
በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በርካታ ዘመናዊ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች አገልግሎት ላይ መሰማራታቸው ለተገልጋዮች አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ፈጥረዋል። የአገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥርም በዚያኑ ያህል ጨምሯል።
በግል ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ አለማየሁ መንግስቴም፣ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ አውቶቡሶቹ ለህዝብ በቂ አማራጭ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። እርሳቸውን ጨምሮ በርካቶችም የአገልግሎቱ ደንበኛ መሆናቸውን ይመሰክራሉ።
ምቹ መቀመጫ፣ አየር ማቀዝቀዛ፣ መፀዳጃ፣ ቀላል ምግቦች፣ ነፃ ኢንተርኔትና ቴሌቪዥን የሚያቀርቡ መሆናቸው አውቶቡሶቹ ተመራጭ እንዲሆኑ ማስቻሉን አቶ አለማየሁ ይጠቁማሉ። ‹‹ከአገልግሎት አሰጣጥ ባሻገር ጊዜ ቆጣቢ በተለይ ከመደበኛዎቹ አውቶቡሶች ቀድመው በመነሳት ደንበኛው የፈለገው ቦታ ባሰበው ሰአት እንዲደርስ ስለሚያግዙ ምርጫዬ ሆነዋል›› ሲሉም ይናገራሉ።
‹‹ምንም እንኳን የሚያስከፍሉት ገንዘብ ከመደበኛዎቹ ጋር ሲነፃፀር እጥፍ በሚባል ደረጃ ላይ ቢሆንም፤ አገልግሎታቸው ግን ክፍያውን የሚያስረሳና የሚመጥን ነው።›› የሚሉት አቶ አለማየሁ፣ በአገልግሎቶቹ ላይ ስለሚስተዋለው ጥንካሬ ብቻም ሳይሆን ያለውን ድክመትም ከመናገር አልተቆጠቡም። አብዛኞቹ አውቶቡሶች ተሳፋሪዎችን የሚጠባበቁትና የሚጭኑት መስቀል አደባባይ ላይ ብቻ መሆኑን ደካማ ጎን አድርገው በቀዳሚነት ይጠቅሳሉ።
ይሕ ችግር በተለይ ርቀት ካላቸው አካባ ቢዎች ለሚመጡ ደንበኞች ከባድ ራስ ምታት መሆኑን የሚገልፁት አቶ አለማየሁ፣ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ደንበኞች አውቶቡሶቹ እንዳያ መልጧቸው በመስጋት በአቅራቢያው ለማደር ሲገደዱ እንዳስተዋሉና ይሕም ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርግ ይጠቁማሉ።
የአውቶቡሶቹን ውጤታማ አማራጭ ይበ ልጥ ለማስፋት ከተፈለገም በተለይ መቆሚያ ስፍራቸውን የማስፋት ብሎም ዘመናዊ ማድረግ ሊታሰብበት እንደሚገባ ነው አቶ አለማየሁ ያስገነዘቡት።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ወይዘሪት ሄለን ታደለም፣ የአውቶቡሶቹ ግልጋሎት በተለይ ለተማሪዎች ጥሩ አማራጭ መፍጠሩን ታሰምርበታለች። በተ ለይ ‹‹በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪ ቅበላ እንዲሁም የትምህርት ማጠናቀቂያ ወቅት በሚፈጠረው ከፍተኛ የትራንስፖርት መጨናነቅ ፋይዳቸው በግልፅ ይታያል።›› ትላለች።
ወይዘሪት ሄለንም የአቶ አለማየሁ ሀሳብ በማጠናከር ውስንነት እንዳለባቸውም ትጠቁ ማለች። አውቶቡሶቹ ተሳፋሪዎችን የሚጠብቁትና የሚጭኑት መስቀል አደባባይ ላይ ብቻ መሆኑ ለደንበኞች ከባድ ፈተና ሆኗል ትላለች።
‹‹አውቶቡሶቹ በተደበላለቀ መልኩ ተሰድረው ተሳፋሪዎችን የሚጠባበቁ በመሆኑ አንዳንድ ደንበኞች ትኬት የቆረጡበትን አውቶቡስ በቀላሉ ለይተው ለማግኘት ሲቸገሩ አስተውያለሁ።›› የምትለው ተማሪዋ፣ አንድ ደንበኛ እክል ገጥሞት ከጉዞው ቢቀርና የቆረጠው ትኬት እንዲመለስለት ቢጠይቅ አገልግሎት አቅራቢዎቹ ግማሽ ያሕ ሉን ብቻ መመለሳቸው አግባብ አለመሆኑን ታመለክታለች።
‹‹የአውቶቡሶቹ አገልግሎት ከውስንነታቸው ይልቅ ጥንካሬያቸው ያመዝንብኛል።›› የምትለው ሄለን፣ አገልግሎታቸው ይበልጥ ተጠናክሮ የሚቀጥሉበትን አሰራር መተግበር እንደሚያስፈልግ ትጠቁማለች።
