የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከየካቲት 5 እስከ የካቲት 7 ቀን 2012 ዓ.ም በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በሀገራቱ በህገወጥ መንገድ ገብተው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አስፈላጊው የጉዞ ሰነድ ስለሌላቸው ለመውጣት የተቸገሩና ጉዳትም የደረሰባቸው ዜጎች መኖራቸውን ከኢትዮጵያ የኮሚዩኒቲ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት አረጋግጠው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሀመድ ቢን ረሺድ አልመክቱም ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ያሉባቸውን ችግሮች የገለፁላቸው ሲሆን ሼክ መሀመድም ችግሮችን ከባለስልጣኖቻቸው ጋር ተነጋግረው እንደሚፈቱ ቃል ገብተዋል።
የዚህ እርምጃ አንዱ አካል የሆነውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ አስፈላጊ የጉዞ ሰነድ የሌላቸውና ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን ይዘው እንዲመለሱ የማድረጉ ውሳኔ ነበር። በዚህም መሰረት እሁድ የካቲት 8/2012 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 135 ኢትዮጵያውያንን ይዘው አዲስ አበባ ገብተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉብኝት ጉዞ የተካተተው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ከተመላሾቹ ጋር ቃለምልልስ አድርጎ ነበር። ተመላሾቹ ሁሉም በህገወጥ መንገድ በደላላ ተጉዘው የነበሩ ሲሆኑ የገጠማቸውን ችግር እና የደረሰባቸውን ጉዳት ለሌሎች ትምህርት ይሆን ዘንድ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ !
ዝናሽ ንጉሴ ትባላለች ተወልዳ ያደገችው አርሲ አሰላ ነው። ከዛሬ ሶስት አመት በፊት የስደት መንገድን ስትመርጥ የምትሄድበት ቦታ በምቾት የሚያኖራት እና ህይወቷ ተደላድሎ የእርሷንም ሆነ የቤተሰቦቿን ኑሮ ለመቀየር በማለም አስባ እንደነበር ታስታውሳለች።
ዝናሽ እንደምትለው ከእርሷ በፊት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በህገወጥ መንገድ ገብተው ስቃይና እንግልት የደረሰባቸው የአካባቢዋ ልጆች የስደትን አስከፊነት ሲነግሯት ችላ ያለችው በደላላ የተነገራትን አማለይ ማታለያ በውስጧ ይዛ የነገን የተሻለ ህይወት በማሰብ ነበር።
በመጀመሪያ ያቀናችው ወደ ቤይሩት ሲሆን በዛም ለአራት ወራት ያህል አንድ ሺህ ሪያል እየተከፈላት ብትሰራም የሚከፈላት ክፍያ ግን አብሯት መዝለቅና ያሰበቸውን ህልም ማሳካት አልቻለም። ዝናሽ ለስድስት ወራት ያለደመወዝ በነፃ ከመስራት ጀምሮ በርካታ የስቃይ ጊዜን አሳልፋለች። ደመወዝ እንዲከፈላት ጥያቄ ስታቀርብ የተሰጣት መልስ ደግሞ “ እኛ ስራ ስለሌለንና በልጃችን ድጎማ ስለምንኖር የምንከፍልሽ ነገር የለም” የሚል ነበር።
የቤይሩት የመከራ ጊዜ ያበቃ ዘንድ በመሻት የተሻለ ስራ ፍለጋ ዝናሽ ከአሰሪዎቿ ተደብቃ በመጥፋት ጉዞዋን ወደ ዱባይ አድርጋ አንድ አመት ከስድስት ወራት በዛው አሳልፋለች። በአረብ ሀገራት በህገወጥ መንገድ ገብተው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ስቃይ የበረታ እንደሆነ የምትናገረው ዝናሽ በዱባይም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟታል።
