እንደመንደርደሪያ፤
የዛሬው የፍረዱኝ አምድ ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ሞጆ አካባቢ ደርሷል።በርካታ የቆዳ እና የቄራ ፋብሪካዎች የከተሙባት የኢንዱስትሪ ማዕከሏ ሞጆ ከተማ የሚገኙት ባለሀብቶቿ ከፋብሪካቸው የሚወጣውን ተረፈ ምርት ማስወገጃ አጥተው እየተማረሩባት ያለውን ጉዳይ ይመለከታል።
የቆሻሻ አወጋገዱ በማስተር ፕላኑ መሰረት የተካለለው የሉሜ ወረዳ አስተዳደር ስር የሚገኘው ጉርማ ፋቶሌ የገጠር ቀበሌ ማህበር ውስጥ ነው።በዚህ ስፍራ ለረጅም ዓመታትም የደረቅ ቆሻሻ ሲጣል ቆይቷል።ግን ከስምንት ወራት በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳይጣል አግደዋል።ምክንያታቸውም ሽታው አላስቀመጠንም፣ በቤተሰቦቻችን ጤና ላይ አደጋ ጋርጧል፣ ማሳችን እንዲበላሽ ያደርጋል እንዲሁም ከብቶቻችን ወደ ቆሻሻ መጣያው ስፍራ እየገቡ ባዕድ ነገር እየተመገቡ ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸው ይገኛል፤ በማለት ቅሬታ በማቅረባቸውና ለቅሬታቸውም ምላሽ በማጣታቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ቦታው እንዲዘጋ ስለማድረጋቸው ይነገራል።
የቴክኒክ ቡድን ተዋቅሮ ቦታው 900 ሜትር ዙሪያው እንዲታጠር፣ አጥሩን ተከትሎ ዛፍ እንዲተከልና ሽታውን እንዲውጥ ማድረግ፣ አሞራዎቹ ሊያርፉበት የሚችለውን ቦታ ግምት በመውሰድ መንግስት ለአርሶ አደሩ ካሳ ከፍሎ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ሃሳብ ቀረበ።ጥናቱም ለሞጆ ከተማና ለሉሜ ወረዳ አስተዳደር ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።በእዚህ ጉዳይም ከህዝብ ጋር ውይይት ተካሄደ። ግን ውጤት አልተገኘበትም።
የእዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ቆሻሻ እንዳይጣልበት የአካባቢው ሰዎች ያገዱት ስፍራ የቆሻሻ መጣያ ቦታን በስፍራው ተገኝቶ አይቷል።ከባለሙያዎች እንደተረዳውም በቅርብ ርቀት ወንዝ መኖሩ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች መገኘታቸው፣ የቦታው ተዳፋት መሆንም እንደምክንያት ይጠቀሳል።ግን ልብ ሊባል የሚገባው አካባቢው ለቆሻሻ መጣያ ቦታ ተብሎ እንደመመረጡ በአካባቢው የሚገኙ ፋብሪካዎች ተረፈ ምርታቸውን ሲጥሉበት መቆየታቸው ነው።
ቆሻሻ እንዳይጣል ሲታገድ በአካባቢው በተለያየ እርከን የሚገኙ አመራሮች ፈጥነው የተሻለ ለቆሻሻ መጣያነት ሊያገለግል የሚችል ስፍራ እንዲዘጋጅ ሊያደርጉ አልያም ቦታው ደረጃውን የጠበቀ ተደርጎ እንዲዘጋጅ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር።ይህ ባለመደረጉ በሞጆ ከተማ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች ቆሻሻ በግቢያቸው ከምረው ለማቆየት ተገድደዋል።ይህ ደግሞ አካባቢው መጥፎ ሽታ እንዲያመነጭ በማድረጉ ምቹ የስራ ቦታ እንዳይኖር አድርጎታል።አንዳንዶቹ ፋብሪካ ለመትከል ያዘጋጁትን ስፍራ ለቆሻሻ ማጠራቀሚያ አድርገውትም ታዝበናል።
በቆሻሻ መጣያ ስፍራው ቆሻሻ እንዳይጥሉ በመከልከላቸው ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ የውጭና የአገር ውስጥ የቆዳ አምራቾች እየተማረሩ ናቸው፡፡ከፍተኛ የስራ ዕድል እንዲፈጥርና የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገባ ተስፋ የተጣለበት ዘርፍም በእዚህ አካባቢ ሰራተኞችንና ምርቱን ለመቀነስ እየተገደደ መሆኑን ዝግጅት ክፍሉ ተገንዝቧል፡፡ፈጣን ምላሽ ለማግኘት ያደረጉት ሂደት ምላሽ በመነፈጉ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትም አስገብተው መልስ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የሚመለከተው አካል ፈጣን ፍርድ ይስጠን እያሉም ይገኛሉ።
