የአገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን ግብርናን ማዘመን፤ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻልና ጥራትን ማስመዝገብ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በግብርና ለሚተዳደሩ አገራት ወሳኝ ነው። በመሆኑም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ማፍራት እና ዘመናዊ ግብርናን ተጠቅሞ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ከፍታ ማድረስ ሲሆን፤ ለዚህም በአገሪቱ የሚገኙ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ከግብርና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የሚወጡ ተማሪዎች ግብርናን ለማዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት በአገሪቱ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ 19 የግብርና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች አሉ። ከእነዚህ ኮሌጆች መካከልም በመንግሥት በተመረጡ አራት የግብርና ኮሌጆች ላይ ATTSVE (Agricultural Transformation through Vocational Education) የተባለው ፕሮጀክት ድጋፍና ክትትል በማድረግ አቅም የመገንባት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
የ”ATTSVE” ፕሮጀክት የአገር ውስጥ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሰለ ጫኔ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ የገባው እ.አ.አ በ2015 ሲሆን፤ 18 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ወጪ ተደርጎበታልም ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተመረጡ አራት የግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች ማለትም ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማይጨው፤ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወረታ፤ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ነጆ፤ እንዲሁም ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በወላይታ ሶዶ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ላይ ተቋማዊ ለውጥ በማምጣት፣ በመምህራን ልማትና የእርስ በእርስ ግንኙነት የመፍጠር ሥራ ይሠራል።
ተቋማዊ ለውጥን ለማምጣት በዋናነት የሙያ ስልጠና እና የግብዓት አቅርቦት፤ ማለትም የመማሪያና ማስተማሪያ ቁሳቁሶችን፣ የሠርቶ ማሳያ፤ እንዲሁም የላብራቶሪ ግብዓቶችን አሟልቷል። ከአራቱ ኮሌጆች የተውጣጡ 150 የሚደርሱ መምህራን በደቡብ አፍሪካ፤ በህንድ፤ በኬኒያና በካናዳ በአይነታቸው 53 የሚደርሱ የሙያ ስልጠናዎች ያገኙ ሲሆን፤ በተጨማሪም የአስተዳደርና የቴክኒክ ስልጠና መሰጠቱን አቶ መሰለ ተናግረዋል።
የመምህራንን ልማት በተመለከተ 73 መምህራን ከዲፕሎማ ደረጃ ወደመጀመሪያ ዲግሪ፤ ከመጀመሪያ ዲግሪ ወደሁለተኛ ዲግሪ የሚያሸጋግር ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ መምህሩ በክህሎት፣ በዕውቀትና በአመለካከት አቅሙን የመገንባት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በዚህም ኮሌጆቹ ገበያው የሚፈልገውንና ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ማፍራት ሲሆን፤ እነዚህ ተማሪዎችም አርሶ አደሩ ጋርም ሆነ በግል እርሻዎች ላይ ተሳትፈው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ ይጠበቃለ።
ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከአራቱም ኮሌጆች የተውጣጡ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በተለያዩ ሙያዎች ተመርቀዋል ያሉት አቶ መሰለ፤ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተማረ የሰው ኃይል አስፈላጊ እንደመሆኑ፤ ፕሮጀክቱ በመሰረታዊነት እየሠራ የሚገኘውም ገበያው በሚፈልጋቸው ተምርት ዓይነቶችና አርሶ አደሩን ሊያግዙ በሚችሉ ዘርፎች ነው። በመንግሥት የሚሰጡ የእንስሳት ህክምና፣ የእፅዋት ሳይንስ የእንስሳት ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ሀብት እና የመሳሰሉ የትምህርት ዓይነቶችን የሚሰጡ ሲሆን፤
