የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከየካቲት 5-7/2012 ዓ.ም በመካከለኛው ምሥራቅ በነበራቸው ጉብኝት አንድ እንግዳና ያልተለመደ ተግባር ፈጽመዋል። የከረረ ግጭት ውስጥ የገቡና ለእርቅ ይበቃሉ ተብሎ የማይታሰቡ ሁለት ሴቶችን ያስታረቁበት መንገድ አግራሞትን ፈጥሯል። እኛም በቦታው ሁኔታውን ተከታትለን ነበርና እንማርበት ዘንድ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታዋን ያቀረበችው ኤልሳቤት ለሁለት ወራት በእሥር ቤት መቆየቷንና በአሁኑ ሰዓት የጭንቅላት እጢ በሽተኛ መሆኗን ትናገራለች። ኤልሳቤት ፓስፖርት ለማሳደስ ወደ ባህሬን ቆንስላ በሄደችበት ወቅት ነፍሰ ጡር የነበረች ሲሆን፤ አንዲት የቆንስላ ሠራተኛ ይህንን በማየት ከወለደች በኋላ “በሕገወጥ መንገድ ወልዳለች” ብላ አሳስራኛለች ነው።
ይህች የቆንስላ ሠራተኛ ባለሥልጣናትን እየጠቀሰች ታስፈራራት እንደነበር ትገልፃለች፤ “ሰይጣናዊ የሆነ ሥራን በእኔ ላይ ሠርታለች፤ በታሰርኩበት ወቅትም እናቴን በሞት አጥቻለሁ፤ የጭንቅላት እጢ በሽተኛም ሆኛለሁም” ትላለች። እንባዋ እየተናነቃትና እያለቀሰች አቤቱታዋን ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አቅርባለች።
ኤልሳቤት ይህ ሁሉ በደል ሊደርስብኝ የቻለው በብሔሬ አማካኝነት ነው ብላ እንደምታምንም ጨምራ ገልፃለች።
ከመካከለኛው ምሥራቅ በባህሬን በክብር ቆንስላነት የምታገለግለውና ቅሬታ የቀረበባት እየሩስ ደግሞ እኔ የተወነጀልሁት በብሔሬ ምክንያት ነው እንጂ ያጠፋሁትም ሆነ የበደልኩት በደል የለም ትላለች። ከዚህም ባለፈ ሕግ በሌለበት አገር ውስጥ ብሆን ኖሮ የደቦ ፍርድ በሚመስል መልኩ ጥቃት ሊፈፀምብኝ ይችል ነበርም ስትል ትከሳለች።
“ለኢትዮጵያ የዜግነት ድርሻየን በመወጣቴ ክብሬ ዝቅ እንዲል ተደርጌያለሁ፤ ተዋርጃለሁም” የምትለው እየሩስ፤ ኤልሳቤት በተሳሳተ መታወቂያ በሕገወጥ መንገድ ልጅ ወልዳ ትኖር ነበር፤ ይህም ከሕግ ውጭ ስለሆነና ሕጉ ስለማይፈቅድ እንጂ የታሰረችው እኔ ምንም ያደረግሁት ተጽዕኖ የለም ትላለች።
“ኤልሳቤት በታሰረችበት ወቅት ከእሥር ቤት ድረስ ሄጄ አይቻታለሁ፤ እኔ ኢትዮጵያዊነቴን ማንም አይቀማኝም፤ ነገር ግን በብሔሬ ምክንያት ውንጀላዎች ስለደረሱብኝና ስለተንገላታሁ ከቆንስላው ሥራየም መልቀቅ እፈልጋለሁ” ስትል ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አቤቱታዋን አቅርባለች።
ኤልሳቤትና እየሩስ በዚህ ደረጃ የፈጠሩት ልዩነትና ጥላቻ እጅግ የከፋ ብቻም ሳይሆን እርስ በእርስ ሊያጠፋፋቸውም እንደሚችል ከንግግራቸው መረዳት ይቻላል። ታዲያ ሽማግሌው ዶክተር አቢይ እነዚህን እጅግ የተጠላሉ እና በብሔር ልዩነትን ፈጥረው በጠላትነት የተፈራረጁ ሁለቱን ሴቶች እንዴት አስታረቁ?
