እንቦጭን ከጣና ለማጥፋት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል። በዘመቻ መልክ አረሙን ከሐይቁ ለመንቀል ሰፊ ርብርብ ተደርጓል። ይሁንና አረሙ ተነቀለ ሲባል የበለጠ ተስፋፍቶ ይገኛል።
የእምቦጭ እየተስፋፋ መምጣት የዓሣ ሀብቱ እየቀነሰ እንዲመጣ እያረገ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ። የሐይቁ ብዝሃ ህይወት ፣ ኑሯቸው በሐይቁ ላይ የመሠረተ ዓሣ አስጋሪዎች፣ የጀልባ አስጎብኚዎችና አጓጓዦች፣ በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ጥንታዊ ገዳማት፣ ዓሣ ነጋዴዎች በእምቦጭ የተነሳ ሥጋት ውስጥ ናቸው።
የኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ዓመታዊ የምርምር ግምገማ ወራሪውን የእንቦጭ አረም ለከሰልነት ማዋል የሚያስችል ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል። ለዚህም የሚረዳ የእንቦጭ ማክሰያ እና የእምቦጭ ክሰልን ለማምረት የሚረዳ የክሰል ቅርፅ ማውጫ መሣሪያዎች መሠራታቸው ተጠቁሟል።
የምርምሩ አቅራቢ አቶ ያለምሰው አዴላ በተለይ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ በመደበኛው ክሰልና ከእምቦጭ ለማምረት በሚፈለገው ክሰል መካከል ልዩነት እንዳለ ይጠቁማሉ። “መደበኛ ክሰል ከዛፍ ግንድ ነው የሚመረተው። እምቦጭ ግን አላስፈላጊ ቦታ ላይ የተገኘ ውሃ ላይ የሚንሳፈፍ አረም ነው።›› ይላሉ። ማገዶንና እምቦጭን ማወዳደር እንደማይቻልም አስታውቀው፣ ከእምቦጭ የሚመረተው ክሰል ከ3ሺ ካሎሪ ኪሎ በላይ ኃይል እንዳለው መታወቁንም ያብራራሉ። ምድጃ ላይ ከተቀመጠ እስከ አንድ ሰዓት በላይ መንደድ እንደሚችል ጠቅሰው፣ ይህ ደግሞ በአንድ ሰዓት ውስጥ ኃይል የሚፈልጉ ተግባሮችን ማከናወን እንደሚያስችል ያብራራሉ።
አቶ ያለምሰው ጥናቱ ስለሚተገበርበትም ሁኔታ ሲጠቁሙ ‹‹እኛ ደረጃውን ጨርሰን ከጥቃቅንና አነስተኛ ለተውጣጡ ወደ ሰባ ለሚሆኑ ባለሙያዎች መሣሪያቹን እንዲያዩ አድርገናል›› ይላሉ። ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ማክሰያውንና ቅርጽ ማውጫ መሣሪያዎቹን እንዲሠሩ ሥልጠና እንደተሰጣቸውም ያብራራሉ። ‹‹የምርምር ተቋሙ ሐሳብ ይፀንሳል፤ ይወልዳል፤ ሥራ ፈጣሪዎች ደግሞ ወደ ገበያ ይዘውት ይገባሉ፤ ማኅበረሰቡ ደግሞ መጠቀም ውስጥ ይገባል›› ሲሉ ይጠቁማሉ። አጠቃቀሙ ቀስ በቀስ ማኅበረሰቡ ውስጥ ይገባል እንጂ አንድን ሥራ ማኅበረሰቡ ዘንድ ወርዶ ይህን ተጠቀም የሚል አካሄድ ዓለም ላይም እንደተሞክሮ እንደሌለ ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ መሣሪያዎቹ ቢበላሹ በቀላል ስልጠና ሊጠገኑ የሚችሉ ናቸው። በቀላል ዋጋ ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የሚገዙም ናቸው። በውሃ አካላት አካባቢ ያለውን ገበሬ ቀጣይነት ባላቸው ሥልጠናዎች አቅሙን በማሳደግ ጥቅሙን እንዲረዳ ይደረጋል፤ በዚህም ገበሬው ይህማ ሀብት ነው እያለ ማሰብ ሲጀምር የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣል፤ እምቦጭን መጠቀም ይጀምራል። ይህ ሲሆን አሁን የሚከመረው እንቦጭ ተመልሶ ሐይቅ አይገባም።
እንቦጭ ለክሰልነት እንደ አማራጭ ሲወሰድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም አቶ ያለምሰው ይጠቁማሉ። ከውሃ አካላቱ ላይ እንቦጭን ማስወገድ ማለት ውሃውን ብቻ ማፅዳት አይደለም፤ የአካባቢው የዓሣ ምርት እንዲጨምር ወይ እንዲቀጥል ያደርጋል፤ በአምቦጭ ምክንያት ሥጋት ውስጥ የገባው በጀልባ መጓጓዝም መፍትሄ ያገኛል ሲሉ ያብራራሉ።
