ማህበረሰባዊ እይታና ልማድ በፈጠረው ተፅዕኖ የሚፈተኑት ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ በፈጠራና ምርምር ዘርፍ ተሳትፎዋቸው አነስተኛ ነው።በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምርና የፈጠራ ስራ የሚሰሩት ሴት ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ለዚህ ማሳያ ነው። አሁን ላይ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
የእንስቶች ማህበራዊ እውቂያ የሰፋ ስለሆነ የሚሰሯቸው የምርምርና የፈጠራ ስራዎች የህብረተሰቡ ችግር ከስር መሰረቱ ሊቀርፉ የሚችሉ ናቸው። የዛሬ ሳይንስ አምድ እንግዳዎቻችን ሶስት ሆነው እንደ አንድ በማሰብ በምርምር ስራ ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን ስራ ምንነትና የፈጠራ ስራቸው አጠቃላይ ሁኔታ ምንነት በዚህ መልኩ አሰናድተን አቅርበናል፡፡
ሀሲና አሊ፤ ሰብለወንጌል የቻለ፤ ሐረገወይን መኮንን ይባላሉ። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ የትምህርት ክፍል በጋራ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባደረጉት ምርምር ከውጪ የሚመጣውን ለማጣበቂያነት የሚያገለግለውን የኮላ ምርት በሀገር በቀል እጽዋት በማምረት መተካት ችለዋል። ወጣቶቹ በእለት እለት እንቅስቃሴያቸው ካጋጠማቸው ችግር በመነሳት መፍትሔ ለማበጀት በማሰብ ባደረጉት ጥናትና ምርምር ያገኙት ውጤት ይበል የሚያስኝ ነው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኦርጋኒክ ኬሚስትሪ ተማሪዎች የነበሩት እነዚህ ሦስት እንስቶች ከትምህርታቸው ጋር ተያያዥነት ያለውን የምርምር ስራ በመስራት፤ከውጪ በሚገባው ኮላ ምርት የሚወጣው የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት፤ ከውጭ ከሚገባው ኮላ ምርት ጋር የሚስተካከል ኮላ ከሀገር በቀል እጽዋት በማምረት መላ መዘየድ ችለዋል።
ለፈጠራ ስራቸው መነሻ የሆነው ሀሳብ የመነጨው የሦስተኛ ዓመት ተማሪዎች እያሉ ነበር። በሚማሩበት ወቅት የሚገለገሉባቸው ደብተሮችና መጽሐፍት ለማጣበቅ ኮላ እንጠቀም ነበር የሚትለው ሀሲና አሊ፤ ኮላ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ በመሆኑ እንደልብ ማግኘት ይከብድ ነበር። ይህንን ለመቅረፍ አቅሙ ስላለን ለምን በሰፊው አንስራበትም በማለት ተመካክረው ለመስራት እንደተስማሙ ትናገራለች። ይህ አጋጣሚ ለምርምር ስራቸው ምክንያት ሆኖ ወደ ኮላ ምርት አሸጋገራቸው።
የፈጠራ ስራዎች
የጓደኛሞቹ የግል ፈጠራ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል ኮላ ሲሆን የፈጠራ ስራቸው በተፈጥሮ ከሚገኙ እጽዋቶች እንደ ቁልቋል፤ ቅንጭብ፤ ደም ካላቸው አበባዎች ለማጣበቂያነት የሚያገለግል ኮላ ነው፡፡
የፈጠራ ስራው ለየት የሚያደርገው
የእንስቶቹ የፈጠራ ውጤት የሆነው ኮላ በአካባቢያቸው ከሚገኙ ቁሳቁሶች በቀላሉ የሚመረት በመሆኑ በገበያ ላይ ካለው ምርት ይለያል። ከዚህ በፊት በሀገራችን ኮላ አይመረትም። ከውጪ የሚመጣውም በዶላር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ነው። በዚህ ምርት በሀገር በቀል እጽዋት የመተካት ስራን ሰርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኮላው የተመረተው በተፈጥሮ ከሚገኙ እጽዋቶች በመሆኑ ለጤናም ጎጂ አይደለም። ነገር ግን ከዚህ በፊት ከውጪ የሚገባው ኮላ ኬሚካል ይጨመርበታል። የምርምር ውጤታቸው የሆነው ኮላ የማጣበቅ ኃይሉም ከውጪ ከሚመጣው ጋር ሲነጻጸር እኩል ነው።