“ሽማግሌው” አቢይ በመጀመሪያ ሁለቱን ሴቶች (ኤልሳቤትና እየሩስ) በትይዩ ከአዳራሹ ጫፍ እና ጫፍ አራርቀው አቆሟቸው። የመጀመሪያ ጥያቄያቸውን ተበደልሁ ላለችው ኤልሳቤት እንዲህ ብለው ጠየቁ “ኢትዮጵያን ትወጃታለሽ ?” መላሽም “አዎ በጣም እወዳታለሁ” አለች። ቀጠሉ “ከፊት ለፊትሽ ካለችው ሴት ከኢትዮጵያ ምን ታያለሽ?” አሉ። ኤልሳቤትም “በዚች ሴት ላይ ብዙ ክፋት ይታየኛል፤ ምንም ጥሩ ነገር አይታየኝም” አለች እያለቀሰች። ሽማግሌው ቀጠሉ “ግድ የለሽም ክፉውን ተይውና አንድ የሚታይሽን መልካም ነገር ንገሪኝ” አሉ። ኤልሳቤት አሁንም በለቅሶ “ምንም አይታየኝም” አለች። “መዳን ከፈለግሽ የሚታይሽን ንገሪኝ፤ እስኪ ቀና ብለሽ እያት መልኳ ምን ይመስላል?” አሉ። አሁንም ኤልሳቤት “እሷን ሳያት በሽታየ ይብስብኛል፤ የሞተች እናቴን ያስታውሰኛል፤ አልችልም ይቅርታ” አለች በለቅሶ። አሁንም ሽማግሌው እንዲህ አሉ “በማልቀስሽ የእርሷ ሀጢያት ሊብስ አይችልም፤ ኢትዮጵያዊነትሽን ታምኛለሽ?” አሉ። ኤልሳቤትም “አዎ” አለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትራመድ አዘዟት፤ መላሽም ወደ ፊት ተራመደች።
ሽማግሌው ‹‹በዳይ›› ወደተባለችው እየሩስ ፊታቸውን አዞሩ ፤ “ከፊትሽ ስላለችው ሴት ምን ትያለሽ?” አሉ። “አንዲት ሰዎች መጠቀሚያ ያደረጓት ሴት ትታየኛለች” አለች። “ታሳዝናለች?” ሲሉ ደግመው ጠየቁ። “በጣም” አለች መላሽ። “አንድ እርምጃ ወደፊት ተራመጅ” ሲሉ ተራመደች።
ወደ ተበደልሁ ባይ ኤልሳቤት ዳግም ተመለሱ ሽማግሌው፤ “እናትሽን ትወጃቸዋለሽ ?” አሉ። ኤልሳቤት ስቅስቅ ብላ በማልቀስ የእናቷን አሟሟት ስትናገር አዳራሹን የሀዘን ድባብ ደፋችበት። ሽማግሌው ቀጠሉ “የምጠይቅሽን ብቻ ሳታለቅሺ ብትመልሽልኝ እናትሽ የሰላም እረፍት ያርፋሉ፤ እናትሽ ደግ ነበሩ ?” ሲሉ ደግመው ጠየቁ። ኤልሳቤትም “አዎ” አለች። “ያንን ደግነት ከየት አመጡት ?” አሁንም ተጠየቀች። “እግዚአብሔር ሰጥቷት ነው” አለች ሳግ እየተናነቃት። የዚህን ጊዜ አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትሄድ በሽማግሌው አቢይ ታዘዘች፤ አደረገችውም።
