ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸሯት ገፀ በረከቶች የጠላት ዓይን ማሳረፊያ ሆና እንድትቆይ አድርጓታል። መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧ፣ ተስማሚ አየሯ፣ ለም አፈሯ፣ ታላላቅ ወንዞችና ሐይቆቿ ለመስፋፋት ዓላማ የነበራቸው ታላላቅ የሚባሉ የዓለም አገራት ትኩረትና ቀልብ እንድትስብ ዋነኛ ምክንያቶች ነበሩ። ይህም ታዲያ ታሪኳን በተጋድሎ፣ በመስዋዕትነትና በጀግንነት ሞልቶታል። በዚህ ሒደት ውስጥ የአገሪቱ ህልውና ተጠብቆ፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረና ከራሷ አልፎ ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች አኩሪ ታሪክ እንድታስመዘግብ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ጀግኖች አርበኞች መሆናቸው አይካድም። ይሁን እንጂ “በእጅ ያለ ወርቅ…” እንደሚባለው ሆነና ትኩረት ተነፍጓቸው የችግር አቀበትን ለመውጣት እንደተገደዱና ሰሚ ጆሮ እንዳጡ በመግለጽ የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት ቅሬታቸውን ለተቋማችን አቅርበዋል።
የቅሬታው ጭብጥ
በማኅበሩ ሒሳብ ሹምም ኦዲተርም አንድ ሰው ነው፣ መንግሥት ለጀግኖች አርበኞች የሰጠውና የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሊቀትጉሃን አስታጥቄ አባተ የተጠቀሙባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውሳኔ ካረፈበት በኋላም መፍትሔ አላገኘም፣ ከሕንፃው ቢሮዎች ኪራይ በየወሩ የሚገኘው ገቢ መድረሻው አይታወቅም፣ ትክክለኛዎቹ አርበኞች ተገፍተው፤ አርበኞች ያልሆኑት ደግሞ ተመዝግበው አለአግባብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል፣ አርበኞች በነፃነት ሐሳባቸውን ወይንም ቅሬታቸውን የሚያስተናግዱበት መንገድ ጠባብ ነው፣ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ለንጉሳውያን ቤተሰቦችና ለጀግኖች አርበኞች በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተሰጠው የዘላቂ ማረፊያ ስፍራ አስተዳደሩ ሌሎች አካላት እንዲጠቀሙበት አድርጎታል፣ ይገነባል የተባለው ሙዚየምም የት እንደደረሰ አይታወቅም የሚሉና መሰል ቅሬታዎችን አቅርበዋል።
የቅሬታቸው መነሻ
አርበኛ መሪ ጌታ አምዴ ወልደጻዲቅ የማኅበሩ አመራሮች ላይ የሚስተዋሉ የአሠራር ጥሰቶች፣ አትንኩን ባይነትና አግላይነት እንዲሁም የምዝበራው ክፉ ምግባር አርበኞችን እየጎዳ መሆኑን ይጠቁማሉ። በተለያዩ ሰበቦች ገንዘቡን ወጪ ቢያደርጉም ለዚህ ሁሉ ግን ምንም ዓይነት ሕጋዊ ማረጋገጫ የሚሆን ደረሰኝ አለመኖሩን ነው የሚናገሩት። አመራሮቹ መንግሥት ለሥራ ኃላፊዎች ሹመት ሲሰጥ ሙክት ሲወስዱ፤ በሌላ በኩል በጉልበታቸው ዘመን ለአገራቸው የዋሉ አርበኞች ግን የሚያቀናቸው አጥተው በየቤታቸው ተኮራምተው ይገኛሉ። ማህበሩ ሊደገፍ ሲገባው አባላቱን ዘንግተቶ ለሌሎች ፌሽታ ማክበሪያ ከመሆኑም ባሻገር ለራሳቸው መቀራመትን ምርጫቸው ያደረጉ አመራሮች እየበዘበዙት መሆኑንም ነው የሚጠቁሙት።
በማኅበሩ አመራርነት የሚቀመጡት ግለሰቦች አርበኞች አለመሆናቸው ለችግሩ ብዙም ትኩረት ላለመስጠታቸው እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል የሚገልጹት መሪጌታ አምዴ፤ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ከካዝና ውጪ ከተለያዩ አካላት በአርበኞች ሥም የሚገኘውን ድጋፍ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ግለሰቦች መኖራቸው ነው ይላሉ። በአንድ ወቅት መንግሥት ለአርበኞች በሚል የሠጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የቀድሞ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሊቀትጉሃን አስታጥቄ ለራሳቸው እንደወሰዷቸው በሐዘን ይናገራሉ።
