ሮቦቶችን የመፍጠር ብቃት የቴክኖሎጂ ልህቀትንና የሰው ልጆች የፈጠራ አቅምን የሚያሳዩ ብቻ ሳይሆኑ የሰው ልጆች የህልውና ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ስለመሆናቸው የሆሊውድ የሲኒማ ባለሙያዎች በተለያዩ ጊዜያት በሠሯቸው ፊልሞች ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
የመጀመሪያው ሥጋትም የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጫፍ በሚነካበት ዘመን ሥራዎች በሙሉ በሮቦቶች የሚሠሩበትና ሠርቶ ማደር ለሰዎች እየከበደ የሚሄድ መሆኑ ነው፡፡ ይህ በጥናት የተረጋገጠ ትንበያ ቢሆንም ሮቦቶች ለሰው ልጆች በቀላሉ እና በተሻለ ፍጥነት አገልግሎትን እንደሚሰጡም ምሁራኑ ያስረዳሉ። በተለይ ባደጉ ሀገራት ሰዎችን ተክተው የተለያዩ ተግባራትን እንዲያከናውኑ በማድረግ ላለባቸው የሰው ኃይል እጥረት እንደዋነኛ መፍትሄ ሲጠቀሙባቸው እናያለን።
ሮቦቶች ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በታማኝነት የተሰጣቸውን ስራ በማከናወናቸው በሰዎች ዘንድ ተመራጭ ያደርጋቸዋል። አሁን ላይም በአለማችን እንደ ሰው በቋንቋ መግባባት የሚችሉ፣ ያለ ጠባቂ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ሌሎችም ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጡ ተፈጥሯዊ ባህሪያትን ከሰዎች የሚጋሩ ሮቦቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡
በሀገራችን በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ለማህበረሰቡ ችግር ፈች የሆነ መሰል የፈጠራ ስራ ሰርተዋል። ዩኒቨርሲቲው ያለውን እምቅ እውቀትና ሀብት ለማህበረሰቡ በማድረስ በመማር ማስተማር ሂደቱ ተጨማሪ እውቀት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውና ከፍተኛ የፈጠራ ስራ የመስራት ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በማስተማር ላይ ይገኛል።
ተማሪዎቹ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በማግኝታቸው የተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመስራት ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው። የካምፓሱ ተማሪዎች በቡድን ከሰሩት የፈጠራ ስራዎች መካከል የአንዱን የፈጠራ ስራ የቡድኑ ተወካይ ዓናንያ ሙላቱ ገለፃ አድርጎልናል።
«የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለመስጠት የሚረዳ ሮቦት ነው የሰራነው። ሮቦቱም ውሃ ውስጥ የሚገኘውን ኦክስጅን በቀላሉ ከውሃው አካል በመለየት፤ ድንገተኛ አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች በፍጥነት ወደቦታው በመሄድ ኦክስጅን እንዲያገኙ በማድረግ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለመስጠት ይችላል። በተጨማሪም ሮቦቱ ከውሃ ኦክስጅንን እስኪያጣራ ድረስ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል የኦክስጅን ታንከር መሸከምም ይችላል።
«ይህንን የፈጠራ ስራ አንድ አይነት ፍላጎትና ተነሳሽነት ያለን አራት የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ነን የሰራነው። የፈጠራ ስራውንም በ2010 ዓ.ም የመጨረሻው ወር ላይ ነው የሰራነው» በማለት የፈጠራ ስራቸውን ጠቀሜታ መዝርዝር ገልፆልናል።
