በድሮ አጠራር ከፋ ክፍለ ሀገር ኩሎ ኮንታ አውራጃ ቢሻዬ ወረዳ፤ በአዲሱ አጠራር በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ዞን ኢሰራ ወረዳ ነው የተወለዱት። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት እዚያው ነው። በትምህርታቸውም ጠንካራ ስለነበሩ አንደኛ ደረጃ የእርሳቸው ብቻ ነበር። የስድስተኛና የስምንተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ውጤታቸውም ከፍተኛ ነበር። አባታቸው እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማሩ የገጠር የወረዳ ፋይናንስ መስሪያ ቤት የስራ ሃላፊ ይሁኑ እንጂ በጣም ጎበዝ ተማሪ ስለነበሩ ሞዴል ሆነውታል።
ለአፈወርቅ ጉብዝና የእናታቸው የወይዘሮ ተዘራወርቅ ይመኑ ሚናም ከፍተኛ ነበር። በ1982 ዓ.ም የ 12 ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ተፈትነው በማለፋቸው ለከፍተኛ ትምህርት አስመራ ዮኒቨርሲቲ ተመደቡ:: በወቅቱ በነበረው ጦርነቱ ወደ ስፍራው ሳይሄዱ አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋክልቲ ገቡ። ከምርቃት በኋላም በእዚሁ ዩኒቨርሲቲ ስራ ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ረዳት ምሩቅ በህክምና ሳይንስ ኮሌጅ በመምህርነት ተመደቡ።
ከመምህርነት እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት፤ ከረዳት ምሩቅነት እስከ ሙሉ ፕሮፌሰር የደረሱት ጎንደር ዮኒቨርሲቲ ነው። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ፣ በሶስተኛ ዲግሪያቸውን ጃፓን ቶኪሽማን ዩኒቨርሲቲና አሜሪካን ኮሎራዶ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል። ከ150 በላይ የምርምር ስራዎች ጽፈው በአገር አቀፍና አለም አቀፍ የምርምር መጽሃፎች ላይም አሳትመዋል። በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታነትና በዲፕሎማትነት ሰርተዋል። የአሁኑ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የዛሬው የተጠየቅ እንግዳችን ናቸው።
አዲስ ዘመን፤ እርስዎ እየመሩት ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የመቋቋሙ አላማ ምን ነበር?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ የቀድሞው የትምህርት ሚኒስቴር አሁን ለሚገኙት ሕዝቦች የሚያስፈልገውን እውቀትና ክህሎት እንዲያሸጋግር ሃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። በአደረጃጀት አጠቃላይ ትምህርት የሚባል ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል፤ በመሃል ደግሞ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አለ። ቀጥሎም ትምህርትና ስልጠና አለ። ይሄንን በሙሉ ተሸክሞ ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች መስጠት፣ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሃብት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፍላጎት አዘጋጅቶ ማቅረብና በትስስር መስራት የሚያስፈልጉትን ዘመናዊ ነገሮችን በሚፈለገው ደረጃ መስራት አልቻለም።