ዝናሽ ምንም እንኳን ህይወት ምርር ቢላት ከሀገሯ የወጣችበትን ቀን እና እድሏን እየረገመች ሌላ የስቃይ ጊዜን በዱባይ ማሳለፍ እንደጀመረች ትናገራለች። ለስራ የገባችባቸው ሰዎች ህገወጥ መሆኗን ስላወቁ ከስራ ጫና ጀምሮ ደመወዝ እስከመከልከል ደርሰው ምሬቷን አብዝተውባታል። የገባችው በህገወጥ መንገድ በመሆኑ ወደ ሀገሯ መመለስ አትችልም፤ በነፃነት ሰርታ መኖር፣ ችግር ሲገጥማት ለህግ አካላት ማሳወቅም ለዝናሽ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው።
ኑሮን እንዲህ እየገፋች ሳለ የካቲት 7/2012 ዓ.ም ስልኳን አንስታ ወደ ግል የፌስቡክ ገጿ ስትገባ ያየችው መልዕክት ዝናሽን አስደንግጦ የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ከቷታል። ደስታና እንባ እየተናነቃት እንዲህ የሚል ፅሁፍ ማየቷን ትናገራለች፡- “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የመካከለኛው ምስራቅ ጉዟቸውን አጠናቀው ነገ ወደ ሀገራቸው ስለሚመለሱ በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገራቱ ገብታችሁ የጉዞ ሰነድ የሌላችሁና ሀገራችሁ መመለስ የምትፈልጉ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መመለስ ስለምትችሉ በአካባቢያችሁ ባለ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ተመዝገቡ” የሚል ነበር።
ዝናሽ ወዲያውኑ ወደ ቆንስላ በመሄድ ምዝገባዋን ካከናወነች በኋላ በቀጥታ ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ኤምባሲ አቅንታ አዳሯን በዚያው በማድረግ እሁድ የካቲት 8/2012 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ከ135 ኢትዮጵያውያን አንዷ በመሆን አዲስ አበባ ገብታለች።
“ በቆይታየ ከሀገር የመውጣትን ቀላልነትና ወደ ሀገር ለመመለስ የሚደረግ ትግልን ፈታኝነት ተረዳሁበት” የምትለው ዝናሽ፤ ዛሬ ላይ ያኔ የስደት ህይወትን አልማ ልቧ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲኮበልል የመከሯትን ጓደኞቿን እያመሰገነች የእርሷ የህይወት ውጣ ውረድ ለሌሎች እህቶቿ መማሪያ ይሆን ዘንድ “ እባካችሁ ህገወጥ ጉዞ በወጣትነት ዘመኔ ብዙ ስቃይ እንዳይ አድርጎኛልና ይህንን መንገድ ፈፅማችሁ አትሞክሩት” ትላለች።
“በሀገራችን ጠንክረን ብንሰራ የተሻለ ኑሮ መኖር እንችላለን” የምትለው ዝናሽ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ በርትተው በመስራት ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን እንዲቀይሩ ጥሪዋን አስተላልፋለች።
ሌላኛዋ ወጣት ጥሩነሽ ሞሼ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ነው። ጥሩነሽ ከአራት አመት በፊት ነበር በደላላ አማካኝነት ወደ ዱባይ በህገወጥ መንገድ የገባቸው። ጥሩነሽ ስራ በጀመረችበት ቤት ውስጥ ለአንድ አመት ያህል ብትሰራም የሚደርስባት ስቃይ ስለበረታባት ጥላ ለመጥፋት በመወሰን መዳረሻን ወደ ሌላ ቤት እንዳደረገች ትናገራለች።
ጥሩነሽ ሌላው ስራ የጀመረችበት የሀበሻ ቤት ውስጥ በስራ ላይ እያለች ባጋጠማት የመውደቅ አደጋ እጅጉን ተጎድታ የዲስክ መንሸራተት አደጋ ደረሰባት። ይሁን እንጂ በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ለማግኘት ህጋዊ ሰነድ ስለሌላት ህክምናዋን መከታተል አልቻለችም። አንድ አመት በዚሁ ቤት ብትሰራም ህመሟ እየባሰባት በመምጣቱ ምክንያት ስራዋን ለማቆም ተገደደች።
ከዚያም በኋላ በተለያዩ ቤቶች ውስጥ በመቀጠር ለመስራት ያደረገቸው ሙከራ አንዴ ሲሳካ ሌላ ጊዜ ተመልሶ ሲበላሽባት ቆይታለች። 600 ድርሀም ከፍላ ቪዛዋን ለማሳደስ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካላት እንደቀረ የተናገረቸው ጥሩነሽ ለአንድ ወር እና በሌላም ጊዜ ለሶስት ቀናት ያህል በእስር ቤት ማሳለፏን እንባ እየተናነቃት ትናገራለች። 1000 ድርሀም ከፍላ ከእስር ብትለቀቅም በእስር ቤት ቆይታዋ ፈታኝ ጊዜ ማሳለፏን ትናገራለች።
