
የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ፤ ዓለም የአሸናፊዎችና የጉልበተኞች መድረክ ሆና ተገልጣለች። በተለይም እንደ አሜሪካ እና ሌሎችም የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ ሀገራት ጥቅምና ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ዘልቋል። ይሄን ሚዛን አስጠባቂ ለመሆን በሚደረገው ጥረት ውስጥም እንደ ሩሲያ ባሉ ሀገራት እና ኃያላኑ መካከልም ፍጥጫው ነግሶ፤ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመንን ተመልክተናል።
ይሄ ጉዞ ታዲያ ቀስ በቀስ መልኩን እየቀየረ ያለ ይመስላል። በተለይም የሩሲያ አልበገር ባይነት፤ የእነ ቻይና በሁሉም መስክ እየፈረጠሙ መዝለቅ፤ የእነ ሕንድ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገራት በፈጣን የኢኮኖሚም፣ የወታደራዊም ሆነ የቴክኖሎጂ አቅም መስመር ውስጥ መግባት ለዚህ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
ይሄን መሰሉ የሀገራት ለውጥ ታዲያ፣ የዓለም የአንድ ወገን ዘዋሪነት መንገድን ለመግታት ወደሚያስችል አቅጣጫ እየመራው መጣ። በተለይ በሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት እውን የሆነው ብሪክስ፤ ዓለም ኢ-ፍትሐዊ ከሆነው የኃያላን ፍላጎት አዳሪነቷ ተላቅቃ፤ ወደ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ባለቤትነት፤ ወደ እኩልነትና ፍትሐዊነት ዓውድነት እንድትሸጋገር የሚያደርግ መደላድል መፍጠር ጀመረ።
በሂደትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብፅ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ኢራንን በአባልነት ተቀበለ። ይሄም ስብስቡ በአባላት ቁጥርም፤ በኢኮኖሚ አቅምም ሆነ በሌሎች መልኮች የሚገለጥ አቅምን ወደመፍጠር ተሸጋገረ። በወቅቱም፣ ዓለም በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም፣ በዲፕሎማሲ እና ሌላውም መስክ የአንድ ወገን ተመልካችነቷን መልክ መቀየር ጀመረች።
ብሪክስም፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የዲፕሎማሲ አቅም መፍጠሪያና ማሳያ፤ የኢኮኖሚ እድገት ፍላጎቶችን ማሟያ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት አማራጭ መመልከቻ፤ የሁለትዮሽና የባለብዙ መድረክ ትብብሮች ፍትሐዊነትና እኩልነት መድረክ ሆኖ ወደማገልገል ተሸጋገረ። በአባል ሀገራቱም መካከል ሁሉን አቀፍ ትብብር እያጎለበተ ሄደ።
ከሰሞኑም 17ኛ ጉባኤውን እያካሄደ ያለው ብሪክስ፣ ከነባር አባላቱ ባሻገር እንደ ዑጋንዳ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያ፣ ታይላንድ፣ ቤላሩስ፣ ቦሊቪያና ሌሎችንም ሀገራትን በአጋርነት አካትቷል። ይሄም የስብስቡን እያደገም እየፈረጠመም መሄዱን የሚያረጋግጥ፤ የብሪክስንም የሚዛን አስጠባቂ መድረክነት አይቀሬነት የሚናገር ነው።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም፣ “ብሪክስ በዓለም አቀፉ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ያለው ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል” በሚለው መልዕክታቸው ያረጋገጡት ይሄንኑ ነው። በተለይ ስብስቡ የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ ታዳጊ ሀገራትን እያቀፈ መሄዱ፤ ከአባል ሀገራቱ መካከል ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዲፈጠር አድርጓል።
ይሄም በዓለም አቀፉ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ በጎ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ለምሳሌ፣ የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለማችንን ኢኮኖሚ 40 በመቶ ይሸፍናሉ። ይሄ ደግሞ በአባል ሀገራቱ መካከል በሀገራቸው ገንዘብ የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ እያደገ እንዲመጣ አድርጓል። በግብርና ምርት ልውውጥ፣ በስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ያላቸው ትብብርም እያደገ መጥቷል። በቀጣይም የሀገራቱን የካፒታል ኢንቨስትመንት የበለጠ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።
በዚህ መልኩ እየጎለበተ የመጣው የአባል ሀገራቱ ትብብር ታዲያ፣ ብሪክስ የባለብዙ ዋልታ ዓለምን የማረጋገጥ ዓላማውን እንዲወጣ የብሪክስ በይነ መንግሥታት ስብስብ ከፍ ያለ ኃላፊነትም ይሆናል። ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ መልኩ ከፍ ያለ ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች።
በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሃሳብ ተነስቶ ለዓለም አቀፍ ለውጥ የሚሠራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል። አዳዲስ አባላት በመጨመራቸውም የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል። የጋራ ዓላማችን የበለጠ ይጠራል። አቅማችንም ይሰፋል።” ሲሉ መናገራቸውም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከጉባዔው ጎን ለጎን፣ ከብራዚል ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ ጋር በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በተመሳሳይ፣ ከቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር ሁሉን አቀፍ በሆነው የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ላይ መክረዋል።
እነዚህ እና ሌሎችም የባለብዙም ሆነ የሁለትዮሽ ትብብር ውይይቶች ደግሞ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በብሪክስ አባልነቷ በአንድ በኩል ለራሷ እያገኘች ያለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ መኖሩን፤ ሁለተኛም እንደ ሀገር እኩልነትና ፍትሐዊነት የሰፈነባት ዓለምን በመፍጠር ሂደት ውስጥ እየተወጣች ያለውን ሚና የሚያመላክቱ ናቸው። ብሪክስም ዓለም የበለጠ የእኩልነት እና ፍትሕ የሰፈነበት እንድትሆን የሚያደርግ መሆኑን አይቀሬነት፤ የአባል ሀገራቱ መሪዎችም ለዚሁ መሳካት ቆርጠው መነሳትን የሚያረጋግጥ ነው!