ሴቶች ወደ ማጀት በሚባልበት ማህበረሰብ ውስጥ አድገው ያለውን የስራ ጫና ተቋቁመው ለስኬት የበቁት ጥቂት ሴቶች ናቸው። እነዚህም ቢሆኑ የኑሮን ዳገት ቧጠው በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ አሁን ያሉበትን የተስፋ ብርሃን ለማየት ችለዋል። ዛሬ ስኬት ማማ ላይ ሆነው ያሳለፉትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለተመለከተ የማያልፍ ነገር እንደሌለ መገንዘብ አያዳግተውም። የከፈሉት ዋጋ ከባድ ነው። ይህ ደግሞ የተፈተኑበትን የህይወት ውጣ ውረድ በአሸናፊነት እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ትጋታቸው፣ ጥንካሬያቸውና ስኬታቸው ለሌሎች ሴቶች ተምሳሌት ሆኖ የሚታይ ነው።
ሴቶች ከማይደፍሯቸው የስራ ዘርፎች አንዱ የሳይንስ ትምህርት ነው። ከኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት ውስጥ ግማሹን የሚይዙት ሴቶች ናቸው። አሁን አሁን መንግስት እና መሰል አካላት በጉዳዩ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል። ይህም ሆኖ ግን በዘርፉም የተሰማሩት ቁጥር አነስተኛ ነው። በዚህ መስክ ላይ ደፍረው የገቡት ሴቶች ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተጠቃሽ የሆኑ ውጤቶችን እያስመዘገቡ የሚገኙም ብርቱዎች ግን አልጠፉም።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በተሳት ፏቸው ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙ ሴቶች አንዷ የሆኑት የዛሬ እንግዳችን ናቸው። ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ፀጋዬ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቪርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ላብራቶሪ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርትና ተመራማሪ ናቸው ። እኚህ ውጤታማ ሴት ለዚህ ስኬት የበቁት ህይወት አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ሳይሆን በርካታ መሰናክሎችን በማለፍ ነው። እንደ ሴትነታቸው ያለባቸውን ድርብ ድርብርብ ኃላፊነት በመላና በብልሃት በማለፍ ያነገቡትን ዓላማ ማሳካት ችለዋል። የህይወት ልምዳቸው ለሌሎች ሴቶች የሚጠቅም ነውና ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርገን የህይወት ተሞክሯቸውን ከዚህ እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀረብን። መልካም ንባብ!
ትውልድና እድገት
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ፀጋዬ የተወለዱት አዳማ ከተማ ነው። ቤተሰቦቻቸው በስራ ምክንያት ወደ ሐረር ከተማ ተዘዋወረው ኑሯቸውን እዚያው በማድረጋቸው እድገታቸው በዚያው ሊሆን ቻለ። ትምህርታቸውን ከቄስ ትምህርት ጀምሮ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የፍቅር ከተማ እየተባለች በምትጠራዋ ሀረር ጨርሰዋል። በመሀል በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ እንደገና በአዳማ ከተማ በመመለስ ለተወሰነ ጊዜ አጼ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ተምረውም ነበር።