በመሆኑም ጥናት ተሰርቶ ትምህርት ሚኒስቴር ሶስት ቦታ እንዲሆን ሃሳብ ቀረበ። እነዚህም አጠቃላይ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ስልጠናና የከፍተኛ ትምህርት ናቸው። የቀድሞው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርም ሳይንስና ቴክኖሎጂንና ፈጠራን እንዲመራ ተብሎ የተፈጠረ ነው። እድገት የሚለካው በቴክኖሎጂ አቅም ክምችት ነው። ሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂ ክምችቱን ማምጣት አለበት። መሰረቱ ደግሞ ሳይንስ ነው። ፈጠራ ስራዎች መምጣት አለባቸው። የተግባራዊ ሳይንስ ስራ እየመራ የሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ስራ በማስገባት ከውጭ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችንም በማምጣትም ለኢንደስትሪው ፍላጎት፣ በአገልግሎት ዘርፉ ፍላጎት፣ በአገር ፍላጎት ማያያዝና ፈጠራ እንዲሰሩ ማድረግ ለእዛ ኢንደስትሪ ሰፊ ስራ ነው። ሲጠና ሚኒስቴሩ ትኩረቱን ከእድገት ጋር ለመጓዝ ፈጠራ ላይ በማተኮር ከቴክኖሎጂ ጋር አያይዞ እንዲሰራ ነው።
የሳይንስ ስራ የሚሰሩት በአብዛኛው የከፍተኛ ትምህርት ምሁራን ስለሆኑ የሳይንስ ስራ ወደ ቤቱ እንዲመጣ ተደርጎ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ተቋቋመ። በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣኖችም ሳይንስን መሰረት አድርጎ የትምህርት ጥራትን ማምጣት በሚችል መልኩ ለኢትዮጵያ ገበያ የሚያስፈልግ በከፍተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ነው።
የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ ያላት ኢትዮጵያ ናት። ግን ያንን ከከፍተኛ ትምህርት ስርዓት ጋር አገናኝቶ እውቀት አድርጎ ማሳደግ የሳይንስ ስራ ነው። በግእዝ መጽሃፍቶች ብዙ እውቀቶች አሉን። በመሆኑም ግእዝን አውቀን እውቀቶቹን ለይተን ወደ ስራ ማስገባት አለብን። የሰው ኃይል ያለው ከፍተኛ ትምህርት ውስጥ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ነው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ያቋቋመው።
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ይገናኛል። እንደአገር በጣም ብዙ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ። እነዚህ ጥቃቅን፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች አገልግሎት የሚሰጡትም በሙሉ ለምርታቸው እድገት ቴክኖሎጂ ይፈልጋሉ። ቴክኖሎጂውን ደግሞ እሴትን ጨምሮ የተሻለ አድርጎ መፍጠር ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሚኒስቴር ያስፈልጋል። ብዙ አገሮች ወደእዚህ አይነት መዋቅር እየመጡ ናቸው። ስራው በጣም ሰፊ፣ አገራዊና በጣም አስፈላጊ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠኑ እውቀትን ያሳደጉ ሰዎችን ለኢንደስትሪው የሚያፈራ ነው። በመንግስት (600 ) ስድስት መቶ በግሉ ዘርፍ ደግሞ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አሉ። እነዚህ ከኢንደስትሪው ጋር የተያያዘ ስራ መስራት አለባቸው። ስልጠናው ከኢንደስትሪ ጋር በትብብር የሚሰጥ ነው። ይህንን ዘርፍ መምራት ከባድ ሃላፊነት ነው። በልዩ ሁኔታም የተፈጠረ ነው። ሌላው በከፍተኛ ትምህርት በመንግስት ብቻ 50 (ሃምሳ) ዮኒቨርሲቲዎች አሉ። 45 የሆኑት ለእዚህ ሚኒስቴር ተጠሪ ናቸው። አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች፣ 35 ሺ የሚጠጉ መምህራን ይገኛሉ። ይህንን አቅም ተጠቅሞ ጥራት ያለው ትምህርት ሰጥቶ ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃብት ማፍራት ይከብዳል። በአንድ ዓመት ቆይታችን ብዙ ነገሮችን ተመልክተናል።
አዲስ ዘመን፤ ኢትዮጵያ በሳይንስ ዘርፍ ልማት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ናት ለምን?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ሳይንስ ከሚለካበት አንዱ መሰረተ ልማት ነው። በዚህ ደግም ብዙ ይቀረናል። ሳይንስ የሚሰራባቸው የመስክ ቤተ ሙከራዎች ጨምሮ ብዙ የምርምር ቤተ ሙከራዎች:: ከፍ ያለ ዕውቀት የምናመነጭባቸው ሳይንሳዊ መሳሪያዎች ያስፈልጉናል። እነዚህን ስናይ ብዙ ይቀረናል።
