የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት በሚቀርፉ የምርምርና ፈጠራ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። በምርምርና በፈጠራ ስራ ግኝቶች የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በማሻሻል ምርታማ የሆነ የሰው ሀይል በመፍጠር ረገድም ድርሻቸው ላቀ ያለ ነው።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አገራዊ የሆኑ የህብረተሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ፤ ውጤታማ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ለተጠቃሚው ለማስተላለፍ የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት የተለያዩ ድጋፎችንና የእውቅና ሽልማቶችን የሰጠ ይገኛል ።
በዚህ ዝግጅት የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በምርምርና በፈጠራ ስራዎቻቸው የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነውን የፈጠራ ባለሙያ ኢንጂነር አረጋ አንቶኒዮስ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
ኢንጂነር አረጋ አንቶኒዮስ የፈጠራ ስራ ከልጅነቱ ጀምሮ የጀመረ ቢሆንም የሚያበረታታውና የሚደግፈው አካል አለመኖሩ ዝንባሌውን ለማውጣት ረጅም ጊዜ ወስዶበታል። ይህንን የተዳፈነ ፍላጎቱን ለማሳካትም ሆነ በስፋት ለመስራት እድሉ የተከፈተለት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የማኑፍክቸሪንግ ምህንድስና ተማሪ በነበረበት ጊዜ ነው።
ኢንጂነር አረጋ ‹‹ማኑፋክቸሪንግ ምህንድስና በጣም ደስ እያለኝ ፈልጌ የተማርኩት ትምህርት ነው። የመረጠኩበት ቀድሜ አስቤበት በመሆኑ አሁን ለተሰማራሁበት ስራ አጋዥ ሆኖኛል ።›› በማለት ለወደፊት ለመስራት ላቀደው ስራ መሠረት እንደሆነው ይናገራል።
የፈጠራ ስራዎቹ ምንነት
ኢንጂነር አረጋ የበርካታ የፈጠራ ስራዎች ባለቤት ነው። እነዚህም ኮምፕኔሽን ሲኤንሲ ማሽን/Combination CNC Machine /Mill and Lather/ ፣ የመሰላል ቅርጽ ማውጣት፤ እንዲሁም ፑል የመስራትና ሌሎች አገልግሎቶች ያሉት ነው። ሁለተኛው መልቲ ስፔንዳል/ 4 ስፔንዳል/ 7 አክሲስ ሲኤልሲ ማሽን /Multi Spindel/4 Spindel /7 Axis Machine , ሙሉ ለሙሉ በኮምፒውተር የሚቆጣጠር ማሽን ሆኖ ማንኛውንም አይነት ምስሎች በብረት፤ በአሉሙኒየም፤ በጣውላ፤ በፕላስቲክ ላይ መቅረጽ የሚችል ነው።
ሦስተኛው ሰልፍ ፓውር ኢንጂን /Self powerd Engine/ በአይነትም ሆነ በይዘት አሁን ካሉት የሚለይ ሆኖ፤ ነዳጅ ወይም ኤሌክትሪክ ቻርድ የማይጠይቅ እራሱ በራሱ ቻርድ የሚያደርግ ነው። አራተኛው ስፔሻል ፐርፐዝ ጊር ከቲንግ ማሽን/ Special purpose gear cutting Machine/ የተለያዩ ጥርሶችን ማውጣት የሚችል ማሽን ነው። አምስተኛው ዲጅታል ኬሚካል ሪአክሽን /digital chemical reactor/ የኬሚካል ውህደት የሚያቀላጥፍ ነው። ስድስተኛው ሃይ ኤንድ ሎው ዴንሲቲ ፕላሰቲክ ግሬንደረ ማሽን/ high and low density plastic Grinding Machine/ ማንኛውንም አይነት ፕላስቲክ መፍጫት የሚችል ማሽን ነው።