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ፤ ለዛሬ ማንነታቸው መሠረት የሆናቸው የቄስ ትምህርት ቤት መምህራቸው የነበራቸው ጥንካሬ ነበር። ‹‹መምህሩ ሁለት ክፍል በማስተማር አቦጊዳውንም መልእክተንም በአንድ ላይ ያስቆጥሩ ነበር። ባንዴ ሁሉም ቦታ የመገኘታቸው ጥንካሬ ውስጤ ዘልቆ ገባ። አቦጊዳ የቻለ ተማሪ ሌላውን ስለሚያስተምር ከህጻንነት ጀምሮ ነው አስተማሪ መሆን የቻልኩበት። የቄስ ትምህርት ቤት በራስ መተማመን ፈጥሮልኛል›› ይላሉ መለስ ብለው ስለ ሁኔታው ሲያስታውሱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውም ሴቶች ብቻ በሚማሩበት ወይዘሮ የሺ እመቤት ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን ከቄስ ትምህርት ቤት መምህራቸው ቀጥሎ የአሁን ማንነታቸው ያነፀው ያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤታቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ለዛሬ ህልማቸው እውን መሆን አጋዥ የሆኗቸው የአማርኛ መምህራቸው ነበሩ። ‹‹ የአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ምን መሆን ትፈልጋለችሁ? ሲባል “እኔ ነርስ” አልኩ። ሴት ነርስ ብቻ የምትሆን ይመስለኝ ስለነበር። መምህሯ ግን “ዶክተር መሆን ትችያለሽ ‘’ አለችኝ። ሴትም ዶክተር መሆን ትችላለች ለካ የሚለው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአእምሮዬ ተቀረጸ›› ሲሉ የህይወት መስመራቸውን ስለወሰነው አጋጣሚ ይናገራሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራኖቻቸው እንዲሁም ሌሎች የስራ አጋሮቻቸው አርአያ ሆነዋቸው ህልማቸውን እውን ለማድረግ እንዳገዛቸው ይጠቅሳሉ።
ቆይታ በዩኒቨርስቲ
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ታዲያ ከልጅነታቸው ጀምሮ ሀኪም የመሆን ራዕይ ሰንቀዋል ። በተጨማሪም በልጅነታቸው በአካባቢያቸው ላይ ይመለከቱት የነበረውን የስጋ ደዌ ህሙማንን የማከምና የመንከባከብ ፍላጎታቸውን ለማሳካት በይበልጥ ወደ ህክምናው ለመሳብ ተገደዋል። ሆኖም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ክፍል ተመደቡ። ምርጫ ስላልነበራቸው የስነህይወት ትምህርት ተምረው እንደ ጨረሱ ይናገራሉ።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከትምህርት ገበታቸው እስከመባረር ያደረሰ ፈተና ገጥሟቸው ነበር። የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ ታላቅ ወንድማቸው የመኪና አደጋ ይደርሰበታል። ሙሉ ፖራላይዝ በመሆኑ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለዓመት ከስድስት ወራት በመተኛቱ በቤተሰብ ላይ ያልተጠበቀ ምስቅልቅልን ያለ የፈተና ጊዜ ሆነባቸው። እሳቸውም ወንድማቸውን በማስታመም ደፋ ቀና ሲሉ ትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ ገና ከጅምሩ ከዩኒቨርሲቲ አንደኛ ዓመት ትምህርታቸው ተባረሩ። በልጅነታቸው የደረሰባቸውን ፈተና መቋቋም አልቻሉም ። ‹‹ በኔ የደረሰው ፈተና ለሌሎች ትምህርት ይሆን ዘንድ ሁሌም ለተማሪዎቼ እነግራቸዋለሁ። ችግር ሲደርስብኝ እኔ ላይ ሁሉም ችግሮች የተከመሩብኝ ነው የመሰለልኝ ። ከዚያም ከትምህርቴ ተባረርኩኝ ። ጠቅልዬ ወንድሜን ወደ ማስታመም ገባሁ›› በማለት ጊዜውን ያስታውሱታል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር፤ ተመልሰው እንደገና ወደ ትምህርት ለመግባት ተቸግረው ነበር። ‹‹ ወደ ትምህርት እንድመለስ አጋዥ መካሪ የሆነችኝ ወይዘሮ ትህትና ሰመረ ትባለለች። አሁን ዶክተር ሆናለች። በጣም አመሰግናታለሁ። እሷ “ ዋናው መውደቁ ሳይሆን ወድቆ መነሳቱ ነው” አለች። በዚህ ጠንካራና አነቃቂ ምክር ወደ ትምህርት ገበታዬ ተመለስኩ›› ይላሉ።
በህይወት መንገድ ላይ ብዙ መሰናክሎች እንደገ ጠሟቸው የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር፤ ይህም በዚህ ሳያበቃ ከአንደኛ ዓመት እስከ ሦስተኛ ዓመት ወንድማቸው ምንም አልተሻላቸውም ነበር። አንዴ ደህና ይሆናሉ፤ ሌላ ጊዜ ይብስባቸዋል ። ሶስተኛ ዓመት ጨርሰው ክረምት እረፍት ላይ ሆነው የወንድማቸው ጤና እጅግ በመባሱ በሞት ተለያቸው። ብዙም ሳይቆይ አሜሪካ ሀገር የሚኖር ሌላኛው ወንድማቸውም እንዲሁ አረፉ ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነባቸው። ሁለቱንም ወንድሞቻቸውን ሞት ነጠቃቸው። በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ተዋጡ። አራተኛ ዓመት ትምህርታቸውን ለመቀጠል እጅግ ተቸገሩ ሀዘናቸው እጥፍ ድርብርብ ሆነባቸው ።
‹‹ከቀድሞ ውድቀት ትምህርት መውሰድ በመቻሌ ወደ ኋላ ማየት እንደሌለብኝ አመንኩ። ዛሬ አድጌለሁ፤ ትልቅ ሆኛለሁ። ስለዚህ አስቴር አርፈሽ ተማሪ በማለት እራሴን በማጽናናት ወደ ትምህርቴ ተመልስኩ። የሀዘን ሰሜት እጅግ ከባድ ከመሆኑም በላይ ፤ በድጋሚ ሰማይ የተደፋብኝ ያህል ተሰምቶኝ ነበር ›› የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሯ፤ በመጠንከራቸውና ከውድቀታቸው በመማራቸው የገጠማቸው ፈተና በቀላሉ ማለፍ ቻሉ። የተሻለ ውጤትም አስመዘገቡ። ይህን የህይወት ውጣ ውረዳቸውን አሁን ላይ ሆነው ለተማሪዎቻቸው ማነቃቂያ ይጠቀሙበታል። የሰው ልጅ በተለያዩ ምክንያቶች ሊወድቅ ይችላል። ዋና ችግሮችን ተቋቁሞ ከውድቀት በመነሳት ፈተናዎችን እንደየአመጣጡ ማለፍ ይኖርበታል። መማርም፣ ስራ መያዝም፣ መመራመርም፣ ልጅ ማሳደግም እንዲሁም ኃላፊ መሆንም ይቻላል። ይህን እሳቸው አድርገው አሳይተዋል። አሁን ደግሞ ትውልድ ለመቅረፅ ይጠቀሙበታል።
የስራ ላይ ቆይታ
