ከአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2018 የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ከ210 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በስጋ ደዌ በሽታ የሚያዙ ሲሆን፣ በአፍሪካ ደግሞ 20 ሺህ ያህሉ በየአመቱ በበሽታው ይጠቃሉ። በኢትዮጵያም በየአመቱ ከሦስት እስከ አምስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በስጋ ደዌ በሽታ እንደሚያዙ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም በተለይ በኢትዮጵያ ለበሽታው በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ እንደሌሎቹ በሽታዎች ባይሆንም ስርጭቱ ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማል።
በሀገሪቱ ትልቁ የስጋ ደዌ ህክምና ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው አለርት ማዕከል ቢሆንም፤ በደቡብ ወሎ ቦሩ ሜዳ፣ በአገሪቱ በስተደቡብ ኩየራ፣ በአርሲ ጊምቢ እና ትግራይ ሆቡ ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምናው እየተሰጠ ይገኛል። ቀደም ሲል የስጋ ደዌ ህክምና በአለርት ማዕከል እየተሰጠ የቆየ ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ማዕከሉ ወደ ጠቅላላ ሆስፒታል መቀየሩን ተከትሎ ከሌሎች ህክምናዎች ጋር ተቀላቅሎ በጋራ ይሰጣል።
የስጋ ደዌ በሽታ በቶሎ ካልታከመ በአካል ላይ ጉዳት ስለሚያስክትል ታማሚዎች በህብረተሰቡ መገለል ሲደርስባቸው ቆይቷል። ይሁንና በታማሚዎች ላይ የሚደርሰው መገለልና አድልዎ አሁንም ቢታይም በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ለውጦች ይታያሉ። የስጋ ደዌ ታካሚዎች በማህበረሰቡ አድልዎና መገለል እንደሚደርስባቸው ሁሉ በህክምና ቦታዎች ላይ ርህራሄ፣ አክብሮትና እንክብካቤ የተሞላበት አገልግሎት ያገኛሉ ወይ? የሚለውም የብዙዎች ጥያቄ ነው።
ዶክተር ይሄይስ ፈለቀ፣ በአለርት ማዕከል የአጥንት ህክምና ስፔሻሊስትና የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው። የስጋ ደዌ በሽታ ቀደም ሲል በዘር እንደሚተላለፍ ይነገር የነበረ ቢሆንም፤ በሽታውን የሚያመጣው ባክቴሪያ ከታወቀ በኋላ ግን መድሃኒት እንደተገኘለት ያስረዳሉ። ከአሁን ቀደም ማዕከሉ ቲቢና የስጋ ደዌ በሽታዎችን በዋናነት ስለሚያክም ለስጋ ደዌ ታካሚዎች የቆዳ፣ የፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና፣ የአይን፣ የአጥንትና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ህክምናዎችን ይሰጥ እንደነበረም ያስታውሳሉ።
በተጨማሪም ማዕከሉ ለስጋ ደዌ ታካሚዎች ሌሎች ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ያደርግ እንደነበርና የተቋቋመበትን አላማ ይዞ እንደቆየ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ጠቅላላ ሆስፒታል ከመሆኑ አኳያና የድንገተኛ፣ የአይን፣ የጥርስ፣ የማዋለድ፣ የቀዶ ህክምናዎችን ጨምሮ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን መስጠት በመጀመሩ ቀደም ሲል ለስጋ ደዌ ታካሚዎች ይደረግ የነበረው እንክብካቤ እንደቀነሰም ይገልፃሉ።
