ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ የላቀ ስፍራ የሚሰጠው ነው።በዚህ ዘመንም ከነበሩ የአገሪቱ ነገስታት መካከል አፄ ቴዎድሮስ የውጭ ስልጣኔ ማርኳቸው ለአገራቸው ለማቋደስ በጓጉበት ወቅት ከምዕራብ አውሮፓ አገራት ጋር ጠንከር ያለ ግንኙነትን ሲመሰርቱ፤ በአፄ ምኒሊክ የንግስና ዘመን ደግሞ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተከናውነው ኢትዮጵያም አብዛኛዎቹን የአውሮፓ አገራት መድረስ የቻለችበት ወቅት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ርምጃ ዘመናዊነትን ተላብሶና ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሮ አገሪቱን በቋሚነት የሚወክሉ ዲፕሎማቶችን በመሾም በታሪክ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል።የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ዋናው ዓላማ በአገር ውስጥ በሚሠራው ሥራ ላይ እንዲሆን፣ ኢኮኖሚውን ማዕከል እንዲያደርግ፣ በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ ከውጭ የሚገኙ ጥቅሞችን አሟጦ መጠቀምና አደጋዎችን መቀነስ እንደሚገባ፣ ብቃት ያለው የመከላከያ አቅምና ጠንካራ የማስፈፀም ብቃት መገንባት እንደሚያስፈልግ በግልጽ በማስቀመጥ ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመለከት ጤናማ የውጭ ግንኙነት ፖለሲ በማዘጋጀት በእስካሁን ሂደቱ ውጤታማነቱን አስመስክሯል። በተለይም ደግሞ ለዜጎች ክብር የተለየ ትኩረት ይሰጣል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማስፈንና አህጉራዊ ትስስርን ለመፍጠር በምታደርገው እንቅስቃሴ ከኃያላን አገራት ትኩረትን አግኝታለች።ለዚህም ነው ታላላቅ የአገራት መሪዎች አዘውትረው በመጎብኘት መንግሥት የያዘውን ለውጥ በመደገፍና ከፍተኛ ዕርዳታ በማድረግ ላይ የሚገኙት።
ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ኢትዮጵያን የጎበኙ አገራት ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ለዲፕሎማሲው ስኬታማነት ዋቢ ናቸው።ከእነዚህም መካከል የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት ቤንጃሚን ኔታንያሁ፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞጌሬኒ፣ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ፣ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዎን የመሳሰሉ ይጠቀሳሉ።
አፍሪካ በመልክአ ምድራዊና ጆኦ-ፖለቲካዊ የስትራቴጂ ምክንያቶች ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲና የጸጥታ ተለዋዋጭነት ያለው፣ የሃያላኑ ጣልቃ ገብነት የሚስተዋልበት፣ ተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው፣ ሽብርተኝነትና የባህር ላይ ውንብድና የተስፋፋበት፣ ብዝሃነት መለያው የሆነ፣ አያሌ ቁጥር ያለው ስደተኛና ተፈናቃዮች የሚወጡበትና የሚገቡበት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት በማያቋርጥ ሁኔታ ለዘመናት ሲካሄድበት የኖረ የአለማችን ክፍል ነው።
ኢትዮጵያ በዚሁ ያልተረጋጋ አካባቢ የምትኖር ነገር ግን የሰላም እና መረጋጋት ደሴት ተብላ በቀጠናው ተንታኞች የምትታወቅ አገር ናት። ባለፉት ዓመታት የልማትና የዕድገት ጎዳናን ቅድሚያ በሰጠ ስትራተጂ፣ በአካባቢዋ ከሚገኙ ጎረቤት አገራት ጋር በሰላምና በመተጋገዝ ላይ በተመሰረተ የውጭ ግንኙነት ላይ በማተኮሯ፣ በጦርነት ለተፈናቀሉ የማናቸውም አገር ዜጎች መጠለያ በመሆኗ፣ በአገራት መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን በድርድር እልባት እንዲያገኝ የበኩሏን ድርሻ በማበርከቷ በርካታ አገራት ያላቸውን አድናቆት ከመግለጽ ባለፈ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ በኩል ይበል የሚያሰኝ ተግባር ፈጽመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚፈትኑ ቀጣናዊና አለም አቀፋዊ ክስተቶች ባሉበት አካባቢ ተገኝታ የክስተቶቹ ተጋሪ ብትሆንም ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሳል የዲፕሎማሲ ክንውኖችን ስታደርግ ኖራለች። ይህ በሳል የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ አገሪቷ በቀውስ ውስጥ ባለ ቀጠና ውስጥ የመረጋጋትና የሰላም ደሴት እንድትሰኝ አድርጓታል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በመልካም ጉርብትና፣ ሰጥቶ በመቀበል፣ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት፣ የጋራ ደህንነትና ሌሎች የዓለም አቀፍ ግንኙነት ወርቃማ መርሆች እየተመራ የኃያላን አገራትን ትኩረት መሳቡ በቀጣናው ሊሰፍን ከሚፈለገው ሰላም፣ ለዕድገትና ለብልጽግና ጉዞ ተጨማሪ ጉልበት ስለሚሆንና የመሪዎቹ ተከታታይ ጉብኝት የመልካሙ የዲፕሎማሲ ውጤት ማሳያ በመሆኑ ይህንኑ አጠናከሮ መቀጠል ለአፍታም ቢሆን ቸል መባል ያለበት አይሆንም!
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2012