ሌሊቱ ተጋምሶ ንጋቱ እስኪቃረብ ዕንቅልፍ በአይኗ አይዞርም።ጨለማው ገፎ ብርሀን እኪታይም ትዕግስት ይሉትን አታውቅም። በሀሳብ ውጣ ውረድ ስትጨነቅ ያደረችበትን ጉዳይ ልትከውን ፈጥና ከመኝታዋ ትነሳለች።የቤት የጓዳ ጣጣዋ ደግሞ በቀላሉ የምትተወው አይደለም።ለልጆቿ ቁርስ ማዘጋጀት፣ አባወራዋን መሸኘትና የጎደለውን ሁሉ ማሟላት የእሷ ኃፊነት ይሆናል።
ለወይዘሮ ብዙነሽ እሸቴ ይህ አይነቱ ልፋትና ከባድ ሸክም የየዕለት ግዴታዋ ከሆነ ከራርሟል።እርሷ ሁሌም ቢሆን ያሰበችውን ከውና ከዳር እስክታደርስ እፎይታ ተሰምቷት አያውቅም፤ስራ የሚወዱ ሻካራ እጆቿና መሮጥ የለመዱ ፈጣን እግሮቿም ለደቂቃ ዕረፍትን አይሹም። ከዚህ እውነት በስተጀርባ በእርሷና መሰሎቿ የላብ ወዝ፣በትከሻቸው ብርታትና ጥንካሬ የሚለካ አንድ ውጤት አለ።
ወይዘሮዋን ከሞቀ ዕንቅልፏ ቀስቅሶ ከጨለማው የሚያጋፋትን ሀቅ ጠንቅቃ ታውቀዋለች።ከቤት ያሉ ልጆቿዋን ሸንግላ ወደ ሌሎች የሚያፈጥናትን ሩጫም አታጣውም።ይህን ስታስብ የእርሷን መድረስ የሚናፍቁ የበርካታ ነፍሶች ገጽታ ውል ይልባታል። ስለእነሱ የተረከበችው ታላቅ ኃላፊነትና ከውጤቱ ጀርባ የሚኖራት እርካታም ዘወትር በትጋት እንድትበረታ አጽንቷታል።
ብዙነሽና ሌሎች እናቶች በማኅበር ተደራጅተው ተማሪዎችን መመገብ ከጀመሩ ጊዜያት ተቆጥረዋል። ምግቡ ተዘጋጅቶ ከአፍ እስኪደርሰም የሁሉም እናቶች ድርሻና ኃላፊነት በእጅጉ የላቀ ነው።ውሎው ተጠናቆ ምሽቱ እስኪለያቸው እያንዳንዳቸው ለቆሙለት ዓላማ እረፍት የላቸውም።
ዘወትር የሚከፍሉት ዋጋ የበዛ ቢሆንም ስለነገው ደግሞ በድካም ሰበብ ቦዝነው አያውቁም። ተማሪዎቹን ለመመገብ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን ለማሟላትም ዕድሉን ለገበያ ግዢ አሳልፈው አይሰጡም።ለእነርሱ በርበሬና ሽሮን በአግባቡ ቀምሞ ማዘጋጀት ሁሌም ቢሆን የሚጠበቅባቸው ግዴታ ነው።ሁሌም እንደ እህትማማቾች ተሳስበውና ተመካክረው የድርሻቸውን ይወጣሉ።
ማለዳ ገበያ ወጥቶ እህል መሸመቱ፣አትክልት ተራ መግባቱ፣መዋከቡ የእናቶቹ የየዕለት ህይወት ነው።ድካማቸው በእፎይታ ትንፋሽ ተቋጭቶ አያውቅም።አካል በድካም እየዛለም ቢሆን ለቀጣዩ ግዳጅ መሰለፉ አይቀሬ ይሆናል።
ሽንኩርት መላጡ፣ በኩንታል የሚመዘን ድንችና ካሮት ከትፎ ማዘጋጀቱ፣ጥሬ እህልን ለቅሞና አጥቦ ማስጣጣቱ ሁሉ በእነርሱ ትከሻ ላይ ይከወናል።ሁሌም እንጀራ በማገዶ የመጋገር ኃላፊነቱም በትከሻቸው የወደቀ ተግባር ነው።
እኛም ምግብ የሚዘጋጅበትን ማዕድ ቤት ለመቃኘት ወደውስጥ ዘለቅን።ከመስኮት አልባው ምድጃ የሚትጎለገለው ጥቁር ጭስ መድረሻ ቢያሳጣን ፈጥነን ወደኋላ ተመለስን።የቦታው መጥበብ የሥፍራው አለመመቸትና ጥበት እያስገርመን ‹‹እንዴት?›› የሚል ጥያቄ አጫረብን።
በስራ ደፋ ቀና የሚሉት እናቶች ግን ከጭሱ እየታገሉ የዘወትር ውሏቸው ይህን እንደሚመስል ነገሩን።ጣራውን ቀና ብለን አስተዋልነው።አሮጌና ለአደጋ የተጋለጠ ነው።በዚህ ስፍራ በኤሌክትሪክ መጠቀም ብሎ ነገር አይታሰብም።ለቦታው ጥበት ደጁን እንደአማራጭ የሚያበስሉበት ሌሎች እናቶች ደግሞ ከንፋስ እየተጣሉ እንጨቱን ለማንደድ እየታገሉ ነው።