ተባባሪ ፕሮፊሰር አስቴር፤ያኔ ገና ብዙ ሴቶች በሌሉ በት የሳይንስ ትምህርት ዘርፉን ለመቀላቀል ችለዋል። ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀድሞ ብሔራዊ የጤና ኢንስትቲዩት በመባል የሚታወቀው በተለምዶ ፓስተር በአሁን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የስራን ዓለም አሃዱ ብለው ላብራቶሪ ምርምር አገልግሎት ጀመሩ። የሚፈልጉትን ባያገኙም የተመደቡበት የጤና ላብራቶሪ ላይ የመሆኑ አጋጣሚ ወደ ሚፈልጉት ትምህርት እንዲያመሩ መሰረት ሆናቸው። ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርቲ ተቀይረው ከ20 ዓመታት በላይ በመምህርነትና ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮች በማካሄድ እያገለገሉ ይገኛሉ። በጊዜው የሴት ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ የነበረ ቢሆንም ሴቶች ከተጣጣሩ የማይደርሱበት ምንም ነገር ባለመኖሩ ወደ ፈለጉበት ለመድረስ እንደቻሉ ይናገራሉ።
እኚህ ብርቱና ትጉህ ሴት የህክምና ላብራቶሪ ተማሪዎች በቅድመና በድህረ ምረቃ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። የጥናታዊ ምርምሮች አማካሪም ናቸው። ከተማሪዎችና ከመምህራን ጋር በመሆን በርካታ የምርምር ስራዎችን በማከናወን እንዲሁም በበጎ ፈቃድ ስራዎች በመሳተፍ ይታወቃሉ። ከላብራቶሪ ጋር በተያያዘ የሚያከናወኗቸው ችግር ፈቺ ምርምሮች የላብራቶሪ አገልግሎቱን እንዲያሻሽሉ የሚያደርጉ ናቸው።
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር፤ በደም ላይ የሚያጠና ትምህርት ክፍል (ሂማቶሎጂ) በኃላፊነት፣በኢትዮ ኔዘርላንድ ኤድስ ሪሰርች ፕሮጀክት የላብራቶሪ ስራ አስኪያጅነት፣ የብሔራዊ ኤችአይ ቪ ምርምራና ስልጠና አስተባባሪነት፣ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ትምህርት ቤት የላብራቶሪ ዳይሬክተርነት፣እንደገናም የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ህክምና ሆስፒታል ኃላፊ በመሆን ሰርተዋል። በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በቦርድ አባልነት፣ በሰብሳቢነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሴት ሳይንቲስቶች ማህበር መስራችና የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። ‹‹በኃላፊነት በሰራሁበት ጊዜ የገጠመኝ መጥፎ ነገር የለም። አብረውኝ የሚሰሩ ቡድኖችን አስተባብሬ በመስራት፤ እንዲሁም ሰዎችን በሙያቸው በማክበር መወጣት ችያለሁ። ››የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሯ ፤ሴት የኃላፊነት ቦታን መወጣት አትችልም ብለው ሊያስቡ የሚችሉ ሰዎች እንደማይጠፉ ይናገራሉ። ነገር ግን በብልሃት መወጣት እንደሚቻል እንደሚያምኑ ይገልፃሉ።
የቤተሰብ ህይወት
ባለትዳርና የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ከትምህርት ቤት ጀምሮ ለዚህ እስከ መድረሳቸው በዋናነት የቤተሰብ ድጋፍ እንዳልተለያቸው ይናገራሉ። በተለይ ፒኤችዲ ትምህርታቸውን አምስተርዳም በሚማሩበት ወቅት ሁለት ህጻናት ልጆቻቸውን ትተው በመሄድ ነበር። ‹‹ በተለይ ከአእምሮዬ የማይጠፋው የሦስት አመቱ ልጄ ምርር ብሎ አልቅሶ ተመለሺ ሲለኝ ልጆቼን ከማሰቃይ ለምን ፒኤችዲ አይቀርም ያልኩበት ወቅት ነበር። ያን! ጊዜ የተሰማኝ የእናትነት ስሜት ፤ እንደገናም ትንሹ ልጄ ወደ አምስተርዳም እስከምሄድ ጡት ይጠባ ነበር። ጡቴ እስኪለምድ የመፍሰስ ፤ የእናትነት ስሜት፤ ናፍቆት ብዙ ነገሮች ፈታኝ ነበሩ ›› በማለት ያጋጠማቸውን የእናትነት ፈተና ያስረዳሉ።
