ደም ግፊት (Hypertension) ወይም በተለምዶ በአገራችን ደም ብዛት ስለሚባለው በሽታ አብዛኛው ሰው መጠነኛ ግንዛቤ አለው ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን በደም ግፊት ምክንያት የሚደርሰውን ሌሎች ተያያዥ የጤና ጉዳቶች የሰውነት ጉዳትና የህይወት ህልፈት በሚመለከት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው። የደም ግፊት እንደ በሽታ የሚቆጠረው ከጤናማ በላይ ሲሆን ነው። ይህ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሰዎች ደግሞ መድኃኒት መጀመር እንዳለባቸው ይታወቃል። ነገር ግን መድኃኒት የሚጀመርበት የደም ግፊት መጠን ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ነው የሚሆነው። በተለይም በእድሜ በኩልና ሌሎች ተደራቢ በሽታዎች ባሉባቸው ሰዎች ላይ የተለየ ሁኔታ ያለው በመሆኑ እነኝህን መመሪያዎች ማወቅ አስፈላጊ ነው።
ለደም ግፊት ሕክምና መከተል ያለብን የጥንቃቄ መመሪያ
እንደሚታወቀው የደም ግፊት ሲለካ ሁለት ቁጥሮች አሉ በእንግሊዝኛ (systolic ) የላይኛው እና (diastolic ) የታችኛው ቁጥር። እነዚህ ቁጥሮች አንዱ ወይም ሁለቱ ከመጠን በላይ ሲሆኑ የደም ግፊት አለ ይባላል። ማስተዋል ያለብን እነዚህ ቁጥሮች ከመጠን በላይ ሲሆኑ ምንም የህመም ስሜት ወይም ምልክት ላይኖር እንደሚችል ነው። ዋናው ችግር ይህ የደም ግፊት በጊዜ ካልታወቀ ሊያስከትል የሚችላቸው የተላየዩ በሽታዎች መኖራቸው ነው። ዋነኞቹ ችግሮች ስተሮክ (stroke) ወይም የነርቭ ምች (ከህይወት ማለፍ ጀምሮ የሰውነት ክፍልን ሽባ በማድረግ የሚታወቅ)፣ ድንገተኛ የልብ ህመም (Heart attack)፣ የኩላሊት መድከም (Kidney failure) እና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ። ስለዚህ እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል የህመም ስሜትም ባይኖርም የደም ግፊት ምርመራ አልፎ አልፎ ማድረግ ተገቢ ነው፤ ችግሩ መኖሩ ከታወቀም በመድኃኒት አማካኝነት ጤናማ ደረጃ ወይም መጠን ላይ ማድረግ ተገቢ ነው።
ደም የመለካት ልማድን ማዳበር
በአሜሪካ (Joint National Committee – JNC) በሚባል የህክምናና ሌሎች ባለሙያተኞች ያሉበት ኮሚቴ ሐኪሞች ለደም ግፊት ሕክምና ታካሚዎች መቼ መድኃኒት መጀመር እንዳለባቸው እንዲሁም ምን ዓይነት መድኃኒቶች መጠቀም እንዳለባቸው መመሪያ ያወጣል። ይህ መመሪያ በየጊዜው ሲወጣ ቁጥርን መሰረት ያደረገ ሲሆን በቅርቡ የወጣው መመሪያ (JNC 8) ተብሎ ይጠራል።
ይህ መመሪያ ለአሜሪካውያን የወጣ እንደመሆኑ መጠን አገር ቤት ለሚኖሩ ሰዎች ተግባራዊ መደረግ አለበት ለማለት በሀገር ቤት በቂ ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ሁኔታው ያን ያህል የሰፋ ልዩነት የሚኖረው እንደማይሆን ግምቶችን መውሰድ ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜም ለተለያዩ በሽታዎች የምዕራባውያኑን የሕክምና ትምህርት ስለምንጠቀም ይህ መመሪያ ደግሞ አገልገሎት ላይ መዋል ይችላል ብለን ልንወስድ እንችላለን። ሌላው ተጨማሪ ነገር ከመድኃኒቶች ጋር ሌሎች የሚደረጉ ነገሮች ለምሳሌ የሚበላውን የጨው መጠን መቀነስ፤ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ የመሳሰሉት አስፈላጊ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል።
በተጨማሪ ይህን መመሪያ የምናካፍለው አብዛኞች ሰዎች በየቤታቸው ወይም በሌላ አጋጣሚ ደም ግፊታቸው ለክተው ቁጥሮችን የሚያውቁ ከሆነ ወደ ሐኪም ቀርበው ህክምና እርደታ እንዲጠይቁ ለማነፃፀሪያነት እንዲጠቀሙ ነው። እነኝህ የቁጥር መመሪያዎች የሚከተሉት ናቸው።
1. ለአዋቂዎች እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች መድኃኒት መጀመር የሚገባው (systolic ) የላይኛው ቁጥር ከ150 ወይም ከ 150 በላይ ከሆነ ወይም (diastolic ) የታችኛው ቁጥር 90 ና ከዛ በላይ ከሆነ ነው።
2. እድሜያቸው ከ60 ዓመት በታች ለሆኑ አዋቂዎች ደግሞ መድኃኒት መጀመር የሚገባው የላይኛው ቁጥር 140 ወይም ከዛ በላይ ሲሆን የታችኛው ቁጥር ደግሞ 90 ወይም ከዛ በላይ ሲሆን ነው።
3. የኩላሊት በሽታና የስኳር በሽታ ላለባቸው ሰዎች ግን በማንኛውም እድሜ ክልል ቢሆኑም የደም ግፊት መድኃኒት የሚጀመረው የላይኛው 140 ወይም ከዛ በላይ ከሆነ የታችኛው ደግሞ 90 ወይም ከዛ በላይ ከሆነ ነው።
4. ሰዎች መድሃኒቶች ከጀመሩ በኋላ አስፈላጊ ክትትል ማድረግ የሚኖርባቸው ሲሆን የሚፈለገው የደም ግፊት መጠን በአንድ ወር ውስጥ አስፈላጊ መጠን ካልወረደ የመድሃኒቱ ጉልበት መጨመር ወይም ሌላ ተደራቢ መድሃኒት መታዘዝ ይኖርበታል። ከዚህ ላይ ግን ደም ግፊታቸው አደገኛ ደረጃ የሆነባቸው ሰዎች አንድ ወር ድረሰ ይቆዩ ማለትም አይደለም። ሰለዚህ ነው ሐኪምዎ የሚወስንልዎትን ነገሮች በትክክል መከተል አስፈላጊ የሚሆነው።
እንግዲህ ከላይ እንደተጠቀሰው የደም ግፊት መጠን ከፍ ሲል ስሜትና ምልክት ስለማይሰጥ በጊዜ ካልታወቀና ከቁጥጥር ሥር ካልዋለ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ጉዳት ስለሚያደርስ ማንኛውም እድሜው 18 ዓመት የሞላው ሰው የደም ግፊቱን መጠን አልፎ አልፎ እንዲለካ የሚመከረው። ከተለኩ በኋላ ቁጥሮች ከፍ ያሉ ከሆነ የግድ ሐኪም ማማከር ተገቢ ነው። የደም ግፊትዎን ይለኩ!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012