ሳይንስ በሰው ሃብትም ይለካል። የሚሰራ ሰው ዕውቀት ደረጃ ከፍ ያለ መሆን አለበት ምክንያቱም በዩኔስኮ ደረጃ ተመራማሪ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው ሳይንስ ይሰራሉ የሚባሉት። ከአንድ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ገና 87 ነን፤ ጎረቤቶቻችን እነ ኬንያን በአንድ ሚሊዮን ሕዝብ 318 ገደማ ተመራማሪዎች አሏቸው። ደቡብ አፍሪካን ብናይ ወደ 900 ገደማ ይጠጋሉ። ስለዚህ ገና ብዙ ስራ ይጠብቀናል። መሰረተ ልማቱም የሰው ሃብቱም ገና ነው።
ሳይንሳዊና የምርምር ስራ ተሰርቶ የጥናት መጽሄቶች ላይ ይታተማል የሚለው ሌላው መለኪያ ነው። ቶምሰን ኤንድ ሮይተርስ የተባለ ድርጅት ያለፉት ዓመታትን ተሞክሮዎች ባወጣው መሰረት እንደተጀመረ በ 1950 ዎቹ አለም አቀፍ መጽሄቶች በዓመት እውቅና የነበራቸው 800 ብቻ ነበሩ። ከ1990ዎቹ ወዲህ ግን ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል። ይህ ተስፋ የሚሰጥ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥራቸው በመብዛቱ፣ መንግስት ለዮኒቨርሲቲዎች ለምርምር ፕሮግራም በጀት መመደቡ፣ ዮኒቨርሲቲዎችም ስርዓት ፈጥረው ለወጣትና ለነባር ተመራማሪ እቅድ አቅራቢዎች ገንዘብ ስለሚያቀርቡ፣ በገንዘቡ ምርምር ሰርተው ስለሚያሳትሙና ያሳተሙት ምርምርም (ከመምህርነት ወደ ረዳት ፕሮፌሰርነት፣ ተባባሪ ፕሮፌሰርነትና ፕሮፌሰርነት) ስለሚያደሳድጋቸው ነው።
እንዲህም ሆኖ ከብዙ የአፍሪካ አገራት ጋር ስናነጻጸረው ገና ነን። በመሆኑም በሳይንስ፣ በበጀትና በሰው ሃብት ልማት ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ኢንስቲትዮት በምርምርና ልማት ላይ የሚመደብ አገራዊ ሃብት ከጥቅል ኢኮኖሚ (GDP) አንጻር ምን ያህል እንደሆነ የዛሬ ሁለት ዓመት አጥንቶ ነበር። በዚህም የተመደበው ገንዘብ ዜሮ ነጥብ ሁለት ዘጠኝ (0.29) በመቶ ሲሆን የምትመድበው ትንሽ ነው። ብዙ የአፍሪካ አገራት ዜሮ ነጥብ አምስት፣ ዜሮ ነጥብ ሰባት፣ ዜሮ ነጥብ ስምንትና አንድ በመቶ ያለፉም አሉ። በጣም ትልቁን የምትመድበው አገር ኮሪያ ስትሆን ከጥቅል ኢኮኖሚ (GDP) አራት ነጥብ ስምንት ገደማ ትመድባለች::
የአፍሪካ አገር መሪዎች ለምርምርና ልማት ከጥቅል ኢኮኖሚ (GDP) አንድ በመቶ ድረስ እንመድባለን ብለው ፈርመዋል። ኢትዮጵያም እንደ አባል አገርነቷ ስምምነቱን ብትፈርምም ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም የተቋማትን የመጠቀም አቅም አሳድገን መንግስትን በመገፋፋት ለምርምርና ልማት የሚመደበውን በጀት ወደ አንድ በመቶ ከፍ ማለት ይኖርበታል።
ጅምሮቻችን ጥሩ ቢሆኑም ወደኋላ ሄደን ከአገር በቀል እውቀትና ሳይንሳዊ ስራዎች ጋር ማገናኘት አለብን። ሃይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ትልቅ የሳይንስ ስራ አለ። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ብዙ ዕውቀት አስቀምጠዋል። በእጅ የተጻፉ ጽሁፎች ውስጥ ትልቅ እውቀት አለ።
ያልተጻፈው የሳይንስ ስራ ደግሞ ከሰዎች መፈጠር ጋር አብሮ የመጣ ነው። የመጀመሪያዋ ሰው ሉሲ (ድንቅነሽ) እሳት አንድደው ምግብ ለመስራት የተጠቀሙት አካባቢያቸው ላይ ያለ ድንጋይን አጋጭተው ነው። ያ ዕውቀት የሳይንስ አፈጣጠር ነው:: ይህም ቢሆን ግን ወደ ሳይንሱ ዘግየት ብለው የገቡ አገራት ዛሬ ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል::
አዲስ ዘመን፤ የህብረተሰቡ ሳይንስን የመቀበልና የማላመድ ባህሉ ለምን አነስተኛ ሆነ?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ወደኋላ ሄደን ከነሉሲ ዘመን ጀምሮ ብናይ ሳይንስ የሕይወታችንና የኑሮ ዘዬአችን አካል ነው፤ ሞፈርና ቀንበርን የሰሩት አያቶቻችን ትልቅ እውቀትን ተጠቅመዋል። በጣም በርካታ አገር በቀል ሳይንሳዊ እውቀቶች አሉ። እነዚህን ዘመናዊ አድርገንና እሴት ጨምረን ሕዝቡ በደንብ እንዲጠቀምበት ከማድረግ አንጻር ክፍተት አለብን።
ስርዓቱን ተጠቅመን፣ አቅም ገንብተን ማህበረሰብን አሳምነን ለኑሯችን፣ ለእድገታችን፣ ለልማታችን ሳይንስ መሰረት ነው የሚለውን አስተሳሰብ ማስጨበጥ ይኖርብናል።