የባለሀብቶቹ ቅሬታ ከአንደበታቸው
የጂያንሲን ዛንግ ቆዳ ፋብሪካ
የጂያንሲን ዛንግ ቆዳ ፋብሪካ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊው አቶ ቶላ ጫላ፤ ፋብሪካው በ2004 ዓ.ም በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል ሚስተር ዛንግ በተባሉ ቻይናዊ ባለሀብት የተቋቋመ መሆኑን ይጠቁማሉ።ያለቀለትን ቆዳ ወደ ውጭ አገር እየላከ 500 ያህል ሰራተኞችን ያስተዳድር የነበረው ፋብሪካው መጣያ ያጣው ቆሻሻ በጊቢው ውስጥ ተሰብስቦ በፈጠረበት ተጽእኖ የሰራተኞቹን ቁጥር ለመቀነስ መገደዱን ይናገራሉ።በአሁኑ ወቅትም 300 ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞችን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።
በርግጥ ይላሉ አቶ ቶላ፤ በአለም ገበያም የቆዳ ገበያ መቀዛቀዝ አሳይቷል።ይህም ፋብሪካው የሚጠበቅበትን ያህል ለማምረት እንዳይችል አድርጎታል።ከእዚህ ባሻገርም ቆሻሻውን የምንጥልበት ስፍራ በመቸገራችን ስራን ቀስ በቀስ ለመስራት ተገድደናል፡፡ተረፈ ምርቱን በጊቢው ውስጥ ለማጠራቀም ተገድደናል።ይህ አደጋ ጋርጦብናል ይላሉ።
ሌላ የማምረቻ ማሽን ለመትከል ያሰብንበትን ቦታ አማራጭ በማጣታችን ቆሻሻ ማከማቻ አድርገነዋል።ለአረንጓዴ ቦታነት አዘጋጅተነው የነበረውን ስፍራ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ለማድረግ ተገድደናል።አካባቢው እየተበከለ ይገኛል።ከዚህ በፊት ፋብሪካው ውስጥ ያልነበረ ሽታ አሁን ተፈጥሯል።ይህም በሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።ለዝንብ መፈጠርም ምክንያት ሆኗል ሲሉም ያብራራሉ።
ተረፈ ምርት በዓይነት ተለይቶ የሞጆ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አሰናድቶት ወደነበረው የቆሻሻ ማከማቻ ወስደው ይደፉ እንደነበረ ይጠቁማሉ።ከማዘጋጃ ቤቱ ኩፖን ወስደው ቆሻሻውን ይጥሉ እንደነበረና ማዘጋጃ ቤቱም በየጊዜው ቁጥጥር ያደርግ እንደነበረም ያስታውሳሉ።
12 የሚደርሱት የቆዳ እና 5 የቄራ ፋብሪካዎች በጋራ ተግባቦት በየዓመቱ ገንዘብ በማዋጣት የቆሻሻ ማከማቻውን ያጸዱና ያስተካክሉ እንደነበረም፤ ከስምንት ወራት በፊት ቆሻሻ ይደፋበት የነበረው ቦታ ላይ እንዳይደፋ መከልከሉንና ኩፖንም መሰጠት ማቆሙን፤ ድርጊቱ በምርት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን በመግለጽም ያማርራሉ።
በተደጋጋሚ ወደ ከተማው ማዘጋጃ ቤት ስንመላለስ ነበር።ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋርም ስብሰባ ተካሂዶ በመተማመን ጉዳዩ እንደሚጠናቀቅ ቢገለጽልንም ሳይሳካ ቀርቶ ክልከላው ቀጥሏል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው፤ ለመፍትሄውም ለሞጆ ከተማ ከንቲባ ቢሮ፣ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ቢሮ፣ ለኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቢሮና ለኢትዮጵያ ቆዳ ኢንስቲትዩት ቅሬታ ብናቀርብም ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም ይላሉ።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንስቲትዮት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ስብሰባ መደረጉን አስታውሰው፤ አርሶ አደሩ እንዳይጎዳ አካባቢውም እንዳይበከል ፋብሪካዎቹን ተባብረን ቦታውን ለማጠር፣ እንስሳትም እንዳይገቡ ለማገድ፣ የአርሶ አደሩ ማሳ እንዳይጎዳ ለመከላከል፣ ለአካባቢው አርሶ አደርም ተገቢው ካሳ ተከፍሎ ሁኔታው እንደሚስተካከል ውይይት መደረጉን ይናገራሉ።
