
ስለእርሷ መፅናት እልፎች የተዋደቁላት፤ ማህፀነ ለምለሟ አገር ኢትዮጵያ ከዛሬ 124 ዓመት በፊት መቆየቷን የሚፈታተን ሉዓላዊነቷን የሚንድ ከባድ አደጋ ተጋርጦባታል። ይቺ በተደጋጋሚ ከርቀት የሚጎመዧት ተፈጥሮ ያደላት አገር ኢትዮጵያ፤ በልጆቿ አጥንት ታጥራ የኖረች ምድር ቀርበው ሊወርሯት እና ደፍጥጠው ሊገዟት ሽተው ተደጋጋሚ ሙከራ አደረጉባት። ከሙካራም አለፉና እንዳሻን እናድርግሽ አሏት።
ብለውም አልቀሩ ከሰሜን አቅጣጫ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በታጠቀ እብሪተኛ የተወጠረው በጄኔራል ባራቶሪ የተመራው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ይቺን ለዘመናት አልደፈር ያለች አገር ተነኮሱ። የማይደፈረውን ደፍሮ ህልውናዋን በመፈታተን ዳር ድንበሯን ተሻገረ። መሪዋ ምኒልክም አገሬን ተዋት ቢልም የወራሪው አመጣጥ ለመመለስ አልነበረምና አሻፈረኝ አለ።
በወቅቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩ አንዳንድ መሳፍንት በንጉሡ ደስተኛ አልነበሩም። ይሁንና ከንጉሣቸው ተኳርፈው ቅሬታ ውስጥ የነበሩትና የየራሳቸውን ግዛት እያስገበሩ ህዝባቸውን እየመሩ የነበሩት መሳፍንት በአንድ አገር ጥላ ሥር መሆኗቸውን በማመን የንጉሡን አዋጅ፤ አገር ተወርሯል እንዝመት ጥሪን አድምጠው ተቀብለዋል።
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም ጠላት አገር ሊወርር፤ ሉዓላዊነት ሊደፈር ነውና በሕብረት እንዝመት ባሉ ጊዜ፤ አዋጁን አድምጦ አገር በመወረሩ ያልተቆጣ እና ምላሽ ለመስጠት እራሱን ያላዘጋጀ ዜጋ አልነበረም።
ውስጣዊ ቅያሜውን ትቶ አገሩን አስቀድሞ እራሱን ሊሰጥ ንጉሡን አጅቦ ወደ ዓድዋ ዘመተ። የካቲት 23 ቀን 1888 ከየአቅጣጫው በአገር ፍቅር ስሜት ስለ አገሩ ለመዋደቅ ባህላዊ መሣሪያዎችን ታጥቆ ከሰፊ ዝግጅት ጋር ዘመናዊ ጦር መሣሪያ ከታጠቀው የኢጣሊያ ሠራዊት ጋር በወኔ ተፋለመ።
እኩለ ቀን ላይ ዘመናት የሚሻገር የጥቁሮችን አንገት ከፍ ያደረገ የድል ብሥራት ከዓድዋ ታሪካዊ ተራሮች ሥር ለዓለም ደረሰ። ኢትዮጵያውያን በአገር ፍቅር ስሜት እየሸለሉና እየፎከሩ የኢጣሊያንን ሠራዊት ጠራርገው አባረሩ፤ የተቀረውን ማረኩ።
በኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመው ጠላትን ድል ያደረጉበትና አንድነታቸውን ለዓለም ያሳዩበት መሆኑን ይናገራሉ። በጊዜው በተለያዩ መሳፍንቶች የነበሩ የአስተዳደር ቅሬታዎችን ወደጎን በመተው አገርን አስቀድመው በጋራ መዝመታቸው የላቀ የአገር ፍቅር ማሣያ መሆኑን ያስረዳሉ።
በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ የዓድዋ በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሴሚናር ላይ ዓድዋን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር አልማው፤ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ለጥቁር ህዝብ ያበረከቱት ታላቅ ድል መሆኑን ያነሳሉ። የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ በአንድነት የፀናች አገር እንድትሆን ምክንያት መሆኑንም ይገልፃሉ።
የዛሬው ትውልድ በሰከነ መንፈስ አባቶቹ ያስረከቡትን አገር አንድነት ጠብቆ በፍቅር መኖር እንደሚገባው ይመክራሉ። ኢትዮጵያውያን አለመግባባታቸውን በውይይት በመፍታት እንደ አገር አንድ ሆነው ዘርፈ ብዙ ድል መቀዳጀት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አሳስበዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ አቶ ዳንኤል ወርቁ በበኩላቸው በሴሚናሩ ላይ ባቀረቡት ዓድዋን በተመለከተው ጥናታዊ ጽሁፋቸው፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ታላቅ የትብብርና የአንድነት ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ። በወቅቱ የነበሩ መሳፍንቶች ለአገራዊ ጥሪ ከልብ ምላሽ በመስጠትና በመዝመት ለአገራቸው ክብር የተዋደቁበት ታላቅ ገድል መሆኑን አስታውሰዋል።
ኢትጵያውያን ተገድደው የገቡበትንና ዝግጅት ያላደረጉበትን ጦርነት አሸናፊ መሆን ያስቻላቸው በአንድነት መቆማቸውና ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅር ስሜት መላበሳቸው እንደሆነ ያስረዱት አቶ ዳንኤል፤ ዓድዋ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የሚዘከር ታላቅ ድል መሆኑን በማስታወስ፤ የዛሬው ትውልድ ከቀደምት አያቶቹ ሕብረትንና አንድነትን ሊማርና በጋራ አገርን ጠብቆ ሊያቆይ ይገባዋልም ብለዋል።
የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ገረመው ከበደ፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን እራሳቸውን በመክፈል ለትውልድ ያበረከቱት ስጦታ ነው ብለዋል። ዓድዋ ኢትጵያውያን አንድነታቸውን ያረጋገጡበት ልዩ ድል መሆኑንም አውስተዋል። የዛሬው ትውልድም የአንድነት ድር እና ማግ ሆኖ የአገሩን አንድነት ጠብቆ ለለውጥ እንዲተጋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
ተገኝ ብሩ