ለምሳሌ እምቦጭ ጣና ሃይቅ ላይ በጣም እያስቸገረ ነው። በተቃራኒው ደግሞ እነ ሕንድ አምርተውት ጥቅም ላይ ያውሉታል። ስለዚህ ለማህበረሰቡ የዚህን አይነት ወራሪ አጥፊ አረምን የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀትን ተጠቅሞ ምርታማና ሀብት የሚያመጣ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩልም የአሳ ምርትንና ውሃ ውስጥ ያሉ አካላትን ሳይጎዳ ቦታ ከልለን ለኢንደስትሪ የምንሸጥበትን ሁኔታ ማየት አለብን። በዚህ መልኩ ህዝቡን ማሳመን ከተቻለ ሳይንስን ባህል በማድረግ ለእድገታችን መጠቀም ይቻላል። እናቶችና አባቶች አሁንም ሆዳቸውን ሲያማቸው ምች ሲመታቸው ዳማከሴንና ጤናዳምን ይጠቀማሉ ይህ ትልቅ እውቀት ነው። ሳይንስ ደግሞ ዳማከሴ ውስጥ ምን ስላለ ነው ምችን የሚያድነው፣ ጤናዳምስ ሆድ ቁርጠትን የሚያሽለው የሚለውን በቤተ ሙከራ ያጠናል። ያንን በክኒን መልክ ያወጣል። ሳይንስ ዘመናዊ ለመሆን የሚጠቅመው በእዚህ መልኩ ነው። በመሆኑም ሳይንስን የእለት ተእለት የስራ አካል አድርጎ ሳይንስን ማህበረሰቡ እንዲያምነውና እንዲቀበለው ለማድረግ ከፍተኛ ስራ ይጠይቃል። ይህን ከተገበርን እንሻገራለን።
አዲስ ዘመን፤ አሁን ባለው የትምህርት ጥራት ችግር ሳይንስን ለመፍጠር አስቸጋሪ አይሆንምን?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ አጠቃልሎ መናገር አስቸጋሪ ነው። ባለንበት የትምህርት ስርዓት ያለፉ እንቁ ኢትዮጵያውያን ብዙ ፈጠራዎችን አበርክተዋል። አዳዲስ ግኝቶች እያመጡ የሚያማልሉ ስራዎችን እየሰሩ ነው። ለምሳሌ ጃንአሞራ በሚባል ቦታ በኬሚስትሪ በዲፕሎማ ተመርቆ ሲያስተምር የነበረ አንድ መምህር የዛሬ አምስት አመታት ገደማ መብራት እየጠፋ ሲያስቸግረው እውቀቱን ተጠቅሞ አፈርን መሬት ውስጥ አምቆ ነዳጅ በመፍጠር ለአካባቢው ህብረተሰብ ሀይል መሸጥ ጀምሯል።
ሌላው በቅርቡ የተሸለመ አንድ ወጣት ደግሞ ከአየር ላይ ሃይል በመሰብሰብና በማገናኘት ያለገመድ የበይነ መረብ አገልግሎት በመጀመር አገር አቀፍ እውቅና ያገኘ አለ። በአካባቢ ካሉ መሳሪያዎች እቃዎችን ገጣጥሞ አውሮፕላን ፈጥሮ ያበረረም አይተናል። የትምህርት ስርዓቱ የፈጠራቸው የእነዚህ አይነት በጣም ብዙ ኢትዮጵያን አሉ።
በየዘርፉ ገብተው የኢትዮጵያን እድገትና ልማት እየደገፉ ያሉ የሳይንስ ልዮ ግኝቶች እየተፈጠሩ ይገኛሉ። ጎንደር ዮኒቨርሲቲ ውስጥ እኔ ያስተማርኩት መምህር ከኬንያና ከሱዳን ተመራማሪዎች ጋር በጋራ በሰራው ምርምር ጉበትና ጣፊያን አሳብጦ የሚያሳምመውን የቆላ በሽታ ህክምናውን የሚያድን ለአንድ ወር ይወሰድ የነበረውን መርፌ ወደ 17 ቀናት ዝቅ የሚያደርግ የምርምር
ስራ በመስራት በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቷል።
የትምህርት ጥራቱ የወደቀ አለመሆኑን ማሳያ የሚሆኑ ብዙ ሳይንሳዊ ግኝቶች ማሳየት ይቻላል። የትምህርት ጥራታችን ክፍተቶች አሉበት እነርሱንም ማስተካከል ይገባል። በአለም አቀፍ መመዘኛ ሰፍረን በጥናት ተደግፈን ካልሆነ በቀር በደፈናው የትምህርት ጥራቱ ስለደከመ ሳይንስ ለመስራት አይቻልም ማለት ከእውነት የራቀና ሊታሰብ የማይገባ ነው።
ጎጃም ጋምቤላ፣ ወሎ ወይም ጋምቤላ እየተማሩ ያሉ ልጆች በአሜሪካን ፈተና ትልቅ ውጤት እያመጡ በነጻ የትምህርት እድል (ስኮላርሽፕ) እየሄዱ ነው። ስለዚህ አጠቃላይ አስተያየቱ ትክክል አይደለም። በሚፈለገው ልክ ግብአቶችን አሟልተን፣ ሂደቶችን አስተካክለን ውጤቱን በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል። ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በአለም ትልቅ የሳይንስ መጽሄት በሆነው ‘ኔቸር’ ና ‘ሳይንስ’ በተባሉት መጽሄቶች ላይ የሚያሳትሙ ምሁራን አሉ። በጠቅላላው የትምህርት ጥራት ችግር ሳይንስ ለመስራት ያስቸግራል የሚለው ትክክለኛ ድምዳሜ አይደለም።
