አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ900 በላይ ለሚሆኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ፡፡አገልግሎት መስጠት የጀመሩት 275 ብቻ ናቸው።
የኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፈቃድ የተሰጣቸው የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የቱርክ፣ የቻይና፣ የአሜሪካና የጀርመን አገር ትልልቅ ኩባያዎች ናቸው፡፡
ፈቃድ የተሰጣቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በሦስት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሂደቶች ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ የሂደት ደረጃዎቹ ቅድመ ትግበራ፣ ትግበራ እና ወደ አገልግሎትና ምርት የተሸጋገሩ ተብለው እንደሚከፈሉ ተናግረዋል፡፡ በቅድመ ትግበራ ሂደት ባለሀብቶች ፈቃድ ካወጡ በኋላ ወደ ትግበራ ለመግባት አስፈላጊውን ሁኔታ ለማሟላት የሚንቀሳቀሱበትና የኢንቨስትመንት ሂደት የሚጀመርበት ሲሆን፤ትግበራ ደግሞ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የግንባታና የመሳሰሉ አስፈላጊ ሥራዎች የሚከናወኑበት ነው፡፡ ሦስተኛው ሂደት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱ አገልግሎት ወይም ምርት መስጠት የሚጀምርበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ መኮንን ገለጻ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት መካከል 500 ያህሉ በቅድመ ትግበራ ሂደት ላይ ሲሆኑ፤ በትግበራ ላይ የሚገኙት ደግሞ 136 ናቸው፡፡ ወደ ምርት ወይም አገልግሎት መስጠት የተሸጋገሩ ደግሞ 275 ናቸው፡፡
የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ የተሰማሩት በግብርና፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 4/2011
ሰላማዊት ንጉሴ