ሽማግሌው በዚህ መሐል እንዲህ አሉ ”ጥላቻን ስትይዙ፣ ቂምን ስትይዙ የምትጠሉትን ሰው አይደለም ራሳችሁን ነው የምትጎዱት። ኤልሳቤትን እንደምታዩዋት በጥላቻና ቂም ውስጥ ሆና መናገር አልቻለችም። የምታስታውሰው ሁሉ ሐዘን ነው። ይህንን ከውስጧ ማውጣት የምትችለውና የምትድን መጀመሪያ ጥላቻን ማስወገድ ስትችል ነው። ልትማሩ ይገባል ጥላቻና ቂም ሲኖር የሚበላው ራሳችሁን ነው። እናቷ ባሉበት ሆነው ደስ የሚላቸው ስትስቅ ቢያዩ ነው፤ ለማንኛውም እናትሽ ይቅርታን ያውቁ ነበር ? የፍቅር ሰው ነበሩ?” አሉ ሽማግሌው። ኤልሳቤት “እኔ ይቅር አልላትም…” ሽማግሌው አቋረጧት “ ስላንቺ አላልሁም፤ ስለእናትሽ ነው። ይቅርታ ያውቁ ነበር ?” ሲሉ በድጋሚ ጠየቋት። “አዎ” ስትል መለሰች፤ አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትራመድም ተደረገች።
ሽማግሌው ወደ እየሩስ ፊታቸውን አዙረው “አንድ እህትሽን በማታውቂው መንገድ ሌሎች ሰዎች አውቃም ይሁን ሳታውቅ በድለዋት ሁልጊዜ በለቅሶና በሐዘን ውስጥ ብትሆን ምን ትያለሽ ?” ሲሉ ጠየቋት። መላሽም “በጣም አዝናለሁ” አለች። ወዲያው “እና ከፊትሽ ያለችዋ ሴት አታሳዝንሽም?” ተብላ ተጠየቀች። “እኔ የምታሳዝነኝ ከቤቴ ውስጥ ያለች በዳይፐር የምትኖርና በእንፉቅቅ የምትሄደው በባለቤቴ ድጋፍ ያለችው ሴት ናት። እኔ ለእነሱ ስል እየተሰደብኩ አለሁ። ይሄ ድራማ ነው፤ በትወና በልጣኛለች፤ ይቅርታ ያድርጉልኝ ለዚች ሴት ማዘን አልችልም። እንዲህ ማልቀስ ቀላል ነው፤ በጣም አዝናለሁ ጊዜ ባናባክን ይሻላል” አለች።
ሽማግሌው እንዲህ አሉ “አሁን ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ የገባችው የአንቺና የኤልሳቤት አይነት ሰዎች ስለበዙ ነው። ሰው ደካማ መሆኑን ሊሳሳት የሚችል መሆኑንም ማመን አለበት። ሰው ተሳስቶ ጥፋቱን አምኖ ከሆነ የአንቺ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን የሚገባው ያንን ሰው ማዳን ነው። ተሳስታ ነው እንኳን ብንል እየጎዳችው ያለው ራሷን ነው። የአንቺ ቀዳሚ ተግባር እሷን ማዳን እንጂ የእሷን ትክክል አለመሆን መግለፅ አይደለም። እሷን ለማዳን እጅሽን ካልዘረጋሽ ኢትዮጵያ አትድንም።” አዳራሹ በጭብጨባ ደመቀ።
“በራሳችሁ ሰው ላይ ስለምትጨክኑ ማንም አያዝንላችሁም። ትናንት ከትናንት ወዲያ ሳናጠፋ ሰው አልሆንንም። ጀነራል አሳምነው በጣም ብዙ ውለታ የዋልሁለትን ሰው ብዙ ሰዎች ገድሎታል፤ አስገድሎታል ብለው አወሩ። እንኳን ልገድለው ሳላየው ሞተ። ስለዚህ እንደዛ ስላላችሁኝ የተናገረውን ሁሉ ሰው ባሥር ያዋጣል? ለእኔ እንደዚያ ላሉት ፈራጅ ስላለ ለእርሱ ትቸዋለሁ። አንቺም ንፁህ ሰው ከሆንሽ እሷም ተበድላ ከሆነ ፈራጁ እሱ ነው። እኔ የምፈልገው ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ነው። አሁን ከአንቺ የምፈልገው አንድ እህትሽ በዚህ ሁኔታ አዝና እያለቀሰች ከምትኖርበት ሁኔታ ማውጣት የሚችል አንድ ሰው ብታገኚ ምን ትከፍይዋለሽ ? ስለእህትሽ ነው የማወራው።” ሲሉ ጥያቄያቸውን ለእየሩስ አስከተሉ።
