‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የሚባለው ልብ ወለድ ድርሰት ዛሬም ድረስ
በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን ያተረፈ ዘመን ተሻጋሪ የጥበብ ስራ ሆኖ ዘልቋል። የ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››
መጽሐፍ ደራሲ የክብር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በስፋት የሚታወቁት በዚህና በሌሎች የድርሰት ስራዎቻቸው
ነው። ይሁን እንጂ ሐዲስ ዓለማየሁ ከስነ -ጽሑፍ ስራዎቻቸው የበለጠ የኖሩት በፖለቲካ ስራ ላይ ነው። ለዛሬ ሐዲስ ዓለማየሁ ከድርሰት
ስራዎቻቸው ባሻገር ለነበራቸው የፖለቲካ ሕይወታቸው ትኩረት በመስጠት በጥቂቱ እንመለከታለን።
ሐዲስ ከአለቃ ዓለማየሁ ሰለሞን እና ከወይዘሮ ደስታ ዓለሙ በ1902 ዓ.ም ጎጃም ውስጥ ተወለደ። አያቱ (የእናቱ አባት) አለቃ ዓለሙ ስዩም በእንዶዳም ኪዳነ ምኅረት ገዳም የዜማ መምህር ስለነበሩ ስድስት ዓመት ሲሞላው የግዕዝ ፊደሎችን ማጥናት ጀመረ። ከእንዶዳም ኪዳነ ምኅረት በተጨማሪ በደብረ ኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና በዲማ ጊዮርጊስ ገዳማት ተዘዋውሮ የድጓ፣ የቅኔና የመጻሕፍት ቤት (ትርጓሜ) ትምህርቶችን ተማረ። በትምህርቱም ከጓደኞቹ ሁሉ የላቀ ነበር። በ1918 ዓ.ም ሐዲስና ሌሎች ጓደኞቹ ከመምህራቸው መሪጌታ በላይ ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።
አዲስ አበባ ደርሰው ጥቂት ጊዜያትን ካሳለፉ በኋላ አቶ አያሌው ንጉሤ ከተባሉና በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ያስተምሩ ከነበሩ ግለሰብ ጋር ተዋወቁ። አቶ አያሌውም ሐዲስና ጓደኞቹ ወደ ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብተው ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ መከሯቸው። ሐዲስ ትምህርት ቤቱ ሐይማኖቴን ሊያስለውጠኝ ይችላል ብሎ በመፍራቱ ጥቂት አመነታ። በመጨረሻ ግን ወደ ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን ጀመረ። በሂደትም የዘመናዊ ትምህርትን ጥቅም በማወቁ የመንግሥት ትምህርት ቤት መግባት እንዳለበት ወስኖ ተፈሪ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ። ከራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት ግምጃ ቤት ባገኘው ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍም ከሦስተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ያለውን ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታተለ።
በወቅቱ በትምህርት ቤቱ ውስጥ አመፅ ተቀስቅሶ ነበር፡ ‹‹ … የአመፁ ጠንሳሾች በእድሜያቸው በሰል ያሉት ተማሪዎች ናቸው … ›› ተብሎ በመታመኑ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ተማሪዎች ማደሪያቸው ከትምህርት ቤቱ ውጭ ሆኖ እንዲማሩ ተወሰነ። ይህ ውሳኔ አዲስ አበባ ውስጥ ቤተሰብና የቅርብ ዘመድ ለሌላቸው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አስደንጋጭ ነበር። ሐዲስ አዲስ አበባ ውስጥ ቤተሰብም ሆነ የቅርብ ዘመድ ስላልነበረው ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ።
በወቅቱ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ይሰጥ የነበረውን የመምህርነት ስልጠና ወስዶ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመረ። ከዘጠኝ ወራት የመምህርነት ስራ በኋላ ዳንግላ አካባቢ በነበረው የብሪታኒያ ቆንስላ ውስጥ እንዲሰራ ተመደበ። ዳንግላ አካባቢ የነበረው የብሪታኒያ ቆንስላ ከተዘጋ በኋላ ሐዲስ በአካባቢው የነበረው ጉምሩክ ተቆጣጣሪ ሆኖ መስራት ጀመረ። በዚህ ስራውም ላይ ብዙም አልቆየም። በወቅቱ በአካባቢው የባሪያ ንግድ ይካሄድ ስለነበር የባሪያ ንግድ እንዲቆም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት ያወጣቸውን ድንጋጌዎችን የማስፈጸምና የመከታተል ኃላፊነት ተሰጥቶት ኃላፊነቱን አከናወነ። ከዚያም በዳንግላም ሆነ በመላው አገው ምድር የመጀመሪያ የሆነውን የዳንግላ ትምህርት ቤትን እንዲያቋቁም የተሰጠውን ኃላፊነት ተወጣ። ሐዲስ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርና መምህር ሆኖ አገልግሏል።