በተገባው ቃል መሰረት መፍትሄ ሊሰጣቸው አለመቻሉን በማንሳት ይወቅሳሉ፡፡ተስፋ ቆርጠውም ጉዳዮን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለፌዴራል ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና ለፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አቤቱታ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ነው የነገሩን፡፡
እንደቅሬታ አቅራቢው ገለጻ አርሶ አደሩ መጎዳት የለበትም፣ እኛም ስራችን መስተጓጎል አይገባውም በመሆኑም ቦታው በባለሙያ ታይቶ አስፈላጊው ማስተካከያ ተደርጎለት ስራችን ሊቀጥል ይገባል።ኢንቨስትመንቱም መደናቀፍ የለበትም።አብዛኞቹ ባለሀብቶች የውጭ አገር ዜጎች እንደመሆናቸው ኢንቨስትመንቱም ለአገር ገጽታ ግንባታ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ዕልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ጉዳዩ መፍትሄ ሳይሰጠው ረጅም ጊዜ በመቆየቱ ባለሀብቶቹ ላይ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ እየታየባቸው ነው።ለውጭ ምንዛሬ ግኝቱም፣ ለአካባቢው ህብረተሰብ የስራ ዕድል የፈጠሩት ፋብሪካዎቹ ህልውናቸው ሲቀጥል በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተውት ፈጣን እልባት ሊያገኝ ይገባል ሲሉም ያሳስባሉ።
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጆቢም፤የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በመጥፋቱ ላለፉት ስምንት ወራት በፋብሪካው ግቢ ቆሻሻ ለማከማቸት መገደዳቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ሂደቱም በስራ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ይናገራሉ።ሁኔታው በሰራተኞች ጤና እና በምርት ላይም ጫና ማሳደሩን ይጠቁማሉ፡፡‹‹በፊት በቀን ከአንድ ሺ በላይ ያለቀለት ቆዳ እናመርት የነበረውን አሁን የተረፈ ምርት መጣያ ቦታ በመቸገራችን ምርት በመቀነስ 500 ብቻ ለማምረት ተገድደናል›› ሲሉም ያመለክታሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ስንገባ ያለቀለት ቆዳ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ነበር የሚሉት ሚስተር ጆቢ፤ አሁን በቆሻሻ መጣያ ቦታ እየተቸገርን እንገኛለን፣ ባሰብነው ልክም ለማምረት አልቻልንም የሚመለከተው አካል ምላሽ ሊሰጠንና ስራችንን እንድንቀጥል መደረግ ይገባል ይላሉ ሚስተር ጆቢ።ምርት ባግባቡ ለማምረት፣ ያሉትን ሰራተኞች ባግባቡ ለማስተዳደር ካልቻሉና ሁኔታው በእዚህ መልኩ ከቀጠለ ስራችንን ለማስቀጠል ያስቸግረናል፣ ምርትም ሰራተኞችን ለመቀነስ እንገደዳለን ይላሉ፡፡ፋብሪካው ለሰባት ወራት ችግሩን ተቋቁሞ ቀጥሏል፣ መፍትሄ ካላገኘን ግን ከእዚህ በላይ መቀጠል አንችልም ለመዝጋትም እንገደዳለን ሲሉም አመልክተዋል፡፡
ሆዳኦቼ /ፔሌ ሌዘር/ ቆዳ ፋብሪካ
