
“የኢትዮጵያውያን አንድነትና ሰብዕና በዓድዋ ማማ ላይ ተገንብቷል” ያሉት የአዲስ አበባው ነዋሪ አቶ አሳድረው ዘሪሁን፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቀና ብሎ ለመሄዱ የዓድዋው ድል ጥሎት ያለፈው ሥነ ልቦናዊ መተማመን ጠንካራ መሆኑን ገልፀዋል።
“በእጅ የያዙት ወርቅ…” እንዲሉ ሆኖ እንጂ ዓድዋ ሚዛኑ ትልቅ ነው። በተለያዩ ምክንያቶች አንድ መሆን ተስኗቸው የነፃነታቸውን ዋጋ አሳልፈው የሰጡ አፍሪካን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አገራት ዛሬም ድረስ የእግር እሳት እንደሆነባቸው አንስተዋል።
ለአብነትም አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት በገዥዎቻቸው ችሮታ የተሰጡትን ቀን ነው የ“ነፃነት ቀን” እያሉ የሚያከብሩት፤ ጥቂቶቹ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ እና ናሚቢያ የመሳሰሉት ውጭ ተምረው በመጡ ልጆቻቸው አነሳሽነት በመሣሪያ አፈሙዝ ነፃነታቸውን እንዳስከበሩ አብራርተዋል። በመሆኑም ብዙዎቹ የሚያከብሩት የነፃነት ቀን (ኢንድፔንዳንስ ደይ) ሲሆን ኢትዮጵያ የምታከብረው ደግሞ የድል ቀን (ቪክትሪ ደይ) እንደሆነ አቶ አሳድረው ይናገራሉ፤
“ይሄ ድል ለአንድ ለተወሰነ የኢትዮጵያ አካባቢ ሕዝብ የሚሰጥ አይደለም” ያሉት አቶ አሳድረው፣ በዓድዋ ጦርነት ያልታገለ ብሔር በዚች አገር የለም። ነገር ግን ድሉ የአንድነታችን፣ የመተባበራችን፣ ለአገር ፍቅር እኩል የመሰዋታችን መገለጫ እንዳይሆን የሚሠሩ አካላት አሉ። ይሄን ማድረግ የሚገባት የሽንፈትን ጽዋ እየመረራት የተጎነጨችው ወራሪያችን መሆን ሲገባት እኛ ግን ርዕስ በራሳችን ልንጠላለፍበት እየሞከርን እንደሆነ ያስረዳሉ።
ትውልዱ የአገርን ፍቅርና የመንግሥትን ፍቅር በቅጡ መለየት አለበት። ያንን ማድረግ ካልቻለ መንግሥት ባልተመቸው ጊዜ አገሩን የሚጠላ አላዋቂ ትውልድ መፈጠሩ አይቀርም። የዓድዋ ዘማቾች ሁሉ የአፄ ምኒልክን ሥርዓት የሚወዱና የሚያፈቅሩ ተደርገው የሚወሰዱ ሳይሆን አገራቸውን የሚወዱ ናቸው። ድሉም የአገራቸው ፍቅር አንድ ያደረጋቸው የመላው የአገሪቱ ሕዝቦች በሕብረት ተነስተው የተጎናጸፉት ድል ነው ሲሉም ልዩነቱን ዜጎች እንዲያስታውሉ አመላክተዋል።
የአርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል የታላቅነት ምንጭ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያን መጠበቅና ገናና ማድረግ ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለፅ፤ ሕዝቡ ራሱ ተነስቶ ለአገሩ ዘብ መቆም አለበት። ይሄን ለማድረግ የመጀመሪያው ሥራ ደግሞ የራሱን ሰላም መጠበቅ ነው። በታሪክ ሂደት ውስጥ ጥሩ እና መጥፎ መኖራቸው አይቀሬ መሆኑን በመረዳት ጥሩ ጥሩውን ማስቀጠል ከመጥፎው ትምህርት ቀስሞ ማለፍ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ታሪክ የሌለው ሕዝብ ሊኖርም ሆነ ሊቀጥል አይችልም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የትናንትናውን ያወቀ ሕዝብ ዛሬ ላይ ቆሞ ነገን ማሰብ ይኖርበታል። የትምህርት ሥርዓቱን ጨምሮ በየዘርፉ የሚስተዋሉ ለውጦችን ተረድቶ “ነገ ለአገሬ ምን አደርጋለሁ?” በሚል ወጣቱ ሰንደቅ ዓላማውን ይዞ እንደ ጥንት አባቶቹ አገሩን ማስከበርና መጠበቅ ይኖርበታል። በማለት ከትውልዱ የሚጠበቀው ይህ ነው ብለዋል።
“አሁን ላይ የአገርን ክብር ማስጠበቅና አገርን ማሳደግ የሚቻለው ጦርነት በመክፈት፤ ጎራዴ በመምዘዝ እና አካኪ ዘራፍ በማለት አይደለም። ይልቁንም የተሻሉ ዶክተሮች፣ የተሻሉ የቴክኖሎጂ ሰዎች፣ የተሻሉ መሪዎች እና አስተዳዳሪዎች የሚፈጠሩበትን ስልት በመቀየስና ለችግሮቻችን መፍትሔ በማፍለቅ እንጂ፤” በማለት ትውልዱ ታሪኩን አክብሮ የራሱን ታሪክ መሥራት እንዳለበት ጠቅሰው፤ የዓድዋን 124ኛ ዓመት በዓል የሚችል ዓድዋ አደባባይ ወጥቶ የማይችል ደግሞ በየቤቱ የአገሩን ሰንደቅዓላማ በክብር አውለብልቦ እንዲያከብር ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ጠይቀዋል።
የአባድር መስጂድ ኢማም ሼህ መሐመድ ሳኒ በበኩላቸው፤ “የዓድዋ ድል ለአንድ ብሔር፣ ለአንድ እምነት እና ለአንድ አካባቢ ማህበረሰብ ተነጥሎ የሚሰጥ አይደለም። ምክንያቱም በዘር በእምነት እና በጎሳ ሳይለያዩ ኢትዮጵያውያን የተጎናጸፉት ክብር ነው” በማለት፤ የአሁኑ ትውልድ በመካከሉ የሚከፋፍለውን “ሰይጣን” እርግፍ አድርጎ መርሳት አለበት። ከዚህም በላይ ለአገሩ ሉዓላዊነት ዘብ በመቆም ዛሬ የካቲት 23 ቀን 2012 ዓ.ም በሚከበረው 124ኛው የዓድዋ ድል በዓል ዳግም ድል ለመሥራት ዜጎች በተለይም ወጣቶች ቃል የሚገቡበት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
ሙሐመድ ሁሴን