Methicillin-Resistant Staphylococcus Aureus ሜቲሲሊን ሬሲስታንት ስታፍሎኮከስ ባጭሩ መርሳ( MRSA ) ተብሎ የሚታወቀው ባክቴሪያ በተፈጥሮው ለብዙ ፀረ ህዋስ (antibiotics) መድኃኒቶች የማይመለስ ወይም የማይድን በሽታ ይፈጥራል። ባለፉት አስር ዓመታት ይህ ባክቴሪያ በሰዎች ላይ የሚያደርሰው የሚያመረቅዝ ቁስለት (infection) እየጨመረ በመሄዱ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ይገኛል። ይህ ባክቴሪያ እንደስሙ አጠራር ሜቲሲሊን የተባለ ፀረ ህዋስ መድኃኒቶችን መቋቋም የሚችል ሲሆን ከሜቲሲሊን አልፎ ሌሎች መድኃኒቶችን ማለትም ፔኒሲሊን፤ አምፒሲሊን፤ ኦክሳስሊን የመሳሰሉትን የመቋቋም ችሎታ አለው። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መድኃኒቶች ደግሞ ከቁስልና ሌሎች ዓይነት የባክቴሪያ ልክፍቶች ሐኪሞች በየጊዜው የሚጠቀሙባቸው መድኃኒቶች ናቸው። ታዲያ እነዚህ መድኃኒቶች የማይሠሩ ከሆነ ችግሩ የከፋ ሊሆን ነው። ምክንያቱም ሌሎች መድኃኒቶች ለጊዜው በእጅ ስለማይገኙ ነው፤ ቢኖሩም ዋጋቸው በጣም ውድ ስለሚሆን ነው።
መርሳ (MRSA)፣ ለፀረ ህዋስ (antibiotics) መድኃኒቶች የማይመለስ በሽታ
ወደ ባክቴሪያው ስንመለስ የመርሳ በሽታን የሚያስከትሉት ሁለት ዓይነት ባክቴሪያዎች ሲሆኑ አንደኛው በህበረተሰብ ውስጥ የሚገኝ (Community acquired) ሲባል ሁለተኛው ደግሞ በሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ (Hospital acquired) ናቸው። ሁለቱም ክብደቱና ዓይነቱ የተለያየ ቁስለት ወይም ልክፍት ያስከትላሉ። አብዛኛው ጊዜ በህበረተስብ ውሰጥ የሚታየው በሽታ ቆዳና ከቆዳ በታች የሆነውን የሰውነት ክፍል ላይ ችግር የሚፈጥር ነው። ይህ ሁኔታ እንደ ቡግንጅ አንዳንዴም ሰፋ ያለ የመግል መቋጠር ያለበት ቁስለት ያስከትላል። አልፎ አልፎ ግን በተለይ በህፃናት ላይ ወደ ሳንባ በመዝለቅ ለህይወት አስጊ የሆነ የሳንባ ምች (pneumonia) ሊያስከትል ይችላል። በአዋቂዎች ላይ ደግሞ ኢንፍሉዌንዛን ተከትሎ የሳንባ ምች በማምጣት ይታወቃል። በህብረተሰቡ የሚታየው ባክቴሪያ ከላይ ለተጠቀሱት ፀረ ህዋስ መድኃኒቶች የማይመለስ ቢሆንም ለሌሎች በአፍ መወሰድ ለሚችሉ ውድ ባልሆኑ ፀረ ህዋስ መድኃኒቶች (ቴትራሳይክሊን፤ ዶክሲሳይክሊን፤ ክሊንዳማይሲን፤ ባክትሪም) መታከም ይችላል። ቡግንጅ ወይም መግል በመቋጠር የሚከሰቱ በሽታዎች ዓይነተኛ መፍትሄ መግሉን ከሰውነት ማሰወገድ ነው። ይህንን በሚመለከት ለአንባብያን “መግልና ሽንት ከሰውነት መውጣት አለበት” ተብሎ የሚነገር አባባል እንዳለ ለማስታወስ እንወዳለን።
መግል የቋጠሩ ቁስለቶችን መግሉን በማፍረጥ ማፅዳት ያስፈልጋል
ሌላው ዓይነት ደግሞ ሰዎች በሆስፒታል ቆይታቸው የሚጋለጡበት የሆስፒታል ዓይነቱ መርሳ ነው። ይሄኛው ባክቴሪያ ጠንከር ያለና ለህይወት አስጊ ሲሆን የውስጥ ሰውነት ክፍሎች ላይ በሽታ በማምጣት የሚታወቅ ነው። ይህ ባክቴሪያ የሚታከመው በጣም ቁጥራቸው ባነሰ በመርፌ አማካኝነት በሚሰጡ መድሃኒቶች ነው። የነዚህ መድኃኒቶች ዋጋ ደግሞ በጣም ውድ የሚባል ነው። የባክቴሪያዎች መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ(Resistance) በአሁኑ ወቅት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ይገኛል። ከመርሳ ውጭ ሌሎች ፀረ ህዋሳት መድኃኒቶችን መቋቋም የሚችሉ ለህይወት አስጊ የሆነ በሽታ የሚያመጡ በርከት ያሉ ባክቴሪያዎች አሉ። ፀረ ህዋሳት መድኃኒትን ያለአግባብ መጠቀም ወይም የታዘዙ መድኃኒቶችን በትክክል አለመጨረስ የዚህ የባክቴሪያዎች መቋቋም ችሎታ መንስኤ መሆኑ ይታወቃል።
ባክቴሪዎች የፀረ ህዋስ መድኃኒቶችን እየተቋቋሙ መምጣት