ልጆቻቸው እንደ ልጅነታቸው በቂ ጡት አልጠቡም ። ምክንያቱም እረፍት ለመወሰድ የማይች ሉባቸው የስራ መስኮች ላይ ነበሩ ። የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲወልዱ በኢትዮ ኔዘርላንድ ኤድስ ሪሰርች ፕሮጀክት የላብራቶሪ ስራ አስኪያጅ ስለነበሩ እረፍት ማግኘት አልቻሉም ። ‹‹ ጡት አለማጥባቴ፣ ስራ ቤት ይዤ መሄዴ ፤ ቅዳሜና እሁድ ስራ መዋሌና ለልጆቼ በቂ ጊዜ አለመስጠቴ ያጎደልኩባቸው ያህል ይሰማኛል። ልጆቼ ግን ይረዱኝ ነበር። በቂ ጊዜ እንዳላገኙ አይነት አይደሉም። ነገር ግን ከስራ ውጪ ያሉት ሰዓቶቼን ሙሉ ለሙሉ ለልጆቼ አውል
ነበር ››ይላሉ። በዚህም ልጆቻቸው ያሰቡት ደረጃ እየደረሱላቸው መሆኑንም ይናገራሉ።
በምርምር መስክ ያሉ ፈተናዎች
ካላቸው ተሞክሮ በመነሳት በምርምር ላይ የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑን ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ይናገራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሴቶች ቁጥር ከወንዶች እኩል የመሆን ተስፋ አለ። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሴቶች ቁጥር እጅግ እየቀነሰ ይመጣል። በአመራርነት ፣ በምርምርና ፈጠራ ሲታይ ደግሞ ልክ እንደሚያፈስ ቧንቧ ነው ይላሉ። የሴቶቹ ቁጥር እየሳሳ እንደሚሄድ ያነሳሉ።
ለዚህም በምክንያቱነት የሚጠቀሱት ቤተሰብ፣ማህበረሰብና ትምህርት ቤቶች ለሴቶች ምቹ አለመሆናቸው ነው። በአፍሪካ ሀገራት ዙሪያ በተጠና ጥናት ለሴቶች ምቹ የሆኑ የመፀዳጃ ቤት አለመኖር፣ የንጽህና መጠበቂያ ጉድለት ጋር የተያያዙ ችግሮች ይጠቅሳሉ። ሌላው ሴቶቹ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ወደ ኋላ የሚጎትቷቸው በርካታ የግል ጉዳዮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ተባባሪ ፕሮፌሰሯ፤ ሴቶቹ ከአእምሯቸው አልችልም የሚለው መንፈስ ሙሉ በሙሉ ያልወጣ መሆኑ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።
አሁን ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ ተባረውም ሆነ ተመርቀው የሚወጡት ተማሪዎች ቀድሞ ሲሰሩት የነበረውን ስራ ተመልሰው ሲገቡበት፤ ‹‹ትምህርት እንዲህ ከሆነ ለምን እንማራለን?›› የሚል ስሜት እንደሚፈጠርባቸው ይናገራሉ። ዩኒቨርሲቲ የገባችው ሴት ስኬታማ መሆን አለባት የሚል እምነት አላቸው። ሰንሰለቱ የተያያዘ በመሆኑ ቀድማ የገባችው ስኬታማ ካልሆነች ከታች ያሉትን ጨምሮ ይጎዳሉ በማለትም ከታች ላሉት አርአያ መሆን እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። ከዚህ በላይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ ሲታይ ደግሞ የጾታ ጥቃት እየጨመር መሆኑን ተባባሪ ፕሮፌሰሯ ይገልጻሉ። ይህን ድርጊት ማውገዝና ማቆም እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዥነት የሚያነሱት የዩኒቨርሲቲ ሴት መምህራን በኩል የቤተሰብ ኃላፊነት ላይ ብቻ በማተኮር ምርምሩ የማይቻል አድርጎ አክብዶ የመውሰድ አመለካከቶች እንዳሉባቸው ይናገራሉ። ሁለቱም አጣምሮ ማስኬድ የሚያስቸግር እንደሚመስላቸውም ይገልፃሉ። እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎችም ለሴቶች ምቹ ሁኔታ ያለመፍጠራቸውን ይጠቅሳሉ ። ይሁን እንጂ በአንዳንዱ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ጥሩ ጅማሮ እንዳለም ከመናገር አልተቆጠቡም።
የልጆች ማቆያ ያላቸው እንዳሉ ታዝበዋል። ሴቶች ብቻ የሚወዳደሩበት የምርምር ገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ስልጠናዎችን የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸውን እንደ በጎ ጅምር ይመለከቷቸዋል። ሴቶች ወደ ኋላ የሚጎትታቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በኢትዮጵያ ቤተሰብ ብዙ በመሆን ኃላፊነት እየሰፋ ስለሚሄድ፤ ሴቶች ድርብ ድርብርብ ጫናዎችን መቋቋም አይችሉም። የፈተናው መጠን ሰፋ ከማለቱ አንፃር ችግሩን ለመቅረፍ የሴቷን እችላለሁ የሚል መንፈስ ከማሻሻል ጀምሮ ከታች እስከ ላይ ባሉት ሴቶች ላይ መስራት እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
ተማሪዎች አላማ ሊኖራቸው ይገባል ይላሉ። ቤተሰቦቻቸውን ትተው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲቀላቀሉ ዓላማቸው ትምህርታቸው ላይ ብቻ መሆን እንዳለበት ይገልፃሉ። ተማሪዎች ስኬታማ ለመሆን ጊዜያቸውን በአግባቡ ከተጠቀሙ፤ ለትምህርት ትኩረት መስጠት ከቻሉ፤ በትጋትና ጥንካሬ ከሰሩ፤ በተለያዩ ጊዜያዊ ነገሮች የማይታለሉ ከሆነ ስኬታማ የማይሆኑበት ምንም አይነት መንገድ የለም። ‹‹ የአሁኑ ትውልዶች እድለኞች ናቸው። ማንኛውንም አይነት የሳይንስ መረጃ በየቀኑ እጃቸው ላይ ይገባል። ለምሳሌ አንድ ትምህርት ባይገባቸው ከማህበራዊ ድረገጽ በማውጣት ከነማብራሪያው ማግኘት ይችላሉ። በመሆኑ በቀላሉ ችግሮቻቸው መፍታት፤ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም ይችላሉ። ማህበራዊ ሚዲያው ለመልካም ነገር ቢጠቀሙበት በጣም ውጤታማ ይሆናሉ። ተማሪዎች ለምንም አይነት ሱስ ተጋላጭ መሆን የለባቸው። የአቻ ግፊትም በመቋቋም ያሰቡበት በመድረስ ስኬታማ መሆን ይቻላል›› ሲሉ ይናገራሉ።
ገጠመኝ
የልጅነት ገጠመኛቸውን እንዲህ ያስታውሳሉ። ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ጨረቃ ላይ ስለ መውጣት የሚዘምሩት መዝሙር ነበር። መምህራቸው በጋራ ስፖርት ሊያሰሯቸው ተማሪዎቹን በጠዋት እንዲመጡ ይቀጥሯቸዋል። በዚያ ለመገኘት በሌሊት መሄድ ነበረባቸው። ሲደርሱ ግን መምህሩ እንደአጋጣሚ ሆኖ የዚያን እለት አልመጡም ነበር። ሲቀሩባቸው ጨረቃዋ ፍክት ብላ ሲያዩአት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የመዝሙሩ ጨረቃ ላይ መውጣት ታወሳቸው። ለመውጣት ፈልገው ወደ ጫካ ሄደውም ነበር። የህጻናት አምላክ አለና ፤ ከጅብ ጎሮሮ እንደታደጋቸው በትዝታ ያወጋሉ።
