መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የያዘውን አቅጣጫ ተከትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን እውን ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ:: ዘርፉን የሚመሩ ተቋማትም ሙያዊ እገዛና ድጋፍ በማድረግ ምቹ የሥራ ሁኔታን በመፍጠር የኢንዱስትሪውን ዞን ጤናማነት ለማስጠበቅ ይታትራሉ::
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች በተፋጠነ መልኩ እንዲስፋፉና የማኒፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፣ በዘርፉ የሚታየውን የክህሎት ክፍተት በመሙላት የተደራጀ የኢንዱስትሪ ግብዓት ድጋፍ በማድረግ ዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን የማስቻል ተልዕኮ ይዞ እየሰራ ያለ ተቋም ነው:: ተቋሙ በሳሙና፣ በቀለም፣ በማዳበሪያና በፔትሮ ኬሚካል፣ በፐልፕ ወረቀትና ወረቀት ውጤቶች፣ በመሰረታዊ ኬሚካል፣ በጎማና ፕላስቲክ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ከኮንስትራክሽን ግብዓቶች በሲሚንቶ፣ በሴራሚክ፣ በመስታወት፣ በፈርኒቸር፣ በማርብል በግራናይትና በቴራዞ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲመረቱ ድጋፍና ክትትል የማድረግ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል::
የኬሜካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ ተቋሙ በ2012 በጀት ዓመት አጋማሽ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አስረድተዋል:: በተለይም ፋብሪካዎች የካይዘንን አሰራርና ፍልስፍና እንዲተገብሩና ምርታማነታቸውን እንዲያሰድጉ ከማድረግ አንጻር የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አስታውሰዋል::
የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ድርሻን ከማሳደግ አንጻር በበጀት ዓመቱ አጋማሽ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግበዓቶች ዘርፍ የኢንዱስትሪውን ኢኮኖሚ ድርሻ ከስምንት ቢሊየን ብር በላይ ማድረስ መቻሉ ተጠቅሷል:: የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ድርሻ በዚህ ደረጃም ቢሆን ለማደጉ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች ኢንዱስትሪዎች የታሪፍ ማበረታቻ ተጠቃሚ መሆናቸው፣ የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ እንዲያገኙ መደረጉ፣ አዳዲስ የውጭ ባለሃብቶችን መጋበዝ መቻሉ፣ ማስፋፊያዎች መበረታታቸውና አዳዲሶችም ወደ ማምረት እንዲገቡ መደረጋቸው መሆኑ ተጠቅሷል::በኢንስቲትዩቱ የኢንቨስትመንት ካፒታል ዕድገትንም ሁለት ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር ማድረስ እንደተቻለ ተገልጿል::
በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ በመጀመሪያው ግምሽ ዓመት የማምረት አቅም አጠቃቀምን ማሳደግ ተችሏል:: ለዚህም የረዳው በኢንዱስትሪዎች የሙያ ምዘና፣ የግብዓት አቅርቦት ድጋፍ፣ የእርስ በእርስ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር መደረጉና በጥራት ወደ ውጭ ሀገር ልከው እንዲያስፈትሹ በመደረጉ መሆኑ ተጠቅሷል:: በኬሚካል ኢንዱስትሪ ዘርፍ የምርቶችን አጠቃላይ ዋጋ ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉም ተገልጿል:: ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተያዘው እቅድም በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከተያዘው ዕቅድ ከሰባ በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉ ተጠቁሟል::
የሀብት ምንጭን ከማሳደግ አንጻር ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነት በመፍጠር አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል:: ለአብነትም ከጃፓን መንግስት በተገኘ ድጋፍ አገልግሎት የሰጡ ጎማዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል:: ከሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች የሚመነጨውን የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ ከአውሮፓ ህብረት የስምንት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ተገኝቷል::