የፈጠራ ስራው ጠቀሜታ አሁን ያለበት ደረጃ
ኮላ ለኢንዱስትሪዎች፤ ለጣውላ ቤቶች፤ ለትምህርት ቤቶች፤ ለተለያዩ ግልጋሎቶች ይውላል። እንስቶቹ ስራቸውን ለማስተዋወቅ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ። በጎንደር በዩኒቨርስቲ ውስጥ ለሚገኙ ትምህርት ክፍሎች ለሙከራ በመስጠት እንዲሞክሩት አድርገን ውጤታማ መሆን ችለዋል፡
ይህ ስራ ህብረተሰቡ ዘንድ ድረስ ተጠቃሚ ለማድረስ ከትምህርት ጋር ስላልቻሉ በሚቀጥለው በሰፊው ለመስራት ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የፈጠራ ስራው ያስገኘው እውቅና ሽልማት
እነዚህ እንስቶቹ በስራዎቻቸው የፈጠራ ባለቤትነት መብት ከአእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት፤ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ /ስኮላርሺፕ/ ነጻ የትምህርት እድል አግኝተዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ሽልማት የእውቅና ሰርተፍኬትና የብር ሜዳሊያ ሽልማት አግኝተዋል። ዘንድሮ በተካሄደው የአፍሪካ ኢኖቬሽን ሳምንት ላይ በመሳተፍ የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተዋል፡፡
የፈጠራው ስራ ያጋጠሙ ፈተና
እነ ሀሲና በተማሪነታቸው ለምርምርና ፈጠራ ስራዎች የሚያገለግሉት ማቴሪያሎች እጥረት መኖሩ ከባድ ፈተና ነው። ለዚህ ፈጠራ ስራቸው የተጠቀሙበትን ማቴሪያሎች በዩኒቨርሲቲ በማመቻቸት እገዛ ያደረገላቸው መሆኑን ጠቁማለች። ለፈጠራ ስራው የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመመካከር እንዲፈታላቸው ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። እንደ ማቀዝቀዛ /ፍሪጅ/፣ ትልቅ የውሃ ማሞቂያ/ቦይለር/ እንዲሁም ለመዘፍዘፊያነት የሚያገለግሉ ሰፊ እቃዎች ለስራቸው አስፈላጊ መሆናቸውን ትናገራለች።
የእንስቶቹ ህልም የተሻሉ ስራዎችን በመስራት የራሳቸውን አሻራ ማስቀመጥ፤ ለፈጠራ ስራቸው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን በአንድ ላይ አድርጎ የሚያዘጋጅና የሚያሟላ ማሽን ለማሰራት የዲዛይን ስራው እየሰሩ ይገኛሉ። ለወደፊቱ የፈጠራ ስራቸውን ከዳር በማድረስ ኮላ ሀገር ውስጥ በማምረት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ማድረግ፤ ሀገሪቱም ከውጪ የምታስገባቸውን የኮላ ምርት በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ በማዳን ሀገርን የሚጠቅም ስራ ለመስራት አቅደዋል፡፡ የታታሪ እንስቶች እቅድ ከዚህም ከፍ ይላል።
ስራቸው በሰፊው ለመቀጠል የመስሪያ ቁሳቁሶችን በማምረትና በማሟላት ለመስራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ማሽን በመሟላት የተለያዩ ጥረቶች እንደሚያደርጉ የናገራሉ። ለእነዚህ ነገ የሀገር ተሰፋ የሆኑ ወጣት እንስቶች ህልማቸውን እውን ለማድረግ ይችሉ ዘንድ የምርምር ግኝታቸው በማበረታተት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ማበረታቻ ሊያደርላቸው ይገባል። በተጨማሪም የፈጠራ ስራቸው ለህብረተሰቡ እንዲደርስና ጥቅም ላይ እንዲውል ቢደረግ የውጪ ምንዛሬ የመቀነስ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 30/2012
ወርቅነሽ ደምሰው