መኖሪያ ቤቶቹ የት እንደገቡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ተጠይቀው እንደነበር በማስታወስ፤ ጉዳዩ ከምን ደረሰ? ሲሉ ቢጠይቁም ምላሽ ቀርቶ ጭርሱን መረጃው እንደጠፋ ያስታውሳሉ። በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው አካላት እንዲፈትሹ በየደረጃው ቢያመለክቱም ውሳኔ ግን የሚሰጥ እንደሌለ ነው በሐዘን የሚያስረዱት። በዚህም 12 ዓመታት ሙሉ ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ ተንገላተዋል። ለአርበኛው መብት የሚከራከር ሰው ተጎጂ እንደሚሆንና የማህበሩ አመራሮች የሚፈልጉት ያለማንም ከልካይና ጠያቂ እንዳሻቸው መሆን እንደሆነ ያጋጠማቸውን ችግር መነሻ በማድረግ ያብራራሉ።
በሌላ በኩል ቤተክርስትያን የጦር ተሳታፊ በመሆኗ በንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ውስጥ የሚገኘው ዘላቂ ማረፊያ ስፍራ ለንጉሳውያን ቤተሰቦችና ለአርበኞች የተፈቀደ ቢሆንም ዳሩ ግን ይህንን ወደ ጎን በማለት አርበኛው መቀበሪያ አጥቶ ሲንከራተት እየተመለከቱ የማኅበሩ አመራሮች አላስፈላጊ ተወዳጅነትን ለማትረፍና የግል ጥቅማቸውን በማስቀደማቸው ዝምታን መርጠዋል። በአሁኑ ወቅት የማኅበሩ አባላት በጭራሽ በቤተክርስትያኑ መቀበር የማይችሉ ሲሆን፤ ከተወሰኑ ዓመታት አስቀድሞ ጥያቄው ለቅዱስ ፓትርያርኩ ቀርቦ ይታያል የሚል ምላሽ ተሰጥቶ ነበር ይላሉ።
የሚከናወኑት ምዝበራዎችና ገዘፍ ያሉ ችግሮች እንዳይወጡና ሕዝብ እንዳያውቃቸው ደግሞ ማኅበሩ በኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ስር ሆኗል። ነገር ግን ማኅበሩ የበጎ አድራጎትም ሆነ የሙያ ማኅበር ሳይሆን እንዴት በኤጀንሲው ስር ሊታቀፍ ቻለ? የሚለው አጠያያቂ ነው በማለት መሪጌታ አምዴ አሠራሩን ይተቻሉ። እነዚህና ሌሎች በማህበሩ የሚስተዋሉ ችግሮች መበራከታቸው መንግሥት እንደዘነጋው ሁነኛ ማሳያ ይሆናሉ ባይ ናቸው።
በማህበሩ ውስጥ ባሉ ችግሮች ዙሪያ የቀድሞ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሊቀትጉሃን አስታትቄ አባተን ሊያነጋግሯቸው ቢሞክሩም በራቸውን ዝግ በማድረጋቸው ተስፋ ቆርጠው ወደ ክስ መግባታቸውን የሚናገሩት መሪጌታ አምዴ፤ ደረጃ በደረጃ ቅሬታቸውን አቅርበው ጉዳዩ ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱ አራት ሆነው ክስ እንደመሰረቱ ያስታውሳሉ። ነሐሴ 30 ቀን 2003 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወቅቱ አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ ለነበሩት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ለፌዴራል ሥነምግባርና ፀረሙስ ኮሚሽን፣ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለፍትሕ ሚኒስትሩ ችግሩን ዘርዝረው በደብዳቤ ያመለክታሉ።
በየጊዜው በአርበኞች ላይ የሚደርሰውን ችግር በመቃወም ትግል በማድረጋቸው የማኅበሩ አመራሮች ባገኙት አጋጣሚ ሊያጠቋቸው እንደሚፈልጉ በመግለጽ፤ በአንድ ወቅት አርበኛ እንዳልሆኑ ገልፀው ፍርድ ቤት ከስሰዋቸው እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን በመጀመሪያው ክስ ቅሬታ በማቅረባቸው ብቻ እንደተከሰሱ ፍርድ ቤቱ በማመኑ መዝገቡ እንደተዘጋላቸው፣ በኋላ ላይም ዳግም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረበባቸው ክስ ችሎቱ ነፃ መሆናቸውን አምኖ ቢለቃቸውም ደመወዛቸው ግን ተይዞባቸው እንደነበር ይገልፃሉ።
ዳግም ለደመወዛቸውና ለአርበኝነታቸው ከስሰው በፍርድ ቤት በመርታታቸው ስድስት ዓመታት ሙሉ ያጡትን ደመወዝ በአሁኑ ወቅት ውዝፍ ቢከፈላቸውም ወደ ቅጥር ግቢው እንዳይገቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል። ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ ውሳኔ ያገኙ አካላትን ለጥፋታቸው ማበረታቻ እስኪመስል በየወሩ ደመወዝ ሲያስከብር፤ ለአርበኞች ጥቅም የሚሟገቱትን ደግሞ መብታቸውን ሲረግጥ ይስተዋላል። ይህን መሰል የማህበሩ አመራሮች ድርጊትም ለአርበኛው የሚያስብም ሆነ ጥያቄ የሚያቀርብ እንደማይፈለግ ያሳያል ይላሉ።