ቀደም ሲል የአለርት ማዕከል የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ ክልሎች በመሄድ የህክምና አገልግሎትና መድሃኒት በመስጠት፤ በተጨማሪም ልዩ ጫማዎችንም በማቅረብ ታካሚዎች አዲስ አበባ ድረስ መጥተው እንዳይንገላቱ ሰፊ ስራዎችን ይሰሩ እንደነበርም ጠቅሰው፤ ይሁንና በአሁነ ወቅት ይህ ነገር እንደሌለ ያብራራሉ። ማዕከሉ ወደመንግስት ከዞረ በኋላና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጠቅላላ ሆስፒታል ከመሆኑ አኳያ የስጋ ደዌ ታማሚዎችን በልዩ ትኩረት ማከም እንዳልተቻለም ያስረዳሉ።
ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው በተለይም ለስጋ ደዌ ህክምና በመንግስት በኩል የሚያዘው በጀት አነስተኛ መሆን፣ በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ከመኖሩ አኳያ ማዕከሉ ዋነኛ የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማዕከል በመሆኑና ሌሎችም ናቸው። በማዕከሉ እየተሰጡ ያሉ ልዩ ልዩ የህክምና አገልግሎቶችና ሌሎችም ተደምረው የስጋ ደዌ ህክምና አገልግሎቱን እየተጋፉት ይገኛሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በማዕከሉ ያለው አብዛኛው የጤና ባለሙያ ለስጋ ደዌ በሽታ ያለው አመለካከት መልካምና ህክምናውም በተቻለ አቅም በተገቢው መንገድ እየተሰጠ ቢሆንም፤ አልጋን በሚመለከት በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው የከፋ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታሉ ለሚመጣ ታካሚ በመሆኑ የስጋ ደዌ ታካሚዎች አልጋ አጥተው ሲንገላቱ ይታያሉ።
ሆስፒታሉ ለስጋ ደዌ ታካሚዎች ቅድሚያ ለመስጠት ጥረት ቢያደርግም የክፍል፣ የአልጋ፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ የበጀትና ሌሎች የግብአት እጥረቶች በመኖራቸው ለታካሚዎች ተገቢውን ህክምና በጥራት መስጠት አልቻለም። ይህም የህክምና ባለሙያውን ስነ ምግባርም የወረደ ነው አስብሏል። ይሁን እንጂ ጥቂቶቹ እንጂ ሁሉም የህክምና ባለሙያዎች የስነ ምግባር ጉድለት አለባቸው ማለት አይደለም። የሚያስማማው ጉዳይ ግን ለስጋ ደዌ ታካሚዎች ያለው ስሜት ባይቀንስም የሚደረግላቸው እንክብካቤ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ ነው።
ሜዲካል ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ የስጋ ደዌ ታካሚዎችን ልክ እንደበፊቱ ተገቢውን ህክምና እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ በተለይ የሆስፒታሉን አሰራር ማስተካከል ያስፈልጋል። በሀገሪቱ ያሉ የህክምና ቦታዎችም ካለው ታካሚ ቁጥር አንፃር በቂ ባለመሆናቸው ሊስፋፉ ይገባል። ለህክምና የሚያዘው በጀትም በቂ ባለመሆኑ ይህንን መንግስት ማስተካከል ይኖርበታል።
በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ አብዛኛው የነፃ ታካሚ በመሆኑ ክፍያ አይፈፅምም። በዚህም ምክንያት በመንግስት በኩል የሚለቀቀቀው በጀት በቶሎ ያልቃል። ይህም ተገቢውን የህክምና አገልግሎት በጥራት ለመስጠት አንዱ እንቅፋት ይሆናል። በመሆኑም ሆስፒታሎች የራሳቸሰውን ገቢ የሚያሳድጉበትን መንገድ መንግስት ሊያመቻች ይገባል።
ሪፈር ተፅፎላቸው ወደ ሆስፒታሎች የሚመጡ ታካሚዎችን ቁጥር ለመቀነስም ጤና ጣቢያዎችን ማሻሻል ያስፈልጋል። ለጤናው ሴክተር የሚያዘውን በጀትም ማሳደግ ይገባል። የግዢና የጨረታ ስርዓቱም መስተካከል ይኖርበታል። ይህ ከሆነም የጤና ባለሙያዎች ስራቸውን በትጋት በማከናወን ታካሚን ያረካ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2012
አስናቀ ፀጋዬ