አዲስ አበባ፡- በተለያየ መልኩ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ከችግሮቻቸው ለመታደግ የተቀናጀ ድጋፍ ማድረግ ከሁሉም አካላት የሚጠበቅ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ።
ትናንት የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ እንደተገለጸው፤ ሴቶች በተለያየ ምክንያት ለአካላዊ፣ ለጾታዊ፣ ስነልቡናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እየተጋለጡ ይገኛል። ይህ ደግሞ ለዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ እያጋለጣቸው ሲሆን፤ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ከችግሮቻቸው መታደግ የተቀናጀ ድጋፍ ማድረግ ከሁሉም አካል የሚጠበቅ ተግባር ነው።
የሴቶችና ህጻናት ሚንስትሯ ወይዘሮ ያለም ፀጋዬ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት፤ በየመድረኩና በየአጋጣሚው ሲነገሩ የሚደመጡ ጉዳዮች በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ግዝፈት አመላካች ነው። በዚህ መልኩ ጥቃት እየደረሰባቸው ለዘርፈ ብዙ ችግር የሚጋለጡ ሴቶችን ከችግሮቻቸው ለመታደግ ደግሞ ከሁሉም የሚጠበቅ የተቀናጀ ድጋፍ ያስፈልጋል።
እንደ ሚንስትሯ ገለጻ፤ የሴቶች ቀን በዓለም ላይ ያሉ ሴቶች በጋራ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ነው። በዚህ ዓመት ሲከበርም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶችን በማሰብና በመደገፍ ሲሆን፤ መንግስትም የሴቶችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት እየሰራ ይገኛል። በማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ የባለሃብቱን ተሳትፎ እያጎለበተ በሚያከናውነው ተግባርም ውጤት እያሳየ ነው። ሆኖም አሁንም ከግንዛቤ ጀምሮ በቅንጅት ችግር ምክንያት ባሉ ክፍተቶች ችግሩን በሚፈለገው ልክ መግታት፤ የሕግ ተጠያቂነትንም ማረጋገጥ አልተቻለም። ሚኒስቴሩም በቀጣይ በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን፤ በቀጣይ ምርጫም የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ይሰራል።
በሚኒስቴሩ የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ እንዳሉት፤ በሴቶች ላይ የአካል፣ የጾታ፣ የስነልቡና እና የኢኮኖሚ ጥቃቶች የሚደርሱ ሲሆን፤ አብዛኞቹም በቤት ውስጥ በቤተሰቦቻቸውና በአሰሪዎቻቸው የሚፈጸም ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩትም 23 በመቶው አካላዊ፣ 10 በመቶው ጾታዊ እንዲሁም 34 በመቶው አካላዊም ጾታዊም ጥቃቶች ይደርሱባቸዋል።
ይሄን ጥቃት ለመከላከል እንዲቻልም ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ የሕክምናና ድጋፍ እንዲሁም የማረፊያ ማዕከላትን የማደራጀት ተግባራትም ተሰርተዋል። ይሁን እንጂ ጥቃት ፈጻሚዎችን ለህግ ከማቅረብና እርምጃ ከማስወሰድ አኳያ አሁንም ትልቅ ችግር በመኖሩ በቀጣይ የሁሉንም ተሳትፎ በማጠናከር የሚሰራ ይሆናል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካይ ኮማንደር ፋሲል አሻግሬ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የፖሊስ የመጀመሪያ ተግባር ወንጀልን መከላከል ሲሆን፤ ሴቶችና ህጻናትን ከጥቃት መታደግና ጥቃት ሲፈጸምባቸውም ተገቢውን ድጋፍና እርዳታ ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። ይሁን እንጂ በህብረተሰቡ ውስጥ ባለ የግንዛቤ እጥረት ምክንያት በሚስተዋል የተባባሪነት ማነስ ችግር ስራውን በሚፈለገው ደረጃ መግታት አልተቻለም። ይሄን ለመቀልበስም በቀጣይ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ የኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግ እንዲጠናከር ይደረጋል። ህዝቡም ለችግሩ መገታት አጋዥነቱን ሊወጣ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2012 ዓም
ወንድወሰን ሽመልስ