በማህበር የተደራጁት አስራ ስድስቱ እናቶች በመስከረም አጸደ ህጻናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች የቁርስና ምሳ ምገባን ያከናውናሉ። የእናትነት ፍቅራቸውን ሲለግሱም በተለየ የትህትና አቀባበል ነው።
እናቶቹ በግቢው ያሉትን ልጆች ሁሉ እንደ ራሳቸው ልጆች ይቆጥራሉ።አልፎ አልፎ የባህሪይ ስብራት ቢያዩባቸው እንኳን ባዕድነት ይዟቸው አይከፉም። ልጆቹም ቢሆኑ እናቶቻቸው ከሞሰብ ቆርሰው የሚያጎርሷቸውን ያህል የግቢውን እናቶች እጅ ይናፍቃሉ።
የምገባው ሰአት ደርሶ የትኩስ ወጥ ሽታ ግቢውን ማወድ ሲጀምር ተማሪዎች የምሳ ሰሀኖቻቸውን ይዘው በሥርዓት ይሰለፋሉ። በአግባቡ ተዘጋጅቶ የሚቀርብላቸውን ትኩስ ምግብ ይዘውም በአንድ ይታደማሉ።ይህኔ ልጆቹ በአግባቡ ስለመብላታቸው የሚቃኙ እናቶች እየዞሩ ያረጋግጣሉ።ገሚሶቹም ከጓዳ ሆነው አቅርቦቱን ያሟላሉ።
በርካቶቹ ያለአንዳች ልዩነት በአንድ የመመገባቸው አጋጣሚ አብሮነታቸውን አጣምሮታል።ዛሬ ላይ ማናቸውም የሌላቸውን የምግብ ቋጠሮ አሻግረው አይቃኙም። እኩል በልተው እኩል ጠግበው ይነሳሉ።
የዛሬን አያድርገውና ከአንድ አመት በፊት የመስከረም ትምህርት ቤትን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎች ይህን ዓይነቱ ልምድ አልነበረም።ምሳ ዕቃቸው በምግቦች ተሞልቶ ጠግበው የሚደፉ የመኖራቸውን ያህል ይቀምሱት አሮባቸው በረሃብ አንጀት ተምረው የሚመለሱ ተማሪዎች ጥቂት አልነበሩም።
አሁን ግን ያለፈ ክፉ ትዝታ ሆኗል።ዛሬን በአንድ ገበታ መሰባሰባቸውም በርካቶችን ከረሀብ ጉዳት ታድጎ ለውጤታማ ትምህርት እያበቃ ነው።በዚሀ የምገባ ሰርአት በሌላ ትምህርት ቤት የሚማሩ የእርሷን ልጆች ጨምሮ ብዙዎቹ ወላጆች ተጠቃሚ መሆናቸውን ብዙነሽ ትናገራለች ።ለዚህም ለመንግስት ያላት ምስጋና ከቃላት በላይ ነው።
አንዳንዴ ግን በግቢው የእነርሱን ድካምና ልፋት ከፈተና የሚጥል አጋጣሚ አይታጣም። አንዳንድ ወላጆች ስለሚቀርበው ምግብ ደጋግመው ቅሬታቸውን ያሰማሉ።ጥቂቶቹም‹‹ልጆቻችን ይህን አይመገቡም።›› ሲሉ ምሳ ዕቃ አስቋጥረው ይልካሉ።ይህ አይነቱ መገለል የማይመቻቸው ተማሪዎች ግን ከቤት የያዙትን ምግብ ትተው ከጓደኞቻቸው ጋር ይታደማሉ።የሚዘጋጀውን በአንድ ቆርሰውም ተደስተው ይውላሉ።
ትምህርት ቤቱ አጸደ ህጻናትን ያካተተ እንደመሆኑ ለልጆቹ የተለየ ትኩረት ይሰጣል።የህጻናቱን ፍላጎትና የአመጋገብ ባህርይ በመጠነ መልኩም ምግቡ በጥንቃቄ ይዘጋጃል።በተለየ ፍቅርና እንክብካቤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ለማድረግም ተችሏል።
