ማንኛውም ኃላፊና የህዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ መደንገጉ ይታወቃል፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው የቱንም ያህል በአገሪቱ ካሉት የስልጣን እርከኖች ውስጥ ከፍተኛ የሚባለው ላይ ተሹሞ የተቀመጠ ቢሆንም ሲያጠፋ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ አመላካች ድንጋጌ ነው፡፡ ከሰሞኑም በአገራችን የታየው እውነታም ይኸው ሲሆን፣ በተለይ በሙስና ወንጀልና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉና ሌሎችም ተይዘው በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግም እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪዎች ከመያዛቸው አስቀድሞ ወንጀሉን ስለመፈጸም አለመፈጸማቸው ለማጣራት የአምስት ወር ጊዜ ፈጅቶበታል፡፡ አስቀድሞ ወደ ማጣራቱ ስራ የመግባቱም ምስጢር ከዚህ ቀደም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የስልጣን መንበራቸውን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ሰዎች ከመታሰራቸው በፊት ተጠርጣሪ ሊያደርጋቸው የሚያስችል ማስረጃዎችንና መረጃዎችን ማግኘት የግድ እንደሚል በመናገራቸው ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ቃላቸው ተጠብቆ ሰሞኑን የተያዙ ሰዎች ከመያዛቸው በፊት በወንጀሉ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ከህግ አንጻር ተፈትሾ ለማደራጀት የተወሰደው ሰፊ ጊዜ የፍትህ ሥርዓቱን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማስኬድ በጎ ጅምር ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በእርግጥም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል ሕግን ተላልፈዋል በተባሉ ሰዎች ላይ በሕግ መሰረት እርምጃ የመውሰድና እንዲወሰድ የማድረግ ሂደት አንዱ ተጠቃሽ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ይህንንም ስራውን በመወጣት ላይ የሚገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ህግን ተላልፈዋል ተብለው የተጠረጠሩትን ሰዎች ስለመጠርጠራቸው መረጃ በማሰባሰብ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደረገ ሲሆን፣ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ ሶስት ላይ እንደሚደነግገውም የተያዙ ሰዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት በማቅረብ የፍርድ ሂደቱ እንዲጀመር መደረጉ የፍትህ ሥርዓቱን ተዓማኒነት እንዲጨምር የሚያደርገው አካሄድ ነው፡፡ ቀደም ሲል በዘርፉ ሲደረግ የነበረው ግፍና በደል በመቀነሱ በኩልም የራሱ ሚና አለው፡፡
ከዚህ ቀደም ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገራችን ሲደረግ የነበረው ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች የተለያየ በደል የሚደርስባቸው ከመሆኑም በላይ ጭካኔ የተሞላበት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ክብርን የሚያዋርድ ተግባር ሲፈጸምባቸው መክረሙ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የነበረው የፍትህ ሥርዓት ብዙዎቹ ታራሚዎች በህይወት እንዳይኖሩ የህይወት ቀበኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ሌሎች ደግሞ ለአካለ ስንኩልነትና ለስነ ልቦናም ችግር ተዳርገው በመኖርና በሞት መካከል ጥሏቸው ማለፉም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
በህገ መንግስቱ ላይ ስለ እስረኛ ሰብአዊ መብት አያያዝ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም፤ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ግን ህገ መንግስቱ የሚፈቅድላቸው ሰብአዊ መብቶች በአሳሪዎቻቸው ከመጣሱም በተጨማሪ አገራችን ተቀብላ ያፀደቀቻቸው አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ተፈጻሚነትን እንዳያገኙ ያደረገ ሆኖ ቆይቷል፡፡
አሁን አገራችን ኢትዮጵያ የተያያዘችው የለውጥ ጎዳና ቀጣይ ጉዞዋን ብሩህ የሚያደርግ እንደሆነው ሁሉ በፍትህ ሥርዓቱ ላይም እየታየ ያለው ለውጥ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስም በለውጥ ሂደት ላይ ያለው መንግስት ከፍተኛ ትግል ያካሄደ ስለመሆኑ መናገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይቆጠራልና ለዚህ ሥርዓት መምጣት ድርብ ኃላፊነትን ለመወጣት የተደረገ እርምጃ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ይሁንና የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ እንዲሉ አበው፤ የፍትህ ሥርዓቱን ቀና ለማድረግ እየተኬደበት ያለው መንገድ መልካም ጅማሬ ሆኖ ሳለ ሊያጎድፉ የሚችሉ አካሄዶች እንዳይኖሩ መጠንቀቅ ግን ብልህነት ነው፡፡ በፍትህ ዘርፉ ላይ መልካም የሆነ ጅማሬን በተግባር የማሳየት ጥረት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ የቀድሞውን አካሄድ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ አበክሮ መስራትን ይጠይቃል፡፡
መጠንቀቅ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር የትናንቱ ታሪክ ዛሬ ላይ እንዳይደገም ነው፡፡ ትናንት ሲደረግ ከነበረው ግፍ መካከል፤ አንድ ተጠርጣሪ ጽኑ እስራት እንዲፈረድበት ቀደም ተብሎ መረጃዎች መገኘታቸውን በተለያዩ መንገዶች መገለጹ ነው፡፡ አሊያም ደግሞ አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሳያውቀው ያለ ዓቃቤ ሕግ ክስና ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደ ጥፋተኛ ተቆጥሮ ጥቂት ለማይባል ዓመታት በእስር ቆይቶ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ደርሶበት ሊወጣ ይችላል፡፡ ይህ ዛሬም እንዳይደገም መስራት ተገቢ ነው፡፡
ቀደም ሲል ሲደረግ የነበረ አካሄድ ሕግን ያልተከተለና የታራሚውንም ሰብዓዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ሊወገዝ የተገባ ሂደት ነው፡፡ የአገራችንንም ስም የሚያጠለሽ ከመሆኑም በላይ የዛሬው ትውልድ ሊማርበት አይችልምና ይህን አካሄድ ልናወግዝና በድጋሚ እንዳይፈጸም ለማድረግ በተለይ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች በፍትህ ሥርዓቱ ላይ የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በፍትህ ዘርፉ የተጀመረው የተጠርጣሪዎች አያያዝ እንቅስቃሴ መረጃዎች ቀድመው ስለመሰብሰባቸው አመላካች ነውና ቀጣይ የምርመራ ሂደቱ በተጀመረው መልካም ጉዞ ልክ እንደሚቀጥል ተስፋ ተጥሎበታል። በዚህም ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተናገሩት ቃል በተግባር እየተገለጸ በመሆኑ ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ መልዕክታችን ነው።
Your passion for what you do is evident in every post It’s inspiring to see someone truly fulfilling their purpose and making a positive impact
I always look forward to reading your posts, they never fail to brighten my day and educate me in some way Thank you!