አዲስ አበባ፡- የጅማ ዩኒቨርሲቲ በአንድ ቢሊዮን 225 ሚሊዮን ብር የግብርና፣ ቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ፣የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)ና ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ፣ ካምፓስና ማዕከላት የማስፋፊያ ግንባታዎች እያካሄደ እንደሚገኝ አስታወቀ።
በጅማ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኮራ ጡሾኔ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርስቲው በ305 ሚሊዮን ብር የአጋሮ የማስተማሪያና የምርምር ካምፓስ፣ በ400 ሚሊዮን ብር የቱሪዝምና ሆስፒታልቲ እንዲሁም በ520 ሚሊዮን ብር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከልና ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታ እያካሄደ ይገኛል።
የካምፓስና ማዕከላት ግንባታዎቹ በተለያየ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ ኮራ፣ የአጋሮ ካምፓስ ግንባታ ከአምስት ዓመት በፊት የተጀመረ ቢሆንም የስራ ተቋራጩ በገባው ውል መሰረት በተቀመጠለት ጊዜ ሊያጠናቅቅ ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ ተነጥቆ ለሌላ ስራ ተቋራጭ በመሰጠቱ ግንባታው እየተፋጠነ እንደሚገኘ ገልጸዋል።
በአጋሮ ከተማ በ305 ሚሊዮን ብር የሚገነባው ካምፓስ በተለይ የቡና ምርምር የሚካሄድበትና የተለያዩ በትምህርት መስኮች ትምህርት የሚሰጥበት መሆኑን አመልክተው በያዝነው ዓመት ግንባታው ተጠናቆ በሚቀጥለው ዓመት ተማሪ ተቀብሎ ማስተማር እንደሚችል ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኮራ ገለጻ፤የመማሪያ ሆቴሉ ከማስተማሪያነት በተጨማሪ ዘመናዊ የሆቴል አገልግሎትም የሚሰጥ ነው።ሌላው ዋና መስሪያ ቤትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ(አይሲቲ) ማዕከል የሚያካትተው ህንጻ ግንባታ አፈጻጸሙ 80 በመቶ ደርሷል።
በአገራችን ስመ ጥር ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ጅማ ዩኒቨርሲቲ፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደሆነም ይነገርለታል። ተቋሙ ዩኒቨርሲቲ ከመሆኑ በፊት በግብርና ኮሌጅነት፣ በተወሰነ አቅምና በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮች ስራውን የጀመረ ሲሆን፤ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው ደግሞ በ1992 ዓ.ም ነው። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እምብዛም ያልተሞከሩ አሰራሮችን በመጠቀምና ጥናትና ምርምር ላይ በማተኮር ውጤት እያስመዘገበ ያለ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነም ይነገራል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2012 ዓም
ጌትነት ምህረቴ