እየሩስም “ምስጋና ነው የማቀርበው፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ እለዋለሁ” አለች። “አሁን እህትሽን ከገባችበት ችግር ለሚያወጣልሽ ሰው ምስጋና ለማቅረብ ዝግጁ ነሽ ? ብለው ጠየቁ ሽማግሌው። እየሩስም “አዎ” አለች፤ አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትራመድ ታዘዘች አደረገችውም።
ሽማግሌው ፊታቸውን አዞሩና ኤልሳቤትን ጠየቁ። “የታሠሩ፣ የተደፈሩ፣ የተዘረፉ እህቶቻችን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያውያን ችግር በኢትዮጵያውያን ስለሆነ አንቺ በምትሠሪው ሥራ እህቶቻችን ወንድሞቻችን ተለቀው እፎይ ቢሉ ደስ ይልሻል?” ኤልሳቤትም” ከዚያ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝም” አለች። ሽማግሌው “ስለዚህ ለእነሱ ምሳሌ መሆን ትፈልጊያለሽ ማለት ነው፤ እንደ እናትሽ ደግ ነሽ ማለት ነው፤ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራመጅ” አሉ። ተራመደች።
ፊታቸውን ወደ ኤልሳቤት አዙረው “በይቅርታ የማይፈታ ችግር እንደሌለ ታምኛለሽ ? የልብ ጠማማነትና ለይቅርታ አለመገዛት ችግራችን ነው ብለሽ ታምኛለሽ ? ዛሬ አንቺ የያዝሽው ጉዳይ የሚፈታው በይቅርታ ብቻ መሆኑንስ ታምኛለሽ ? ኢትዮጵያውያን ችግራቸው የሚፈታው በይቅርታ መሆኑንም ታምኛለሽ?” መላሽ “አዎን አምናለሁ” አለች፤ አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትጠጋም ታዘዘች፤ አደረገችው።
ወደ እየሩስ ዞር አሉ- ሽማግሌው፤ “እኛ ኢትዮጵያውያን ብንተጋገዝ፣ ብንደጋገፍ፣ ከሌሎች አለማት የሚሻል ህዝብ እንዳለን ታምኛለሽ ?” ሐሳባቸውን አልጨረሱም መላሿ “ከሁሉም እንበልጥ ነበር ክፋት ባይኖር” አለች። ቀጠሉ ሽማግሌው አቢይ “የኢትዮጵያውያን ችግር ልግመኝነት መሆኑን ታውቂያለሽ? ከልግመኝነት ከተገላገልን አገራችን እንደምታድግ ታምኛለሽ ? ሲሉ ጠየቁ መላሽም “አዎ” አለች “አንቺ ለጥፋቱ ሁሉ ምንጭ እሷ ናት ካልሻት እና በእኔ በኩል ችግር የለም ብለሽ ካሰብሽ መፍትሄ አይገኝም። የብሔር ጉዳይ እያነሱ እንዲህ መሆን ትክክል አይደለም።” ሲሉም መከሩ።
