ከብዙ ጊዜያት በፊት በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ነበሩ። እነርሱንም የሚያስተዳድር አንድ ንጉሥም ነበር። ይህ ንጉሥ የሚያስተዳድራቸውን ነዋሪዎች በደስታ ያኖራቸው ነበር። በእሱ የአገዛዝ ዘመን ሁሉም ነዋሪዎች በነፃነት ተገቢውን ነገር በማድረግ በሰላም ኑሯቸውን ይመራሉ። ንጉሣቸው እርሱ በመሆኑም በጣም ደስተኞች ነበሩ።
በአንድ ወቅት ንጉሡ በአገሪቷ ላይ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን፣ የአምልኮ ስርዓት የሚፈፀምባቸው ቤተክርስቲያናትን እንዲሁም እርሱ በአገዛዙ ወቅት ያልተመለከታቸውን እና በርቀት ያሉ አካባቢዎችን ለመመልከት ይወስናል። እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው እርሱ የሚያስተዳድራቸውን ቦታዎች ለማወቅ እና ሁሉም ስፍራዎች ምቹ እና የማህበረሰብ ክፍሎችም በሰላም እና በተድላ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ስለፈለገ ነበር።
ንጉሡ ጉብኝቱን በእግሩ በመጓዝ ለማድረግ ይወስናል። አገልጋዮቹን እና አብረውት የሚጓዙ ቤተሰቦቹንም ከእርሱ ጋር በእግራቸው እንዲጓዙ አደረገ። ንጉሡ ይህንን ለማድረግ የወሰነበት ምክንያት በቀላሉ የሚያስተዳድራቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲያገኝ ስለሚያስችለው ነበር። በዚህ የተነሳ እርሱ ጉብኝት በሚያደርግባቸው አካባቢዎች የሚያገኛቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ንጉሣቸውን በማግኘታቸው እና ከእርሱም ጋር በማውራታቸው ፍፁም ደስተኛ ሆኑ። እነርሱ በዚህ ንጉሥ ስር ስለሚተዳደሩ እና ቅን ልቦና ያለው መሪ ስላላቸው ደስተኞች ሆኑ።
ይህ ቅን ንጉሥ በርካታ የአገሩን አስደናቂ ቦታዎች መመልከት ቻለ። ታሪካዊ ቦታዎችን፣ የእምነት ስፍራዎችን በተፈጥሮ የተዋቡ አካባቢዎችን እንዲሁም በርካታ ባህል ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ማግኘት በመቻሉ በጣም ደስተኛ ሆነ። አገሩ እጅግ የበለፀገች በመሆኗም የሚያምነውን አምላክ አመሰገነ።
ይህ ንጉሥ በሚደርስበት አካባቢ ሁሉ እጅግ በከበረ ሁኔታ አቀባበል ይደረግለት ነበር። ነዋሪዎቹም ቅን እና ለማህበረሰቡ ከልቡ አሳቢ በመሆኑ እጅ እየነሱ ያመሰግኑታል። ከብዙ ቀናት የጉብኝት ቆይታ በኋላ ጉብኝቱን አጠናቀቀ ወደ መኖሪያ ስፍራውም ደስተኛ ሆኖ ተመለሰ። እርሱ የሚያስተዳድራቸው ሰዎች በተድላ እና በደስታ መኖራቸውንም በዓይኑ አይቶ መመስከር ቻለ። ሁሉም ነዋሪዎች ኑሯቸውን ያለምንም ችግር ይመሩ ነበር። አብዛኞቹ በግብርና ሥራ፣በከብት ማርባት እና በብረታብረት ምርት ላይ አድርገው ነበር። ኑሯቸውን የሚያቀልላቸው አዳዲስ ማሽኖች ይፈጥሩ እና ይገለገሉባቸውም ነበር።
ነገር ግን ይህ ንጉሥ በጉብኝቱ ወቅት አንድ ያዘነበት እና ቢስተካከል ብሎ ያሰበው ጉዳይ ነበር። ረጅም ርቀት በመጓዝ ጉብኝት ባደረገበት ወቅት እግሩን በጣም ታሞ ነበር። እግሩን የሚከላከልለት ምንም ነገር ስላልነበረም በጣም ለሚያስጨንቅ ህመም ተዳርጓል። የውስጥ እግሩም ቆስሎ መሬት ለመርገጥ በጣም ተቸግሮ ለትንሽ ጊዜም ቆየ። ባለሟሎቹ እና ቤተሰቦቹ በተፈጠረው ነገር በጣም በማዘን በቶሎ እንዲያገግም ዕርዳታ ያደርጉለት ጀመር።
ከህመሙ እንዳገገመ አንደኛውን ሚኒስትሩን በመጥራት ስለተፈጠረው ነገር አናገረው። እንዲህም አለው «አገሪቷ ላይ ያሉትን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሃይማኖታዊ ስፍራዎች በመመልከቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ህዝቦቼም በተድላ እና በደስታ በመኖራቸው እረክቻለሁ። ነገር ግን አንድ ጉዳይ አላስደሰተኝም። ይህም የተጓዝንበት መንገድ በጣም የማይመች እና ኮሮኮንቻማ ነበር። ጠጠር እና ሹል ድንጋዮችም ይበዙበት ነበር። እኔ ለጥቂት ግዜያት በእነዚህ አካባቢዎች ስጓዝ ይህ ችግር አጋጥሞኛል። ነገር ግን ሁል ጊዜ በእነዚህ መንገዶች የሚገለገሉት ህዝቦቼ ምን ያክል ይሰቃያሉ? ይህ ጉዳይ ለህዝቤ ምቾትን የሚቀንስ እንደሆነ ተረድቻለሁ። ነገሩ በጣም አሳስቦኛል» አለው።
ለሚኒስትሩ ይህን ካለው በኋላ እንዲህ በማለት ትዕዛዝ ሰጠ « በሁሉም መንገዶች ላይ የበሬ ቆዳዎችን አንጥፉ። በዚህ ምክንያት ህዝቦቼ እንዲሰቃዩ አልፈልግም። ይህን ቆዳ ካነጠፋችሁ ግን ሁሉም ሰው በምቾት መንቀሳቀስ ይችላል» አለው።
ሚኒስትሩ ንጉሡ ይህን ሲል በመስማቱ በጣም ግርምት እና ጥያቄ ተፈጠረበት። ምክንያቱም የንጉሡን ትዕዛዝ በማክበር እነዚህ ቆዳዎች እንዲነጠፉ ቢደረግ በጣም በብዙ መቶ ሺ የሚገመቱ ከብቶች መሞት ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ አርሶአደሩ ለወተት ምርት እና ለግብርና ሥራ የሚጠቀምባቸውን ከብቶች ሊያጣ ይችላል። በመንገዶቹ ላይ ቆዳውን ለማንጠፍ ደግሞ በጣም ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ እና ከባድ ነበር። የአገሪቷን ሀብትም በቀላሉ የሚያጠፋ ነበር። በዚህ የተነሳም ከንጉሡ ትዕዛዝ ሲቀበልና ሲወያይ የነበረው ሚኒስትሩ ለሥራ አጋሮቹ ሃሳቡን አጋራቸው። እነሱም በእርሱ ስጋት ተስማሙ። በርካታ ገንዘብ እና በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ከብቶች መጥፋቱ አሳሳቢ ሆነባቸው።
ሚኒስትሮቹ በጉዳዩ ላይ በጣም ተጨንቀው መፍትሔ በማፈላለግ ላይ ሳሉ፤ ከመካከላቸው የነበረ አንድ ብልህ ሚኒስትር ሃሳብ እንዳለው ተናገረ። ይህን መፍትሔም ለንጉሡ ማቅረብ እንዳለባቸው ተስማምተው ሰውዬው ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄደ።
ሚኒስትሩ አማራጭ ነው ብሎ ያቀረበውን ሃሳብ ንጉሡ ጠየቀው። ሚኒስትሩም እንዲህ በማለት መለሰለት «ንጉሥ ሆይ መንገዱን በቆዳ ከመሸፈን ይልቅ፤ ለምን በእግር ልክ ተስተካክሎ የተቆረጠ ቆዳ ሁሉም ሰው አያደርግም። ይህ ሲሆን አንድ ቆዳ ብዙ የእግር ሽፋኖችን መሥራት ይችላል» በማለት መለሰለት።
ይህ ብልህ ሚኒስትር ባቀረበው ሃሳብ ንጉሡ በጣም ተገረመ። ሃሳቡም በጣም ትክክል እና በቶሎ መተግበር ያለበት
ጉዳይ እንደሆነ ተናገረ። ለሚኒስትሩ አድናቆት እና ሽልማት አበረከተለት። በቶሎም ለራሱ ሁለት ከቆዳ ላይ የተቆረጡ መሸፈኛ ጫማዎችን
አዘዘ። ህዝቦቹም ልክ እርሱ እንዳደረገው ጫማ እንዲያደርጉ እና እራሳቸውን ከጉዳት እንዲጠብቁ ጠየቃቸው። ህዝቦቹም ንጉሣቸው ከልቡ
እንደሚያስብላቸው በማወቃቸው እና የቀረበላቸውን ሃሳብ ስላስደሰታቸው በሃሳቡ ተስማሙ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ህዝቡ በተለያየ ፋሽን
ጫማዎችን ማድረግ እና እግሮቹን ከጉዳት መከላከል ጀመረ። የተሻለ አማራጭ ሃሳብ ያለው ሁልጊዜም ተመራጭ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012
ዳግም ከበደ