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓመት 17 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠር ቢቻልም እየተመረተ ያለው ከዘጠኝ ሚሊዮን ቶን እንደማይበልጥ ከመድረኩ ተገልጿል:: ለዚህ እንደምክንያት የተጠቀሱት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል አለመኖር፣ የፋይናንስ አቅርቦት በተለይም የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የሀይል አቅርቦት መዋዠቅና መቆራረጥ፣ የግብዓት አቅርቦትና የሀገሪቱ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ባለማምረታቸው እንዲሁም በየጊዜው በሀገሪቱ እየጨመረ በመጣው ግንባታ ምክንያት ሲሚንቶን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሂደቱ እየቀነሰ መምጣቱም ተገልጿል:: በዚህም ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ እንደቀነሰ ተጠቁሟል::
ባለፉት ስድስት ወራት በዘርፉ ወደ ግንባታ በገቡና የማስፋፊያ ስራ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለአራት ሺ 987 ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ከነዚህም አንድ ሺ 464 የሚሆኑት ሴት መሆናቸው ተቋሙ አሳውቋል::
ተቋሙ የግማሽ ዓመቱን አፈጻጸም በገለጸበት ወቅት በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል:: ሱዞ ኢንዱስትሪ ያገለገሉ ወረቀቶችን በግብዓትነት በመጠቀም በይበልጥም ሶፍት በማምረት ሥራ ላይ የተሰማራ ፋብሪካ ነው:: እንደ ችግር የጠቀሰውም በተለያዩ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት የሰጡ ወረቀቶች የሚወገዱበት መንገድ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ መንግስት ደንብ አውጥቶ ጥቅም የሰጡ ወረቀቶች ለፋብሪካዎች ግብዓት እንዲውሉ የሚያደርግ አሰራርን እንዲከተል ይመክራሉ:: መንግስት ኢንዱስትሪዎችን በመጋበዝ ሥራ ከማስጀመር ባሻገር ሥራ ከጀመሩ በኋላ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እየለየ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ይገልጻሉ:: በየቢሮው ያለአግባብ የሚባክኑ ወረቀቶች እያሉ ፋብሪካዎች በግብዓት እጥረት ስራቸው መስተጓጎሉ ቅንጅታዊ አሰራር ያለመኖሩን የሚያመለከት ነው ብለዋል::
የሲካ አብሲኒያ ኮንስትራክሽን ኬሚካል ፋብሪካ ተወካይ በበኩላቸው ባነሱት ችግር ፋብሪካው ሰማኒያ በመቶ ግብዓት የሚያገኘው ከውጭ እንደሆነ በመጥቀስ በምንዛሬ እጥረት ጥሬ እቃ ማስገባት ባለመቻሉ ስራው መስተጓጎል እንደሚገጥመው ገልጸዋል:: በተያያዘም ፋብሪካው የሚያመርተውን ምርት ለውጭ ገበያ አቅርቦ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሲሞከርም በ28 ቀናት በሽያጭ የተገኘውን ዶላር መጠቀም ካልተቻለ ብሄራዊ ባንክ ዶላሩን ወደ ብር እንደሚቀይርባቸው ገልጸዋል:: ይህ የመንግስት አሰራር ቢሆንም ብሩን ለማስለቀቅ በሂደት ላይ እያሉ የተሰጠው ጊዜ እንደሚያልቅባቸውና የግብዓት እቃዎችን ለመገብየት የሚያስችል ጊዜ ያለመሆኑን ይጠቅሳሉ:: በሌላ በኩል እውቅናና ደረጃ የማሰጠት ችግር መኖሩንም ያነሳሉ::
ለተነሱ ሀሳቦች በተሰጠው ምላሽም ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት የመንግስት ዋና የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ በመግለጽ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላት ልምድ አናሳ መሆኑን ተከትሎ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸው እውን እንደሆነ ተገልጿል:: ተቋሙ ወደፊት ክትትልና ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሰራ ተገልጿል::
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2012
ኢያሱ መሰለ