
እንኳን ለ124ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ፡፡
ዓድዋ በየትውልዱ እየተመነዘረ ለብልጽግና ጉዟችን ልንጠቀምበት የምንችለው ታላቅ ሀብታችን ነው። ዓድዋ ኢትዮጵያውያን አንድም ብዙም መሆናችንን ያሳየንበት ታሪክ ነው። በባህል፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በእምነት የየራሳችን ማንነት አለን። ይህ ማንነታችን በአገራችን ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ታግለናል፣ እንታገላለን።
ከዚህ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ ያሰኘን አንድነትም አለን። ጣልያኖች ወደ ዓድዋ ሲመጡ የታያቸው ልዩነታችን ነው። በልዩነታችን ላይ ሠርተው ኢትዮጵያውያንን በማዳከም ቅኝ ግዛትን ሊጭኑብን አስበው ነበር። የኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ፀጋዎች መከፋፈያዎች የሚሆኑ መስሏቸው በተለያየ መንገድ ሞክረው ነበር። ወደ ዓድዋ ሲመጡ ግን ያሰቡትን አላገኙም።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ፤ በሉዓላዊነታቸው ጉዳይ፣ በነፃነታቸው ጉዳይ፣ የማይደራደሩ መሆኑን አዩ። ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ፀጋ እንጂ መለያየት እንደሌላቸው ዓድዋ አሳያቸው። ኢትዮጵያውያን ሕብራዊ አንድነት እንዳላቸው ዓድዋ መሰከረ።
ልዩ ልዩ ፀጋዎቻችንን የመለያያ ምክንያት የማድረግ ዘመቻ ፈፅሞ እንደማይሳካ ዓድዋ ህያው ምስክር ነው። ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ዘመቻ ዋዜማ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ነበሯቸው። ከወቅቱ መሪዎች ጋር በሁሉም ነገር የሚስማሙ አልነበሩም። የዘመኑ አስተዳደር ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አልነበረም።
እነዚህን አገራዊ ችግሮች አቀጣጥለው አገር የማዳከሚያ መሣሪያ ለማድረግ ጣልያኖች ሞክረዋል። ቁስሉን ለማዳን ሳይሆን በቁስሉ ለማስለቀስ ጥረዋል። ኢትዮጵያውያን ግን ችግራችንን እንፈታለን፤ አገራችንን እንጠብቃለን ብለው አልተቀበሉትም።
ጥያቄዎች ሁሉ የሚመለሱት አገር ስትኖር መሆኑን ኢትዮጵያውያን ያውቁ ነበር። ኢትዮጵያውያን ለቁንጫ ሲሉ ቤት የሚያቃጥሉ፤ ለአረም ሲሉ ማሳውን የሚያጠፉ አልነበሩም። ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በተመለከተ ዘላቂ መርህ አላቸው። ዋልታና ማገሩን እጠብቃለሁ፤ ውስጡንም አፀዳለሁ የሚል።
ቤቱ ቤት ሆኖ እንዲኖር ዋልታና ማገሩን ማጥበቅ ያስፈልጋል። ቤቱን ለማጽዳት መጀመሪያ ቤቱ ቤት መሆን አለበት። ቤቱ በሌለበት የቤቱ ጽዳት አይኖርም። ቤቱ ግን ሊቆሽሽ ወይም ተባይ ሊያፈራ ይችላል። ቤቱን እያጠበቅን፥ እያጸናን ውስጡን ደግሞ እናፀዳለን።
ዓድዋ ሌላም ትምህርት ሰጥቶናል። ችግሮቻችንን እንዴት ማየት እንዳለብን። ዐፄ ምኒልክና የዓድዋ ዘማቾች ለዘመኑ ችግር በቂ ዝግጅት አድርገው ነበር። ያዘጋጇቸው መድፎች ከጣልያን መድፎች የተሻሉ ነበሩ። ጣልያን ወታደሮቹን ካንቀሳቀሰበት አቅም በላይ ሕዝቡን ለማንቀሳቀስ ችለዋል። የት ቦታ፣ እንዴት፣ ጠላታቸውን ገጥመው ሊያሸንፉት እንደሚችሉ አቅደዋል። የዓድዋ ድል የዚህ የላቀ ዝግጅት ውጤት ነው።
ከአርባ ዓመት በኋላ ጣልያን ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ልንቋቋመው ያልቻልነው በዓድዋ ዘመቻ ያደረግነውን ነገ ተኮር ዝግጅት ስላላደረግን ነው:: ጣልያን በአየር ሲመጣ በመሬት ገጠምነው:: ጣልያን የምድር ላይ መሣሪያዎቹን አዘምኖ ሲመጣ እኛ ያለንን ይዘን ጠበቅነው። ከዘመኑ ቀድመን አልተገኘንም።
ዛሬ ከትናንት የተሻልን መሆናችን ብቻ በቂ አይደለም። ሥልጣኔ ማለት ከነገ መቅደም ነው። ነገ ከሚመጣው ችግር በልጦ መገኘት ነው። ከዓድዋ የምንማረው አንዱ ትልቅ ትምህርት ይህ ነው። ትናንት ለገጠመን ችግር መፍትሔ መስጠት ችሎታ ነው:: ዛሬ ለሚገጥመን ችግር መፍትሔ ማስቀመጥ ብልሐት ነው:: ወደፊት ከሚመጣው ችግር በልጦ መገኘት ግን ጥበብ ነው::