የማህበሩ አመራሮች ሊቀትጉሃን አስታጥቄ የወስዷቸውን በፍርድ ቤት የተወሰኑትን ስድስት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳያስመልሱ እንደቀሩና ይልቁንም ለአጥፊው በየወሩ ደመወዝ እንደሚከፍሉ መሪጌታ አምዴ ይናገራሉ። ቤቱን ከጥፋተኛው ላይ ተረክበው ለአርበኞች መስጠት ቢገባቸውም ይህንን ግን አላደረጉም። በተጨማሪም ከሕንፃ ኪራይ የተገኘ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የት እንዳደረሱት ሳይታወቅ ቀርቷል። ኪራይ ሲፈፀምም ያለጨረታና ያለግልጽ ማስታወቂያ ነው። ገቢውም ወደማን ኪስ እንደሚገባ አይታወቅም፤ በማለት የሚታዩትን ችግሮች ይዘረዝራሉ።
በአሁኑ ወቅት አርበኞች ተበትነው እንዳሉና አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን የሚል አስታዋሽ ማጣታቸውን በሐዘን የሚናገሩት መሪጌታ አምዴ፤ የአርበኛው ጉዳይ ተረስቷል፤ መታወቂያቸውም ይቀደዳል፤በማለት የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ያስረዳሉ። ጉልበታቸው በመድከሙ ጉዳያቸውን እንኳ ተሯሩጠው መጠየቅ የማይችሉት አባላቱ መብታቸው ባይከበርም ማኅበሩ ገና ያልተወለዱ የወደፊቱ የአገሪቱ ተረካቢዎች ሁሉ ሀብት ነውና ሊጠበቅ ይገባልና የሚመለከተው አካል ችግሩን መርምሮ ተገቢውን ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ በቁጭት ይጠይቃሉ።
አርበኞች ማኅበር በ1996 ዓ.ም ለሥራ በደብዳቤ እንደጋበዛቸው የሚያስታውሱት አቶ ደስታ ኤርቤሎ በበኩላቸው፤ በማህበሩ ልማትና ህልውና ኮሚቴ ውስጥ እንዲሁም የታሪክ ክፍል ፀሐፊነት ባገለገሉባቸው ጊዜያት ችግሮችን እንደተመለከቱ ይናገራሉ። በሒደትም ሲያጠኑ ጀግኖች አርበኞች ከሚያገኙት ይልቅ በግለሰቦች የሚጠፋው ሐብት ስለሚበዛ በወቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ለነበሩት አቶ ወርቅነህ ተገኝን ጉዳዩን ያማክራሉ። ማስረጃ በማሰባሰብም በ2000 ዓ.ም ክስ ይጀምራሉ። በወቅቱ ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በደብዳቤ በማሳወቃቸውም ሁኔታውን የፌዴራል ሥነምግባና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲይዘው ይደረጋል። ነገር ግን ኮሚሽኑ ጉዳዩን የተመለከተ አንዳች ምላሽ ሳይሰጥ እንዳጉላላቸው ይገልፃሉ።
በቆይታም ጉዳዩ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መላኩን አቶ ደስታ ይናገራሉ። በኋላም የማህበሩን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሦስት ግለሰቦች እንዲከሰሱ ተደርጎ ጥፋተኝነታቸው ቢረጋገጥም የሕግ ባለሞያዎች በሠሩት ሥራ አቅልለውላቸው በተራ ወንጀል እንዲከሰሱ ይደረጋል። በዚህም የጥፋቱ ዋነኛ ፈፃሚ የነበሩት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሊቀትጉሃን አስታጥቄ በስድስት ወራት እስርና 1500 ብር መቀጫ ከፍለው እንዲወጡ ተደርጓል። በማለት አቶ ደስታ ተጠያቂነቱ ላይ የነበሩትን ክፍተቶች ያብራራሉ።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የማኅበሩን ገንዘብ ማጥፋታቸውን በመጠቆም፤ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አቶ ደስታ ያስረዳሉ። ፕሬዚዳንቱ መንግሥት ለጀግኖች አርበኞች የሰጠውን ከ30 በላይ የሚሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወይንም ኮንዶሚንየም ለራሳቸው ጥቅም አውለዋል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ስድስቱ በፍርድ ቤት የተወሰነ ሲሆን፤ በዚህ ብቻ ሳያበቁ ማኅበሩ ሕንፃውን ለአምስት ዓመት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አኮናትሮ ከኪራይ ያገኘውን 4 ሚሊዮን 150 ሺህ 764 ብርም ወስደዋል ይላሉ።