ሽማግሌውም ቀጠሉ ”እኔ የምፈልገው ሰላም ነው፤ አንቺን እየለመንሁ ያለሁት በእኛ መሐይምነት፣ ሃይማኖተኛ ሆነን ሃይማኖት የማናውቅ፣ ከእኛ በላይ ሃይማኖተኛ የሚመስል የለም ግን ሃይማኖት በውስጣችን የሌለ፣ ጠዋት ማታ ሰላም የምንል ሰላም ግን በውስጣችን የሌለ፣ ይቅርታን የማናውቅ አስቸጋሪ ሰዎች ስለሆንን ነው። በነገራችን ላይ እንግሊዝም ይሁን አሜሪካ ወይም ጅቡቲ ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደተዋረደ ነው። ኢትዮጵያን ያላከበረ ብቻውን ሊከበር አይችልም፤ ለዚህ ነው አገራችንን እናክብራት የምንለው። አንቺ ሌሎችን ለመርዳት ፍላጎቱ ካለሽ በቅድሚያ መከባበርን ማስቀደም ያስፈልጋል። ይህንን ታምኛለሽ ? አሉ። የኤልሳቤት ምላሽ “ አዎ” የሚል ነበር። አንድ እርምጃ ወደፊት እንድትራመድ ተነገራት አደረገችው።
ይህ እጅግ የከረረ ጥላቻ አሁን እየረገበ የሄደ ይመስላል። ለማስታረቅ አይደለም ለማቀራረብ እንኳ የሚፈሩ የሚመስሉት ሁለቱ እህቶች በሽማግሌው ነገሮችን አለሳልሶ የማስማማት ብቃት እና በአንድ እርምጃ ትእዛዝ አሁን ፊት ለፊት ተቀራርበዋል።
ወደ ‹‹በዳይ›› የተባለችው እየሩስ ፊታቸውን አዙረው ”አሁን ጊዜ ስለሌለኝ አንቺን ልለምን። በተባለው ጉዳይ ውስጥ የአንቺ ጥፋት አንድ በመቶ ሊሆን ይችላል፤ በእሷ ሂሳብ ደግሞ መቶ በመቶ ሊሆን ይችላል፤ እኔ አላውቅም፤ ግን በአንቺና በእሷ መካከል ያለውን ጉዳይ መፍታት ይቻላል ብየ ስለማስብ ነው ጊዜ እየወሰድሁ ያለሁትና ቅድም ለጠቀስሻትና እየተሰቃዩ ላሉ እህቶች ስትይ ጎንበስ ብለሽ ይቅርታ ጠይቂ” አሉ። ጎንበስ ብላም ይቅርታ ጠየቀች፤ አዳራሹ በረጅም እልልታና ጭብጨባ ደመቀ፤ እነዚያ በነፍስ የሚፈላለጉ እህቶችም ተቃቀፉ።
ሽማግሌው ‹‹ተበዳይ› ነኝ ወዳለችውም ኤልሳቤት ዞረው “አሁን እርሷ የተናገረችውን ያደረገችውን እንተወውና አንቺ ደግሞ እስካሁን ችግሩን በተለየ መንገድ መፍታት ስትችይ በልህ፣ በብስጭት የመኖሩን ጥፋተኝነትሽን አስበሽ ዝቅ ብለሽ ይቅርታ ጠይቂያት” አሉ። ዝቅ ብላ ይቅርታ ጠየቀች፤ አዳራሹም በጭብጨባና እልልታ ዳግም ደመቀ፤ ባላንጣ የነበሩት ሁለቱ ሰዎችም ተቃቅፈው ተላቀሱ።
ይህንን አርአያነት ያለው ተግባር ለሌሎችም ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ሁሉም ወደየመጡበት ሲመለሱ የተጋጩትን እንዲያስታርቁና አንድነታቸውን እንዲያስጠብቁ ሽማግሌው አቢይ ትዕዛዝ ሰጥተው በመካከለኛው ምሥራቅ ሰማይ ሥር እርቅ አወረዱ።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- ዳኜ አበራ