• ለካራማራ የድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚከፈሉ መሥዋዕትነቶች የአገሪቱ ታሪካዊ ኩራት መሆናቸውን ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካራማራ ድል በዓል አስመልክተው ለኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ትናንት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመልእክታቸው እንደገለጹት፤ “ከዚያድ ባሬ መራሹ የሶማሊያ ወራሪ ኃይል ጋር በነበረን ተጋድሎ ወሳኝ ድል ላስመዘገብንበት የካራማራ ድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው እንዳሉት፤ የ1967ቱ የሶማሊያ ወረራ አገሪቱን ከአብዮት ፍንዳታው ጭጋግ ባልወጣችበትና የእርስ በርስ ግጭት ላይ በነበረችበት ጊዜ የተከሰተ ነው። ኢትዮጵያን የወረሩ አብዛኞቹ ኃይሎች የሰሩት ዓይነት ስሕተት ዚያድ ባሬም ተሳሳተ።
አገር የደከመች መስሎት ኢትዮጵያን የማሸነፊያ ጊዜ የደረሰለት መሰለው፤ በዚህ የተሳሳተ ስሌት ተመርቶ ወረራውን ፈጸመ። በመጀመሪያ አካባቢ እንዳሰበውም የጎላ መከላከል ሳይገጥመው ሰፊ የአገሪቱን መሬት ማካለል ችሎ እንደነበር የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫው ነገር ግን ኢትዮጵያውያን እንደፍግ ተኝተው እንደ እቶን በተነሡ ጊዜ ምን እንደሚያደርጉ በዚህ ወረራ ጊዜ ታየ ብለዋል።
በአጭር ጊዜ “የእናት አገር ጥሪ” የተሰባሰቡ፣ በቂ የሥልጠናም ሆነ የዝግጅት ሁኔታ ያልነበራቸው፣ ነገር ግን ከየትም የማይበደሩት የአገር ፍቅርና የማሸነፍ ወኔ ያላቸው ውድ ኢትዮጵያውያን ወረራውን በስኬት መቀልበስ መቻላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል።
መንግሥታትን በአገር ውስጥ ክዋኔያቸው በአንድም በሌላም ልንመዝናቸው እንችላለን፤ ነገር ግን የአገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የሚከፈሉ መሥዋዕትነቶች በየትኛውም ዘመን ቢፈጸሙ የአገሪቱ ታሪካዊ ኩራት ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የደርግ መንግሥት በአጭር ጊዜ ጥሪ አቅርቦ፣ አሠልጥኖና አደራጅቶ የአገርን ክብር ለማስመለስ ያደረገው ተጋድሎና ያስመዘገው ድል የሁላችንም የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነትና ለአገር የመሥዋዕትነት የመክፈል ታሪካችን አካል ነው። ሁሌም በውስጣችን ክፍተት ሲኖር የውጭ ጠላት እንጋብዛለን፤ ስንጠናከር ግን የታፈርንና የተከበርን እንሆናለን ብለዋል።
በዚህ አጋጣሚ ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሠልፈው የተዋጉትንና ውድ ሕይወታቸውን የሰውትን የኩባ እና የየመን ወታደሮችን ውለታ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል።
ክብር አገርን ለማቆየት ራሳቸውን መሥዋዕት ላደረጉ ኢትዮጵያውያን! ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2012 ዓም
በጋዜጣው ሪፖርተር