚዘጋጁ ኤግዚቢሽኖችም አምራቾች ያለምንም ክፍያ ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ እንዲችሉ መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ትናገራለች። ይሁንና በአሁን ወቅት የመሸጫ ቦታ እጥረት ያለባት መሆኑን በመግለፅ፤ መንግስት ድጋፍ ቢያደርግላት የበለጠ በመስራት ወደፊት ትልቅ ማምረቻ ድርጅት ለመክፈት እቅድ እንዳላት ትገልፃለች።
አብዛኛው ህብረተሰብ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን የመግዛት ዝንባሌው ደካማ መሆኑን የገለፀችው እሌኒ፤ በአገር ውስጥ የሚመረቱት የቤተ ውበት ዕቃዎች አገር በቀል በሆኑ ዋንዛ፣ ወይራና ቀረሮ ከተባሉ ዛፎች በመሆኑ ጥራት ያላቸውና ጠንካራ ምርቶች ናቸው። ነገር ግን ህብረተሰቡ ከአገር ውስጥ ምርቶች ይልቅ የውጭ አገር ምርቶችን ይመርጣል። ስለዚህ “ማህበረሰቡ ወደ ውጭ ከመመልከት ይልቅ ወደ ውስጥ ቢመለከትና አምራቾቹን ቢያበረታታ ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት ይቻላል›› በማለት ሀሳቧን ቋጭታለች።
የኢቲ መባቻ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አክሊለ በለጠ፤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. 2018 የአሥር ቢሊዮን ብር የፈርኒቸር ግዥ የፈጸመች ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ አምራቾች 20 በመቶ ያህሉን ብቻ በመግዛት 80 በመቶው ከተለያዩ አገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የገባ መሆኑን በማስታወስ፤ አገር በቀል ድርጅቶችን መደገፍ እንደሚገባ ያብራራሉ። በዚህም ድርጅቶቹን ከመንግስት አካላት ጋር በማገናኘት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ በውጭ ምንዛሪ ማስገኘትም ሆነ፤ ጠንካራ የንግድ ትስስር በመፍጠር አገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን ማሳደግ እንደሚቻል ይናገራሉ።
በወርልድ ባንክ በተደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ለፈርኒቸር ምርት ግብዓት የሚውል መጠነ ሰፊ የሆነ የደንና የቀርከሃ ሀብት ያላት መሆኑን ያስታወሱት አቶ አክሊለ፤ ጥራትን በመጨመር ብክነትን በማስወገድና በተሳለጠ የንግድ ሰንሰለት ወደ አምራቹ የማይደርስ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም በቀርከሃ ምርት ከአንድ ሺህ በላይ ምርቶችን ማምረት የሚቻል መሆኑን የጠቆሙት አቶ አክሊለ፤ በቻይናውያኑ ቀርከሃን በስፋት የሚጠቀሙበት መሆኑን ገልፀዋል።
የቀርከሃ ምርት በኢትዮጵያ 67 በመቶ ወይም 10 ቢሊዮን ብር ማንቀሳቀስ ከመቻሉም በላይ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የሚችል የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑን ያብራራሉ። በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚታዩ ግዙፍና በርካታ ግንባታዎች የፈርኒቸር ምርቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ከውጭ አገራት የሚያስገቡ መሆናቸውን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ አገር በቀል ፈርኒቸር አምራቾችን ማበረታታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
ፍሬህይወት አወቀ