ሌላኛው ገጠመኝ አስራ ሁለተኛ ክፍል እንዳ ጠናቀቁ ለሦስት ወራት ሐረር ጃርሶ ኢጀርሳ ጎሮ በመባል ከምትታወቀው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የትውልድ ቦታ የሰባት ሰዓት መንገድ መሠረት ትምህርት ለማስተማር ሄደው ነበር። የተመደቡ ቦታ ገጠር በመሆኑ በወቅቱ ምንም ውሃ ፣ መብራትና የህክምና ተቋም ያልነበረው ነበር። እሳቸው የነበሩበት የገበሬ ማህበር ውስጥ አንድ ቀን ሌሊት ሰርጎ ገብ የነበሩ ታጋዮች በመምጣታቸው ምክንያት ወደሌላ ቦታ እንድንሸሽ ተደረገ። ሌሊቱን ሙሉ ከሚጠብቋቸው የሀገሬው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በዚያ ጨለማ፤ አስፈሪ ሌሊት ያሳለፉት ውጣ ውረድ ከባድ እንደነበር ያስታወሳሉ። የሀገሬው አርሶ አደርም እነሱን ለማሸሽ የከፈለው መሰዋዕትነት ሁሌም በአእምሮአቸው አይረሴ ሆኖ ታትሟል።
የወደፊት እቅድ
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር፤ የህክምና ላብራቶሪ መምህርና ተመራማሪ እንደመሆናቸው መጠን ለወደፊት ለህክምና ላብራቶሪ የሚጠቅም ምርምሮች እያደረጉ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት እጃቸው ላይ ያሉ ስራዎች ማጠናቀቅ ይፈልጋሉ። በላብራቶሪ ሳይንስ ትምህርት ጥራት ለመጠበቅ የሚጠቅሙ ማስተማሪያ መረጃ መሳሪያዎች ላይ የተጀመሩ ስራዎች በማጠናቅቅ የትምህርቱ ጥራት ማሻሻል ላይ እንደሚሰሩ ይናገራሉ።
‹‹በምርምሩ የላብራቶሪ አገልግሎት ለማሻሻል የሚችሉ የተጀመሩ ስራዎች ከዳር ለማድረስ እስራለሁ። በሙያዬ ከምርምሩ በተጨማሪ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ሴት ልጆች ፣ተማሪዎችና መምህራንን አይቻልም ብለው እንዳይደነቃቀፉ የእውቀት ክፍተት ለመሙላት የጀመሩኩትን ስራ ማስቀጠል እፈልጋለሁ። በማስተማርና ችግር ፈቺ ምርምሩን በመቀጠል በሴቶች ዙሪያ በመስራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን እሰጣለሁ›› በማለት ያላቸው ዓላማ ይገልጸዋል።
መልዕክት
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር፤ በየዓመቱ የሴቶች ቀን መከበሩ ጥሩ ነው ይላሉ። ስኬታማ የሆኑ ሴቶች ያለፉበትን፣ የወጡ የወረዱበትን መንገድ ማየት እና ማንበብ ለሌላው ተሞክሮ በመሆን ያስተምራል የሚል እምነት አላቸው። ለሴቶች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ያሳያል። በአጠቃላይ ‹‹የማንቂያ ደውል ነው›› ይሉታል ጠንከር ባለ አገላለፅ። ነገር ግን በማንቂያው ደውሉ ነቅቶ መቅረት ሳይሆን 365 ቀናቱንም የሴቶች ቀን ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው።
ሴቶች በተሰማሩበት መስክ ምንም አይነት ችግር ቢገጥማቸው ሁሉን ሊያልፉ እንደሚችሉ በማሰብ በጥቃቅን ምክንያት ሳይደነቃቀፉ ያሰቡበት ላይ መድረስ ይችላሉ በማለት እራሳቸውን እንደምሳሌ ያነሳሉ። ቤተሰብ መመስረት ፣ ልጆች መውለድ፣ ይቻላል የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር፤‹‹ ሴቶች የሚያግዘኝ የለም ብለው ከማሰብ ፤ እንኳን እርስ በርስ ከመደጋገፍ፤ከመመካከር መፍትሔ ማግኘት ይቻላል። አላማ ካለን ጊዜያችን በአግባቡ ከተጠቀምን እርስ በርሳችን በመመካከር ፣ ያለን በማካፈል፣ የሌለን በመቀበል እየተጋገዙ ማደግ ይቻላል። ›› በማለት የስኬት ቁልፍ ሚስጥሩን ለሴት እህቶቻቸው ያጋራሉ።
