የሰዎች ጤና መቃወስ ለታማሚው ብቻ ሳይሆን ለአስታማሚው ጭምር ትልቅ ዕዳና ጭንቅ ነው። ሰዎች ለሕክምና በቂ ገንዘብ በሌላቸውና ባላሰቡት ጊዜ ከበድ ያለ የጤና ቀውስ ሲያጋጥም ሕክምና ተቋማት ወስዶ ማሳከም ወጪው የናረ ነው። አስታማሚዎች የጤና ቀውስ ያጋጠመውን የቤተሰብ አባል ለማሳከምም በየሰፈሩ፣ በየመንገዱ፣ በመኪና ላይ እና በየመስሪያ ቤቱ የሰው ፊት እየገረፋቸው የሕክምና ምጽዋት መጠየቅ ግድ ይላል። የጤና ጉዳይ ሆኖ እንጂ ባይሰበሰብስ ቢቀር ያሰኛል። በአሁኑ ጊዜ ለዚህ ማህበራዊ ቀውስ በመንግሥት በኩል መፍትሔ ተዘይዶለታል።
የማህበራዊ ጤና መድን ተጠቃሚ ከሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መለሰች ደሱ ተጠቃሽ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የማሕበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት በተለይ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ትልቅ ጠቃሜታ አለው። በኑሮ ውድነቱ የተነሳ ብዙ ቤተሰብ ያላቸው አባወራዎች ወይም እማወራዎች ከዕለት ቀለብ የዘለለ ገንዘብ ማስቀመጥ ይቸገራሉ። ስለሆነም ልጆች በታመሙ ቁጥር የጤና ተቋም ወስደው ለማሳከም በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው ይጨነቃሉ፣ ሰላማቸው ይቃወሳል፣ እረፍት ያጣሉ። ጤና መድን መኖሩ ከዚህ ስጋት ይገላግላል። የአባልነት ክፍያውም በጣም አነስተኛ ስለሆነ በነፃ የመታከም ያህል የሚቆጠር ነው ይላሉ።
መንግሥት አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶች አሟልቶ በተጠናከረ መንገድ ሥራ መጀመር ይኖርበታል። ማህበረሰቡም በዚህ ሥርዓት መታቀፉ ለሕክምና የሚያወጣውን የተጋነነ ወጪ ለሌላ አላማ ማዋል ያስችለዋል ሲሉ ጥቅሙ ፈርጀ ብዙ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ መነሻ የጤና መድን ዓይነቶች
አቶ ዘመድኩን አበበ የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ናቸው። የጤና መድን አገልግሎት ሁለት ዓይነት የመድን (ኢንሹራንስ) ዓይነቶች ይዞ በኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ በኩል የሚሰራ እና የሚመራ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
አንደኛው የተጀመረው ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማህበራዊ ጤና መድን ይሰኛል።
ባህሪያቸው ምን ይመስላል?
ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ምንድን ነው? ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ ማህበረሰብ አቀፍ ማለት በአንድ አካባቢ ተመሳሳይ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተል፣ መደበኛ ገቢ የሌለው የኅብረተሰብ ክፍል ነው። መደበኛ ገቢ የሌለው ሲባል በአጠቃላይ የገጠሩ ማህበረሰብ ተጠቃሽ ነው። በገጠር የሚኖረው ማህበረሰብ በአብዛኛው በግብርና የሚተዳደር በመሆኑ በዓመት አምርቶ ያንን በመሸጥ ገቢ የሚያገኝ ነው። በተጨማሪም የተለያዩ መደበኛ ያልሆኑ ሥራዎች በመስራት በሚያገኘው ገቢ የሚተዳደር ሰው ጭምር የሚያካትት ነው። በሚሰራው አነስተኛ ሥራ መደበኛ ያልሆነ ገቢ አግኝቶ የሚተዳደርና ትርፍና ኪሳራ አለው ሊባል የማይችል ማህበረሰብን የሚያጠቃልል ነው። እነዚህ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ሊጠቃለሉ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።
የማህበራዊ የጤና መድን ታካሚ፡- ይህ የጤና መድን ሥርዓት ሰው ለማህበራዊ ሕይወቱ ዋስትና የሚሰጥ ነው። ይህ ሥርዓት አንዱ ከሌላው ጋር የጋራ ትስስር ኖሮት በጋራ የሚከወን ነው። ሥርዓቱ በሙያ ብቃት፣ በትምህርት ደረጃ እና መሰል ጉዳዮች ተመሳሳይነት ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ያሳትፋል ተብሎ ታሳቢ የተደረገ ነው። በግልም ሆነ በመንግሥትም ተቀጥሮ የሚሰራና ወርሃዊ ደመወዝ የሚከፈለውን የማህበረሰብ ክፍል የሚያካትት ነው። በትምህርት ደረጃውም፣ በግንዛቤውም፣ በቋሚ ገቢውም፣ በአኗኗር ዘይቤውም ተመሳሳይነት ያላቸውን ጭምር የሚያካትት ነው። ስለዚህ ይህ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የራሱ የሆነ መመሪያና ደንብ ያስፈልገዋል። ከደመወዙ ሊያዋጣ የሚገባው ስንት በመቶ ነው? ባልና ሚስት ተቀጣሪዎች ቢሆኑ መዋጮው ከሁለቱም ይሰበሰባል ወይ? የሕክምና አገልግሎቱ እስከ ምን ድረስ ነው? ከሌላው ጋር ተመሳሳይ ነው ወይስ ይለያያል?፣ እስከ ምን ያህል ደመወዝ ያላቸው ሠራተኞች ይካተታሉ? የሚሉ እና ሌሎችም ጉዳዮች በጥልቀት ታይተውና ተዳስሰው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥናቱ መላኩን አቶ ዘመድኩን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ዘመድኩን ገለጻ፤ የማህበራዊ የጤና መድን አገልግሎት ቀደም ሲል መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ተጀምሮ እንዲቆም የተደረገ ነው። ረቂቅ አዋጁ አዋጁ ግብዓቶች ተጨምረውበት ሲጠናቀቅ ሥርዓቱ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት በአገሪቱ በተወሰኑ ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች ተጀምሯል። በአንድ ወረዳ ላይ ከሚኖረው እማወራና አባዎራ ቁጥር ብዛት ከግማሽ በላይ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል፣ የአባልነት መዋጮ ክፍያ የከፈለ፣ መታወቂያ ያለው ከሆነ አገልግሎቱ እንዲጀመር ይደረጋል። በዚህ መሠረትም የጤና አገልግሎቱ የሚሰጠው በአካባቢው በሚገኝ ጤና ተቋም ሲሆን ለአንድ ዓመት የሚሆን ሕክምና የማግኘት መብት እንዳለው ገልጸዋል።
የማህበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታት ማስቆጠሩን የገለጹት አቶ ዘመድኩን፤ ባለፉት ዓመታት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች የተሰሩበት ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አለመገኘቱን ያወሳሉ። አሁንም ገና በመስፋፋት ላይ የሚገኝ አገልግሎት ሲሆን በመላው አገሪቱ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ገና ብዙ ሥራ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል። ሕክምናው እስከየት ድረስ ነው?
ዓላማውም ማህበረሰቡ በሚደርስበት የጤና እክል ለሕክምና ከፍተኛ ወጪ ተዳርጎ ማህበራዊ ሕይወቱ እንዳይናጋ ማድረግ ነው። ስለዚህ መዋጮውም ዝቅተኛውን ማህበረሰብና መደበኛ ገቢ የሌለውን ማህበረሰብ ያማከለ ነው። ኅብረተሰቡ ማንኛውንም ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ ሕክምናዎችን ለምሳሌ፡- የስኳር፣ የደም ግፊት፣ ካንሰር፣ የኩላሊት ዲያሌስስ የጤና እክል የሚያጋትማቸው ብዙ ቤተሰቦች አሉ። እነዚህን ሰዎች በግላቸው ቢታከሙ የሕክምና ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ ቤትና ንብረታቸው አሟጠው ሸጠው ይጨርሳሉ። ይህም ቤተሰቡ ይበተናል፤ የማህበራዊ ቀውስም ምንጭ ይሆናል። ስለዚህ አባላት በዓመት በሚከፍሉት 250 ብር መዋጮ ብቻ ቤተሰቡ ሲታመም ያለምንም መሳቀቅ መታከም የሚያስችል ነው።
ባለፈው ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ ኤጀንሲው በአገሪቱ በሚገኙ በ559 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። በቤተሰብ ደረጃ 22 ሚሊዮን እማዎራና አባዎራ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮኑ እማዎራና አባዎራ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ገልጸዋል። የጤና መድን አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በአማካይ ዝቅተኛው አምስት ቤተሰብ ከፍተኛው ደግሞ ስምንት ቤተሰብ ያላቸው በመሆኑ ቁጥሩ ከፍተኛ ነው።
ተደራሽነቱ ምን ይመስላል?
በአርብቶ አደር እና በከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የማህበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት አልተጀመረም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ በአፋር፣ ሱማሌ፣ በጋምቤላ፣ ከፊል ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። በአጠቃላይ ባልተጀመሩባቸው አካባቢዎች ለማስጀመር የተጠናከረ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።
በአጠቃላይ የጤና መድን አገልግሎት ለታለመለት ዓላማ መሠረት ተግባራዊ እንዲሆን የተጠናከረ አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ ነው። በየደረጃው ያሉ አካላት የጠራ መረጃ ከማደራጀት ጀምሮ በየጤና ተቋማቱ አስፈላጊውን ግብዓት እስከማቅረብ ድረስ የተናበበ ሥራ መስራት አለባቸው። አሠራሩ የተሳለጠ ሆኖ የማህበረሰቡን የጤና ችግሮች የሚያቃልል እንዲሆን የሚታዩ ክፍተቶች ወዲያው መፍትሄ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ሙሐመድ ሁሴን