የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአዲስ አስተሳሰብና አሰራር መቃኘት ከጀመረ ከሁለት ዓመት ወዲህ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያከናወኑ ባለው ተግባር የህዝብ ድጋፍ አልተለያቸውም:: በቅርቡም በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ታላላቅ የድጋፍ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወሳል:: በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ወጣቶች ለድጋፍ ሰልፉ ያነሳሳቸውን ምክንያት እንዲህ ይገልጻሉ::
ወጣት አምዴ ቶሎሳ የደገም ወረዳ ነዋሪ ነው:: አምዴ ድጋፍ ለመስጠት ያነሳሳውን ምክንያትም እንዲህ ያስረዳል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በርካታ ተስፋ ሰጪ ተግባራት አከናውነዋል:: ትናንት ስልጣንን መከታ አድርገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ የነበሩና የህዝብና የመንግስትን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉ የነበሩትን ተጠያቂ አድርገዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተረከቡትን የሀገሪቱን የተራቆተ ካዝና ለመሙላት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ዲፕሎሚሲያዊ ግንኙነትን በማጥበቅ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ አድርገዋል:: በግፍ እስር ቤት ተወርውረው የነበሩ ዜጎችን አስፈትተዋል:: ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሀገራቸው ገብተው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥተዋል:: እውነተኛ ፌደራላዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በሀገሪቱ እንዲተገበርም ጅምሮችን አሳይተዋል:: ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እያደረጉ ያሉት ትኩረትም ተስፋ ሰጪ ነው:: በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርጉት ጥረትም ዓለም የመሰከረው ነው ይላል- ወጣት አምዴ::
‹‹እኔ የጀነራል ታደሰ ብሩ ልጅ ነኝ:: ጀነራል ታደሰ ብሩ ስለኦሮሞ ህዝብ በደል የሚቆጭ፣ የኦሮሞ ህዝብ እንዲማርና አንድነቱን እንዲጠብቅ ወደ አመራርነት እንዲመጣም የሚፈልግ ሰው ነበር:: ዶክተር አብይም የጀነራል ታደሰ ብሩን ህልም እውን ያደረገ መሪ ነው:: ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ከህዝብ ላይ የጭቆናን ቀንበር ያነሳና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ ተስፋን ይዞ የመጣ መሪ በመሆኑ እደግፈዋለው::›› የወጣቱ ሀሳብ ነው::
አሁንም የኢትዮጵያ መጻኢ እድል ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲታነጽ የህዝቦች እኩልነትና አንድነትን ለማጠናከርና የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠን እንዲያግዝ የብልጽግና ፓርቲን እውን አድርገው በመነሳታቸው ልደግፋቸው ተነሳስቻለሁ ይላል – አምዴ:: ዶክተር አብይ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ተስፋ ናቸው:: እርሳቸውን መደገፍ ከገባንበት ችግር ሁሉ የምንወጣበት ብቸኛ አማራጫችን ነው:: የኦሮሞ ህዝብም በሀሳብ መለያየቱንና መከፋፈሉን ትቶ በአንድ ልብ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንዳለበትና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር አንድነቱን በማጠናከር የክልሉንም ሆነ የኢትዮጵያን ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚገባው ወጣት አምዴ ይመክራል:: አጠቃላይ በሀገሪቱ የሚገኙ ወጣቶችም የተለያየ አጀንዳ ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተጠለፉ አላስፈላጊ ተግባራትን ከመፈጸም ይልቅ ይህን ወርቃማ ጊዜ ተጠቅመው ትኩረታቸውን በስራ ላይ እንዲያደርጉ ይሻላል ይላል ::