አዲስ ዘመን፤ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ከፍቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ቁጥጥርና ክትትሉ ምን ይመስላል?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ በአዋጅ የተቋቋመው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የሚቆጣጠር አካል ነው። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፖሊሲዎችን፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በትምህርት ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ይሰጣል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመዘገቡበት፣ እውቅና የሚያመለክቱበትና የሚያገኙበት፣ ክትትልና ድጋፍ ሲደረጉም የሚታዩበት አግባቦች አሉት። አሁን 229 ዕውቅና የተሰጣቸው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሉ። ከእዚህ ውስጥ አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ዮኒቨርሲቲ ኮሌጆችና ኮሌጆች ናቸው። ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ እመርታ ነው።
ዜጎች እንደየአቅማቸውና ፍላጎታቸው ዕውቀትን የሚገበዩበት ነው። አንዳንዶቹ ገጠር ድረስ ቅርንጫፍ ከፍተው በተቀመጠው መመዘኛ መሰረት እየሰሩ ናቸው:: ዜጎች ደረጃውን በማያሟሉ ተቋማት ገብተው እንዳይጎዱ ኤጀንሲው ይቆጣጠራል። ችግር ከተገኘባቸው ከቀላል ማስጠንቀቂያ እስከ መዝጋት ድረስ እርምጃ ይወስዳል። የግል ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በጥራት አሳድገው ተቀባይ እንዲሆኑ ለማድረግ ህግና ስርዓት አክብረው መስራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፤ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን (ፈጠራ) የሚባሉ ቃላቶች ከብያኔያቸው በመነሳት አንድነታቸውና ልዩነታቸው አይታወቅም ምን ማለት ናቸው?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ብዙዎች መለየት አይችሉም። በተግባርም መለየት ያስቸግራል። ሳይንስ ቀላሉ ፍቺ ዕውቀትን ፍለጋ ነው። በሳይንሳዊ ዘዴ የሚሰራ የሳይንስ ህግጋቶች አሉ። ጥያቄዎችን እየጠየቀ በህግጋቶቹ መሰረት ምላሽ የመስጠት ሂደት ነው። ሲሰበሰብ እውቀትን ፍለጋ ይሆናል። ለምሳሌ እጃችን ላይ እንደምናስረው ሰዓት የተገኘው እውቀት ጥቅም ላይ ሲውል ቴክኖሎጂ ይባላል። የተገኘውን እውቀት ተጠቅመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልግ ቴክኖሎጂን ስንፈጥር ውጤት ነው:: ምርምር በማህበራዊ ሳይንስ ጥናቶችን እንሰራና ጥናቱ ጥሩ መልስ ይሰጠናል። ምላሹ የአሰራር ስርዓትን፣ ሂደትን የሚቀይር ሊሆን ይችላል። ጥቅም ላይ የሚውሉት እቃዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የምንሄድባቸው ስርዓቶቹ ቴክኖሎጂዎች ይባላል።
ኢኖቬሽን ፈጠራ ነው። ከኢንቬንሽን የሚለየው እሴት የታከለበት መሆኑ ነው። አዲስ ነገር መፍጠር ኢንቬንሽን ሲሆን፤ የተፈጠረው አዲስ ነገር እሴት ታክሎበት ጥቅም ላይ ሲውል ኢኖቬሽን ይባላል። ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተቋቋመውም ለእዚህ ነው። ብዙ አገሮች ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ብለው ያቋቁማሉ። ውሃ የሚመረትበትና የሚታሸግበት ሂደት ሁለት ሰዓታት የሚፈጅ ከሆነና አዳዲስ ፈጠራዎችን አክሎ በአንድ ሰዓት እንዲመረት ማድረግ ከተቻለ ሂደቱ ኢኖቬሽን ይባላል። በጥቅሉ እውቀትን መፈለግ ሳይንስ ነው፣ የተፈጠረውን ጥቅም ላይ ማዋል የቴክኖሎጂ ሂደት ነው፣ አዳዲሶቹን ፈጠራዎች እሴት አክሎ ጥቅም ላይ ማዋል ደግሞ ኢኖቬሽን ይባላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህን በሚመለከት አገራዊ ፖሊሲ አለ። የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ አለ። በ1986 ዓ.ም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ተቀርጾ ነበር። ኢኖቬሽን ስላልነበረው በ2004 ዓ.ም የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ተዘጋጀ። ፖሊሲው ሲዘጋጅ እነዚህ ሙያዊ ቃላቶች የሚያደናግሩ ስለሆኑ በግልጽ ፍቺያቸው ተቀምጧል። ፖሊሲው አነስ ያለ በመሆኑም የፖሊሲ ማስተግበሪያ እስትራቴጂም ተዘጋጅቷል።