በ1928 ዓ.ም ወደ ደብረ ማርቆስ ተዛውሮ በንጉሥ ተክለሃይማኖት ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛና የሂሳብ መምህር ሆነ። የወቅቱ የጎጃም ገዢ የነበሩትን የልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ልጆችንም ያስተምር ነበር። እስከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜ ድረስም በዚያው በደብረ ማርቆስ ቆየ።
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሐዲስ ከመንግስት ሳይጠብቅ ራሱ ጠመንጃ ገዝቶ፣ የራስ እምሩን ጦር ተቀላቅሎ በአርበኝነት መዋጋት ጀመረ። የሕዝቡንና የአርበኛውን ስሜት የሚቀሰቅሱ የኪነ ጥበብ ስራዎችንም እየሰራ አቅርቧል። በ1929 ዓ.ም ጎጀብ ወንዝ አካባቢ በተደረገ ውጊያ ላይ ተማርኮ ፖንዞ እና ሊፓሪ ወደሚባሉና በሳርዲና አካባቢ (ደቡባዊ ኢጣሊያ) ወደሚገኙ የሜዲትራኒያን ደሴቶች ተወስዶ ታሰረ። ከሰባት ዓመታት የእስራት ጊዜ በኋላ አርበኛው ሐዲስ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።
ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰም በማስታወቂያ ሚኒስቴር የፕሬስና ኢንፎርሜሽን ምክትል ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ። ሐዲስ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት ሚኒስቴሩ በሰው ኃይልና በቁሳቁስ የተደራጀ እንዲሆንና ስራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ስለማድረጉ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረሕይወት [የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ ሆነው ያገለገሉ] ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውሮ የአሜሪካ ጉዳዮች ክፍል ዳይሬክተር ሆነ።
በ1938 ዓ.ም አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቆንስላ ተጠሪ ሆነው ተሾሙ። በዚህ ወቅት ነው የትዳር አጋራቸውን ወይዘሪት ክበበፀሐይ በላይን ያገኙት። የዋግሹም ተፈሪ ወሰን የልጅ ልጅ የሆነችው ወይዘሪት ክበበፀሐይ በወቅቱ በወይዘሮ አማረች ወለሉ አሳዳጊነት በኢየሩሳሌም ትኖር ነበር። በ1939 ዓ.ም በአትላንታ የቴሌኮሙኒኬሽን ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ወደ አሜሪካ ተጉዘው ለአምስት ወራት ያህል በአሜሪካ ቆይተዋል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል በሌሎች ጉባዔዎች ላይም ተሳትፈዋል። በመቀጠልም በዋሺንግተን ዲ.ሲ የሚገኘውና በራስ እምሩ ኃይለሥላሴ የሚመራው የኢትዮጵያ ለጋሲዮን ዋና ጸሐፊ ሆኑ። ከዚህ ኃላፊነታቸው ጎን ለጎን መደበኛ ባልሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔዎች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል አገልግለዋል። በ1941 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ የሽግግር ኮሚቴ የኢትዮጵያ ተወካይ ሆኑ። አቶ ሐዲስ በወቅቱ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ በዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ትምህርት ጀምረው የነበረ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ በመታዘዛቸው የጀመሩትን ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁት ቀርተዋል።