ኑሮውን ከዓሣ ሀብት ጋር ያደረገው ማኅበረሰብ በእንቦጭ ምክንያት የዓሣ ሀብቱን ካጣ ደን ሊያወድም እንደሚችልም በመጥቀስ፣ ‹‹አንድን ሥርዓተ ምህዳር ጤናማ ባደረግነው ቁጥር በዋነኝነት ሌላኛውን የሥርዓት ምህዳር አካል እየደገፍነው እንሄዳለን›› ሲሉ ተመራማሪው አቶ ያለምሰው ያስረዳሉ። እምቦጭ እያለ የውሃ አካላት እንዲሁም ውሃውም አይኖርም ያሉት አቶ ያለምሰው፣ ውሃው ከፍተኛ የጥራት ችግር እንዳለበትም ይጠቅሳሉ። ይህን አጣርቶ የመጠጥ ውሃ አርጎ ለህዝብ ለማድረስ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅም ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ያለምሰው ማብራሪያ፤ እንቦጭን ለክሰልነት እንደአማራጭ የመጠቀም ቴክኖሎጂ እንቦጭን ከሥር ከመሠረቱ ነቅሎ ይጥለዋል ማለት አይደለም። እንቦጭን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አንድ አማራጭ ሆኖ ግን ይቀርባል፤ ተሰብስቦ የወጣን እንቦጭ አርሶ አደሩ በውሃ ዳር ከምሮ ንፋስ ከሚበትነው ቤት ውስጥ ኃይል አድርጎ መጠቀሙ በቀን የሚያስፈልገውን ኃይል እንዲያገኝ ያስችላል።
የኢትዮጵያ አካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አጌና አንጁሎ ተመራማሪዎች እምቦጭን ወደ ከሰል ለመቀየር እንደሚቻል በምርምር መድረሳቸው ፣ ሌሎች ወራሪ ዛፎችንም ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ያመላከተ ነው ይላሉ። እስካሁን እንቦጭን እንዴት እናስወግድ እንጂ እንጠቀምበት የሚል አካሄድ እንደሌለም ዶክተር አጌና ጠቅሰው፣ የተወገደው እምቦጭ ተከምሮ ከማየት ይልቅ ለምን ለማገዶነት እንዲውል በማድረግ የሥራ ዕድል አይፈጠርም፣ የማገዶ ጥያቄንም እንዲመልስ አይደረግም በሚል ፕሮጀክቱ መጀመሩን አስታውቀዋል።
‹‹በሀገሪቱ ከፍተኛ የኢነርጂ ፍላጎት አለ። ወደ 60 በመቶ የሀገራችን የኃይል ምንጭ እየቀረበ ያለው ከባዮ ማስ (ዕፅዋት) ነው። ይህም በአብዛኛው የሚገኘው ከዛፍና ከቁጥቋጦ ነው።›› ያሉት ዶክተር አጌና፣ ወራሪ ዛፎችንና አረሞችን አክስሎ ብሪኬት ሠርቶ ጥቅም ላይ ማዋል ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ። ብሪኬቶች እናቶች በጭስ አልባ ማገዶ ምግብ እንዲያዘጋጁ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ለደህንነታቸው የተሻለ አማራጭ መሆኑን ይገልፃሉ።
ማክሰያውም ከበርሜል ተሻሽሎ የተሠራና ብቃት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ወጣቶች በምርምር ውጤቱ እንዲጠቀሙበት ስልጠና ጭምር እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ወጣቶቹ ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ከአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ ተቋማት ብድር ወስደው እንዲያመርቱ ይደረጋል። ለአክሳዮችም ማክሰያውን ሊሸጡ ይችላሉ፤ ህብረተሰቡም በግል በቤቱ መጠቀም ይችላል፤ በእዚህም እንቦጩን እየነቀሉና እየቆለሉ በላዩ ላይ አፈር ከመከመር ማክሰያ ውስጥ በመክተት ብቃት ያለው ከሰል ማዘጋጀትና ዛፎች ለከሰል ሲባል እንዳይቆረጡ ማድረግ ይቻላል። በመሆኑም ከእምቦጭ ክሰል ማዘጋጀት መቻል ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። እምቦጭን ለክሰል – በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ እንደማለት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