ገጣሚና ሐያሲ ሰለሞን ደሬሳ በአንድ ወቅት “አንዳንድ ጥያቄ አለ፤ አስር ጊዜ ተጠይቆ፣ አስር ጊዜ መልስ አግኝቶ፣ ዳግመኛ አስር ጊዜ የሚጠየቅ “እንዳለው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ጥያቄ እንዲሁ አስር ጊዜ የሚጠየቅ ሆኖ ሁለት አስርተ ዓመታትን ዘልቋል። የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት (1987) በመግቢያው ላይ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡-›› ብሎ ይጀምራል። ይቀጥልናም በአንቀጽ 8 “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዐላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ይሆናሉ” ይላል። ግን ሕገመንግሥቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 25 ዓመታት ማንነው ብሔር፣ ማንነው ብሔረሰብ፣ ማንነው ሕዝብ የሚለው ግልጽ በሆነ መንገድ ትርጉም አልተቀመጠለትም። እናም ማንም በመሰለው መልክ ብሔር ብሔረሰቦችን ሰይሞ እንዲጠሩ ሕገመንግሥቱ ዕድል ይሰጣል። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኦሮሞ እና የአማራ ጉዳይ እንመልከት። አንዳንዱ ኦሮሞን ብሔር (የኦሮሞ ብሔር) ብሎ ይጠራል፤ ሌላኛው ብሔረሰብ (የኦሮሞ ብሔረሰብ) ይላል። አንዳንዱ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ብሎ ይጠራዋል። የአማራም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በአንድ ወቅት ያቀረቡት ጹሑፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሆን የሚችል ቁምነገር አለው።
“ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ፣ ነገድ” ይላል። “እነዚህን ቃላት እንድተች ብዙ ጊዜ እጠየቃለሁ። ብዙዎችን የሚገድ ጥያቄ ስላልመሰለኝ ጥያቄውን ችላ ብየው ነበር። የማይገዳቸው ላያነቡት ይችላሉ ብዬ ከዚህ በታች ያለውን አረቀቅሁ። ረቂቁ ሙሉ በሙሉ ጥንታዊ (original) አይደለም። ካሁን በፊት ከጻፍኳቸው ውስጥ “የተኮረጁ” አሉበት።
“ብሔር” የግዕዝ ቃል ነው። ትርጉሙ “ሰው የሚኖርበት ሀገር” ማለት ነው። “እገሌ ዘብሔረ ቡልጋ፥ ዘብሔረ ጅማ፥ ዘብሔረ ሸዋ፥ ዘብሔረ ኢትዮጵያ፥ . . .” ይባላል። (“እግዚአ ብሔር” ማለት “የመላዋ ምድር ጌታ” ማለት ነው።) ፖለቲከኞች የሚጠቀሙበት ግን “ትንሽ ጎሳ” ለማለት ነው። ስሕተት ነው። ብሔር የሚያመለክተው ምድሩን (ቀየውን) እንጂ፥ በምድሩ ላይ የሰፈረውን ሰው አይደለም። ግን አጉል ልማድ ሆኖ ተለምዷል።
“ብሔረሰብ” የሚለው “ብሔር” እና “እሰብ [እ]” ተናብበው የተፈጠረ ቃል ነው። “ብሔር” ያው እንዳልኩት “ሀገር፥ ምድር፥ ቀየ” ማለት ነው። “ሰብ [እ]” በግዕዝ “ሰው” ማለት ነው። “እ” ወድቃ ቃሉ “ሰብ“ ሆኗል። “ቤተሰብ” (የአንድ ቤት ሰው) የሚለውን ቃል እናውቃለን። በዚያው ዘዴ፥ “በአንድ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች” ለማለት “ብሔረሰብ” የሚለውን ቃል ፈጠሩ። የብልጥ ፈጠራ ነው።
“ጎሳ” የኦሮሞ ቃል ነው። ትናንሽ ነገዶች ጎሳ ይባላሉ። የኦሮሞና የሱማሌ ሕዝብ የብዙ ጎሳዎች ስብስብ ናቸው። ነገድ ከጎሳ ይበልጣል። አማራ፥ ትግሬ ነገድ ናቸው። ቦረን እና በረይቱማ ራሳቸውን የቻሉ ነገዶች ነበሩ። ጎሳና ነገድ በባህል አንድ ዓይነት ሕዝብ ነው። አንድ የሚያደርጋቸው ባህል ሆኖ ሳለ፥ ፖለቲከኞች የሥጋም ያደርጉታል።