በ1942 ዓ.ም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመልሰው የሚኒስቴሩ የፕሬስና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ሆነው መስራት ጀመሩ። ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። በዚህ ኃላፊነታቸው ላይ በነበሩበት ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የነበራትን ጣልቃ ገብነትና ጫና አምርረው ይቃወሙ ነበር። ጆን ስፔንሰር ከተባለው አሜሪካዊ አማካሪ ጋርም ሰፊ የሃሳብ ልዩነት ነበራቸው። ስፔንሰር ‹‹Ethiopia at Bay – A Personal Account of The Haile-Selassie Years›› የሚል ርዕስ በሰጠው መጽሐፉ፣ ‹‹ … ራስ እምሩ፣ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ ሲራክ ኅሩይ … ኮሙኒስታዊ እሳቤ አላቸው …›› በማለት ጽፏል። ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ከማይደግፉና ከሶቭየት ኅብረት ጋር ግንኙነት እንድትመሰርት ካደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ሐዲስ እንደነበሩ ስፔንሰር ገልጿል። በሐዲስ የስነ ጽሑፍ ስራዎች ላይ ጥናት ያደረጉት ጸጋዬ ኃይሉ ግን ሐዲስ ከምስራቁ ይልቅ የምዕራቡ ዓለም ርዕዮተ ዓለማዊ እሳቤን ይመርጡ እንደነበር ጽፈዋል። ቢትወደድ ዘውዴ ገብረሕይወት እና ብላታ መሐሪ ካሣ በበኩላቸው ሀዲስ ዓለማየሁ ለምስራቁም ሆነ ለምዕራቡ ርዕዮተ ዓለም የተለየ ፍላጎት አልነበራቸውም። የእርሳቸው ዋነኛ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ነበር›› በማለት መስክረዋል። በእርግጥ ሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?›› በሚለው ስራቸው ላይ ‹‹ …. ኢትዮጵያ ካፒታሊዝምንም ሆነ ሶሻሊዝምን ከመምረጥ ይልቅ ከሁለቱም ወገኖች ጥሩ የሚባሉትን ሃሳቦች በመውሰድ ከራሷ ታሪክ፣ ባሕልና ማኅበረሰብ ጋር የሚጣጣም አድርጋ መቅረፅ ያስፈልጋታል …›› ብለዋል።
ሐዲስ በዲፕሎማትነት ዘመናቸው ኢትዮጵያን ወክለው ከተሳተፉባቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች መካከል የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ጉባዔ (እ.አ.አ 1948፣ሮም)፣ አራተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ (እ.አ.አ 1949፣ኒው ዮርክ)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔዎች (እ.አ.አ 1952፣ኒው ዮርክ እና 1956፣ፓሪስ) እና የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ (እ.አ.አ 1964፣ሌጎስ) ይጠቀሳሉ።
እ.አ.አ በ1956 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ ሆነው በተሾሙበት ጊዜ ዋነኛ ተግባራቸው የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ሶማሊላንድ የድንበር ጉዳይ ነበር። ስፔንሰር ሐዲስ በድንበር ላይ የነበራቸውን አቋም ሲገልፅ ‹‹ … የኢትዮጵያ ንብረት የሆነችን ቅንጣት ታክል ቁራሽ መሬት የመስጠት ፍላጎትና ዝግጁነት አልነበረውም …›› ብሏል። በዚህም ነው ሐዲስ ስለድንበሩ ጉዳይ የሚደራደረው የኢትዮጵያ ቡድን መሪ ተደርገው የተሾሙት። ምንም እንኳ የድንበር ማካለል ድርድሩ ያለስምምነት ቢጠናቀቅም ሐዲስ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ብርቱ ጥረት አድርገዋል።
በመንግሥታቱ ድርጅት የነበራቸውን የአራት ዓመታት ከአምስት ወራት ቆይታ ሲያጠናቅቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ተሾሙ። በዚህ ወቅት ነበር ሐዲስ ‹‹ልዩ ማስታወሻ›› የሚል መልዕክት ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ያቀረቡት። በዚህ መልዕክታቸው በ1953 ዓ.ም የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት መንስዔና ወደፊትም የመንግሥት አሰራር ካልተሻሻለ የከፋ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል በመጥቀስ ኋላ ቀር የሆነው የኢትዮጵያ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅር ሊሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህ መረር ያለ የሐዲስ ምክር ሃሳብ ስልጣናቸውንና ክብራቸውን እንደዓይናቸው ብሌን ለሚጠብቁት ለንጉሰ ነገሥቱ ምቾትን አልሰጠም።