ሰባተኛው ስፔሻል ፐርፐዝ ሲኤንሲ/ Special purpose CNC/ computer Numerical controlled Machine / የተለያዩ ምስሎችንና ሐውልቶችን ይቀርጻል፤ በመቃብር እምነበረድ ላይ የተለያዩ ፅሁፎችንና ምስሎችን መቅረጽ የሚችል ማሽን ነው። ስምንተኛው ታንዶም ፈላክስ ኮርድ ዌልዲንግ ማሽን/Tandom Flax cored welding /mig Welding Machine / ስራ የሚያቃልል የመበየጃ ማሽን ነው። ዘጠነኛው ኮፊ ፕሮሰሲንግ ማሽን / Coffee Processing Machine / የቡና ማቀነባበሪያ ማሽን ነው። አስረኛው ሃይ ኢንደ ሎ ዲንሲቲ ፊበር ቦርድ ኮፊ ሁከር /High and low density Fiber board from coffee huskes/ ቸቡድና ኮምፐርሳቶን ከቡና ቅርፊት የማምረት ማሽን ሲሆን፤ አስረአንደኛው ሃይ ተርስት ተረቦ ሽፍት ጄት ኢንጂን /high Trust Turbo Shaft Jet Engine / ነዳጅ ቆጣቢ ፈጣንና ክብደቱ ቀላል የሆነ የተዋጊና የመንገደኞች አውሮፕላን ሞተር ናቸው።
የፈጠራ ስራው ለየት የሚያደርገው
ኢንጂነር አረጋ የፈጠራ ስራዎች ከሌሎች የሚለይበትን ሲብራራም፤ የፈጠራ ስራው ከዚህ ቀደም ያልተሰራ አዲስ ፈጠራ ነው። ሌዝና ሚሊ ማሽን/Mill and Lather/ አንድ ላይ በማድረግ የተሰራ ሲሆን አነስተኛ ኃይል የሚጠቀም ዋጋውም ተመጣጣኝ ነው። ነገር ግን ሁለቱ ማሽኖች ለየብቻቸው ሚሊ ማሽን እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር፤ ሊዝ ማሽን ደግሞ ከ500 ሺህ እስከ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡና ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ናቸው። ብሏል።
የፈጠራ ስራው ያስገኘው እውቅና እና ሽልማት
ኢንጂነር አረጋ በፈጠራ ስራው ከአዲስ አባባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ሽልማት የእውቅና ሰርተፈኬትና የብር ሜዳሊያ ተሸላሚም ሆኗል።
በተጨማሪም፤ በቅርቡ ኬንያ ላይ ከጥቅምት 17- 23 ሴፍ ዘ ችልድረን የተባለ ድርጅት አማካይነት ስራዎቹን በማቅረብ ሁለተኛ ውጥቷል። እንዲሁም ዘንድሮ አይቤኤም ኢትዮጵያን አት አፍሪካን ኢኖቬሽን / IBM Ethiopia at African innovation week/ ሳምንት ላይ በመሳተፍ የእውቅና ሰርተፊኬት ተሸልሟል።
በፈጠራው ስራ ያጋጠሙ ፈተናዎች
እንደ ኢንጂነር አረጋ ገለጻ የፈጠራ ስራዎቹን ህብረተሰቡ ዘንድ ለማድረስ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም ድጋፍ የሚያደርግለት ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ማግኘት አልቻለም ። የፈጠራ ስራውን የተመለከቱ ድርጅቶች ስራዎቹን ቢውዱም ደፍረው ለመቀበል የሚቸገሩ መሆኑን ይናገራል።
አብዛኛው በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የፈጠራ ስራዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ሆነው ዋጋቸው ተመጣጣኝ ቢሆንም ለመግዛት ባለመፈለግ የሚያጥላሉ ብዙዎች መሆናቸው የሚጠቁመው ኢንጂነር አረጋ፤ የመስሪያ ቦታ ችግር የሚቀረፍለት ከሆነ ቀስ በቀስ የፋይናንስ አቅሙን በማሳደግ ስራዎቹን ከህብረተሰቡ ዘንድ ለማድረስ እንደሚጥር ይጠቁማል።
እንደ ኢንጂነር አረጋ አይነት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን ከማበረታታትና ከመሸለም በዘለለ ለዘርፉ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ላቅ ያለ በመሆኑ ጥቅም ላይ ለማዋል መሠራት እንዳለበት ለመጠቆም እንወዳለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
ወርቅነሽ ደምሰው