“ሕዝብ” የሰው ስብስብ ማለት ነው። አንድ ዓይነት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ገበያ ላይ የምናየው፥ ንግግር ለመስማት የሚመጣው ሕዝብ ያሰባሰባቸው ዝምድና አይደለም። ገበያው ሲፈታ፥ ንግግሩ ሲያልቅ ሕዝቡ ይበተናል። “የእገሌ ነገድ አባል ነኝ” ማለት ይቻላል። “የሐሙስ ገበያ ገበያተኞች አባል ነኝ” አይባልም። “የእገሌ ንግግር ሰሚዎች አባል ነኝ” አይባልም።
“ብሔር፥ ብሔረሰብ” የሚሉት ስሞች የወጡት “Nations and Nationalities” የሚለውን ለመተርጐም ነው። ግን መጀመሪያ በመተርጐም ምክንያት የተፈጸሙትን ሁለት ታላላቅ ስሕተቶች ማረም ያስፈልጋል። አንደኛ፥ አንድ የውጪ ቃል ወይም ስም የሚተረጐመው፥ አንድ እቃ ወይም አንድ ፅንሰ-ሐሳብ ከነስሙ ከውጪ ሲመጣ ነው እንጂ፥ እኛ ዘንድ ላለ ነገር አይደለም። ለምሳሌ፥ “ወምበር” ከነስሙ እኛ ዘንድ ካለ፥ “chair” ለሚለው ስም መተርጐሚያ ቃል ፈልጉ አይባልም። “ነገዶችና ጎሳዎች” ነገዶችና ጎሳዎች ከመባል ይልቅ “Nations and Nationalities” እንበላቸው ማለት ሳይቸግር ጤፍ ብድር ይሆናል።
ሁለተኛ፥ ነገዶችና ጎሳዎች በ“Nations and Nationalities” መተርጐም ሳይቸግር ጤፍ ብድር ብቻ ሳይሆን፥ “Nations and Nationalities” ላይ የሰፈረውን ጣጣ አብሮ ማምጣት ይሆናል። ያ ጣጣ እኮ ነው መፍትሔ ጠፍቶለት ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ በተወያየን ቁጥር ስናገላብጠው የምንኖረው። “Nations and Nationalities” እዚያው ሀገራቸው መንግሥት አላቸው (ወይም ነበራቸው)።
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ነገዶች ከኢትዮጵያ ውጪ መንግሥት ያቋቋሙበት ዘመን አልነበረም። ኖሯቸው ከሆነ፥ በዘመነ መሳፍንት ሸዋ፥ ጐጃም፥ ትግሬ፥ ወሎ፥ አደል (አዳል) ውስጥ እንደተቋቋሙት አናሳ መንግሥታት ቢሆን ነው። ግራኝ ያመፀው እኮ “አልገብርም፥ በክርስቲያን ንጉሥ ስር ያለች አናሳ አገር ኢማም መሆን ያንሰኛል” ብሎ ነው እንጂ፥ ከቀይ ባሕር እስከ ህንድ ውቅያኖስ የተንሳፈፈውና የነገሠባት የአዳል ሀገር የኢትዮጵያ ግዛት አይደለም ብሎ አይደለም።…”
ውብሸት ሙላት የተባሉ ጸሐፊ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ “የብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ተዋረዳዊ ትርጉምና ሕገ መንግሥት ወጥነት” በሚል ያሰፈሩት ሐተታ ለዚህ ጹሑፍ ጥሩ ግብዐት ይሆናል።
‹‹ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ›› ሦስት ቃላት እንጂ አንድ ትርጉም ብቻ ያለው ሐረግ አይመስሉም። ይህንን በትክክል ለመረዳት በሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች የተዘጋጀውን አጭር ማብራሪያ ማየቱ በቂ ነው። በማብራሪያው ላይ ‹‹በ’ብሔር’ ‘ብሔረሰብ’ና ‘ሕዝብ’ መካከል የመጠንና የስፋት ልዩነት ያለ ቢሆንም…›› ይላል። ልዩነታቸውን በማብራሪያው ላይ ባይዘረዝርም በደፈናው ‹‹የመጠንና ስፋት›› ልዩነት እንዳላቸው አስቀምጧል። በምሳሌነትም በአማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩትን በተመለከተ ‹‹አማራን ብሔር››፣ ‹‹አገውን ብሔረሰብ›› እንዲሁም ‹‹ኦሮሞን ሕዝብ›› በማለት በአንቀጹ ማብራሪያ ላይ በመግለጽ በሦስቱ መካከል የመጠንና የስፋት ልዩነት እንዳላቸው ይጠቁማል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን በጠቅላላው እንደ ምሳሌ ‹‹ኦሮሞን ብሔር››፣ ‹‹አፋርን ብሔረሰብ››፣ ‹‹ኮሎን ሕዝብ›› በማለትም ማሳያውን ያጠናክራል።
