ከሰሞኑ በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ላይ በአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ የወጣው መግለጫ ለግብጽም ሆነ ለአሜሪካ የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያን ከጉዞዋ የማያግዳት መሆኑን ምሑራን ይናገራሉ። መግለጫውም አሉታዊ ተጽዕኖን ሳይሆን ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የማንቂያ ደወል በመሆን ለግድቡ ፈጥኖ ከፍጻሜ መድረስ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ስለመሆኑም ይገልጻሉ።
በናይል ተፋሰስና በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የሚሰሩት አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ እንደሚሉት፤ የአሜሪካ ትሬዠሪ ሴክሬታሪ ያወጣው መግለጫ ከመረን የወጣ እና ከትሬዠሪ ሴክሬታሪው የማይጠበቅ፤ ከተሰጠው ሚና አኳያም ምንም የማያገባውና ለአንድ አካል ያደላ፤ ሚዛን የጎደለውና ፍትሃዊ ያልሆነ ነው። ይሄንን መግለጫም የኢትዮጵያ መንግስት ውድቅ አድርጎታል። ከኢትዮጵያ መንግስት ባለፈም ታዋቂ ግለሰቦች፣ አምባሳደር ዴቪድ ሺንን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ ምሑራን ሳይቀር እያጣጣሉት ይገኛል።
ይሁን እንጂ የዚህ መግለጫ መውጣት ምንም የሚያመጣው ተጽዕኖ የለም። ምናልባትም ተጽዕኖው አዎንታዊ ይሆናል። ምክንያቱም መግለጫውን መነሻ በማድረግ በተለያየ አግባብ እየተደመጠ ያለው ተቃውሞና ቁጣ ለግንባታው ሂደት መፋጠን አዎንታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር ያግዛል። የመግለጫው መውጣትም የአሜሪካንን ሚና በደንብ ያሳየ፤ አቋምና ተሳትፏቸውም በሁሉም ዘንድ ታውቆ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚረዳ ነው። መግለጫውም ምንም እንኳን ጥቅም የሌለው፤ ሂደቱንም ሆነ ማንንም የማይጠቅም ቢሆንም፤ እንደ አገር ግን ይሄንን እንደ መማሪያ ወስዶ ወደፊት በጥንቃቄ የሚኬድበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት ደግሞ፤ ምንም እንኳን ወንዙ ድንበር ተሻጋሪ ቢሆንም የግድቡ ስራ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የሚከናወን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሃብት ነው። ሆኖም ግንባታው ሲጀመር ኢትዮጵያ በቀናነት የሚመለከታቸውን አገሮች አሳትፋለች። ስራውም ማንንም የማይጎዳ ይልቁንም የጋራ ተጠቃሚነትንና ዓለም አቀፍ ህጎችም መሰረት በማድረግ የሚከናወን ስለመሆኑ አስረድታለች። ሆኖም የግብጾች አካሄድ ችግር ያለበትና የብቻ ተጠቃሚነትን መርህ የሚያቀነቅን ስለነበር፤ ይሄን የብቻ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሉም እነርሱ ችግር ውስጥ ገብተዋል፤ ኢትዮጵያንም ወደችግር እንድትገባ እያደረጉ ይገኛል። ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ የግድብ ሰርታ በዓባይ የመጠቀም መብት አላት የሚለውን ላለመቀበል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ እያከናወኑ ይገኛል።
በእነርሱ አረዳድ ደግሞ ለብቻ መጠቀም የሚችሉት ኢትዮጵያ ሳትረጋጋ ስትቀርና የውስጥ ሁኔታዋ ሲረበሽ ነው ብለው ስለሚያምኑ፤ ለኢትዮጵያ እርዳታ እንዳይደርስ፣ የውስጥ ሁኔታዋ እንዲረበሽ፣ ከጎረቤትና ሌሎች አገራት እንድትነጠል ለማድረግ ጭምር የሚችሉትን እየጣሩ ናቸው። ኢትዮጵያ ግን ይሄን ሁሉ ተቋቁማ ግድቡን በራሷ አቅም ለዚህ አድርሳለች።
