
አዲስ አበባ፡- ‹‹ኃላፊነት የሚሰማውንና ስራውን በአግባቡ የሚፈጽምን ሚዲያ ህዝብ ያከብረዋል›› ሲሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ ገለፁ። ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት 52 ያህል አባላት እንዳሉትም ተናግረዋል።
ሰብሳቢው አቶ አማረ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት፤ መገናኛ ብዙኃን ለአንድ አገር ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ድርሻ አላቸው። የአገር ሰላምና መረጋጋት ተጠቃሚ የሚያደርገው እገሊትን አሊያም እገሌን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ህዝብ ነው። ኃላፊነት የሚሰማውና ስራውን በአግባቡ የሚሰራን ሚዲያ ደግሞ ህዝቡ ያከብረዋል።
ያልተገባውን ገንዘብ ተቀብሎ ከሚሰራው ሚዲያ ይልቅ ተዓማኒና አንዱን በሌላ ላይ የማያነሳሳ መረጃ የሚሰጥ ሚዲያ በህዝብ ዘንድ አመኔታና ከበሬታ አግኝቶ እንደሚቀጥል ሰብሳቢው ጠቅሰው፣ እንዲህ አይነቱ ሚዲያ የተሻለ እድገት ሊያገኝ እንደሚችልም አስታውቀዋል። ለአንድነቱም፣ ለፍቅሩም፣ ለሰላሙም ሆነ ለእድገቱ የሚሰራ ሚዲያ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንደሚኖረው አመልክተዋል።
‹‹እንደ ህዝብም ሆነ እንደ ግለሰብ የሰላምና መረጋጋት መኖር አጠያያቂ አይደለም።›› ያሉት አቶ አማረ፣ ሚዲያው ይህን የሚሰራው ለእገሌ ብሎ ሳይሆን ለራሱ ህልውናም ጭምር መሆኑን ልብ ሊል እንደሚገባ አስታውቀዋል። ሚዲያው በሚያስተላልፈው መረጃ ጥላቻ መዝራት እንደሌለበትም ጠቅሰው፣ ያንን የሚያደርግ ከሆነ ራሱ ሚዲያውም እንደሚጎዳ ገልጸዋል።
‹‹ሰላም ከታጣ ሚዲያውም መስራትም አይችልም፤ አይኖርምም። ስለዚህ ለሰላም መጠበቅ ዘብ መቆም ያለበት ለራሱም ሲል ነው። አገር ካልጠነከረ እና ከተበተነ አሸናፊ አይኖርም፤ ሁሉም ይሸነፋል። ከተሸናፊዎች መካከል ሚዲያ አንዱ ነውና ይህን አውቆ ጉዳቱ ሳይደርስ ከወዲሁ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል።›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
ሰብሳቢው ምክር ቤቱ 52 አባላት እንዳሉት ጠቅሰው፣ የአባላት ብዛት ከዚህ ማለፍ እንደሚችልም አስታውቀዋል። በርካታ ተቋማት የምዝገባ ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ምክር ቤቱ አትራፊ ድርጅት አለመሆኑንም ገልፀው፤ እስከ አሁን በመዋጮ እየሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።
‹‹በምክር ቤቱ ውስጥ በመሳተፍ አገሩንና ራሱን የሚያድን ሚዲያ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የአንድነት ፎረም መፍጠሩ መልካም መሆኑን አስረድተዋል። ‹‹የሚዲያ ማህበራት፣ የአሳታሚዎች ማህበር፣ ብሮድካስተር ማህበር እና ሌሎችም ተሳስረው ሚዲያ በኢትዮጵያ እንዲያድግ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እና ኃላፊነታችንን እንወጣ።›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2012
አስቴር ኤልያስ