ከላይ ከተገለጸው የምንረዳው፣ መጠንና ስፋትን መሠረት ያደረገ በሦስቱ መካከል ልዩነት መኖሩን ከግንዛቤ በማስገባት ይመስላል ሕገ መንግሥቱ ላይ የተገለጹት። በመቀጠል ‹‹መጠንና ስፋት›› የሚሉት ምንን እንደሚያመለክቱና ሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦችን መለየት የሚያስችሉ ነጥቦችን እናያለን። በእርግጥ በሦስቱም መካከል መብታቸውን ተግባራዊ በማድረግ ላይ በሕግ የተቀመጠ ልዩነት እንደሌለ ከማብራሪያውም ከራሱ ከሕገ መንግሥቱም መረዳት ይቻላል። ነገር ግን በተግባር ሲታይ ልዩነት ያለው ስለሚመስል ልዩነታቸውን እናያለን።
በሕገ መንግሥቱ ለሦስቱም አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ተሰጥቷቸዋል። ይኸውም፡- ‹‹ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚምኑና የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፣›› ይላል።
በክልል ሕገ መንግሥቶችም ቢሆን የተሰጠው ትርጉም ተመሳሳይ ነው። በተወሰኑት የክልል ሕገ መንግሥቶች ላይ ትርጉም የተሰጠው በአጠቃላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማለት ሳይሆን የብሔሩን ስም በመግለጽ ነው። ከዚህ ውጪ የአተረጓጎም ልዩነት አይታይባቸውም።
ከላይ ከተገለጸው ትርጉም በመነሳት ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ ለመባል አምስት መሥፈርቶች መሟላት እንዳለባቸው እንረዳለን። እነዚህም፡- ተመሳሳይ ባህል ወይም ልምዶች፣ መግባቢያ ቋንቋ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና፣ የሥነ ልቦና አንድነትና በአንድ በተያያዘ አካባቢ መኖር ናቸው።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ለብሔርነት ወይም ብሔረሰብነት ወይንም ሕዝብነት ጥያቄ የሚያቀርብ ቡድን ከላይ የተገለጹትን ማሟላት አለበት ማለት ነው። ከላይ ከተዘረዘሩት መሥፈርቶች መካከል ሦስቱ ለመለካት አስቸጋሪ ቢሆኑም የጋራ የሚያግባባቸው ቋንቋ መኖሩንና ተያያዥነት ባለው አካባቢ የሚኖሩ መሆኑን መለየት አስቸጋሪ አይደለም።
በፍቃዱ ኃይሉ በአንድ ወቅት በመንግሥት ታግዶ በነበረው የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ‹ሕዝብ›› ምንድን ነው? በሚል ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
“በክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሙሴ ታሪክ ትልቅ ሥፍራ ይሰጠዋል። ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፆች ቅኝ ተገዢነት ነፃ ያወጣ መሲህ ነው። ይሁን እንጂ ሕዝቡ በሙሴ ላይ ያፈነግጥ እንደነበር ዘጸአት፣ ምዕራፍ 32 (ቁጥር 1 – 4) ይተርክልናል፡-
“ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት። አሮንም፣ በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው።”
በ1997 ተቃዋሚዎችን የመረጠ ሕዝብ በ2002 ገዢውን ፓርቲ ይመርጣል፣ በ2008 ለኦባማ ራሱን የሳተ ሕዝብ በ2012 ለራምኒ ይዘምራል። ይህ ሕዝብ ምን ዓይነት ፍቺ ይገኝለታል? በዚያው በምርጫ 97 ሚያዝያ 29 ኢሕአዴግን በመደገፍ ‹‹ማዕበል›› ለመሰኘት የበቃ ሕዝብ መስቀል አደባባይ ወጣ፤ በማግስቱ ሚያዝያ 30 ከዋዜማው እጥፍ የበዛ (‹‹ሱናሚ›› የተሰኘ) ሕዝብ ወጣ፤ የቱ ነው ሕዝብን በትክክል የሚገልፀው?
ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ሕዝብ›› የሚለውን ቃል ሲፈታው ‹‹በአንድ አገር፣ ከተማ፣ ክልል፣ ገጠር ውስጥ የሚኖር ጠቅላላ የሰዎች ቁጥር፣ ብዛት›› ይለዋል። በርግጥ ይህ መዝገበ ቃላት እንደሚለው ‹‹ሕዝብ›› ቁጥር ብቻ ነው ወይስ ሌላ ትርጉም ይኖረው ይሆን? በየፈርጁ እንመለከተዋለን።
የኢፌዲሪ ሕገመንግስት (1987) በመግቢያው ላይ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡-›› ብሎ ይጀምራል። አካሔዱ ከላይ – ሁሉንም ብሐሮች ካቀፈው ስብስብ (set) ወደታች – ነጠላ ብሔር/ብሔረሰብ (subset) ስለሚወርድ ‹‹ሕዝቦች›› የሚለውን ‹‹የተለያየ የዘር ሐረግ ያላቸው ሰዎች ስብስብ›› ብለን ልንፈታው እንድንዳዳ ያደርገናል። ግን ደግሞ የአገር ውስጥ ፖለቲካ ዕውቀታችንን ስናስታውስ ሕዝቦች የሚባሉት የብሔር ዕውቅና ያላገኙ፣ የአንድ ቋንቋ እና ባሕል ባለቤቶች ናቸው። ይሄ ትርጉም የትም ስለማያደርሰን ሌላ የ‹‹ሕዝብ›› ትርጓሜ ፍለጋ እንጓዛለን።
የሕገመንግስቱ ፈጣሪ ኢሕአዴግ ነውና፣ በግንባሩ ስያሜ ውስጥ ያለው ሕዝቦች ማንን እንደሚወክል እንጠይቅ። ግንባሩ የብሔር ፓርቲዎች ስብስብ ስለሆነ ብዙ ብሔሮችን በአንድነት ‹‹ሕዝቦች›› ብሏል ስንል ደግሞ እላይ ከደረስንበት ድምዳሜ የተለየ ትርጉም እናገኛለን።
ሕዝብ በቁጥር፤ ነገሩን በምሳሌ እንጀምረው፤ ‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሕአዴግን መረጠ›› ሲባል ምን ማለት ነው? በ2000ው የሕዝብ ቆጠራ መሰረት ከ1.88 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፖለቲካዊ ምርጫ ለመምረጥ ዕድሜያቸው ይፈቅድላቸዋል። ነገር ግን ድምጻቸውን የሰጡት 1.04 ሚሊዮን ያክሉ ብቻ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 0.56 ሚሊዮኖቹ ብቻ ናቸው ለኢሕአዴግ ድምጻቸውን የሰጡት (ማለትም ዕድሜያቸው ከደረሱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አንፃር 30 በመቶ ያክሉ ብቻ)። ነገር ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ ኢሕአዴግን መረጠ ይባላል፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት መሪር ሐዘን አዘነ፣ መተኪያ እንደሌላቸውም ተናገረ›› ሲባልስ የትኛውን ሕዝብ ነው? ስንት ያክሉን ሕዝብ ነው?” ሲል በፍቃዱ ይጠይቃል።
እንደመቋጫ
በ1987 የወጣው የኢፌዲሪ ሕገመንግሥት ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዝርዝር ማንነታቸውን ተርጉሞ ከመግለጽ ይልቅ ለሁሉም እኩል ዕውቅና በመስጠት አልፏቸዋል። አንዳንዶች የኢትዮጵያ ሕዝብን ብሔር ብሔረሰብ በሚል ልዩነትን አጉልቶ ያስቀመጠ ሕገመንግሥት ነው በሚል የሚነቅፉበት አጋጣሚዎች የትየለሌ ናቸው። የሕገመንግሥቱ ሁኔታ ሰለሞን ደሬሳ እንዳለው በየጊዜው እየተጠየቀ፣ በየጊዜው እየተመለሰ እንደገና የሚነሳ ጥያቄን ፈጥሯል ብዬ አስባለሁ። ምናልባት ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ ሊካሄድ የሚችልበት ዕድል ከተፈጠረ ይህም አሻሚ ሁኔታ መልስ ያገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
abebeferew@gmail.com
ፍሬው አበበ