የዓድዋ ዘመቻ የጦርነት ዘመቻ ብቻ አልነበረም። የቴክኖሎጂ ዘመቻ፣ የዲፕሎማሲ ዘመቻ፣ የትዕግሥት ዘመቻ፣ የፖለቲካ ዘመቻ፣ የሎጅስቲክ ዘመቻ፣ የፍቅርና የይቅርታ ዘመቻ ጭምር ነበር። በዘመኑ የተሻሉ መሣሪያዎችን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን መሣሪያዎቹን አውቆ መጠቀም ለመቻል ዝግጅት ተደርጓል።
ጦርነትን ለማስቀረት እንዲቻል ብቻ ሳይሆን ለዝግጅት ጊዜ ለማግኘት እንዲቻል ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ተሠርቷል። ችግርን በትክክለኛው ጊዜና ሁኔታ ለመግጠም ሲባል በፈታኝ ትእግሥት ውስጥ ታልፏል። ለዚያ ሁሉ ሠራዊት የሚሆን ስንቅና ትጥቅ ለማዘጋጀት ሕዝቡን አንቀሳቅሰዋል። ውስጣዊ ቅራኔዎች አገራዊ አደጋ እንዳያስከትሉ የእርቅና የመቻቻል ሥራዎች ተሠርተዋል።
ዛሬም እንደ ሀገር የገጠመንን ችግር ለመፍታት የዓድዋ ዘማቾች የተጠቀሙባቸውን ዘርፈ ብዙ መፍትሔዎች መጠቀም አለብን። ቴክኖሎጂ መጠቀም፣ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ማድረግ፣ በትዕግሥት ጊዜ መስጠት፣ የፖለቲካ መፍትሔዎችን መስጠት፣ አቅም ማጠራቀም፣ በፍቅርና በይቅርታ መንገድ መጓዝ፣ ሌሎችም ያስፈልጉናል።
የዓድዋ ዘመቻ፣ ድል እንዴት መጠናቀቅ እንዳለበት ያስተማረ ታላቅ ታሪካችን ነው። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው የመጣባቸውን ወራሪ መክተዋል። መክተዋል ብቻ ሳይሆን አሳፍረው መልሰዋል። ነገር ግን የውጭ ጠላታቸውን ድል ያደረጉበትን አቅም የራሳቸውን ጉዳይ ለመፍታት አላዋሉትም።
አንድ ታላቅ ሀገራዊ ድል ካገኘን በኋላ ውስጣዊ ጥንካሬያችንን በድላችን ልክ ለማድረግ ካልሠራን ድላችንን የሚያሳጣ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመን ይችል ይሆናል። ለምን አሸነፍን? ያሸነፍንበትን ምስጢር ለውስጣዊ የሀገር ግንባታ እንዴት እንጠቀምበት? የዛሬውን ጠላት አሸነፍን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን ነገ ከሚመጣው ጠላት የተሻለች አድርገን እንዴት እናቆያት?
እነዚህን ጉዳዮች አለማየት ከዓድዋ ድል አርባ ዓመት በኋላ በማይጨው ዘመቻ የገጠመንን እንዲገጥመን መፍረድ ነው። ያ እንዲሆን ዛሬ ፈጽመን አንፈቅድም። በዓድዋ ድል የተነሳሱ ብዙ ሕዝቦች ሮጠው ቀድመውናል። የተሻለ ሀገረ መንግሥት ገንብተዋል፤ የተሻለ ብሔረ መንግሥት አዳብረዋል። ዴሞክራሲያቸውን፣ የፍትሕ ሥርዓታቸውንና ኢኮኖሚያቸውን አዘምነዋል። ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ሲቆረጥ ለምን ዝም እንላለን? የመደመር ጎዳና ኢትዮጵያ የዓድዋ ድሏን በሚመጥን ደረጃ እንድትጓዝ የተገነባ መንገድ ነው።
ለዓድዋ ድላችን የሚመጥነው የኢትዮጵያ ከፍታ ብልጽግና ነው። እኛ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የመጣን የዓድዋ ዘማቾች ነን። አንድ ሆነን ጠላታችንን ተዋግተን ድል እንዳደረግነው ሁሉ አንድ ሆነን አገር እንገነባለን። አንድ ሆነን ሀገራችንን ወደ ብልጽግና እናደርሳለን። የትናንት እናቶቻችንንና አባቶቻቸንን ድል ዛሬ እንዳከበርነው ሁሉ የእኛንም ድል ነገ ልጆቻችን ያከብሩታል።
እነርሱ የቅኝ ግዛትን ቀንበር ሰብረው ነው:: እኛ ደግሞ የድህነትን ቀንበር እንሰብራለን። እነርሱ ነፃ ሀገር ፈጥረዋል፣ እኛ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሀገር እንፈጥራለን። እነርሱ በመደመር ተጉዘው የዓድዋን ድል አስገኝተዋል። እኛም በመደመር ተጉዘን የብልጽግናን ድል እናገኛለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፤ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012