የአድዋን ድል ለማክበር የትውልዱ ተረኛ ወጣት በነቂስ ወጥቷል:: ያስገመግማል:: ያጉተመትማል:: ሆ በል ይላል:: በባህላዊ አልባሳትና በጥንት አባቶች የጦር ሜዳ አለባበስ ተውቦ ደምቋል:: አባት አርበኞች ጋሻና ጦር ጎራዴ ይዘው ቁጭ ብድግ እያሉ በወኔ ተሞልተው ይሸልላሉ:: ያቅራራሉ:: ይፎክራሉ:: ‹‹በለው ሲል ገዳይ…ያንን ጥልያን ከተረተሩ ከጉድባው ላይ›› እያሉ:: እናቶች ወጣት ሴቶችና ወንዶች የአባቶችን ወኔና ጀግንነት በማወደስ እልልታውን ያቀልጡታል:: እልልል እንደገና:: እልልል እንደገና:: እንደገና:: የዘንድሮው የአድዋ ድል በምኒሊክ አደባባይ ሲከበር ከሰሞኑ የአሜሪካም መንግስት ለግብጽ በማድላት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሀ መሙላት ስራ አሜሪካ የጀመረችው ማደራደር ሳይቋጭ ኢትዮጵያ እንዳታካሂድ የሚል ቀጭን የድፍረት ትእዛዝ ለኢትዮጵያ ማስተላለፉን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነቂስ ሰምቷል:: ክፉኛ አዝኗል:: ተበሳጭቷል:: ቁጣው ገንፍሎ ይታያል::
ይህን የሰሙ አንድ አባት አርበኛ እዛው ጊዮርጊስ ምኒሊክ አደባባይ ላይ ዙሪያቸውን ለነበሩት አባት አርበኞች ከፍ ባለ ድምጽ የአድዋን ድል በኩራት ስናከብር ሌላ ግራዚያኒ ትራምብ የሚባል ደግሞ መጣብን አይደለም ያሉ ግዜ ዙሪያ ገባው በአባት አርበኞች ሽለላና ቀረርቶ አስተጋባ:: እምቢ ለሀገሬ…እምቢ …እምቢ ለጠላት እምቢ…ኢትዮጵያ ሀገሬ …የነብሮች እናት…የአምበሶች እናት …እልፍ ጀግና አለ የሚሞትላት…ማንአባቱ ነው ችሎ ሚደፍራት…እያሉ አባት አርበኞች በፈላ ወኔ በሚፋጅ ቁጣ ወዲያና ወዲህ እየተንቆራጠጡ ወደፊት እየሄዱ ደሞ ወደኋላ እየተመለሱ ይይዙትን ይጨብጡትን አጡ:: ደሞ የማናባቱ ወሮበላ ነው ትራምብ የሚባለው አሉና አንዱ አርበኛ ጠየቁ:: እንጃለቱ አሉና ቆፍጣናዋ የሴት አርበኛ መለሱ::
ምንድነው ደሞ ትራምብ ብሎ ስም ለጠቁ ሌላው አርበኛ:: ይሄ የሰው ሳይሆን የአጋንንት ስም መሆን አለበት አሉ ከአርበኞቹ ጋር የተሰለፉት ባለነጭ ጥምጣሙ መምሬ:: ሁሉም በአንድ ግዜ የተማከሩ ያህል ልክ ነው፤ ልክ ነው ሲሉ በአደባባዩ አስተጋቡ:: እዚህም እዚያም ጭፈራው ሆታው ሽለላው ፉከራው ቀልጧል:: አራዳ ጊዮርጊስ አደባባዩ ያለወትሮው ደምቋል:: ፈክቷል:: አንዳች ግርማ ሞገስ የተደፋበት መስሏል::