ወይዘሮ ዓለም ጥሩነህ የአራት ልጆች እናት ነች። በትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን የተማሪዎች ምገባ ከሚያካሂዱት መሀል አንዷ እንደመሆኗ ዘወትር በትጋት ውስጥ ትመላለሳች። ዘንድሮ በተጀመረው የተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብር ከመሰል አጋሮቿ ጋር ተደራጅታ መስራቷ የመንፈስ እርካታን ሰጥቷታል።ዘወትር ከልጆች ጋር መዋሏና እነርሱን በሀላፊነት መንከባከቧም ለእሷ የተለየ ትርጉም አለው።
ትምህርት ሳይጀመር በፊት ተማሪዎቹ ቁርስ መብላት አለባቸውና ጨለማውን ጥሳ በፍጥነት ትገሰግሳለች። በስፍራው ከሚጠብቋት ባልንጀሮቿ ተዳምራም ትኩስና ያልበረደ ቁርስ ለማድረስ ትጣደፋለች።
በእነወይዘሮ ዓለም ዘንድ ቅዳሜና ዕሁድ እንደ እረፍት ቀናት ታስቦ አያውቅም።ለሰኞ ስራ ደግሞ ግቢውን በማጽዳት፣ እንጀራ በመጋገርና ስፍራውን በማዘጋጀት ያሳልፋሉ።እንዲህ መሆኑም በየዕምነት ስፍራቸው በአግባቡ እንዳይሄዱና ዘመድ አዝማድን እንዳይጠይቁ ጭምር ተጽዕኖ ፈጥሯል።ያም ቢሆን ግን ‹‹ከልጆቻችን በልቶ ማደር አይበልጥም።›› ሲሉ እውነታውን የሚቀበሉት ከልባቸው ነው።
ዓለም እንደምትለው፤ስራው እጅግ አድካሚና እረፍት የለሽ የሚባል ነው።በተለይ በየቀኑ ሲደጋገም በእጅጉ ሊያሰለችና ሊያማርር ይችላል።እርሷና ባልደረቦቿ ግን ሁሌም ስለልጆቹ ጉዳይ አበክረው ያስባሉ። እነርሱን በአዕምሯቸው እየሳሉም ለስራ ይዘጋጃሉ።ይህም ጥንካሬና ብርታት ሆኖ ነገን አዲስ ሆነው ይነቃሉ።
በትምህርት ቤቱ ያሉ ተመጋቢ ተማሪዎች ፍቅርና አክብሮት ያሳያሉ።አልፎ አልፎ ግን አንዳንድ ወላጆች ካላቸው የግንዛቤ ችግር ልጆቹ ዘወትር ዕንቁላልና ስጋ ተመጋቢዎች እንዲሆኑ ይሻሉ።በዚህ ሳቢያም መጋቢ እናቶቹን እስከመቃወም ይደርሳሉ።ይህ ሁሉ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚገምቱት ትዕግስተኞቹ እናቶች ግን ሁሉን በፈገግታ ተቀብለው ስራቸውን ይቀጥላሉ። የትምህርት ቤቱ መምህራን በጎነትና ቅን አስተሳሰብ አቅም ሆኗቸውም ለነገው ዛሬን ለመበርታት ይተጋሉ።
መምህር ጣዕመ ካሳዬ በመስከረም አጸደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህራን ልማት ምክትል ርዕሰ መምህር ናቸው።በትምህርት ቤቱ ምገባው ከተጀመረ አንስቶ በቅርብ ያሉ እማኝ ናቸውና በተማሪዎቹ በልቶ መዋል ደስተኛ ሆነዋል።
መምህር ጣዕመ መርሀግብሩ ሲታሰብ አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችል በቂ አቅርቦት እንደሌለው ያውቃሉ።የውሀና የኤሌክትሪክ፣የማብሰያና የዕቃ ማዘጋጃ በሌለበት እናቶቹ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያደርጉትን ብርቱ ጥረት ያደንቃሉ።
ጎዶሎን ለመሙላት በሚደረገው ርብርቦሽም የግቢው መምህራን የአቅማቸውን ሲያደርጉ በተለየ ፍላጎት ነው። ብዙ ጊዜ ለማብሰያ እንጨት ሲቸግር የግቢው ማህበረሰብ በአካባቢው ተዘዋውሮ ከየተቋማቱ እንጨት ለምኖ ያመጣል።ይህ መደረጉ የተማሪዎቹ ምገባ በየምክንያቱ እንዳይቋረጥ ለማድረግ ሲባል ነው።የምሳ ሰአት ሲደርስም መምህራኑ የራሳቸውን ትተው ለእነርሱ ቅድሚያ በመስጠት ሲያስተባብሩ ይቆያሉ። እንዲህ መሆኑም የመጋቢ እናቶቹን ድካም ተጋርቶ ሳይበሉ እንዲጠግቡ ያደርጋቸዋል።