አቶ ደስታ ፕሬዚዳንቱ በዚህ ጥፋታቸው እንዳልተጠየቁና ማኅበሩን ኦዲት እንደማያውቀውም ይናገራሉ። ማኅበሩ በኤጀንሲው ስር መሆኑም አርበኛውን ጥርስ እንደሌለው አንበሳ አቅም አሳጥቶታል በማለት የችግሩን መደራረብ ያስረዳሉ። ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም አቶ ኃይለሚካኤል አባይን የማኅበሩ ጊዜያዊ ኃላፊ አድርጎ መሾሙን በማስታወስ፤ እሳቸው ደግሞ 816 ሺህ 955 ብር አጥፍተው ሕይወታቸው እንዳለፈ ይናገራሉ። በኋላ ደግሞ የማህበሩ ፕሬዚዳንት የተደረጉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ከአሜሪካ ከአቶ ነጋ መስፍን ለማህበሩ ገቢ የተደረገ 100 ሺህ ብር ወደ ኪሳቸው እንዳስገቡና 80ኛ ዓመት በዓል በሚከበርበት ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ለአርበኛው መታሰቢያ በሚል ያበረከተው 100 ሺህ ብርም በተመሳሳይ መውሰዳቸውን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ደስታ ገለፃ፤ አመራሮቹ ጥር 1 ቀን 1931 ዓ.ም በተጉለት አንቀላፊኝ በተባለ ቦታ የተቋቋመውና በሐምሌ ወር 1959 ዓ.ም አግባብ ባለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተመዝግቦ የሕግ ሰውነት ያገኘው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲስት እያደረጉት ይገኛሉ። ታሪኩን በሚገባ ጠብቆ በማቆየትና ለተተኪው ትውልድ በምስክርነት እንዲተላለፍ ለማስቻል እንዲሁ ደግሞ የአገርና የትውልድ ባለውለታ የሆኑ ጀግኖች አርበኞች የኑሮ ድጎማና እንክብካቤ እንዲያገኙ ቢቋቋምም ይህ ግን ከሰነድ አልፎ ሊተገበር አልቻለም። በደም የተላቆጠ በርካቶች ጀግንነታቸው የታየበት ይህ የታሪክ ቅርስ የሆነ ቤት መደፈር ባይኖርበትም በገሀዱ ግን ተደፍሯል።
በአሁኑ ወቅት በፕሬዚዳንትነት የተቀመጡት ልጅ ዳንኤልና የሥራ አጋሮቻቸው ጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም በኤጀንሲው ትዕዛዝ መቀመጣቸውን ይጠቁማሉ። ምንም ዓይነት ምርጫ ሳይካሄድ ወንበር መያዛቸውንም ነው የሚናገሩት። በዚህም ፕሬዚዳንቱ እንዳሻቸው እያደረጉት ይገኛሉ። በሣምንት ሁለት ቀን ብቻ ያውም ለግማሽ ቀን ቢሯቸው የሚገቡት ፕሬዚዳንቱ ቀርበው የአርበኛውን ችግርና አቤቱታ እያደመጡ አለመሆናቸውንም ይገልፃሉ። ‹‹ያለአግባብ ለራሳቸው ሥም ሰጥተው ጀግንነትን የቀበሩ በመሆናቸው ታሪክ ይፍረድ›› በማለት ሁኔታውን ፊታቸውን ቅጭም አድርገው ያስረዳሉ።
የማኅበሩ ሕንፃ አራት ወለል ሲደረግ ምንም ዓይነት ማስታወቂያም ሆነ ጨረታ አለመውጣቱንና ፕሬዚዳንቱ
ያለምንም ጨረታ የማህበሩን ሕንፃ አስፈርሰው ለግንባታ በሚል 5 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ከካዝና ወጪ ማድረጋቸውን ይጠቁማሉ። በተጨማሪም በአርበኞች ሥም የውጭ አገር ጉዞዎችን እንዳረጉና በአርበኞች ሥም የሚገኙ ድጋፎች ቢኖሩም ወደ ችግረኛው አርበኛ ኪስ ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ አቶ ደስታ ይናገራሉ። በኢትዮ ቴሌኮም ነፃ የስልክ መስመር 8400 የአርበኞቹ ሙዚየም ይሠራል በሚል የተሰበሰበው ገንዘብም የት እንደገባ አይታወቅም ይላሉ። እነዚህንና መሰል የሚነሱ ቅሬታዎች ላይ ለመነጋገርም ደግሞ በራቸው ክፍት ባለመሆኑ ችግሮቹ ከመቃለል ይልቅ ከዕለት ዕለት እንዲደራረቡ አድርጓቸዋል።