አዲስ ዘመን፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አንድ መስሪያ ቤት ይመስላሉ?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር አራት አንኳር ስራዎች አሉት። አገራዊ የሳይንስን ልማት፣ ከፍተኛ ትምህርት ልማትን በመምራት ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን የሰው ሃይል ማፍራት፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ስርዓትን መምራትና የምርምርና የሳይንስ ስራን የሚሰሩ ተቋማት የኢንዱስትሪ ትስስርን መምራት ናቸው። ሌሎች 14 የሚጠጉ ማቋቋሚያ አዋጁ ላይ የተዘረዘሩ ተግባሮችም አሉት።
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዋናነት የቴክኖሎጂ፣ የኢኖቬሽን ስራ፣ ኢንደስትሪዎች ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዲችሉ በአለም አቀፍ የታወቁ ቴክኖሎጂዎችን የማስገባት፣ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ የኢንተርፕራይዞችን አቅም መገንባትና የመሳሰሉ ተግባራትን ያከናውናል።
ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሁለታችንም ዘንድ ስላለ በጋራ የምንሰራቸው ስራዎችም አሉ። ብዙዎቹ የከፍተኛ ትምህርት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ብለው በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያስቀምጣሉ። የትምህርት፣ የሳይንስና የምርምር ሚኒስቴር ብለውም ያቋቁማሉ። ያ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት ሚኒስቴርን፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርንና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን አንድ ላይ አድርገው ይመሩታል እንደ ማለት ነው።
አሁን በኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እየተጓዝን ስለሆነ ትኩረት እንዲሰጥ ያደርጋል። እነ ኮሪያ፣ ታይላንድ፣ ሲንጋፖር በፍጥነት ያደጉት ለኢንደስትሪው ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው ነው። አቅም ግንባታ፣ እስትራቴጂ ፖሊሲውን ለየት አድርጎ የሚመራ አካልም ፈጥረው ነው። ይሄንን አደረጃጀት በደንብ አውቀነው በትስስር የሚተገበሩትን እያጠናከርን ስንሄድ ውጤታማ እንሆናለን።
አዲስ ዘመን፤ ከአስፈላጊነቱ አንጻር በአጭር ጊዜ ቆይታችሁ ምን ተገበራችሁ?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ አዲስ መዋቅር ተፈጥሮ ወደትግበራ ተገብቷል። ለክትትል እንዲያመች አንድ ሚኒስትርና ሶስት ሚኒስቴር ደኤታዎች አሉት። አንዱ ሚኒስትር ደኤታ የሳይንስ ስራዎችን ይከታተላል፣ ሌላው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠዎችን እንዲሁም ሶስተኛው የከፍተኛ ትምህርት ስራዎችን ይከታተላል። ዘርፉ ቀደም ሲል የነበሩ አመለካከቶችን፣ ተግባቦትንና ዕውቀትን የሚያሳድጉ፣ ስለአካባቢና ስለአገር እንድናውቅ የሚያደርጉ የታሪክ ኮርሶች እንዲካተቱ አድርጓል። ባለፉት ጊዜ በተደረጉ ክለሳዎች ኮርሶቹ ከስርዓተ ትምህርት ወጥተው የነበረ በመሆኑ በወቅቱ ተምረው የወጡ ተማሪዎች የተለያዩ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ቀጣሪዎቻቸው ይናገራሉ። በመሆኑም ጥናት ተሰርቶ በፍኖተ ካርታ እንዲካተት ተደርጓል፤ ክፍተቱን የሚሞሉ የስርዓተ ትምህርት አካል በመሆኑም ኮርሶች