“ይህን የፈጠራ ስራ ለመስራት የፈጠራ ስራ ውድድር እንደሚኖር ቀድመን እናውቅ ስለነበር ምን ዘርፍ ላይ ብንሰራ ይሻላል ብለን እንደ ቡድን ተመካከርን። በሀገራችን ለህብረተሰቡ ትልቁን ግልጋሎት የሚሰጡት ትምህርት፣ ጤናና ግብርና ናቸው። እኛም የምንችለውን ያክል በነዚህ ዘርፎች አስተዋፅኦ ለማድረግ ፍላጎቱ ስለነበረን፤ ከነዚህም ዘርፎች በይበልጥ በሀገራችን የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነትና ዘርፈ ብዙ ችግር የሚታይበትን የጤናውን ዘርፍ መረጥን። እንደ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የሞቱ ሰዎች የሞት ምክንያት ሪከርድ መሰረት 57 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ድንገተኛ አደጋ ደርሶባቸው የመጀመሪያ ህክምና ባለማግኝታቸው ህይወታቸው እንዳለፈ ያሳያል።
«ስለዚህ አንድ ሰው ድንገተኛ አደጋ ቢደርስበት በአካባቢው የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ የሚሰጥ ሰው ላይኖር ይችላል። እንዲሁም አምቡላንስ በተፈለገው ፍጥነት ወደተጎዳው ሰው ላይደርስ ስለሚችል፤ ይህን ሮቦት በቀላል መንገድ በአካባቢ፣ በቤት ውስጥ፣ በስራ ቦታ፣ በገበያ ቦታ፣ እንዲሁም ሰዎች በሚሰበሰቡበት አካባቢ በማስቀመጥ በተገጠመለት ካሜራ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመከታተል ድንገተኛ አደጋ ሲደርስ አደጋው ወደ ደረሰበት ቦታ በተሻለ ፍጥነት በመድረስ ለተጎጂው ሰው የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለመስጠት እንዲያስችል ታስቦ የተሰራ ነው። በዚህም ድንገተኛ አደጋ ደርሶባቸው የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ሳያገኙና ሆስፒታል ሳይደርሱ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር በግማሽ ያክል መቀነስ ያስችለናል” በማለት የፈጠራ ስራውን ለመስራት ምን እንዳነሳሳቸውና የፈጠራ ስራው የሚሰጠውን ፋይዳ ተማሪው ተናግሯል።
“ሮቦቱን ለመሰራት የሚያስችል ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ ገበያ ባለማግኝታችን የፈጠራ ስራውን ለመስራት ተቸግረን ነበር። የፈጠራ ስራውን ለመስራት የሚያስችሉ ቁሶችን ከውጭ በማስመጣታችን ለከፍተኛ ወጪ ተጋልጠናል። እንዲሁም ሮቦት ለመስራት በጣም አስቸጋሪና የተወሳሰበ በመሆኑ የተለያዩ ሙያዊ ችግሮች ገጥሞን ነበር። በዚህም ስራውን ለማከናወን ረጅም ጊዜ ወስዶብን ነበር” በማለት የፈጠራ ስራቸውን ሲሰሩ የገጠማቸውን ችግር የፈጠራ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
በሀገሪቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ገና በማደግ ላይ ያሉ በመሆናቸውና ትልቅ ሙአለ ነዋይ የሚጠይቅ የፈጠራ ስራ በመሆኑ፤ ሮቦቱን ወደተግባር ለውጦ ለማህበረሰቡ ግልጋሎቱን እንዲሰጥ ለማስቻል ተግዳሮት እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።
አንድ ሰው እንደዚህ አይነት የማህበረሰብን ችግር የሚፈታ የፈጠራ ስራ ይዞ ብቅ ሲል ከመንግስት በተጨማሪ እነዚህን የፈጠራ ስራዎች ወደተግባር እንዲገቡ የሚያደርጉ ባለሀብቶች መፈጠር አለባቸው። ባለሀብቱም እነዚህን ጽንስ ሀሳቦች ወደተግባር እንዲለወጡ በገንዘብና በተለያዩ ድጋፎች የፈጠራ ስራ የሚሰሩ ወጣቶችን በመደገፍ ባለሀብቱም ተጠቃሚ የሚሆንበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት አለበት። ለምላሌ ያክል በሀገራችን እንደ «አይስ አዲስ» የመሳሰሉ አነስ ያሉ የሶፍትዌር ፕሮጀክቶች፤ ወጣቶች በሶፍትዌር ምህንድስና የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ሲሰሩ ለፈጠራ ስራው የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ። እንዲሁም የፈጠራ ስራው ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ሲሆን ደግሞ ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች እርዳታ እንዲያገኙ የማገናኘት ስራ ይሰራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ የክልል ከተሞች የኢንዱስትሪ መንደሮችን እያስገነባ ነው። ወጣቶች የፈጠራ ስራዎች ሲሰሩ በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ጽንስ ሀሳቦቹ ዳብረው ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚደረግበት እራሱን የቻለ አንድ ወይም ሁለት ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩ ጥሩ ነው። ምክንያቱም የተለያዩ የፈጠራ ፕሮጀክቶችን ወደ ኢንዱስትሪዎቹ እንዲመጡ በማድረግ በኢንዱስትሪዎቹ ላይ የሙከራ ስራ ከተሰራ በኋላ፤ የፈጠራ ስራዎቹ በፋብሪካዎች ዳብረውና ከፍ ተደርገው ተሰርተው ለማህበረሰቡ ግልጋሎት እንዲሰጡ ያስችለናል። በዚህም ወጣቶች የፈጠራ ስራቸው በተግባር የማህበረሰቡን ችግር መፍታት መቻሉን ሲመለከቱ ለነገ የተሻለ የፈጠራ ስራ ለመስራት ይበልጡን ያነሳሳቸዋል” በማለት ባለሙያዎቹ የፈጠራ ስራቸው ተደራሽ ያልሆነበትን ምክንያትና የመፍትሄ ሀሳብ ይሆናል ያሉትን ይጠቁሟል።
“ሳይንስ ሼርድ ካምፓሱ ከማስተማርና ከማበረታታት ባለፈ ለፈጠራ ስራው የሚያስፈልገንን አንዳንድ ቁሶችን ድጋፍ አድርጎልናል። እንዲሁም መምህራኖች በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የፈጠራ ብቃታችን ከፍ እንዲል እየረዱን ነው። እኛም በመተባበር በቡድን ስራዎችን በመስራታችን በብዙ መልኩ መተጋገዝ ችለናል። እንዲሁም ይህን የፈጠራ ስራ ስንሰራ ወላጆቻችን በተለያየ መልኩ ደጋፍ አድርገውልናል። በተጨማሪም በሰራነው የፈጠራ ስራ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የማበረታቻ የምስክር ወረቀት ተበርክቶልናል”ይገልፃሉ።
“መንግስት ለኛ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ትምህርታችን በከፍተኛ ተቋም እንድከታተል እያደረገን ነው። ትምህርታችን በዚህ ደረጃና በዩኒቨርሲቲ መምህራን መማራችን የተሻለ እውቀት እንድንቀስም የሚረዳን ነው። ነገር ግን ትምህርታችን ከጨረስን በኋላ ይህን የፈጠራ ስራችን አጠናክረን ለማስቀጠል የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ አልተፈጠረልንም። በተለይም ወደተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ስንመደብ በጋራ ስንሰራቸው የነበሩትን የፈጠራ ስራዎቻችንን ወደ ተግባር ቀይረን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እንቸገራለን። እንዲሁም በምንሄድባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የምንፈልገው ዘርፍ ላይ ተሰማርተን የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ላይሟሉ ይችላሉ። ስለዚህ የተሻለ ስራ ለመስራት እንቸገራለን።
«በተለይም አሁን የፈጠራ ስራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎትና ብቃት ያለን ተማሪዎች በአንድ ላይ በመማርና በመስራት ላይ ነን። በዚህም ከፍተኛ የውድድር መንፈስ እንዲኖረን አስችሎናል። ይህም ሁሌም የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ፈጠራ ስራዎችን ለመስራት በጣም ያግዘናል። ስለዚህ መንግስት እነዚህን የፈጠራ ስራዎችን አንድ ላይ የምናስቀጥልበትና ይህን ከፍተኛ የውድድር መንፈሳችን ይዘን በፍላጎታችን የምንሰራበት ራሱን የቻለ እኛን ተቀብሎ የሚያስተናግድ ዩኒቨርሲቲ ቢኖር ጥሩ ውጤት በማምጣት ለህብረተሰቡ ችግር ፈች የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት ያስችለናል። እንዲሁም ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገሮች እየሄድን የፈጠራ ስራዎችን በተግባር ብናይና ልምድ ብንቀስም የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት ያግዘናል። መንግስት ይህን መልዕክታችንን ጆሮ ሰጥቶ ቢሰማን የተለፋብንን ፍሬአችንን ማየት ያስችለዋል” በማለት መልክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
ሰለሞን በየነ