1 ሚሊዮን 881 ሺህ ብር ወጪ ሲደረግ የአስተዳደር ክፍል ኃላፊ አቶ በቀለ ሻሮ የአርበኞች ተመራጭ ሳይሆኑ አባል ሆነው ፈርመዋል። በአሁኑ ወቅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ልጅ ዳንኤል ምንም እንኳ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያለደመወዝ እንደሚያገለግሉ ሲናገሩ ቢደመጥም፤ ዕውነታው ግን በማኅበሩ ካለው ምዝበራ ባሻገር በየወሩ ጠቀም ያለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በማግኘታቸው የአርበኛውን ጥቅም እያሳጡ እንደሆኑም ይገልፃሉ። በተያያዘ ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ ለማህበሩ ደፋ ቀና ብለው በመልፋታቸውና ፍርድ ቤቱ ነፃ ስላሰናበታቸው በሚል 1 ሺህ 200 ብር ክፍያ መፈፀማቸውን እንዲሁም ቤቱን ስላጠፉ ማመስገኛ በሚመስል መልኩ በየወሩ 2500 ብር እንዲያገኙ መደረጉ አሳዛኝ ነው ይላሉ።
ጉዳዩን ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢያመለከቱም ሰባት ወራት ካመላለሳቸው በኋላ ለፌዴራል ኦዲት ቢሮ መጻፉን ይገልፃሉ። የኦዲት ትዕዛዙ ግን ከዚህ ዓመት ጀምሮ የሂሳብ ምርመራ ይደረግ አይልም። ነገር ግን ተከታትለው ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ሊቀትጉሃን አስታጥቄ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ከገቡበት ጀምሮ ያለው ይጣራ በሚል ዋና ኦዲተር ድረስ ማነጋገራቸውን ያስታውሳሉ። በዚህም በተያዘው ዓመት ከጥር ወር በኋላ ይደረጋል ተብለው እንደነበር ይናገራሉ። ችግሮቹ እንዲፈጠሩ በማኅበሩ የሒሳብ ሹሙና ኦዲተሩ አንድ ሰው መሆኑም የራሱን ሚና እንደተጫወተ ይጠቁማሉ።
ማኅበሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ አለኝታ ሲሆን፤ አርበኞቹ በሕይወት ቢያልፉም ታሪክ ግን እንደማይሞት በመግለጽ፤ መተዳደሪያ ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት እንዲተዳደር በሚል አቶ ተፈራ ዋልዋ የሰጧቸው ሰነድ እንዳለም ይናገራሉ። ይህን ሁሉ ወደ ጎን በማለት አርበኛው ከጣሊያን ጋር ከሰማይ የሚዘንብበትን መርዝ ጋዝ ተጋፍጦ ተዋግቶ አሸንፎ የተዋደቀለት መታሰቢያ ቤት ከቸርቻሪ ማህበር ጋር እንዲታይ መደረጉም አግባብነት የጎደለው ተግባር ሲሉም አቶ ደስታ ይተቻሉ። ‹‹እኛ እንሞታለን ታሪክና ትውልድ ግን ቀጣይ ናቸውና መንግሥት ይድረስልን። አሜሪካ መኖሯ ሳይታወቅ ታላቅ የነበረች የአፄ ካሌብ አገር ነበረችና አገሪቱን እናድናት፤ ታላቅ ቦታም እናድርሳት›› በማለት ጥሪያቸው ያስተላልፋሉ።
በማኅበሩ ላይ ችግሮች እንዳሉ የሚናገሩት ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ ሻምበል ግዮን ደሬሳ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በፕሬዚዳንትነት የተቀመጡት ልጅ ዳንኤል በታሪክ በርጩማ ላይ ተቀምጠው ለታሪክ ማንነት ደንታ የማይሰጡ ናቸው በማለት ችግሩን መናገር ይጀምራሉ። በምርጫቸው ማግስት የማይገኙ ማስታወሻ የአርበኞች ምስሎችን (ፎቶግራፎችን) በጆንያ አስጠቅልለው መጣላቸውንም ያስታውሳሉ። በዚህም አርበኞች የት እንደወደቁ ስለማይታወቅ ትክክለኛዎቹ አርበኞች ተቀምጠው ሌሎች ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ሆኗል።
የአርበኞች ሥም ዝርዝር ሊገኝ ባለመቻሉ በሰለጠነ መልኩ ሊያዝና መረጃው ለተተኪ ትውልድ የሚተላለፍበት መንገድ ይፈጠር በሚል ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ይገልፃሉ። ለማሳያም በሰላሌ አውራጃ የሚገኙ ለእናት አገራቸው ከተዋደቁ መካከል አንድም የታቀፉ አርበኞች የሉም። በአልጋ ላይ የቀሩትንም መረጃው ቢኖር ኖሮ በያሉበት ለሚመለከተው አካል ተልኮ እንዲደገፉ ማድረግ ይቻል ነበር። ሆኖም ግን አርበኛውን የሚያሳይ የተደራጀ መረጃ ባለመኖሩ ለችግር ተዳርገዋል በማለት ሻምበል ግዮን የችግሩን ምንጭ ያስረዳሉ።
መረጃ ቢደራጅ ተተኪዎቹ ደግሞ አስመስክረው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር ይላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ባለመሠራቱ ልብስ እንኳ ያጡ አርበኞች እንዲኖሩ አድርጓል። ይህም ለልጅ ዳንኤል ቢነገርም ባጀት የለም የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው በማስታወስ፤ ኤጀንሲው በአስቸኳይ ችግሩ እንዲቃለል በወሰደው እርምጃ ሊፈታ ችሏል። በቀጣይም ችግሮቹ እንዲቃለሉ ማኅበሩ ከኤጀንሲው ስር የሚወጣበት ሁኔታ ቢመቻች ሲሉም ጠይቀዋል።
