እነ ኒያላና ጓደኞቹ በመወደዳቸው፤ ዋልያና ቤተሰቦቹ አልቀመስ በማለታቸው አኮረፉ አሉ። ሰው የሚወደው ነገር ሲወደድ ደስ ሊለው ነው የሚገባው፤ አይደል? ምን ነካቸው? ሰሞኑን በፀደቀው አዋጅ ምክንያት አኩራፊዎች በዝተዋል ሲሉ ተገረምኩ። የእነ ሀበሻ አድናቂዎች የእነ ግስላ ቲፎዞዎች እንዲያው ምን ነካችሁ? ሰው ወዳጁ ወደላይ ከፍ እንዲልለት በብርቱ ሲመኝ እንዴት የወደዳችሁት ነገር መወደዱን ጠላችሁት ግን?
አኮረፉ ‘ለምን? አሉ’ ሲሉኝ እኔ አላመንኩም ነበር። ግን አመንኩ፤ በቢራ መወደድ ማዘናችሁ፤ በሲጃራ ዋጋ ማሻቀብ ማኩረፋችሁ በገጠመኜ እኔም ታዘብኩ። አቤት ግን ግፋችሁ! ቆይ ስንት ሀገራዊ የሆኑ ውድ ውድ ስሞችን ተሸክመው እንዴት እስከ ዛሬ እንደረከሱ ይገርመኛል። ዋልያ የተሰኘ ብርቅዬ እንስሳችን መጠሪያው አድርጎ፣ ኒያላ የተባለው ተወዳጅ ልዩ ብርቅዬ እንስሳን የፓኮው ስያሜ አድርጎ አራክሶ ሲቸበችም ዝም ያልነው እኮ ስያሜያቸውን አይተን እንጂ ውስጡ ያሉትን ጤናን አቃዋሽ ጉዶችን አክብረን አልነበረም።
ስለጤፍ መወደድ፤ ስለ ኑሮ ጣራ መንካት ግድ ሰጥቶት የማያውቅ ሰው እንዴት ሲርበው በልቶ፤ ጠግቦ ለሚጠጣው ኦክስጂን ሰልችቶኛል ሲጃራ ነው አምሮቴ ብለው ያኮርፋል? በነገራችን ላይ፤ ሱሰኞቹ “እኛን ብቻ ለምን?” በማለት ሲሞግቱ ነበር አሉ። በጫትና ሌሎች ነገሮች ላይም ታክስ ይጨመር፤ ካልሆነ ከሌላው በተለየ የእኛ መብት ተገፋ፤ በደል ተፈጸመብን” በማለት ሲሟገቱ ከረሙ የሚል ጭምጭምታ ሰምተናል።
ስለትውልድ ሲታሰብ፤ የትውልዱን መለወጥ ሀገራዊ ለውጥ መሆኑ ይታመንበታልና ትውልድ ገዳይ፤ ሀገር አጠልሺ የሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ማስቆም፤ አሊያም የሚቀንሱበትን መንገድ ማበጀት ከሀገሬው የሚጠበቅ ነውና ጠቃሚው ተተገበረ። እርግጥ ይህ ሲታሰብ መልካምነቱ የማይካድ፤ ውጤቱም አመርቂነቱ የማይታበይ ሀቅ ነው።
ታዲያ ጠጪዎች ይሄንን ማን ጋረደባቸው? ስለ ሀገሩ የሚያስብ፤ ስለ ትውልዱ የሚጨንቀው እንዴት “እኔ ፍላጎቴን ላስታግስ እንጂ ስለሌላው ምን ገዶኝ” ይላል? ሰው ሀገሩንና ህዝቡን ሊወድድ ለውጡንም ሊመኝ ይገባል። ሀገራዊ ለውጥንና እድገትን የወደደ ደግሞ ስለ ሀገሩ መልካም ያስባልና እንዴት መልካም የሆነ ሀገራዊ ነገር ይጠላል?