በዚህ ሂደት ውስጥ በአሜሪካ ግምጃ ቤት በኩል የታየው ሁኔታ በማይመለከተው የመግባት ነገር ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክም አይፈቀድም፤ ዓለምአቀፍ የህግ ማዕቀፍ የለውም፤ የሶስቱ አገራት የጋራ ስምምነትም አይደግፈውም። ይሄን የማድረግ መብትም የለውም። ለምሳሌ፣ አሜሪካ ራሷ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የገነባችው ግድብ 100 በመቶ በባለቤትነት የያዘችው ነው። ከዚህ አኳያ መግለጫው እንደ አገር የአሜሪካ አቋም ሳይሆን የግለሰብ ፍላጎት ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ነው። ምክንያቱም መግለጫው ለግብጽ ቀርቶ ለአሜሪካም ጭምር የማይጠቅም ይልቁንም የዲፕሎማሲ ገጽታዋን የሚያበላሽ ነው። ለኢትዮጵያ ግን ከአሉታዊው ይልቅ አዎንታዊ/በጎ ገጽታን የሚፈጥር፤ በግድቡ ዙሪያ ያላትን የዲፕሎማሲ የበላይነት የሚያሳይ ነው።፡
በቀጣይም ኢትዮጵያ በድርድሩም ሆነ በግንባታው ሂደት በትኩረት እንዲሰራ እና ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ እንድትጓዝ የማንቂያ ደወል የሚሆናት ሲሆን፤ ለግብጻውያንም ቢሆን ለፕሮፖጋንዳ ሊጠቀሙበት ካልሆነ በስተቀር አዋጪው መንገድ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችው አማራጭ መሆኑን ያስገነዝባል። እናም መግለጫው ኢትዮጵያውያን እንዲነቁና እንደ እድል የሚጠቀሙበት ሊሆን ይገባል።
አቶ ፈቅ አህመድ እንደሚሉት ደግሞ፤ ኢትዮጵያ አጋጣሚውን እንደ እድል ወስዳ ከመስራት አኳያ አገራዊ አቅምን እና አንድነትን መፍጠር የመጀመሪያው ስራ መሆን አለበት። ህዝቡም እየተደረገ ያለውን ነገር በግልጽ አውቆ ድጋፉን እንዲሰጥና ለእነዚህ ሃይሎች ያለውን ተቃውሞ በተለያየ መልኩ እንዲያሰማ ማድረግ ይቻላል። ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንም በዚህ ላይ እየሰሩ ሲሆን፤ ህዝቡም በግድቡ ዙሪያ ከመጀመሪያው በላቀ በተጠናከረ መልኩ መሳተፍና ማገዝ ይኖርበታል። የህዝቡ በጋራ መሰለፍ ደግሞ አቅምን ይፈጥራን፤ ተጽዕኖን ማሳደር ያስችላል።
ከዚህ ባለፈ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ በተለይም የላይኛው ተፋሰስ አገራት ግብጽ እየፈጠረች ያለውን ውዥንብር በግልጽ በመግለጽ የቀደመ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ማስቻል፤ እና ሌሎች የተለያዩ የዲፕሎማሲ መድረኮች ማከናወን ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ የናይል ተፋሰስ አገራት በአብዛኛው ተመሳሳይ አቋም ስላላቸው በዚህ ዙሪያ ማሰለፍ ይገባል። ድርድሩም መቀጠል ያለበት ሲሆን፤ በድርድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ አገራትም ሚናቸው ተለይቶ ታዛቢ መሆን ይችላሉ። በዚህ ረገድ ወደፊት ጫና ሊመጣ ይችላል ቢባል እንኳን የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ መድረክን ጨምሮ፣ ኢጋድን እንዲሁም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗም የአፍሪካ ህብረትን ብሎም ሌሎች ተቋማትና ማህበረሰቦችን በማሳተፍ ጫናውን ማለዘብ ይቻላል። ከዛ ውጪ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በሚወስኑት ሁኔታ ግድቡን ማጠናቀቅም ኃይል ማመንጨትም ይቻላል፤ በዚህ ዙሪያ ምንም ተጽዕኖ አይኖርበትም። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ዲፕሎማት ሆኖ በኃላፊነት ስሜት መስራት ይገባል።