መርሳ ባጠቃይ ስታፍ ኦሪየስ ተብሎ የሚጠራው የባክቴሪያ ዘር ነው። ይህ ስታፍ ኦሪየስ የሚባለው ባክቴሪያ በብዙ ሰዎች የሰውነት ክፍል ውስጥ በመቻቻል የሚኖር ነው። ከ 20 እስከ 25% በሚሆኑ ሰዎች ይህ ስታፍ ኦሪየስ የሚባል ባክቴሪያ ባፍንጫቸው ውስጥ ይገኛል ተብሎ ነው የሚገመተው። ይህ ሁኔታ ማለትም ባክቴሪያዎች ቁስለት ሳያመጡ በሰውነት ክፍል መገኘት ኮሎናይዜሽን (colonization) ይባላል። ከ 2% ያነሱ ሰዎች ደግሞ መርሳ ባፍንጫቸው ውስጥ እንደሚኖር ይገመታል።
በአብዛኛው ችግር እየፈጠረ ያለው መርሳ የሚያመጣው በቆዳ ላይ የሚከሰቱ የማይጠጉ ቁስሎች ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ላይ ቁስሎች በተደጋገሚ የሚከሰቱ ናቸው። ታዲያ ይህንን በመርሳ የሚመጣውን የቆዳ ቁስል እንዴት መከላከል ይቻላል። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን ነገር ቢኖር መርሳ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ባክቴሪያ መሆኑን ነው። የአንድ ሰው ቁስል በጥንቃቄ ካልተጠበቀ የቤተሰብና የህብረተሰብ ችግር ነው። በመሆኑም ለራስዎና ለሌሎች ሲሉ የሚከተሉትን ምክሮች ልብ ብለው ይከታታሉ።
መርሳ የሚያስከትለው የማይጠግ ቁስል
ራስዎን ከመርሳ ቁስል መከላከል፡-
1. እጅዎን በደንብ በሳሙና መታጠብ አለዚያም አልኮል ባለባቸው የእጅ ፈሳሾች እጅዎን በደንብ መወልወል፣
2. በቆዳ ላይ የሚታዩ የመቆረጥ ወይም ሎሎች ቁስለቶችን በንፅህና መጠበቅ በተጨማሪም እስከሚድኑ ድረስ በቁስል መሸፈኛዎች መሸፈን፣
3. የሌሎች ሰዎችን ቁስሎች ወይም የተጠቀሙባቸውን የቁስል መሸፈኛዎች ያለጓንት ከመንካት መቆጠብ፣
4. የግል መፀዳጃዎችን፤ ፎጣዎችን፤ የፂም መላጫዎችን ከሌሎች ሰዎች ጋራ አለመጋራት
ንፅህናን መጠበቅ
መርሳ ካለብዎት ደግሞ በሽታው እንዳይዛመት ማድረግ የሚገባዎት የጥንቃቄ እርምጃዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
መግል ወይም ሌላ አይነት ፈሳሽ የሚታይባቸው ቁስሎችን እስከሚድኑ ድረስ በንፁህ የቁስል መሸፈኛዎች መሸፈን፣ የተጠቀሙባቸውን የቁስል መሸፈኛዎች በአግባቡ የቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማስቀመጥ ወይም ማቃጠል፣ መግልና መግሉን የነኩ መሸፈኛዎች መርሳ ስለሚኖርባቸው ወደ ሌሎች ሰዎች በቀላሉ ሊዛመቱ ስለሚችሉ ማስወገድ፣ እንዲሁም የሐኪምዎን ምክርም በደንብ ይከታታሉ።
1. ቁስልዎን ከነኩ በኋላ እጅዎን በሚገባ እስካልታጠቡ ድረስ ሌላ የሰውነት ክፍልዎን ከማከክ ወይም ከመነካካት ይቆጠቡ፤
2. እርስዎም ሆነ የቅርብ ቤተሰብዎ እጅዎን በደንብ በሳሙና መታጠብ አለዚያም ከላይ እንደተጠቀሰው አልኮል ባለባቸው የእጅ ፈሳሾች እጅዎን በደንብ መወልወል። በተለይም ቁስሎችን ካፀዱ ወይም የቁስል መሸፈኛዎችን ከቀየሩ በኋላ እጅዎን ከላይ እንደተጠቀሰው መታጠብ አስፈላጊ ነው።
3. የግል መፀዳጃዎችን አይጋሩ፡ የግል መገልገያዎች እንደ ፎጣ፤ መላጫዎች፤ ልብሶች፤ የመሳሰሉትን ከቁስልዎ ጋራ የተነካኩ ማንኛውንም ዓይነት ነገሮችን አይጋሩ። ፎጣ፤ አንሶላዎችን፤ ልብሶችዎን በልብስ ሳሙናዎችና በበረኪና በደንብ ማጠብና ማድረቅ ተገቢ ነው።
4. በቤትዎ ውስጥም ሆነ በሌላ ቦታዎች ከቁስሉ ጋራ የተነካኩ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማፅዳትና በንፅህና መጠበቅ ያስፈልጋል።
5. ወደ ሕክምና ቦታ ሲሄዱ በመርሳ መለከፍዎን ካወቁ ለሕክምና ባለሙያዎች አስቀድሞ መንገር በሽታው ወደ ሌላ ሰው እንዳይጋባ ለሚያደርጉት መከላከል ይረዳል። በተጨማሪም ትክክለኛውን መድኃኒት ለማዘዝም ይረዳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012