ይሄ ትራምብ የምትሉት ጨፈረር ኢትዮጵያን ሲጣላ፤ ለመሆኑ ማንን እንደነካ ያውቃል፤ መጥፊያው ደርሶ ነው:: የኢትዮጵያ መሪ አሳዳሪ ጠባቂ ሰው ሳይሆን እግዚአብሄር ነው:: ኢትዮጵያን በመዳፈሩ የአምላክ ፍርድና ታላቅ ቁጣ በእሱም በሀገሩም ላይ ይወርዳል አሉ፤ የቄሱ ጓደኛ መሪጌታ ገብረአምላክ:: የተመካበት መሳሪያ፣ ቴክኒዮሎጂ፣ ሳተላይት፣ መንኮራኩር፣ የስለላ ድሮን በሰማይ በውቅያኖስ በምድር በባህር ያሰማራውና የታበየበት ሰራዊት ኃያልነት ሁሉ በአምላክ ፊት ምንም ናቸው:: እንደ ጉም በኖ ይጠፋል:: ይፈራርሳል:: ሀገሩ ምድረበዳ ትሆናለች:: ሰውም አእዋፍም አይኖርበትም:: ታላላቅ ነን የሚሉት ሀገራት መሪዎችና አለምን ያንቀጠቀጠው ወራሪና እብሪተኛ ሠራዊታቸው ሁሉ በአምላክ ክንድ ይደረመሳል አሉና ዝም አሉ:: መምሬ ቀጠሉና የኢትዮጵያ አምላክ ከነኩት ቁጡ ነው:: ሲያሻው በመሬት መንቀጥቀጥ፤ በመብረቅ፤ በአውሎ ንፋስ፤ በክፉ ማእበል፤ በውሀ ሙላት ይመታቸዋል:: ያጠፋቸዋልም:: እነሱ ከፈጣሪ በላይ ነን ብለው አለምና ምድሪቱን ሁሉ ገዢዎቹ መሪዎቹ አስተዳዳሪዎቹ እኛ ብቻ ነን ብለዋል:: ይሄኔ ነው መፍራት አሉ መምሬ::
እንግዲህ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እንዲሉ መጪውን ሁሉ በጥሞና በማስተዋልና በአርምሞ መጠበቅ ነው አሉ:: በበአሉ ላይ ከአርበኞቹ ጋር የታደሙት ሙሉ ቢጫ ከላይ እስከታች የለበሱ ጸጉራቸው ከአናታቸው ወርዶ መታጠቂያቸው ድረስ የተንዠረገገው በሰንሰለት ወገባቸውን የታጠቁት አባ አለም በቃኝ የተባሉ ባሕታዊ:: አባታችን በህልምዎ ነው በምናብ ነው አርምሞውን ያዩት ሲሉ አርበኞቹ ጠየቋቸው:: ሁለቱንም አይቻለሁ አሉ ባህታዊው ረዥሙን ጫፉ ጦር ያለበትን መቋሚያቸውን ተደግፈው:: አባት አርበኞቹ ለአፍታ በዝምታ ተዋጡ:: ወዲያው የበአሉ ጭፈራና እምቢ ለሀገሬ የሚለው ሆታና መዝሙር አነቃቸው::
ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም…እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውድም…የደፈረሽ ይውደም የሚለው የወጣቶች መዝሙር ጎልቶ ይሰማል:: ይሄኔ አባትና እናት አርበኞች እየፎከሩ ተንጫጩ:: እሳት ቢያንቀላፋ…ገለባ ጎበኘው…ባያውቀው ነው እንጂ ባይጠራጠረው…ዘራፍ የኢትዮጵያ ልጅ…ለነጻነቱ በደም የሚዋጅ… ትራምብ የሚባል ሆዳም አውደልዳይ…የግብጾች አሽከር ከርከሮ መሳይ…ሲያናፋ ቢውል እንደ አህያ…ወግድ ክላ አለው ጀግናው ኢትዮጵያ ብለው ፈከሩ ሸበቶውና ደረታቸው በሜዳሊያ የተንቆጠቆጠው አባት አርበኛ:: በእልልታና በጭብጨባ በሆታ በፉከራ አካባቢው ተደበላለቀ::
