ዶክተር ወንጌል ጠና ጅማ ተወልዳ በጅማ በዕውቀት የነገሰች ወጣት ናት። በጅማ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ድህረ ምረቃ በአጠቃላይ ቀዶ ጥገና የህክምና ትምህርቷን ተከታትላ አጠናቃለች። ከሶስት ዓመት ውጣ ውረድ በኋላም ዘንድሮ ሶስት ነጥብ 86 ውጤት አምጥታ ሶስተኛ ዲግሪዋን አግኝታለች ። በጅማ ዩኒቨርሲቲ በድህረ ምረቃ መርሐ ግብር የህክምና ትምህርታቸውን ተከታትለው ከተመረቁት 264 ምሩቃን መካከል ሴቶች 54 ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ተመራቂዎች በከፍተኛ ማዕረግ ውጤት ከተመረቁት ውስን ሰዎች መካከል ደግሞ ዶክተር ወንጌል ጠና አንዷ ናት።
“ሴቶች በትምህርታቸው ስኬታማ እንዳይሆኑ የሚያደርጓቸው ማህበራዊና ባህላዊ ጫና እንዳሉባቸው ታወሳለች። እነዚህን ጫናዎች በመቋቋምና በማለፍ በትምህርታቸውና በሙያቸው ስኬታማ የሆኑት ጥቂት ቢሆኑም አንቱ የተባሉ ሴቶች አሉ። እኔም እነዚህን ሴቶች አንደ አርአያ በመውሰድ ለዛሬ ስኬቴ እንደ ስንቅ ተጠቅሜበታለሁ”ስትል ገልጻልናለች።
ህክምና ሳይንስ ብዙ ቁጭ ብሎ የማንበብና በተመስጦ መስራትን የሚፈልግ ዘርፍ ነው የምትለዋ ዶክተር ወንጌል ፤እንደ ሴትነት አንድ ጊዜ ባህላዊና ማህበራዊ ጫናውን ተቋቁመው ከመጡና ህክምናን ትምህርት መከታተል ከጀመሩ አብዛኛዎቹ ሴቶች ስኬታማ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ ባይ ናት።
“ከልጅነቴ ጀምሮ ህክምና መማርና ዶክተር መሆን የሁልጊዜ ህልሜና ምኞቴ ነው የምትለዋ ወጣቷ ዶክተር ብዙ ጊዜ አጠቃላይ ቀዶ ጥገና ህክምና (ሰርጀሪ ስፔሻሊቲ) ብዙ ሰዓት መቆምና ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ የወንዶች ሥራ ነው ስለሚባል የትምህርት መስኩን ስመርጠው ትንሽ ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር ።ምክንያቱም በዚህ የህክምና መስክ ላይ ሴቶች ደፍረውም አይገቡበትም።እስካሁንም ድረስ በሙያው እየሰሩ ያሉ ጥቂት ሴቶች ናቸው። አሁን አሁን ነው በአገራችን እየተለመደ የመጣው። ሆኖም ወደ ህክምና ትምህርቱ ከገባሁ በኋላ እንደማንኛውም ወንድ ተማሪ ውጤታማ ሁኛለሁ ትላለች።
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ተመራቂዎች ውስጥ በህክምና ዘርፍ 3 ነጥብ 86 አግኝታ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው የ28 ዓመቷ ዶክተር ወንጌል የህክምና የድህረ ምረቃ ትምህርት ብዙ ጊዜ ተግባር ተኮር በመሆኑ ብዙ ውጣ ውረዶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሳለች።በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስር ባለው ሆስፒታል ለታካሚዎች የቀዶጥገና ህክምና እያደረጉ ማምሸት ብቻ ሳይሆን እያደሩ ጭምር ሲሰሩ እንደሚያሳልፉት አውስታለች። ከተግባራዊ ትምህርት ባሻገርም በጥናትና በንባብ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ነግራናለች።
ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ ሶስተኛ ዲግሪዋ ድረስ ጎበዝና የደረጃ ተማሪ እንደነበረች የምትናገረው ዶክተር ወንጌል ፤ በተሰማራችበት ሁሉ ውጤታማ መሆን እንዳለበት መምህራኑ እናትና አባቷ ስላስተማሯት ለዚህ ስኬት መብቃቷን አውስታለች። ይህ ውስጤ የነበረ ነገር ፣አሁንምና ወደፊትም የምተገብረው ነው።በህይወትና በትምህርት ጉዞ ላይ ፈተናዎች ቢበዙ ፈተናዎቹን አልፌ ውጤታማ እንድሆን ያበቃኝ የአባትና እናቴ ፍልስፍና ነው ብላለች።
የህክምና ትምህርት የታካሚዎችን ስቃይና ህመም ጭምር ማድመጥና መጋራት እንደሚያስፈልግ የምት ገልጸው ዶክተር ወንጌል ከብዙ ውጣ ውረድና ልፋት በኋላ በቤተሰቦቿ ድጋፍ፤ በእሷ ሁለንተናዊ ጥረት ተጨምሮበት ለዚህ ደረጃ በቃሁ ትላለች።ሜዲካል ዶክተር ከሆንኩ በኋላ ነው ስፔሻላይዝ ለማድረግ እንደገና መማር የጀመርኩት የምትለዋ ዶክተሯ በትምህርትና በተግባር ያገኘችውን እውቀትና ክህሎት ማህበረሰቡን ማገልገል ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱ አላት።እንዲሁም የህክምና ሴት ተማሪዎችን ለመደገፍና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ ባይ ናት።ወደፊትም በጉበትና ቆሽት ቀዶ ጥገና ትምህርት ሰብ ስፔሻላይዝድ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላት ነው የተናገረችው።