ንጉሰ ነገሥቱ ሐዲስን ቢሯቸው አስጠርተው ‹‹ድፍረት ስለተሞላበት›› ደብደቤያቸው ገሰጿቸው። ሐዲስ ግን በንጉሰ ነገሥቱ ሃሳብ ባለመስማማት በመልዕክታቸው ካሰፈሩት ሃሳብ በተጨማሪ ሌሎችንም ምክረ ሃሳቦችን ለንጉሰ ነገሥቱ ተናገሩ። መልዕክቱ ለንጉሰ ነገሥቱ በደረሳቸው በስምንተኛው ቀን ሐዲስ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሆኑ ተደረገ። ንጉሰ ነገሥቱ ራሳቸው የትምህርት ሚኒስትር ስለነበሩ ሹመቱ ከፍተኛ ትችት የሰነዘሩባቸውን ደፋሩን፣ በግልፅ ተናጋሪውንና ትሁቱን ሐዲስን ከጎናቸው አድርገው ለመቆጣጠር እንደሆነ ግልፅ ነበር።
በአፍሪካ የትምህርት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ጉባዔ ሲካሄድ ሐዲስ በኢትዮጵያ ስለነበሩት ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ቁጥር ያቀረቡት ሪፖርት ንጉሰ ነገሥቱን አናደዳቸው። ይህም የንጉሰ ነገሥቱንና የሐዲስን ቅራኔ እያሰፋው ሄደ። ከዚህ በተጨማሪም ሐዲስ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የትምህርት ዘርፍ እቅድ ላይ፣ ለዘርፉ ከሚመደበው በጀት መካከል 25 በመቶ ያህሉ ብቻ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲሆንና ቀደም ሲል ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲመደብ የቆየው 75 በመቶ የዘርፉ በጀት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለትምህርት ግብዓቶች ማሟያ እንዲውልና እቅዶችን ከማዘጋጀትና አፈጻፀሞችን ከመከታተል በስተቀር ያሉት ስራዎች በዘርፉ ባለሙያዎች ብቻ እንዲከወኑ ያቀረቡት ሃሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። በዚህ ጊዜ ሐዲስ መንግሥት የትምህርት ዘርፉን ለመለወጥ ፍላጎት እንደሌለው በማመናቸው ከስልጣን መልቀቂያ አቀረቡ።
በመቀጠልም ለአምስት ዓመታት ያህል በእንግሊዝና እና በኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገለገሉ። ሐዲስ እንግሊዝ በነበሩበት ወቅት ባለቤታቸው ወይዘሮ ክበበፀሐይ በላይ አረፉ። በልጅ ያልታጀበው ጋብቻ በዚሁ ተቋጨ፤ሐዲስም በድጋሜ ወደ ትዳር አልተመለሱም። አዲስ አበባ ቀጨኔ አካባቢ የሚገኘውን ቤታቸውንም ለሕፃናት ማሳደጊያ እንዲሆን ለከተማው አስረከቡ።
ፀሐፌትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ሐዲስ ከለንደን ተመልሰው የእቅድና ልማት ሚኒስትርነቱን ያዙ። ሐዲስ የተማሩ ወጣት ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ ሚኒስቴሩ በሰው ኃይል የተደራጀ እንዲሆን አደረጉት። ሦስተኛው የአምስት ዓመት የልማት እቅድ (Third Five Year Development Plan) የተዘጋጀውም በዚህ ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ ለእቅዱ ማስፈጸሚያ የተመደበው በጀት ሲቀነስ ሐዲስ ባለመስማማታቸው በድጋሜ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ። ከዚያም እስከ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው እስከ አብዮቱ ፍንዳታ ድረስ ቆዩ።
ደርግ ተመስርቶ ልጅ እንዳልካቸውና ካቢኔያቸው ስልጣን እንዲለቁ ጥያቄ ሲያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በግንባር ቀደምትነት ያጫቸው ሰው ሐዲስ ዓለማየሁ ነበሩ። በሌተናንት ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መታጨታቸው የተነገራቸው ሐዲስ ግን የደርግን ዝርዝር ዓላማና ፕሮግራም የሚያስረዳቸው ሰው ሳያገኙ በመቅረታቸው በዕጩነታቸው ሳይስማሙ ቀሩ። ደርግ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን ከዙፋን አውርዶ ራሱን ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት›› ብሎ ሰይሞ መንግሥታዊ ስልጣን ከጨበጠ ከዓመት በኋላ ባቋቋመውና ከየአካባቢው የተወከሉ እውቀትና ልምድ ያላቸው ግለሰቦች በተካተቱበት የመማክርት ሸንጎ ውስጥ ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመታት ያህል አገልግለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UN Economic Commission for Africa) አዲስ አበባ ላይ እንዲቋቋም የተደረገው በሐዲስ ዓለማየሁ ብርቱ ጥረት ነው። ሐዲስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደርና ቋሚ ተወካይ በነበሩበት ወቅት ብዙ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ስለነበሩና ቅኝ ገዢዎች ቅኝ የሚገዟቸውን እንዲለቁ ሲጠየቁ ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ አገራት «አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ነጻ ቢወጡ በኢኮኖሚ ራሳቸውን አይችሉም» የሚል ነበር። ሐዲስም ምክንያት ነው ተብሎ የቀረበው ነገር ቅኝ ገዢዎቹ ጭቆናቸውን ለማራዘም የሚጠቀሙበት ዘዴ መሆኑ ስለገባቸውና አፍሪካን በዘላቂነት ከቅኝ ግዛት ማላቀቅ የሚቻለው የአፍሪካውያንን ትብብር በማጠናከርና የአሕጉሪቷን የኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት ሲቻል መሆኑን በማጤን አንድ አፍሪካዊ ተቋም እንደሚያስፈልግ አምነውበት ሀሳባቸውን ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አቅርበው የአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ላይ ሊቋቋም ቻለ።
ሐዲስ ዓለማየሁ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቁት ዘመን ተሻጋሪና አስደናቂ በሆኑ የስነ-ጽሑፍ ስራዎቻቸው ነው። ሐዲስ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር››፣ ‹‹ወንጀለኛው ዳኛ››፣ ‹‹የልምዣት››፣ ‹‹ትዝታ››፣ ‹‹ተረት ተረት የመሰረት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?››፣ ‹‹ሐበሻና የወደኋላ ጋብቻ››፣ እና ‹‹የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም›› የተሰኙ ልብ ወለዳዊና ኢ-ልብ ወለዳዊ የድርሰትና የተውኔት ስራዎችን አበርክተዋል።
በተለይ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› የተሰኘው ስራቸው በኢትዮጵያ የአማርኛ ስነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ስራዎች መካከል ከግንባር ቀደምቶቹ ተርታ የሚሰለፍ ሆኖ ዘልቋል። ለስነ ጽሑፍ ስራዎቻቸውም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የስነ-ጽሑፍ ሽልማትን አሸንፈዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል። ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ያሰራላቸው ከነኀስ የተቀረፀ ሃውልት በ2009 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ ቆሞላቸዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበርም በ2002 ዓ.ም ለክብር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ ያዘጋጀው የፖስታ ቴምብር በኢትዮጵያ የፖስታ ድርጅት ታትሞ ተሠራጭቷል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካና የስነ-ጽሑፍ ዘርፎች ላይ ገናና ስም የነበራቸው ደራሲ፣ መምህር፣ ፖለቲከኛ፣ አርበኛ፣ ባለቅኔ፣ … የክብር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ በ1996 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ስርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 18/2012
አንተነህ ቸሬ