ሌላው አርበኛ ተቀበሉና ቀጠሉ:: ለዚያ ሰላቶ ትራምብ ለሚሉት …ለነጫጭባው…ንገር ሂድና…ጦር ልማዱ ነው የኢትዮጵያ ጀግና…ለሀገሩ ይሞታል ደግሞ እንደገና…የታመነ ነው በቃሉ የጸና…ብለህ ንገረው…እስከሚገርመው…ዘራፍ የአምዮ ልጅ የኢትዮጵያ…ከእናቱ በፊት ጥሎ ሚወድቀው …የወኔው ግለት…የሚጋረፈው…ዘራፍ የአባቶቹ ልጅ ….ነበልባል ቋያ… ሰደድ እሳቱ…መጠቃት ሞቱ…መደፈር… ሞቱ …የማይሳሳ ለአንድ ሕይወቱ…ብለህ ንገረው ትራምብ ለሚሉት…ለግብጾች ፈረስ ለሚጋልቡት…ዘራፍ የመይሳው ልጅ የነዮሀንስ የነአባ ዳኘው…የነጎበና የነአባ ዳጨው የነጃገማ የእነ ባልቻ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ…ብለህ ንገረው ለዚያ ለትራምብ እስከሚገርመው እያሉ አርበኛው በቁጣና በጋለ ወኔ እየሸለሉ ሲንደቀደቁ አካባቢው አረገደ::
የአድዋ ድሉን 124ኛ አመት ለማክበር የተሰበሰበው ሕዝብ በሆታ አስተጋባ እምቢ ለሀገሬ እያለ:: የአሜሪካንን መግለጫ ከ2 ቀን በፊት ሕዝቡ ሰምቶ ስለነበር ቁጣውን በባህሉ መሰረት በተለያየ መንገድ ሲገልጽ ውሎ ከአባቶቹ ጋር ወደ ቤቱ ተመለሰ:: ለሀገራቸው ክብር የሚቆሙ ጀግና ወጣቶች ስለተካን ክበር ተመስገን አሉ- አዛውንቶቹ አባትና እናት አርበኞች:: ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ውሀ እንዳትሞላ የሚለው የአሜሪካ ድፍረትና ንቀት የተሞላበት ሉአላዊነታችንን የደፈረ አቋም እጅግ ከፍተኛ የማይበርድ ሕዝባዊ ቁጣን ቀሰቀሰና አረፈው አለ አንዱ የበአሉ ታዳሚ ወጣት:: እብሪትና ድፍረት መዘዙ ብዙ ነው አሉ አባት አርበኛ ደጋጋ ሁንዴ:: ኢትዮጵያን መናቅ መድፈር ታላቅ ዋጋ ያስከፍላል ብላችሁ ለትራምብ ንገሩት አሉ ደገሙና ወደ ወጣቶቹ ዞረው:: ወጣቶቹ ይህን ግዜ እንደ መሳቅ ብለው – አባባ አባባ ትራምብ እኮ አማርኛም ኦሮሚኛም አይሰማም አሏቸው:: የት አባቱ አሉና በዛው በሱ ትብታብ ቋንቋው ንገሩት:: ከእኛ ላይ ይውረድ:: ትራምብ ለግብጽ አሽከርም ገረድም መሆን መብትህ ነው በሉት:: ከኢትዮጵያ ትከሻ ግን ይውረድ አሉ መለሱና:: እምቢ ካለ የኢትዮጵያ ታላቅ አምላክ ሳይውል ሳያድር የሚሰጠውን ፍርድ ይጠብቅ እንዲያውም ተውት አሉ- አርበኛ ደጋጋ ሁንዴ::
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2012
ወንድወሰን መኮንን