አቶ እንዳለ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ጉዳዩ የኢትዮጵያ ህዝብ የመንግስትንም ሆነ የተደራዳሪዎቹን ጥንካሬ መመልከት የቻለበት እንደመሆኑ እምነትን የሚያሳድርበትንና በንቃት የሚከታተልበትን እድል የሚሰጠው ነው። ይህ ደግሞ የነቃ የህዝብ ተሳትፎን ይዞ ግድቡንም በቶሎ ለማጠናቀቅና የሙሌት ሂደቱንም ለማቀላጠፍ የማንቂያ ደወል ይሆናል። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ የውስጥ የቤት ስራዋን በተለይም የውስጥ አንድነትና ጥንካሬ ላይ ትኩረት ሰጥታ መስራት አለባት። አካሄዱ የሉዓላዊነት ጉዳይ እንደመሆኑም በውጭም በውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ በመሰረታዊ የጋራ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ መግባባትና የጋራ አቋም መያዝ ይጠበቅበታል። በዚህ መልኩ በውስጥ ጠንካራ መሆን ሲቻል ማንም አካል ያከብራል፤ የሚባለውንም አምኖ ይቀበላል። በመሆኑም በሃሳብም፣ በገንዘብም፣ በጉልበትም ለግድቡ ከዳር መድረስ ሁሉም ሊተጋ ያስፈልጋል።
ከዚህ ባለፈ በዲፕሎማሲው ላይ በትኩረት መስራት ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን በውጭም በውስጥም ያለ ዜጋ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ማንንም ሳይጠብቁ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ስራው እንደ አድዋው ሁሉ ጠንካራ እርምጃና ስራን የሚፈልግ ነው። በተመሳሳይ የናይል ጉዳይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ የሚመለከታቸው 11 አገራት አሉ። ስለዚህ በናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ አማካኝነት ተስማምታ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካጸደቀችው የስምምነት ማዕቀፍ የወጣ ጉዳይ እንደማይኖር አውቆ ማስገንዘብ፤ ከኢጋድ ጀምሮ የአፍሪካ ኅብረትን፣ የአውሮፓ ህብረትን እንዲሁም እንደ ሩሲያና ቻይና ያሉ አገራትን ጨምሮ የአፍሪካ አገራትም በጉዳዩ ላይ ማሳተፍ ያስፈልጋል።
መግለጫው ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያላቸውን የኢትዮጵያና አሜሪካን ግንኙነት አይጎዳም። አሜሪካም ግንኙነቱን ትፈልገዋለች። ከዚህ ባለፈ የእርዳታ ጉዳይ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ከብሔራዊ ጥቅም የዘለለ አይደለም። ያለእነርሱ እርዳታ ኢትዮጵያ የፈለገችውን መስራት እንደምትችል ደግሞ የህዳሴው ግድብ ማሳያ ነው። እርዳታዎቹም ቢሆኑ ቢዘገዩ እንጂ የሚቀሩ አይደሉም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ሳታቋርጥ ድርድሩንም እንደ ቀድሞው ሁሉ በብስለትና በጥንቃቄ መቀጠል ይኖርባታል።
እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ፤ የግድቡ ጉዳይ የሴኩሪቲ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ግብጽ እስካሁን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የተቻላትን ሁሉ የምታደርገው ግድቡ እውን እንዳይሆን በማሰብ ነው። ሆኖም የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ግድቡን ማፋጠንና ከዳር ማድረስ ከተቻለ ግብጽም ተስፋ ቆርጣ እጇን ስለምትሰበስብ የአካባቢው ሰላም ይረጋጋል። ምክንያቱም በውጭም ሆነ በውስጥ እየተሽከረከረች የምታደርገው የእጅ አዙር ብጥበጣውም ይቆማል። ይሄን ማስረዳት ደግሞ ግልጽ ሆኖ መስራትና ማስረዳት የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን የካቲት 27 /2012 ዓም
ወንድወሰን ሽመልስ