ኢትዮጵያ ብዙ ጀግኖች ነበሯት፤አሁንም አሏት። ወደፊትም ይኖሯታል። ጀግንነት በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ መሆን መቻል ነው። በየተቋማቱ የልጆች ማቆያ እንዲኖር በማድረግና ለሴቶች የሚደረገው የምርምር ድጋፍ እንዲቀጥል ማድረግ ለነገ የሚባል ጉዳይ አለመሆኑን ያነሳሉ። ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር፤ሴቶችም እራሳቸው ምንም ነገር አልችልም ማለት የለባቸውም የሚል ምክር ይሰጣሉ። አልችልምን ከውስጣቸው በማውጣት እርስ በርሳቸው መደጋገፍ አለባቸው፤ አልባሌ ነገሮች ላይ ጊዜን ባለማጥፋት፤ አላማን አንግበው ተግተው በመስራት፤ምንም አይነት የሚያደናቅፋቸው ነገር ሲገጥማቸው ቆም ብለው በማሰብ ከሰሩ ስኬታማ የማይሆኑበት ምንም ነገር የለም ። ጀግንነት ከጦርነት ድል አድራጊነት ጎን ለጎን በተሰማሩበት መስክ በስኬት ድልን መጎናጸፍ ነው።
‹‹ወላጆች በትምህርት ላይ ያሉ ልጆቻቸው በሚችሉት ሁሉ ማገዝ ፣የት እንደሚውሉ መከታተልና ማወቅ አለባቸው። መምህራንም እድሜያቸው፤ ፆታችን ምንም ይሁን ምን ተማሪዎቻችንን ሊወ ልዷቸው ባይችሉ እንኳን እንደልጆቻችን ማየት ይገባናል›› በማለት ትውልድን መቅረፅ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ይናገራሉ። መምህር ደግሞ የተማሪው የቀለም አባት ነውና አባት ልጁ እንዳይጎዳ ስለሚያስብ መምህራንም ለተማሪዎቻችን ማሰብ ጥፋት ሲታይም ማረም ይገባል ባይ ናቸው።
ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ለተማሪዎች ባስተላለፉት ተጨማሪ መልዕክት በየትምህርት ቤት አካባቢ በሚታዩ ጊዜያዊ ነገሮች ሳይሰነካከሉ ያለሙበት ለመድረስ መማር ይጠበቅባቸዋል። ‹‹ በተለይ ሴቶች እንደ እናት የአገር ሰላም አይገባንም ማለት ስለማይችሉ በርካታ ሚና መጫወት አለባቸው። የአገር ሰላም በመጠበቅ እያንዳንዳችን ከተቻለ በመተጋገዝ፤ መተጋገዙ እንኳን ቢቀር እርስ በእርስ እንቅፋት አለመሆን ይገባል። ቢቻለን ብንረዳዳ ይቺን የመሰለች አገር ፈጣሪ ሰጥቶናል ልናደርሳት የፈለግንበት የብልጽግና ማማ ማድረስ እንችላለን። አገር እያንዳንዳችን እጅ ላይ ናት›› በማለት ሁሉም ያለበትን ኃላፊነት ያብራራሉ።
‹‹ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ›› የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አስቴር ፤ መንግሥትም ሰላም በማስጠበቁ ሂደት ቢገፋበት ትምህርት ቤቶች አካባቢ ሊያሰነካክሉ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ ይቻላል ይላሉ። በምሳሌነትም ሺሻ ቤቶች፣ ጫት ቤቶችን መዝጋትና ቁጥጥር ማድረግ ቀዳሚ ስራ መሆኑን ይናገራሉ። በየዩኒቨርሲቲው አካባቢ ላሉ ሁኔታዎች ሁሉም በተዋረድ ይመለከተዋል በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2012
ወርቅነሽ ደምሰው