መምህር ጣዕመ የእናቶቹን ያልተመቸ አገልግሎት አሰጣጥ በቅርብ ሆነው ይታዘባሉ።ስለልጆች ፍቅር ሲሉ የሚከፍሉትን መሰዋዕትነትም በእጅጉ ያስገር ማቸዋል።የተማሪዎችን ባህሪይ ተቋቁመው፣ የአንዳንድ ወላጆችን ያልተገባ ድርጊት ታግሰው ስለነገው በብርታት መቆማቸው እነርሱን በየቀኑ እንዲያከበሩ አስገድዷቸዋል።
በትምህርት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ርዕሰ መምህር ተወካይ መምህር ልዑልሰገድ ሰይፉም፣ በየቀኑ የሚያስተውሉት የመጋቢ እናቶቹ መልካምነት ያስገርማቸዋል።ከዚህ ቀደም በትምህርት ቤቱ ይታዩ ከነበሩ አሳዛኝ አጋጣሚዎች አኳያም የምገባ ሥርዓቱ ታላቅ ጠቀሜታን ሰንቋል ባይ ናቸው።
የዛኔ ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች በምግብ እጦት ምክንያት በየክፍሉ ይወድቁ ነበር።ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ ከአጉል መንፈስ ጋር ስለሚያያዝ ችግራቸውን በወጉ ተረድቶ የሚደርስላቸው አልነበረም።መምሀር ልዑልሰገድ ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአንዲት ተማሪ ላይ ያጋጠመውን አሳዛኝ ታሪክ ሁሌም አይዘነጉትም።
ተማሪዋ ከችግረኛ እናቷ ጋር እየኖረች በባዶ ሆዷ ትምህርት ቤት ትመጣ ነበር።ምሳ የቋጠሩ ተማሪዎች በልተው ሲውሉም እሷ ያለአንዳች ምግብ በርሀብ አንጀቷ ወደ ቤቷ መሄድ ልምዷ ሆኖ ቆይቷል።ወላጅ እናቷ በርኀብ ምክንያት በሞት እስክትለያትም ምስጢሩ አልታወቀም።ቆይቶ ግን መምህራን ባደረጉት የራሳቸው ጥረትና እገዛ ልጅቷ ወተትና ዕንቁላል እየተመገበች ትምህርቷን እንድትቀጥል መደረጉን ያስታውሳሉ።
እንደእርሳቸው ዕምነት፤የምገባውን ስርአት መንግስት መተግበሩ መምህራንን ጭምር ከሰቆቃ ታድጓል። ብዙዎቹን ጠንካራ ተማሪዎች ለማድረግ አስተዋጽኦው የላቀ ነው።በትምህርት ቤቱ የጎዳና ልጆችን ጨምሮ በድህነታቸው ከሚታወቁ ወላጆች የመጡ ተማሪዎችና በሌሎች እገዛ የሚያድጉ ጭምር ይገኙበታል።
መምህሩ እንደሚሉት፤ለሌሎች መኖር ድካም ልፋታቸውን ለሚገብሩ እናቶች የሚደረገው ምቹ የስራ ቦታዎች መፈጠር የግድ ይላል።ዛሬን በጥንካሬ ያለፉ እናቶች ነገን በዚህ መንገድ ይቀጥላሉ ለማለት የሚያስችል ባለመሆኑም ወላጆችን በማወያያት መፍትሄ የመፈለግ ሙከራው ተጀምሯል።ጉዳዩን በዋንኛነት ከያዘው ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመጻጻፍም መፍትሄ እንዲፈለግለት የማድረጉ ጥረት በመጠናከር ላይ ነው። ይህ ዕውን እንዲሆንም ሁሉም እንደ አንድ አንዱም እንደብዙ ሆኖ ትብብሩን ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2012
መልካምስራ አፈወርቅ