የህክምና ትምህርት ግብዓቶችን በተመለከተ ዶክተር ወንጌል እንደገለጸችው ፤ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከቀደምት የህክምና ትምህርት በግንባር ቀደምትነት ከተከፈቱባቸው ጎንደርና አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው። ስሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ነው ። ይህ ዩኒቨርሲቲ ብዙ የህክምና ባለሙያዎችን ያፈራና እውቅና ያለው ተቋም ቢሆንም እንደ ስሙ የትምህርት ግብዓቶች የተሟሉ ናቸው ማለት አይቻልም።ከእጅ ጓንት ጀምሮ እስከ ትልልቅ የቀዶ ህክምና መሳሪያዎች ድረስ እጥረትና ብልሽት ያጋጥማል። እንዲሁም እንደ ስሙና ዝናው ብዙ ስብ ስፔሻሊስቶች የሉትም ። የህክምና ግብዓቶች ማሟላት ረገድም ሊሰራ ይገባል፤ የሰው ሀብት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ መልካም ነው ብላለች ። የህክምና ባለሙያዎችም በከፍተኛ ተቋማት የሚያገኙትን ክህሎትና እውቀት ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ሊጠቀሙበት ይገባል ስትል ምክሯን ለግሳለች።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ በላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበ ረሰብ አገልግሎት ተልዕኮውን ለመወጣት ጥረቶች እያደረገ ይገኛል። በተለይ ዩኒቨርሲቲው ስምና ዝናውን በገነባበት የግብርናና የጤና ትምህርት መስኮች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት ረገድ ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ሙሉ የትምህርት ግብዓቶች፣ ማለትም ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ አይሲቲ ቴክ ኖሎጂዎች ተሟልተው እንዲማሩ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የግዥ ሂደት መራዘሙና ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ ርቆ መገኘቱ በትምህርት ግብዓቶት አቅርቦት ላይ የመዘግየት ችግር እያጋጠመ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም ተማሪዎች በተሟላ የትምህርት ግብዓት እንዳይማሩ እንቅፋት እየፈጠረ ነው። ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ለመፍታትም የትምህርት ግብዓቶች እጥረቱ ሳይፈጠር ግዥ የሚፈጸም አሰራሮች ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ሁሉም ተማሪዎች በቂና የተሻለ እውቀትና ክህሎት ታጥቀው እንዲወጡ ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ይህ ማለት ግን ምንም የአቅርቦት ችግር የለም የሚያስብል አይደለም።ዋናው ነገር ችግሩን ወዲያ መፍታት ተገቢ ይሆናል ሲሉ የግዥ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ዘዴ ቀይሰው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ነግረውናል።
ዩኒቨርሲቲው እውቀትና ክህሎት ሲመግባቸው የቆዩ ምሁራን በአገርና ህዝብ ዕድገትና ህይወት መለወጥ ላይ ለውጥ ጉልህ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ።አሁንም በመማር ላይ የሚገኙት ተማሪዎች በአገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥራት ያለው ትምህርትና በህብረተሰብ ዘንድ ለውጥ የሚያመጡ የተግባር ክህሎቶችን የማስጨበጥ ሥራ እየሰራ መሆኑን ዶክተር አሸናፊ ገልጸውልናል። ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2012ዓ.ም 47ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 27/2012
ጌትነት ምህረቴ