የኦዳ ባስ የኦፕሬሽን ሃላፊ አቶ ቱጁባ ጋምሹም፣ አውቶቡሶቹ ለህዝብ ጥሩ አማራጭ በመሆን ከፍተኛ አስተዋፆኦ እያበረከተ መሆኑን ይገልጻሉ። የእርሳቸው ድርጅትም ባለፉት ሁለት ወራት ከ50 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎት መስጠቱንና የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት መስመሮቹን ወደ 19 ማሳደጉን ይጠቁማሉ።
‹‹በእኛ በኩል በአሁኑ ወቅት ትልቁ ችግራችን የፍጥነት ገደብ አለመኖር ነው።›› የሚሉት አቶ ቱጁባ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች የፍጥነት ወሰን ገደብ አለመዘጋጀቱ በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ከተደቀኑ ፈተናዎች ዋናው መሆኑን ያነሳሉ።
የዘመናዊ አውቶቡሶች ፍጥነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ለመቆጣጠር ፈታኝ መሆንና የሚያደርሱት አደጋም የከፋ መሆኑን የሚያስገነዝቡት ሃላፊው፣ ኦዳን ጨምሮ ሌሎች የአውቶብስ ድርጅቶች አገልግሎት የሚሰጡት የራሳቸውን የፍጥነት ወሰን በማወጅ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ከፍጥነት ወሰን አለመጠበቅ ጋር በተያያዘ የሚደርሰው ጉዳት ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፣ መስተካከል የግድ መሆኑን ያስገነዝባሉ። ‹‹ሁሉም መንገደኛ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ስላለበት መንገድ ትራንስፖርትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጊዜ ሳይሰጡ ለሁሉም እኩል ገደብ ማበጀት አለባቸው።›› ነው ያሉት።
የዘመን ባስ የትራንስፖርት ዘርፍ ሃላፊ አቶ እይላቸው አያናም፣ ድርጅታቸው ለደንበኞች ምቾትና ደህንነት ቅድሚያ መስጠቱና የትራንስፖርት እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ተደራሽ መሆኑ የበርካቶች ምርጫ እንዳደረገው ይገልፃሉ።
በአጠቃላይ በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተለይ ትኬት በመመለስ ረገድ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተመለከተ ሲመልሱም፣ ‹‹በድርጅቶቹ ችግር ለሚከሰቱ መስተጓጎሎች ሙሉ የክፍያ ወጪ ይመለሳል። ተሳፋሪው በራሱ ችግር ሰአት ጠብቆ ሳይገኝ አውቶቡሱ ካመለጠው አሊያም ጉዞውን ማራዘም ከፈለገም ደግሞ በ24 ሰአት ውስጥ ማሳወቅና ግማሽ በመቶ ወጪውን ማስመለስ ይችላል።›› ሲሉ ገልፀዋል።
አውቶቡሶች ተሳፋሪዎችን የሚጠባበቁትና የሚጭኑት መስቀል አደባባይ ላይ ብቻ መሆኑ በተለይ አንዳንድ ፕሮግራሞች የቦታ ማሻሻያ ሲደረግ ከሚከሰቱ መጨናነቆች በስተቀር በአመዛኙ ለደንበኛ ራስ ምታት የመሆናቸው እድል ጠባብ ስለመሆኑም ነው ያስረዱት።
ይሁንና ቦታው ታክሲዎችን ጨምሮ በርካታ ተሸከርካሪዎች ተከማችተው የሚስተዋ ልበት እንደመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት የአውቶቡሶቹ አገልግሎት ህብረተሰቡን በማያ ጉላላ መልኩ እንዲሳለጥ ምቹ መናህሪያን ጨምሮ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በጉዳዩ ዙሪያ የፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስቴርና ትራንስፖርት ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
ታምራት ተስፋዬ