አቶ ሥዩም ተክለብርሃን ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ ሲሆኑ፤ አባትና እናታቸው አርበኛ እንደነበሩ ይናገራሉ። ይህንንም አስመስክረው ወራሽነታቸው ተረጋግጧል። በአርበኛው ሥም የሚመጡ ጥቅማ ጥቅሞች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መድረስ ቢገባቸውም ይህ እንዳልሆነ በመግለጽ፤ ሊታረም የሚገባቸው በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያብራራሉ። አረጋውያኑ ደካማ አርበኞች ሕክምና እንኳ ሳያገኙ ሕይወታቸው ሲያልፍ ሌላው ደግሞ በማን አለብኝነት ሀብቱን ሲበተን መመልከት ከዛም በላይ ምንም መፍትሔ ማግኘት አለመቻል ትልቅ አደራን እንደመብላት ነው በማለት ሁኔታውን በሐዘን ያስረዳሉ። በሌላ በኩል መንግሥት ችግሩን እንደማያውቅ ይናገራሉ። በዚህም ሰሚ ጆሮ አጥተው እየተበዘበዙ ስለሆነ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ይላሉ።
ደንቡ ምን ይላል?
በ1990 ዓ.ም የወጣው የጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ በክፍል አራት አንቀጽ 18 ስለ ጠቅላላ ጉባዔው ሥልጣን አስቀምጧል። በዚሁ አንቀጽ (ለ) ላይ የማህበሩን የሥራ አመራርና የአስተዳደር ምክር ቤት አባላትን፣ የማኅበሩን ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና ዋና ፀሐፊ ከአርበኞች መካከል መርጦ ይሾማል የአገልግሎት ዘመናቸውን ሲጨርሱም ያሰናብታል ይላል። ነገር ግን ተመራጮች ለሥራው ብቁ አለመሆናቸውንና ሌላም ጥፋት ፈፅመዋል ከተባለ፣ ለዚህም ብቁ የሆነ ተጨባጭ ማስረጃ ከቀረበ ጉዳዩ ተመርምሮ ሲታመንበት ተከታዩን የምርጫ ጊዜ ሳይጠብቅ ከኃላፊነታቸው ያለምንም ክፍያ ያሰናብታል።
በደንቡ ክፍል ስድስት ስለ ማኅበሩ ሹማምንት ያስቀመጠ ሲሆን፤ በአንቀጽ 22 ስለማኅበሩ ፕሬዚዳንት ያብራራል። ማኅበሩ ከአርበኞች መካከል በጠቅላላው ጉባዔ የሚመረጥ አንድ ፕሬዚዳንት ይኖረዋል። ፕሬዚዳንቱም የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል። ሆኖም ጠቅላላ ጉባዔው ካመነበት ለተከታታይ የሥራ ዘመናት እንደገና አገልግሎት እንዲሰጥ ያደርጋል በማለት ደንግጓል። በተያያዘ ማኅበሩ ከመንግሥት፣ ከውጭ መንግሥታት፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ድርጅቶች ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች በጠቅላላ ጉባዔ፣ በሥራ አመራርና አስተዳደር ምክር ቤት መመሪያዎችና ውሳኔዎች መሠረት ከእነዚህ አካላት የገንዘብና ቁስ እርዳታ ይጠይቃል፣ ሲገኝም ለማኅበሩ ገቢ እንዲሆን ያደርጋል በሥራም ላይ እንደሚውል አስቀምጧል።
በዚሁ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ኃላፊነት በደነገገው አንቀጽ ላይ እንደሰፈረው፤ የማኅበሩ ገንዘብና ንብረት በሚገባ መያዙንና በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን የመቆጣጠርና የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት። የማኅበሩን ገንዘብ በምክር ቤቱ ዝርዝር መመሪያዎች መሠረት ለተፈቀዱ ሥራዎች ወጪ ያደርጋሉ። በሌላ በኩል አቅም የሌላቸው አርበኞች በኑሯቸውና በጤናቸው የሚደጎሙበትና እንክብካቤ የሚያገኙበት ዕቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ ሥራ ላይ እስከማዋል መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ያብራራል። በምዕራፍ አምስት አንቀጽ 29 ላይም የማኅበሩ የገቢ ምንጮችን ለይቶ አስፍሯል።
ኤጀንሲው