ከመደበኛ ስልጠናዎች በተጨማሪ የአጫጭር ጊዜ ስልጠና በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በወተት ልማት፣ በዶሮ እርባታና መሰል የግብርና ሙያዎች ይሰጣሉ። ለማስተማር የሚያግዙ በአይነታቸው 500 የሚደርሱ የተግባር ትምህርት መለማመጃ ግብዓቶችም ለአራቱ ኮሌጆች ቀርበዋል። ከነዚህም መካከል የአፈር ለምነት መለኪያ፤ የአዝዕርት እርጥበት መለኪያ፤ የመኖ ማቀነባበሪያ እና የወተት ማቀነባበሪያ መሳሪያዎች ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም 532 ኮምፒውተሮች፣ ከ600 በላይ የመማሪያ መፅሐፍቶችና 40 LCD Projectors ለኮሌጆቹ መሰጠቱን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የትምህርት ዘርፍ አቅጣጫ ተመራቂ ተማሪዎችን ሥራ ፈጣሪ ማድረግ በመሆኑ ፕሮጀክቱ፤ ከአራቱም ኮሌጆች የተመረጡ ተማሪዎችን በማደራጀት የሥራ ፈጠራ ዕቅድ እንዲያዘጋጁ ያደርጋል። በዚህም 61 አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የተቋቋሙ ሲሆን፤ እነዚህ 61 ኢንተርፕራይዞች ደግሞ 300 የሚደርሱ አባላት ይዘው በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የራሳቸውን ሥራ መሥራት እንዲችሉ ድጋፍና ክትትል መደረጉን አቶ መሰለ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ፤ ለአራቱም ኮሌጆች በሚሰጠው ድጋፍና ክትትል እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ስለመኖራቸው በትግራይ ክልል ማይጨው የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ ጌታቸው ካህሳይ ይገልፃሉ፤ ፕሮጀክቱ በዋናነት የትምህርት መማሪያና ማስተማሪያዎችን በማሟላት፣ ሰፋፊ ስልጠናዎችን ለመምህራን በመስጠትና አቅም የመገንባት ሥራ እየሠራ ይገኛል።
በተለይም ለትምህርት ጥራት እንቅፋት ሆኖ የነበረውን የኮምፒውተር ችግር ለማቃለል 100 ኮምፒውተሮችን ከፍተኛ አቅም ካለው የኢንተርኔት አቅም ጋር ያቀረበላቸው መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም እያንዳንዱ መምህራን በአሁን ወቅት ኮምፒውተር ተጠቅሞ እያስተማረ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም የተሟላ ላብራቶሪ በመኖሩ ተማሪዎች 70 በመቶ በተግባር መማር እንደቻሉና ውጤታማ እንደሆኑ አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።
በአካባቢው ከሚገኙ ከምርምር ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከአምስት የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ኮሌጆች ጋር በትብብር መሥራት እንዲቻልም ጠንካራ የሆነ ግንኙነት መፈጠሩን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ኮሌጁ ከፕሮጀክቱ ጋር በመተባበር መሥራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይም ከዚህ በፊት በተግባር ሥራ መማር ያልቻሉ ተማሪዎች በአሁን ወቅት የተለያዩ የላብራቶሪ ግብዓቶችን ተጠቅመው በእንስሳት ሀብት እርባታ ላይ ውጤታማ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከኮሌጁ በመጀመሪያ ዙር ተመርቀው የወጡ 45 ተማሪዎችም በዶሮ እርባታ፣ በእንስሳት ማድለብ እና ዳቦ ቤት ከፍተው እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን፤ ወጣቶቹ እራሳቸውን ከመቻል ባለፈ ማህበረሰቡን እያገለገሉ እንደሚገኙ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል። በተጨማሪም የማይጨው የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ከተመረጡት አራት ኮሌጆች አንዱ በመሆኑ በዞኑ እና በክልሉ ለሚገኙ በርካታ ኮሌጆች ተሞክሮውን እያካፈለ ይገኛል።
በግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ሰልጥነው የሚወጡ ተማሪዎች በተግባር ህብረተሰቡን በተለይም አርሶ አደሩን በማገዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ አርሶአደሩ ዘንድ ወርደው ስልጠና በመስጠት ውጤታማ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል። በአጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው በጎ ተፅዕኖ የጎላ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግብርናን ማዘመን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
ፍሬህይወት አወቀ