ጥሩነሽ ወደ አቡዳቢ ከሄደች በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የመመለስ ዜና ስትሰማ እጅግ በመደሰት ወደ ሀገሯ ለመመለስ ወሰነች። ምዝገባዋን ካከናወነች በኋላ ዛሬም ከዲስክ መንሸራተት ህመሟ ጋር ወደ ሀገሯ ተመልሳለች። ጥሩነሽ በሀገሯ ህክምናዋን አግኝታ በሀገሯ ሰርታ የመቀየር ህልም እንዳላት ትናገራለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለዚህ ቀን እንድትደርስ ስላደረጉ ምስጋናዋን ያቀረበችው ጥሩነሽ “በህገወጥ ስደት ያተረፍሁት ህመም ብቻ ነውና እህት ወንድሞቼ ከእኔ ህይወት ተማሩ” ስትል ምክሯን አስተላልፋለች።
አዚዛ ይማም ሁለት ልጆቿን እናቷ እና ባለቤቷ ጋር ጥላ በህገወጥ መንገድ በደላላ አማካኝነት ከኢትዮጵያ ከወጣች በኋላ በአቡዳቢ አራት አመት ከስድስት ወራትን በስራ ብታሳልፍም ጊዜዋ ያለቀው ከአንዱ ቤት አንዱ ቤት በእነሱ አጠራር በ “Run Away” ነት በመስራት ነው ።
በ2019 እኤአ ቪዛዋ ቢታደስላትም ከአሰሪዋ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሰውየው ቪዛዋ እንዲሰረዝ ማድረጉንና ከሀገር እንዳትወጣ እንዳሳገዳት ገልፃለች። አሰሪዎቿ በተደጋጋሚ በደል ሲያደርሱባት እንደነበር የምትናገረው አዚዛ ደመወዝዋን ካለመክፈል ጀምሮ ማንገራገርና ከቤት ማባረር እንዳደረሱባት አስረድታለች።
ምሬትና ስቃይ እንዲሁም ከአንዱ ቤት ሌላው ቤት በድብቅ የመዘዋወር ህይወት ያሰለቻት አዚዛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ሀገራቸው መግባት የሚፈልጉ ዜጎችን ይዘው እንደሚሄዱ ስትሰማ የወሰነችው ውሳኔ “ ሕይወቴን ብቻ ይዤ ሀገሬ ልግባ” የሚል ነበር። በዚህም ማቄን ጨርቄን ሳትል ምዝገባዋን በመጨረስ ለሀገሯ በቅታለች።
አዚዛ የኢትዮጵያን ምድር ስትረግጥ እንባ እየተናነቃት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ያመሰገነች ሲሆን፤ በዚህ የህገወጥ ጉዞ ለመሄድ የሚያስቡ ኢትዮጵያውያን ፈፅሞ ከዚህ አይነቱ አማራጭ ራሳቸውን ሊያርቁ እንደሚገባ መክራለች።
ኢትዮጵያውያን ህገወጥ ደላሎችም ለጊዜያዊ የገንዘብ ጥቅም ብለው እህት ወንድሞችን በዚህ ሁኔታ ከሀገር ማስወጣቱን የስቃይ ኑሮን እንዲገፉ ማድረግ እዚህ ላይ ሊያበቃ ይገባል። ህሊና ላለው ሰው ይህንን መሰሉን ድርጊት መፈፀም አይደለም ሲፈፀም አጥብቆ መታገልና ነገ ከእኔ ቤተሰብ በአንዷ/በአንዱ ላይ ሊደርስ ይችላል ብሎ ማሰብ እንዳለበት አዚዛ ተናግራለች።
መንግስትም ቢሆን ይህንን ድርጊት መቆጣጠርና አጥፊዎችን በህግ መጠየቅ ይኖርበታል፤ ህብረተሰቡም መንግስት ለሚሰራው የክትትልና ቁጥጥር ስራ አጋዥ በመሆን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አዚዛ ይማም መልዕክቴ ይድረስ ስትል አስተላልፋለች።
“ሁሉም በሀገር ያምራል” ያለችው አዚዛ ከስደት መልስ በሀገሯ በምትሰማራበት የስራ መስክ ጠንክራ በመስራት የልጆቿንና ቤተሰቦቿን ህይወት ለመቀየር መወሰኗንና ስራ ሳትመርጥ በመስራት በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ ከሆኑት ጠንካራ ሴቶች አንዷ ለመሆን ጥረት እንደምታደርግ ተናግራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከዚህ በፊትም ለስራ በተንቀሳቀሱባቸው የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ሀገራት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን በራሳቸው አውሮፕላን አሳፍረው ለሀገር ማብቃታቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 13/2012
ድልነሳ ምንውየለት