አዲስ አበባ፡- በአራቱ ክልሎች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አስር የዘመናዊ እርሻ መሳሪያዎች አገልግሎት (መካናይዜሽን) መስጫ ማዕከላት ሊገነቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቀ።
በኤጀንሲው የግብርና ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶክተር ጨመዶ አንጫላ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ለአስሩም ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ግንባታ የሚውል ሶስት ሄክታር መሬት ከአራት ክልሎች ተገኝቷል። ትራክተሮች፣ኮምባይነሮች፣ ጸረ ተባይ መርጫና ሌሎች የእርሻ መሳሪያዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በኤጀንሲው 70 በመቶ (91 ሚሊዮን ብር) ወጪ እና በማህበራትና በግል ድርጅቶች 30 በመቶ ድርሻ ታክሎበት የሚገነቡ ይሆናል።
ለእያንዳንዳቸው የእርሻ መሳሪያዎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ግንባታ 70 በመቶ የግንባታ ወጪአቸውን ኤጀንሲው እንደሚሸፍንና በዚህ መሰረት ለአንዱ ማዕከል ግንባታ ዘጠኝ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልጸው ስምንት የህብረት ሥራ ማህበራትና ሁለት የግል ድርጅቶች 30 በመቶ ድርሻን በመጨመር ግንባታዎቹ በመጪው መጋቢት ወር 2012 ዓ.ም እንደሚጀመሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል አራት፣በአማራ ክልል ሶስት፣በደቡብ ክልል ሁለት፣በትግራይ ክልል አንድ በጥቅሉ 10 የመካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንደሚገነቡ ገልጸው፤ እነዚህ ማዕከላት ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት መሰብሰብ ድረስ ለአርሶ አደሩ ዘመናዊ ማሽነሪዎች አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ የጥገናና ፣ቢሮዎች፣ስልጠና መስጫ ማዕከላት ጭምር ያካተቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በማዕከላቱ የሚገነቡባቸው ቦታዎችም በኦሮሚያ ክልል ባሌ፣አርሲ፣አምቦና ምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች፣ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃምና ምዕራብ ጎንደር፣ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞንና ወላይታ እንዲሁም በትግራይ ክልል ሁመራ አካባቢ ለዘመናዊ የግብርና እርሻ አመች ናቸው ተብለው የተመረጡ አካባቢዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለአርሶ አደሩ የሚቀርቡ የእርሻ መሳሪያዎች ጥራታቸውን የጠበቁና በሌሎች አገራት ተፈትሽው ውጤታማ የሆኑ መሆናቸውን ያመለከቱት ኃላፊው መሳሪያዎቹን በጥንቃቄ ለመያዝ፣ ለመጠቀምና ለባለሙያዎች በተግባር የተደገፈ ስልጠና ለመስጠት የጥገናና የጽህፈት ቤቶችን ያካተቱትን ማዕከላት ለመገንባት ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ ኤጀንሲው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመሆን 300 ወረዳዎች የሚገኙ ገበሬዎችን በፍላጎት በኩታ ገጠም ማደራጀት መቻሉን ገልጸው አርሶ አደሮች እንዴት ዘመናዊ የምርት ማሳደጊያዎች መጠቀም እንዳለባቸው ትምህርት የሚሰጣቸው መሆኑንና የትራክተርና የኮምባይነር አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
አርሶ አደሩ የዘመናዊ የግብርና ግብቶችና መሳሪያዎችን በመጠቀሙም በ300 ወረዳዎቹ ምርትና ምርታማነት መጨመሩን ገልጸው በቀጣይ ወደ 500 ወረዳዎች ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በእርሻ ከሚሸፈነው መሬት በመካናይዝድ እርሻ የምትጠቀመው ከ10 በመቶ በታች ነው ። በአገር ደረጃ ከ12 ሺህ በላይ ትራክተሮችና የማጨጃና የመውቂያ (ኮምባይነሮች) መሳሪያዎች እንዳሉ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች ከ50 እስከ 60 በመቶ የምርት ጭማሪ ሊያስገኝ እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ።ዘመናዊ እርሻ መሳሪያዎችን መጠቀም ባለመቻሉ ዛሬም አርሶ አደሩ በእጅ ለማጨድ፣ በበሬ ለማረስ ተገዷል ። አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም እርሻ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን የሚጠቀምበት ዕድል ቢፈጠር የምርት ብክነትን ይቀንሳል፣ጥራትን ያስጠብቃል፣ጊዜን ይቆጥባል ።
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2012 ዓም