በኢፌዴሪ የሲቪል ማህበራትና ድርጅቶች ኤጀንሲ የክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ ሲራጅ አብዱልሽኩር፤ አገር በቀልና የውጭ ድርጅቶች የሚታቀፉበት ቢሆንም ማኅበሩ ግን በኤጀንሲው ስር መታቀፉ ትክክል አይደለም በማለት ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚያነሱት አቤቱታ ትክክል እንደሆነ አምነዋል። ማኅበሩ ከመነሻው በኤጀንሲው መመዝገብ አልነበረበትም ይላሉ። የኤጀንሲው አዋጅ ማኅበሩን አያቅፍም በማለትም ያስረዳሉ።
ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በውርስ ለልጅ ልጅ ይተላለፋል ይላል። በሌላ በኩል የኤጀንሲው አዋጅ ቁጥር 113/2011 መሠረት ብሎም ቀደም ብሎ በነበረው አዋጅ አባልነት በውርስ አይተላለፍም በሚል የሚደነግግ በመሆኑ ማኅበሩ በኤጀንሲው መታቀፍ አልነበረበትም። በዚህም ሳቢያ የተፈጠሩ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ይጠቁማሉ። ማኅበሩ የአገር ባለውለታዎችን ያቀፈ በመሆኑ መንግሥት በሚሊዮን የሚቆጠር ከፍተኛ ባጀት መድቦ እንደሚደግፈው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በሚደረጉ ክትትልና ድጋፎች የማኅበሩ አመራሮች ላይ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች እንዳሉ እንደተደረሰበት አቶ ሲራጅ ይናገራሉ።
የማኅበሩ አባላት የአገር ባለውለታ እንደመሆናቸው በተቋሙ ሲሄዱ ተገቢውን መስተንግዶ ሊያገኙ ቢገባም ይህ ግን እየተደረገላቸው አለመሆኑን ቡድን መሪው ይናገራሉ። ከዚህም ባሻገር ያልታቀፉ የማኅበሩ አባላቶች አሉ። በተጨማሪም በማኅበሩ ውስጥ የሚያገለግሉ ባለሞያዎች የዕውቀትና የክህሎት ችግር እንዳለባቸውና ይህንንም ለአመራሮቹ ገልፀው እንደነበር ያስታውሳሉ። ነገር ግን መፍትሔ ያልተሰጠው ችግር በመሆኑ በተደረገ ኦዲት ክፍተት መኖሩ እንደተረጋገጠ ይጠቁማሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በማኅበሩ ሒሳብ ሹም ኦዲተር አንድ ባለሞያ ነው በሚል እንዲሁም ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የቀረበውን ቅሬታ እንደማያውቁት ነው የሚናገሩት።
በሌላ በኩል ኤጀንሲው አመራሮቹን እንደሾመ ተደርጎ የሚነሳው አቤቱታ ላይ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለጽ፤ ባለፈው ዓመት ሊደረግ የነበረው ምርጫ ግን በነበሩ ክሶች በጊዜው ሳይከናወን እንደቀረ በኋላም በተመሳሳይ በሌላ ክስ በተደረገ የፍርድ ቤት እገዳ ምርጫ ማድረግ እንዳልተቻለ ነው የሚያስረዱት። ቅሬታ አቅራቢዎችም ዘንድ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውንም ይናገራሉ። ለዚህ ሁሉ በማኅበሩ ለሚነሱ ችግሮች ራሱን የቻለ አደረጃጀት ተፈጥሮለት ተጠሪነቱ ከተቻለ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አልያም ሌላ አማራጭ ቢፈለግ የተሻለ እንደሚሆን በመግለጽ መፍትሔ ያመላክታሉ።
ሰነዶች
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ የተገኙ የሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያመላክቱት ማኅበሩ የተካሰሰባቸው የፍርድ መዝገብ ግልባጮች፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሊቀትጉሃን ላይ የቀረቡ ክሶች የሚያሳዩ ሰነዶች፣ የማኅበሩ የሕግ ባለሞያና ነገረ ፈጅ ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም ለኢፌዴሪ ለሙስና ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን ጠቅሰው የተደረገ ምዝበራን አብራርተው ያቀረቡት ጥቆማ፣ ማኅበሩ ሊቀትጉሃን አስታጥቄ ለሦስት ዓመታት ክስ ቀርቦባቸው ሲከራከሩ መቆየታቸውን ገልፆ፤ ፍርድ ቤት የሰጣቸውን ውሳኔ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የዋሉትን ውለታ በማጤንና በመንገላታታቸው 50 ሺህ ብር መክፈሉን የሚያሳይና መሰል ሰነዶችን መመልከት ችለናል።
የፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሰባተኛ ችሎት በቀን 22/4/2012 ዓ.ም በቁጥር 187281 ወጪ ባደረገው መዝገብ ግልባጭ ላይ በሰፈረው ትዕዛዝ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ግለሰቦች አስመልክቶ ሰፍሮ ተመልክተናል። በዚህ መዝገብ ከሳሾች ቅሬታ አቅራቢዎቹን ጨምሮ ሌሎች 11 ግለሰቦች ሲሆኑ፤ ተከሳሾች ደግሞ ማህበሩና ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሌሎች ሰባት አካላት ናቸው።
መዝገቡ በዕለቱ የተቀጠረበት ምክንያት አራቱ ግለሰቦች ያቀረቡትን የክስ ይሻሻልልን አቤቱታ መርምሮ ትዕዛዝ ለማሳረፍ እንደሆነ በሰነዱ ሰፍሯል። ከዚሁ ጋር የተያያዘው አራቱ ከሳሾች ያቀረቡት የክስ ማሻሻያ እንደሚያመላክተው፤ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሳይመረጡ በሕገወጥ መንገድ አምስት ዓመት ከ11 ወራቶች ማህበሩን በፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል እና አብረዋቸው የተከሰሱት የምክር ቤት አባላት እና ሥራ አስኪያጅ በአስቸኳይ ይታገዱ፣ ተከሳሾቹ በአምስት ዓመት ከ11 ወሮች ውስጥ የማበሩንና የአርበኛውን ተተኪ ወራሾች መብት የሆነውን ገንዘብ እና ቋሚ ንብረት እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ንብረት በኦዲተሮች ተመርምሮ ያለአግባብ የተወሰደው ሁሉ ተከሳሾች ለማህበሩ ተመላሽ እንዲያደርጉ የሚሉ እንዲሁም ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ እና የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ የፈፀሙትን ጥፋት ዘርዝረው ክሱን ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል።
አቤቱታቸውን መነሻ አድርጎ ችሎቱ ባሳለፈው ትዕዛዝ በዚህ መዝገብ ክስ እንዲሻሻልላቸው የጠየቁት ከሳሾች ቀደም ሲልም ከሌሎች ከሳሾች ጋር ክስ ማቅረብ የነበረባቸው በአንድ ተራ የሚመደቡ ተከራካሪዎች ከሆኑ እንጂ የተለያየ ዓይነት የሚጠይቁ ባቀረቡት ክስ የማይስማሙ ከሆነ ከክሱ ውጪ ተደርገው በሌላ ክስ ከሌሎች ከሳሾች ጋር የተለያየ ዓይነት ለመጠየቅ፤ እንዲሁም ከሌሎች ከሳሾች ጋር ተቃራኒ የሆነ ክሶች ካላቸው ከሌሎች ከሳሾች ጋር ተጣምረው ክስ ሊያቀርቡ የሚችሉበት አግባብ ስለሌለ ክሱን ለማሻሻል ያቀረቡትን ክስ ውድቅ በማድረግ አራቱ ከሳሾች ከዚህ መዝገብ ከተያዘው ክርክር ውጪ ሆነው በሌላ መዝገብ የራሳቸውን ክስ እንዲያቀርቡ መብታቸው ተጠብቆ ከክርክሩ ውጪ እንዲሆኑ ማዘዙን መዝገብ ግልባጩ አስፍሯል።
ከሁለት ወራት በፊት በዚሁ ጉዳይ ላይ ምላሽ ሊሰጡን ተስማምተው የነበሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ከተቋማችን ደብዳቤ እንድንሰጣቸው ጠይቀውን ጋዜጣው ለህትመት ሊበቃ ሲል በማህበሩ ጠበቃ በኩል ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንደተያዘ ገልፀውልን ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወደ ተቋማችን ቅሬታቸውን ያሰሙት አራት ግለሰቦች ከክሱ በመውጣታቸው ጉዳያቸውን ሕዝብ እንዲሰማና እንዲፈርዳቸው በድጋሜ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። እኛም ዳግም በደብዳቤ ማህበሩን ምላሽ ጠይቀናል።
ማህበሩ
የአርበኞቹን ቅሬታ ይዘን ወደ ቀዳማዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች አርበኞች ማህበር ዳግም ምላሽ ለማግኘት አቀናን። ከወራት በፊት ፈቃደኛ ሆነውልን እንደነበረ ሁሉ በአሁኑ ወቅትም ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሊሰጡን ቢስማሙም በቆይታ ግን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 18/2012
ፍዮሪ ተወልደ