9በመንግስት እምብዛም ትኩረት ካላገኙ የህክምና አይነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በዚህ የህክምና ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥርም ከአርባ አንድ እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚሁ ባለሙያዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ደግሞ በጡረታ በመገለላቸው ከሙያው ርቀዋል፡፡ ህክምናውን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቢሆንም የህክምና አገልግሎቱ ግን አሁንም ውስንነት ይታይበታል – የአንገት በላይ ህክምና፡፡
የአንገት በላይ ህክምና /ENT/ ጆሮን፣ አፍንጫንና ጉሮሮን ማለትም የአፍ፣ ቶንስልና ተያያዥነት ያላቸው ህክምናዎችን፣ የጭንቅላትና የአንገት ህክምናዎችን ያካትታል፡፡ ህክምናው ውስብስብ ከመሆኑ አኳያ የሰለጠነ ባለሙያና የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰባቸውን የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላትንም ይጠይቃል:: ለዚህም ይመስላል በኢኮኖሚ የዳበሩ ሀገራት ህክምናው የሚጠይቀውን ሁሉ በማሟላት ዜጎቻቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያደርጉት፡፡
በኢትዮጵያም የአንገት በላይ ህክምና አገልግሎት ደረጃውን ጠብቆ እየተሰጠ ያለ ቢሆንም የአገልግሎቱ አድማስ ከከተማ አልፎ ወደ ገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንዳልተስፋፋ ይነገራል፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
ዶክተር ዋለ ልመንህ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የአንገት በላይ እስፔሻሊስት ሃኪም ናቸው፡፡ ዶክተር ዋለ የአንገት በላይ ህክምና በኢትዮጵያ ያለው ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ህክምናው በአብዛኛው በከተሞች አካባቢ እንደሚሰጥና ብዙሃኑ የገጠር ህዝብ አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ከተሞች ለመምጣት እንደሚገደድም ይናገራሉ፡፡ ይህም አገልግሎቱን ፈላጊ የገጠር ህዝብ ለከፍተኛ እንግልትና ለአላስፈላጊ ወጪ እንደሚዳረግ ይገልፃሉ፡፡
እንደ ዶክተር ዋለ ገለፃ፤ የህክምና አገልግሎቱ በሀገሪቱ ተደራሽ ያልሆነበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የህክምና ተቋማት ውስንነትና ለህክምናው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች እጥረት ህክምናውን በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ አላስቻሉም:: በመንግስት ጤና ተቋማት የአንገት ቀዶ ህክምና ለማግኘት ረጃጅም ወረፋዎች መኖራቸውም የዚሁ ምክንያት ውጤት ነው፡፡
ዶክተር ዋለ እንደሚሉት፤ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአንገት በላይ ህክምና አገልግሎት ለማግኘት በቀን በአማካይ እስከ 120 ታካሚዎች ይመጣሉ፡፡ የጆሮ ህክምና ብቻ ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ደግሞ ከ50 እስከ 60 ይጠጋል:: ከግማሽ በመቶ በላይ የሚሆኑት የአንገት በላይ ታካሚዎች ደግሞ ጆሯቸውን ለመታከም ይመጣሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የአንገት በላይ ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሉ ለአንገት በላይ ህክምና አገልግሎት የሚመጡት ከተለያዩ ጤና ጣቢያዎች ሪፈር ተፅፎላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ክትትል የነበራቸው ታካሚዎች ግን ያለሪፈር ቀጥታ መጥተው ህክምናውን ያገኛሉ፡፡
እየተሰጠ ያለው የአንገት በላይ ህክምና አገልግሎት በተለይም የጆሮ ህክምና ረጅም ወረፋ የሚታይበት ነው:: የህፃናት የአንገት በላይ ህክምና ክፍሉ ግን በአንፃራዊነት ብዙም ወረፋ የለውም፡፡ የቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ህፃናት ግን አሁንም ድረስ ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በቂ አልጋ ባለመኖሩና የሃኪሞች ቁጥርም አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡
የሃኪሞች ቁጥር በፊት ከነበረበት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም የህክምና አገልግሎቱ በተሟላ ሃኪሞች እየተሰጠ አይደለም፡፡ ምናልባት በቀጣይ የህክምና አገልግሎቱ በሆስፒታሉ ውስጥ አዲስ እየተገነባ ባለው ህንፃ ውስጥ የሚሰጥ ከሆነ ችግሩ ይቀረፋል ተብሎ ይታሰባል፡፡
እንደ ዶክተር ዋለ ማብራሪያ፤ የአንገት በላይ ህክምና ተደራሽነቱን ለማስፋት መንግስት በተለይ ከአንገት በላይ ህክምና የሚሰለጥኑ የትምህርት ተቋማትን ማስፋት ላይ አተኩሮ ሊሰራ ይገባል፡፡የአንገት በላይ ህክምና ትምህርት ክፍሎች በአንድ ጊዜ ተማሪዎችን የሚቀበሉ ባለመሆናቸው መንግስት ተማሪዎችን ወደ ውጪ ሀገራት ልኮ በማስተማር በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ቁጥር ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡
የአንገት በላይ ህክምና ትምህርት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ እየተሰጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከውጭ ሀገራት ሀኪሞችን በማስመጣትም ጭምር ትምህርት ክፍሉ እንዲሰፋና የህክምና አገልግሎቱም ተዳራሽ እንዲሆን መደረግ ይኖርበታል፡፡
የአንገት በላይ ህክምና አገልግሎት ልክ እንደ ሌሎቹ የህክምና አይነቶች እኩል ትኩረት እንዳላገኘም የሚናገሩት ዶክተር ዋለ፣ መንግስት ብቻ ሳይሆን የዘርፉ ሙያ ማህበራትም ለህክምናው ትኩረት የሰጡ ባለመሆናቸው ችግሩ አሁንም ድረስ ይታያል ይላሉ፡፡ በመሆኑም የጤና ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለህክምናው ትኩረት በመስጠት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በጋራ ሊሰሩ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
አስናቀ ፀጋዬ