እናም ውዶቼ ሀገራዊ ራዕይ ያለው የትውልድን መልካም ፍሬ ማየት የሚወድድ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን የሚያርቅ አዋጅ አይደለም ሊያሳድድ ሊደግፍ ይገባል። ትልቅ ሀገራዊ አላማ ያለው ስለ ለውጥና እድገት በእጅጉ የሚመኝ ሲጃራን “እምቢ” አልኮልን “አይ” ማለት ነው ያለበት፤
አንድ ታወቂና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁንጮ የሆነ አየር መንገድ በደንበኞች አያያዝና በመስተንግዶው ተወዳጅ ስለሆነ ብዙ መንገደኞች ይመርጡት ነበር። አንድ ሰው ከመኖሪያ አካባቢው ወደ ሌላ አገር መሄድ ይፈልግና ይህን አየር መንገድ ይጠቀማል። በአውሮፕላን ውስጥ አስተናጋጆች ደንበኞችን በልዩ ትህትና እያስተናገዱ ወደአንደኛው ሰው ይጠጋሉ። ቀድሞ የጠቀስነው ተጓዥ አጠገብ የደረሰች አንዲት መልከ መልካም አስተናጋጅ፤ ወደሰውዬው ቀርባ በእጇ የያዘችውን መጠጥና ብርጭቆ ታቀርባለች።
የአስተናጋጇ ፍላጎት የደንበኛዋ ጉዞ በፍስሀ እንዲሞላና ሳይሰላች እንዲያሳልፍ ነውና ፈገግታ ተላብሳ አንድ ውድ የአልኮል መጠጥ ከብርጭቆ ጋር አቀረበች። ሰውዬውም እጅግ ትህትና በተሞላበት ሁኔታ ይቅርታ ጠይቆ እንደማይጠጣ ይገልፅላታል። አስተናጋጇ ከዚያ በፊት ይህንን ውድ መጠጥ በፍቅር ይጠጡት የነበሩ ደንበኞቿን እያሰበች በማነፃፀር እየተገረመች ሰውዬውን ትመለከተውና በድጋሚ ጠጋ በማለት “ሌላ አይነት መጠጥ ይሁንልዎ” ብላ ትጠይቀዋልች። ሰውዬው ግን ከአቋሙ ሳነቃነቅ በድጋሚ አለመፈለጉን ይነግራታል።
አስተናጋጇ ደንበኛው በሆነ ጉዳይ ተከፍቶ እንጂ ይህንንማ አያልፈውም ነበር በማለት ለአለቃዋ ሄዳ ስለ ጉዳዩ ትነግረዋለች። አለቃዋም ከርስዋ ይበልጥ በመገረም “በሌላ በሚምያር ብርጭቆና ማራኪ በሆነ መልኩ በድጋሚ አቅርቢለት” በማለት ያዝዛታል አስተናጋጅዋን፤ አደረገችው። ግን የተለወጠ ነገር የለም። ይሄኔ አለቅየው እራሱ ቀርቦ ሰውዬውን ማናገር ይጀምራል።
“ጌታዬ ችግር አለ? መስተንግዶዋችን አልተመ ቸዎትም? ምን እናስተካክል?” እያለ ትህትና የተላበሱ ተከታታይ ጥያቄዎችን ያቀርባል። ሰውዬው ፈገግታ በተሞላበት መንገድ ምላሹን ሰጠ። “አይ መስተንግዶዋችሁም በጣም ጥሩ ነው፤ ነገር ግን እኔ መጠጥ አልጠጣም” ይለዋል። ይሄኔ ኃላፊው ተገርሞ “እንዴ ለምን?” ብሎ ጠየቀው። ለዚህ ምላሽ ግን የሰጠው መልሶ እራሱን በመጠየቅ ነበር። “እስኪ ለኔ ልትሰጠኝ ካሰብከው ፊት ለፊት ባለው በር ከፍተህ ግባና ለፓይለቱ ስጠው በኔ ፋንታ ይጠጣ” ብሎ ጠቆመው።
ይሄኔ ኃላፊው “እንዴ! እሱማ እንዴት ይጠጣል? ይሄን ማደረግማ አይችልም የስንት ሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። ስለዚህ እሱ የመጠጥ ሽታም ሊደርስበት አይገባም።” በማለት ፓይለቱ በመጠጣቱ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ዘረዘረ። ተጓዡም የሚፈልገው እንዲህ እንዲለው ነበርና በመልሱ ላይ የራሱን አስተያየት በማከል የማይጠጣበት ምክንያት ተናገረ። “ወዳጄ እኔ የራሴ የሆነ ልዩ ዓላማ አለኝ አላማዬን ከስኬቱ እንዳደርስ ጥንቁቅ መሆን አለብኝና “ፈፅሞ አልጠጣም” ያልኩት ለዚህ ነው። በማለት መለሰለት።
እናም ዓላማ ያለው፤ እሩቅ መጓዝ ያሰበ እርግጥም እራሱን ሆኖ የትኛውም ቦታ ይደርሳል። ሰሞኑን የወጣውን የኤክሳይዝ ታክስ ተከትሎ በመጠጥና በዘር ማንዘሮቹ፤ በሲጃራና በግብረ አበሮቹ ላይ የተደረገውን የታክስ ጭማሪ ጥቅም በትክክል ከተረዳን ጠጪዎችንና አጫሾችን ቢያስከፋም እነሱኑ የሚያድን መራራ መርፌ ነው። እናም በደንብ መውጋት/መወጋት ነው። ኧረ እንዲያውም ከፍ አድርጎ። ቸር ይግጠመን!
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2012
ተገኝ ብሩ