በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስራ ሁለት ወረዳዎች ለወባ ወረርሽኝ ተጋላጭ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ። ሰፋፊ ኢንቨስትመንት ባለባቸው አራት ወረዳዎችም ተንቀሳቃሽ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ክልሉ አስታውቋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሚገኙ አብዛኛው ወረዳዎች (አስራ ሁለቱ) ለወባ ስርጭት የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በወባ በሽታ ምክንያት የጠፋ የሰው ሕይወት በክልሉ እንዳልተመዘገበ የጠቀሱት ኃላፊዋ፣ አካባቢው ለኢንቨስትመንት አመቺ ስለሆነ ከደጋው የአገሪቱ ክፍል ለስራ በርካታ የሰው ቁጥር ይመጣል። በመሆኑም በእርሻ ቦታዎች አካባቢ በበሽታው ብዙ ሰዎች ይያዛሉ።
ኢንቨስተሮችም ለሚያሰሯቸው ሰዎች በአግባቡ የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድን በተለዩ አራት (ባምባሲ፣ሸርቆሌ፣ማንዱራ፣ዳንጉር) ወረዳዎች በማቋቋም ለአራት ወራት ያህል እዚያው ሆኖ ሕክምናውን እንዲሰጥ እንደተደረገም አስረድተዋል።
ከአየር ንብረቱና ከአቀማመጡ በተለይም በክረምቱ መግቢያ እና መውጫ ወራቶች ለወባ መራባት ምቹ በመሆኑ ስርጭቱ እንደጨመረም ገልጸዋል።
የወባ ትንኝ ሊራባባቸው በሚችልባቸው አካባቢዎችና ቦታዎች በሕብረተሰብ ተሳትፎ የአካባቢ ጥበቃ፣ ውሃ የሚያቁሩ አካባቢዎችን የማፋሰስ ስራዎች መሰራታቸውንና በተጨማሪም የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ስርጭት እና የቤት ለቤት የመድኃኒት ርጭት እንደተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል።
ኃላፊዋ እንደተናገሩት በዘንድሮው ዓመት ከሁለት ቀበሌዎች በስተቀር በሁሉም ቀበሌዎች የወባ ትንኝ ማጥፊያ የመድሃኒት ርጭት መከናወኑን ገልጸው፣ አልፎ አልፎ ቤቶች የማይመረጉባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው እነሱም በርጭቱ እንዳልተካተቱ ተናግረዋል።
እነዚህ የመከላከል ስራዎች ተሰርተውም የወባ ስርጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፣አሶሳ ዞን ሸርቆሌ፣ባምባሲና ኦዳ ወረዳዎች፣መተከል ዞን ቡለን፣ማንዱራ፣ፓዊ፣ዳንጉርና ጉባ የወባ ስርጭቱ ከፍተኛ ከሆነባቸው አካባቢዎች እንደሚጠቀሱ ዘርዝረዋል።.
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2012 ዓም
ሙሐመድ ሁሴን