በሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከሚጫወቱ ዘርፎች አንዱ ኢንቨስትመንት ነው፡ የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለው።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ባለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የኢንቨስትመንት ሚና የጎላ ነው። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ፌዴራል መንግስት ካስገነባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ ክልሎችም ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ።
የኦሮሚያ ክልል ካለው ተፈጥሯዊ ሀብትና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለኢንቨስትምት ምቹ ከሚባሉ ክልሎች መካከል አንዱ ነው። ክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የዘርፉን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በዋናነትም ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ ከዚህ በፊት በስራ ላይ የነበሩ ኢንቨስትመንቶችን ማበረታታትና ማጠናከር እንደነበር የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሃይሉ ጀልዴ ይገልጻሉ። እንደ ሩዋንዳና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ልምድ በመቀመር የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል የሚያስችል ጥናት ተደርጎ ለቦርድ እንደቀረበም ጠቅሰዋል። በዚህም የተነሳ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን አሻሽሏል፤ ባለሀብቶች የሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ለመመለስም ሞክሯል።
ሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫ የነበረው የሀገርንም ሆነ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ክልሉ መጋበዝ ነው። ከዚህ በፊት አዳዲስ ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በክልል እንዲያፈሱ የሚያደርገውን ኋላ ቀር አሰራር በመተው አስቀድሞ መሬት በማዘጋጀትና ግልጽ ጨረታ በማውጣት በውድድር ላይ የተመሰረተ አካሄድን መከተል የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል። አንድ ባለሀብት ወደ ስራ ለመግባት ከሰባት እስከ ስምንት ተቋማት የሚያደርገውን ምልልስም ማስቀረት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት በአንድ ቦታ ተሰባስበው የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ነው የተናገሩት።
አንድ ባለሀብት በአንድ በተወሰነ ቦታ ሁሉንም አገልግሎት አግኝቶ ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችለው ይህ አሰራር እንግልትና የጊዜ ብክነትን የሚያስቀር ነው። ቦርዱም አዲሱን አሰራር ገምግሞ ተጨማሪ ሃሳብ ሰጥቶ ለማጠናቀቅ ትልልቅ ስራዎች በዚህ ዙሪያ መሰራታቸውን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት እነዚህን ሁለት የትኩረት አቅጣጫዎችን በመከተልም ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ኮሚሽነሩ ያስረዳሉ።
ከክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ጋር በመሆን የኢንቨስትመነትን ሥራ ዲጂታላይዝ ለማድረግ አስፈላጊ ስራዎች ተሰርተው ስልጠና ተሰጥቶባቸው ወደ ስራ መገባቱንም አቶ ሃይሉ ጠቅሰዋል። የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያስረዳው ኢንቨስትመንት ለዕድገታቸው መሰረት ቢሆንም በተወሰነ መልኩም ቢሆን በአየር ንብረት ፣ በመሬት ደህንነትና በሰው ጤንነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ሀገራት እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ የተጠቀሙባቸውን ሳይንሳዊ መፍትሄዎች በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግም የተወሰኑ እርምጃዎችን መሄድ ተችሏል።
ቴክኖሎጂን የመጠቀም አንዱ ፋይዳ ኢንቨስትመንት የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን አስከትሎብናል የሚለውን የህብረተሰቡን ቅሬታ ከመፍታቱም ባሻገር ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው ስለ ክልሉ ኢንቨስትመንት አጠቃላይ መረጃ ማግኘት የሚያስችል የኦን ላይን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ይላሉ። የኦሮሚያ መንግስት አዲስ የኢንቨስትመንት መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ከአሁን በፊት የከተማ ኢንቨስትመንት በመሬት አስተዳደር ይመራ ስለነበርና ኢንቨስትመንት ቢሮው የሚቆጣጠረው የገጠር ኢንቨስትመነትን ብቻ በመሆኑ ክፍተት ስለተፈጠረ ነው። በተሻሻለው መመሪያ የኢንቨስትመንት ጉዳይ በሙሉ ወደ ኢንቨሰትመንት ኮሚሽን እንዲመጣ መደረጉን ነው አቶ ሃይሉ የገለጹት።
ከአሁን በፊት በነበረው አሰራር ቀድሞ የመጣ ባለ ሀብት የሚፈልገውን ቦታና መሬት የማግኘት ዕድል እንደነበረው የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ አዲሱ መመሪያና ደንብ ግን ኮሚሽኑ የሚፈልገውን ቦታ ለጨረታ በማቅረብ አወዳድሮ ለመስጠት የሚያስችል አሰራር እንደሚከተልና ለሁሉም ባለሀብቶች ተመሳሳይ እድል እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። ይህም የባለሀብቱን ጥያቄ በተገቢው መንገድ ለመመለስና ፍትሃዊ አሰራርን ለማስረጽ እንደሚያግዝ አስረድተዋል። ደንቡ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችም ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገሩ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል። አርሶ አደሩ መሬቱን በኢንቨስትመንት ስም ለባለሀብቱ ከመልቀቁ በፊት ከባለሀብቱ ጋር በሽርክና የሚሰራበት ሁኔታ በአዲሱ ደንብ ውስጥ ተካቷል። ይህም በየጊዜው በኢንቨስትመንት ምክንያት መሬቱን እያስረከበ ለተለያዩ ችግሮች የሚዳረገውን አርሶ አደር ችግር የሚፈታ ነው ብለዋል።
ደንቡ የክልሉን የኢንቨስትመንት ስርጭት ለማመጣጠን የሚያግዝም ነው። በክልሉ የሚገኙ ዞኖች ለኢንቨስትመንት የለይዋቸውን መሬቶች አወዳድሮ በመስጠት በዞኖች መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት ስርጭት ፍትሀዊነት ለማስጠበቅም ይረዳል ተብሏል። አዲሱ መመሪያና ደንብ ከተዘጋጀ ወዲህ 31 ሺ 851 ሄክታር መሬት ለጨረታ መዘጋጀቱን አቶ ሃይሉ ያስረዳሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ጨፌ ኦሮሚያ በአምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤው ‹‹የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን›› ለመመስረት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። በንግግራቸው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ክልሉ ካለው ተፈጥሯዊ ሀብት በሚፈለገው ደረጃ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን አለማረጋገጡን ጠቅሰዋል። በክልሉ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንዳለ ገልጸዋል። ‹‹ ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን›› ለማቋቋም የወጣው አዋጅም ይህንኑ የሚያጠናክር እንደሆነ አመልክተዋል።
ከዚህ በኋላ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ኢንቨስትመንት በክልሉ ሊኖር እንደማይችልና ከባለሀብቱ ጋር በሽርክና ለመስራት የሚያስችል አዲስ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅም በመጠቀም የኢኮኖሚ አመንጪ ቀጣና የማድረግ አቅጣጫ እንደተያዘ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2012
ኢያሱ መሰለ