እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም ዓድዋ፤ የኢጣሊያ መንግስት የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ። ጣልያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው ነበር። ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮታል። ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው። ከዓድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪካን ምድር ለቆቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ።
ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረ። የወረራው ስልትና የአገዛዝ ዘመኑ እጅግ አሰቃቂ እንደነበር ለበርካታ ጊዜያት በምሁራን፤ በፖለቲከኞች፤ በጋዜጠኞችና በሌሎች ዓለም አቀፍ የማህበረሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ ተገልጿል። የፋሺስት ኢጣሊያ የጦር ውጊያና አገዛዝ ጭካኔም ሆነ የኢትዮጵያውያን ጀግንነትና መስዋዕትነት እንኳንስ በዐይኑ ለማየት ከቻለው ይቅርና በታሪክ ከሰማውና ካነበበው ሰው ህሊና የሚጠፋ አይደለም። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ላይ የተቀዳጀችው የዓድዋ ድል እስከ ዛሬ ድረስ የበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል። መገናኛ ብዙኃኑ ድሉ የተገኘበትን መንገድና ለኢትዮጵያ የነበረውን ፋይዳ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ አንድምታውን እየዘረዘሩ ጽፈዋል።
ኳርትዝ የተባለው ድረ-ገፅ “የአፍሪካን ታሪክ ማወቅ ከፈለግን የዓድዋ ድል እውቀቱ ሊኖረን ይገባል” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ ኢትዮጵያና ኢጣሊያ ያደረጉትና በመጨረሻ በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የዓድዋ ጦርነት የአፍሪካ ታሪክ አካል በመሆኑ የዓድዋ ድል ያልተካተተበት የአህጉሪቱ ታሪክ ሙሉ ታሪክ እንደማይሆን ያትታል።
እንደ ጽሑፉ፤ ድሉ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ አካል ለማድረግ የነበራትን የወቅቱን ምኞት ያከሸፈባት ከመሆኑም በላይ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩ አፍሪካውያንን ያነቃቃ ነበር። ከጦርነቱ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ የተፈረመውና አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የነደፉት እቅድ አካል የሆነው የውጫሌ ውል (Treaty of Wuchale) ለዓድዋ ጦርነት እንደመነሻ ተደርጎ ቢወሰድም ቅሉ፤ የጦርነቱ መሰረታዊ መንስዔ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ አካል ለማድረግ የነበራት የረጅም ጊዜ ፍላጎት ነበር።
ድሉ ኢትዮጵያ ለየትኛውም የአውሮፓ አገር ተገዢ ያልሆነች ሉዓላዊት አገር እንደሆነች ማረጋገጫ የሰጠ ታሪካዊ ክስተት ነው። የዓድዋ ድል የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የዜና ማድመቂያ ሳይሆን አውሮፓውያንን ያስገረመና ያስደነገጠ ድል ነበር። አውሮፓውያን መንግሥታት የጦርና የቅኝ ግዛት አስተዳደር ስትራቴጂዎቻቸውን እንዲያጤኑና እንዲከልሱ ምክንያት ሆኗል።
ኢጣሊያ ባላሰበችውና ባልጠበቀችው ሁኔታ በቀላሉ አሸንፋታለሁ ብላ በገመተቻት ኢትዮጵያ መሸነፏ በአውሮፓ አጋሮቿ ዘንድ ዝቅ ተደርጎ የመገመት ጫና አሳድሮባታል። ይህን ጫና ለማቃለልና የዓድዋውን ሽንፈት ለመበቀልም በ1928 ዓ.ም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመውረር ሽንፈቷን ለመበቀልና የረጅም ጊዜ ምኞቷን ለማሳካት ሞክራለች።
“የዓድዋ ድል በሁሉም መመዘኛ እጅግ አስደናቂ ነበር” የሚለው ድረገጹ፤ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን ነፃነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል ያስቻለና መላው ዓለም በድሉ ተደንቆ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲያከብር ያስገደደ አጋጣሚ የፈጠረ ድል እንደሆነ በጽሑፉ አመልክቷል።
ኢንተርናሽናል ኢንተረስት የተባለ ድረ-ገፅ የዓድዋን ድል “አፍሪካን ያስገረመ ታላቅ ድ”› በማለት ገልጾታል። የድረ-ገፁ ጽሑፍ እንዳተተው፣ ድሉ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንድትቆይ ከማስቻሉም በተጨማሪ፤ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የነደፉት እቅድ ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል። ከዚህ ባሻገር ድሉ ኢትዮጵያ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ሞዴል ሆና እንድትታይና ሌሎች የአፍሪካ አገራት በቅኝ ገዢዎቻቸው አውሮፓውያን ላይ እንዲያምፁ ተምሳሌት ትሆናለች ተብሎ እንደታሰበም ጽሑፉ ይገልፃል። ድረ-ገፁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ለጦርነቱ ያደረጉትን ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅትም ጠቅሷል። ንጉሡ ካደረጉት ጠንቃቃነትና ዝግጅት በተጨማሪም የኢጣሊያ ጦር አዝማቾች በጦርነቱ ላይ የሠሯቸው ስህተቶችም ለድሉ የራሳቸውን አስተዋፅዖ እንደነበራቸው በጽሑፉ ጠቁሟል።
ዝነኛውና አንጋፋው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ “አቢሲኒያውያን ኢጣሊያውያንን አሸነ”› በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና፣ ኢትዮጵያን ለመውረር የገሰገሱት የኢጣሊያ ጦር መሪዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ስለመሸነፋቸውና “አቢሲኒያውያን” ብሎ የጠቀሳቸው ኢትዮጵያውያን ኃይለኛ የማጥቃት ዘመቻ ከፍተው የኢጣሊያን ጦር ስለማሸነፋቸው ጽፏል። የኢጣሊያ ጦር አዛዦች ወደ ዓድዋ ሲገሰግሱ ብዙም መከላከል እንዳልገጠማቸውና ዓድዋ ከደረሱ በኋላ ግን ነገሮች ሁሉ ስለመቀያየራቸው ጋዜጣው ዘግቧል። የኢጣሊያንን ሽንፈት “አሰቃቂ ሽንፈት” ሲል የገለጸው አንጋፋው ጋዜጣ፣ የጀኔራል ባራቶሪ ጦር ከባድ መከላከልና ማጥቃት ገጥሞት ብትንትኑ እንደወጣ በወቅቱ እትሙ አመልክቷል።
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዓድዋ በዓል ወቅት ከወጣ ፅሑፍ የተወሰደ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
መርድ ክፍሉ