ፍቅሩ ግርማ ሌላው የድጋፍ ሰልፉ ታዳሚ ነው:: የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ከዶክተር አብይ አህመድ ጋር ወደ ፊት መጓዝ ለክብሩ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው:: አመራሮች ባደረጉት ትንቅንቅና ወጣቶች በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን ይህን የብርሀን ጭላንጭል አዳፍነው ወደ ቀድሞው ጭለማ ሊመልሱን እየሞከሩ ያሉ አካላትን በአንድ ድምጽ ልንቃወማቸው ይገባል ይላል:: ዛሬ የተሰጣቸውን ዲሞክራሲያዊ መብት በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ህገ ወጥ ስራ የሚፈጽሙ አካላት ትናንት ባልሰሩት ሥራ ምን ያህል በደል ሲፈጸምባቸው እንደነበር ማስታወስ ይኖርባቸዋል:: አንዳንዶቹም በነበረው ፖለቲካ ምክንያት በሰው ሀገር ተሰደው ይኖሩ እንደነበር መርሳት የለባቸውም ይላል – ክብሩ:: እንደ ልባቸው እንዲናገሩ፤ እንደ ፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ ያደረጋቸውን ይህን ለውጥ ተንከባክበው ወደፊት ማራመድ ሲገባቸው ወደ ኋላ ሊመልሱ መሞከራቸው የሚያሳፍር ነው ይላል::
ዶክተር አብይ እስከ አሁን እያደረገ ባለው ነገር ሁሉ ደስተኛ በመሆኔ ሁሌም ከጎኑ እንደምቆም በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ የሚለው ወጣት ፍቅሩ፤ ብልጽግና ፓርቲ ለኦሮሞ ህዝብም ይሁን ለመላው ኢትዮጵያዊ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ህብረተሰቡ ድጋፍ በማድረግ ከውጤቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እመኛለሁ ይላል:: ለኦሮሞ ህዝብ በተለይም ለወጣቱ ባስተላለፈው መልዕክትም ከምንም ጊዜ በላይ አንድነቱን አጠናክሮ በመቀጠል ከለውጡ በፊት የነበረውን አንድነትና መተባበር በማስቀጠል ለውጡን ለፍሬ ማብቃት ይኖርበታል ይላል:: በተለይም ወጣቶች በግለሰቦች እየተመሩ በግብታዊነት ተነሳስተው ከሚፈጽሟቸው ህገ ወጥ ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚገባቸው ይመክራል:: ዶክተር አብይ በሀገሪቱ የሚንጸባረቁ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ወደ አንድ ለማምጣት ሲጥሩ አካሄዳቸው ሁሉንም አካል ላያስደስት ይችላል፤ ነገር ግን አስቀድመን ሀገርን የምናስብ ከሆነ የዶክተር አብይ አካሄድ ትክክለኛ መሆኑን ልንረዳ እንችላለን ይላል-ወጣት ክብሩ::
በሰልፉ ላይ ከታደሙት ወጣቶች ሌላው ግዛቸው ረታ ይባላል:: ግዛቸው ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ያከናወኗቸው ተግባራት እንዳስደሰቱት ይገለጻል:: የመላው ህዝብ የትግል ውጤት የሆኑና በአዲስ አስተሳሰብና ፍልስፍና ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ይዘው የመጡ መሪ መሆናቸውን ያስረዳል:: የእኚህን መሪ ዱካ መከተልና ሃሳባቸውን መደገፍ የዘወትር ተግባሩ አድርጎታል:: ዶክተር አብይ ስለሰላም፣ ስለእኩልነትና አንድነት፣ ስለ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት፣ስለልማትና ብልጽግና፣ ስለመፈቃቀርና መከባበር፣ ስለመቻቻልና ይቅርባይነት የሚያቀነቅኑና በተግባርም ያሳዩ መሪ ናቸው ይላል:: የዶክተር አብይ መንግስት በተለይም ለወጣቱ ልዩ ትኩረት መስጠቱና የስራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ድጋፍ ቢታከልበት ችግር ፈቺ እንደሆነ ይጠቅሳል:: ወጣቶች ከለውጥ ሃይሉ ጋር ተቀራርበው ቢሰሩ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንላቸው አመላክቷል:: በተለይም ወጣቱ ከለውጡ ውጤት ተቋዳሽ እንዲሆን ከዶክተር አብይ
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2012
ኢያሱ መሰለ