በአንደኛ ዓመት ትምህርት ማካተት ተችሏል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሰራቸው የአጭር ጊዜ ተግባራቱ መካከል ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ራስን አስተሳስሮ የመሄድ ክፍተትን ለመሙላት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚባሉትን መገልገያዎች የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እንዲያውቁት ተሰርቷል። አለም ዛሬ በኢንደስትሪ መንደር አንድ ሆናለች ቶኪዮ የሚፈጠር አንድ ነገር ወዲያው ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ውስጥ ይሰራጫል። የአለም ፖለቲካ፣ የታሪክ ሁኔታና የኢኮኖሚ ጉዞ፣ የታላላቅ አገራት ተጽእኖ፣ አብሮ የመኖር ጉዳይ እንዲታወቅ ግሎባል ትሬንድስ የሚል ኮርስ ተካትቷል። የአለም ሁኔታዎችን እንዲያውቁም ይረዳቸዋል። አንትሮፖሎጂ ኮርስ በማስገባትም ባህልን ታሪክን እንዲያውቁ ተደርጓል።
እኔ አስመራ ዩኒቨርሲቲ ስሄድ የቀሩት የአሁኑ ሐሮማያና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ነበሩ። ከዛ በኋላ የትምህርት ዘርፍ ልማት በመከተል የማስፋፊያ ስራዎች ተሰርተው 50 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ደርሰዋል። እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀዱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አይነት ነው። ዩኒቨርሲቲዎቹ ልዩ ተልእኮ ኖሯቸው ልዩ አይነት ምሩቃንን የሚያመርቱ አይደሉም። አንዱ በፍኖተ ካርታ ጥናት የተመለከተው ዩኒቨርሲቲዎቻችን አንድ አይነት መሆናቸው ነበር። ዩኒቨርሲቲዎቻችን በአንድ ምጣድ የተጋገሩ እንጀራ ናቸው። ለኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት ብቻ አያስፈልጉም። በዚህ ታሳቢነት መንግስት ከአምስት ዓመታት በፊት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉንም ትምህርቶች አያስተምሩም። ልዩ ስርዓተ ትምህርት አዘጋጅተው ከኢንደስትሪው ጋር ተቀራርበው የሚሰሩ፣ በትምህርት ስርዓት ውስጥም የኢንደስትሪ ባለሙያዎች ተሳትፈው እየተጋገዙ ምሩቃንን የሚያፈሩበት አሰራር ተፈጥሯል። የእዚህ አይነት ዩኒቨርሲቲዎች ለኢትዮጵያ በብዛት ያስፈልጋሉ።
መምህራንን፣ ሃኪሞችን ብቻ የሚያመርቱ በግብርናውና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ዩኒቨርሲቲዎች ያስፈልጋሉ። ትኩረታቸው ለአንድ ልሕቀት ብቻ ያተኮረ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ያስፈልጋሉ የሚል አስተሳሰብ ነበረ። የትምህርት ፍኖተ ካርታ ያንን አዳብሮ መጣ እኛ ስራ አደረግን። ዩኒቨርሲቲዎች አሁን በተልዕኮና በልሕቀት ለይተናቸዋል። አዋጅም አስከልሰናል። የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችም ያስፈልጋሉ። በአለም አንደኛ የሚባለው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ነው። ጀርመን አገርም ተወዳዳሪ የሌለው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ነው። ቴኪኒካልም አጠቃላይም ዩኒቨርሲቲዎች አሏቸው።
በአሜሪካም የትምህርት ስርዓት ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሲስተም የሚባል አለ፤ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሳንፍራንሲስኮ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ቨርክሊን… እየተባሉ የሚጠሩ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። ሁለተኛ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች የሚባሉም አሉ። ካሊፎርኒያ እስቴት ዩኒቨርሲቲ የሚባሉ አሉ። እስቴት ዩኒቨርሲቲዎች ሁለተኛ ደረጃ ኮምፕርሄንሲቭ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። ወረድ ሲል ደግሞ ኮሚዩኒቲ ስኩል አሉ። እንደአሜሪካ ያደጉ አገራት ዩኒቨርሲቲዎቻቸውን እንደዚህ በተልዕኮ ከፋፍለው እያስተማሩ ናቸው። ከእነሱ ተምረን ለምርምር የዩኒቨርሲቲ የሚሆኑትን ለይተናል። የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ፣ አጠቃላይ የምንላቸውን ለይተናል። የማጠቃለል፣ የማጸደቅና የማሳወቅ፣ ወደተመረጡበት እንዲሻገሩ የመደገፍ ስራ ይቀረናል። ጥናቱ ከስምንት ወራት በላይ ፈጅቷል። አሁንም ይፋ አልሆነም። ይሄ ከሰራነው ትልቁ ስራ ውስጥ ይመደባል። ከበርካታ የአውሮፓ አገራት ጋር የአለምአቀፋዊና የግንኙነት ስራዎችንም ጀምረናል።
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 በመቆየቱና የከፍተኛ ትምህርትም በፍጥነት እያደገ በመሆኑ መስተካከል የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች ነበሩ። እነሱን አሻሽለን የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2011 ወጥቷል። ደንቦችም አዘጋጅተን የጸደቁና በሂደት ላይ የሚገኙ አሉ። 20 የሚደርሱ ስራዎችን አሳልጠው ወደውጤት የሚወስዱ በሳይንስ ዘርፍ፣ በትስስር ዘርፍ የሚወርዱ መመሪያምችም ተዘጋጅተዋል። በስርዓተ ትምህርት ክለሳው መስተካከል ያለባቸው፣ መጨመርም መቀነስም የሚገባቸው ኮርሶች ላይ እየሰራን ነው። በአስተዳደር ስራ ከመምህራን ቅጥር እስከ እድገት የሚመሩበት ከዕድገት፣ ከነጻ የትምህርት እድል (ስኮላርሽፕ) ጋር የተያያዙ ህጎችን ከልሰን ወደስራ አስገብተናል።
ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘም አምስት ኪሎ ባለን ትልቅ መሰረተ ልማት ኢትዮጵያን የትምህርት ጥናት (ኢዱኬሽን ሪሰርች ኔትወርክ) ውስጥ በርካታ መጽሀፎች እንዲኖሩ ተደርጓል። ከበይነ መረብ ጋር የተገናኙ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በማዕከል በዲጂታል ቤተ መጻህፍት ያስቀመጥናቸውን ሃብቶች መጠቀም የሚያስችላቸውን ክላውድ ዳታ ቤዝ ሲስተም አዘጋጅተን ወደ ቴክኖሎጂ በመቀየር እየሰራን ነው። በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ የኢትዮጵያ ይዘቶች ለአለም የምናሳይበት ስርዓት የለንም። በርካታ ምርምሮች በዩኒቨርሲቲዎቻችን ቢሰሩም፤ አንዱ የሚሰራው ከሌላው ጋር እንዲታይ የሚያደርግ ስርዓትም የለንም። የዚህ አይነት ስራን የሚያዘምን ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ጋር የሚቀራረቡ በፍጥነት ወደ ስራ አስገብተናል። ዩኒቨርሲቲዎች ተቋማዊ ቋት በመፍጠር እንዲያጠራቅሙ የሚያስችል ስራ ተግብረናል።
አዲስ ዘመን፤ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያመጠቀችው ETRSS1 ሳተላይት ምን የሚሉኝ ነገር አለ?
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ኢትዮጵያ እስከ አሁን በርካታ የሳተላይት መረጃዎችን ስትገዛ ነበር አሁን መረጃ ከሚሸጡ አገራት ተርታ ገብታለች። ስለአየር ንብረት፣ መሬቷ ስላለው ሃብት የእኛ አይን ሆና የት ምን እንዳለ መረጃ ታስገኝልናለች። መንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የነዳጅ፣ የጋዝ መስመሮችን ለመስራት፣ ከደህንነትና ከጥገና አንጻር በርካታ መረጃዎች በማስገኘትም ለልማታችን በጣም ታስፈልገናለች። የሳተላይትን መረጃ ወስዶ ለየዘርፎቹ በሚሆን መልኩ ተንትኖ መስጠትና አስፈላጊ የሰው ሃብት ማፍራት ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ጥንታዊ የሰው ልጅ መገኛ፣ የጥንት ስልጣኔ የነበራት:: በርካታ ባህላዊ እውቀት ያላት፣ በመሬት ውስጥና በላይ የተለያዩ ሀብቶች ያሏት በመሆኑ ይህንን አቀናጅተን ከድህነት ለመውጣት መስራት፤ ሕዝቡ በአንድ ልብ ወደ ብልጽግና ወደ እድገት፣ ወደ ልማት አስተሳሰብ መንቀሳቀስ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
ዘላለም ግዛው