ሆዳኦቼ /ፔሌ ሌዘር/ ቆዳ ፋብሪካ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ለለ ፋብሪካውን ከአራት ዓመታት በፊት በ22 ሚሊየን ብር ከባንክ እንደገዙት፣ ካፒታሉን ወደ 207 ሚሊየን ብር እንዳሳደጉት ይናገራሉ።የፋብሪካው የበግ ቆዳና የፍየል ሌጦ እንደሚያመርት፣ ምርቱን በሙሉ ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ፣ 560 ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞችን እንደሚያስተዳድርም ይጠቁማሉ።
አሁን ፋብሪካው ተረፈ ምርቱን የሚያስወግድበት ቦታ ተቸግሯል።ከተጠራቀመው ተረፈ ምርት የሚወጣው ፍሳሽ ወደ ማምረቻ ክፍል እየገባ ሰራተኞችን ስራ እያገደ ይገኛል፤ ሲሉ ሚስተር ለለ ይጠቁማሉ።ቆሻሻን አግባብ ባለው ቦታ ብቻ መጣል እንደሚገባ በመጥቀስም፤ ላለፉት ጊዜያት ማዘጋጃ ቤቱ ከልሎት ቆሻሻ ሲጣልበት የነበረው ስፍራ እንዳይጣልበት በመከልከሉ ስራቸው መስተጓጎሉን ይናገራሉ።የሚመለከታቸው ቢሮዎች እየተመላለሱ ቢጠይቁም ጠብቁ እንጂ መፍትሄ ለማግኘት እንዳልቻሉም ይገልጻሉ።አማራጭ የቆሻሻ መጣያ ቦታ ሳይሰጠን መከልከሉ ተገቢ አይደለም የሚሉት ሚስተር ለለ፤ ማስወገጃ ቦታ በመጥፋቱ ቆሻሻው በግቢው እንዲከማች አድርጓል፣ ይህም በሰራተኞች ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ይላሉ።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ቆሻሻው በፋብሪካው ግቢ እየተጠራቀመ የሚቀጥል ከሆነና መጥፎ ሽታው ከቀጠለ ምርትንም ሰራተኞችንም ለመቀነስ፣ በሂደትም እስከመዝጋትና ሰራተኞችንም ለመበተን እንገደዳለን።በቀን 10 ሺ ቆዳዎችን ይነክር የነበረው ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በገጠመው ችግር ምክንያት ምርቱን ቀንሶ ሁለት ሺ 300 ያህል ብቻ እየነከሩ መሆኑንም ነግረውናል።
በአካል በመቅረብና በደብዳቤ የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን መጠየቃቸውን አስታውሰው፤ እስካሁን መፍትሄ ሳይሰጠው መቆየቱን ይታዘባሉ።አሁንም እየተከማቸ የሚገኘው ቆሻሻ የምርት መቀነስ እያስከተለብን፣ የሚፈጥረው ሽታ በፋብሪካው ብቻ ሳይሆን በከተማውም ላይ ከፍተኛ ጠረን በማመንጨት ችግር በማድረሱ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው ሚስተር ለለ።ምርታችንን አሳድገን በርካታ የስራ እድል እንድንፈጥርና የውጭ ምንዛሬ ለማስገባት እንድንችል ፈጣን መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ይላሉ ሚስተር ለለ።
ዲኤክስ ቆዳ ፋብሪካ
የዲኤክስ ቆዳ ፋብሪካ የሰው ሃይል አስተዳደሩ አቶ ወርቅነህ ከፈኒ፤ በ2005 ዓ.ም፤ በ32 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደተቋቋመ፣ አሁን ካፒታሉ ወደ 84 ሚሊዮን ብር እንዳደገ ይናገራሉ፡፡አምና 422 ሰራተኞችን ቀጥሮ ሲያሰራ የነበረው ፋብሪካ ምርት በመቀነሱ ምክንያት 266 ሰራተኞችን ብቻ እያሳተፈ መሆኑን ይገልጻሉ።የአለም ገበያ መቀዛቀዝና የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ማጣት ለመቀነሱ ምክንያት እንደሆኑም ይናገራሉ።
ቀደም ሲል በወር አራት ጊዜ ያክል ምርቱን ወደ ውጭ ይልክ እንደነበር በመጥቀስ፣ አሁን በየሁለት ወራቱ አንዴ እየላኩ መሆኑን ነው የሚጠቁሙት።ድርጅቱ እ.ኤ.አ 2017/18 የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እውቅና ተሰጥቶት እንደነበረ ያስታውሳሉ።የፍየል ሌጦ ብቻ የሚያመርቱ ሲሆን፤ በፊት ከአምስት ሺ እስከ ስድስት ሺ ያለቀለት ቆዳ ያመርቱ እንደነበር፤ አሁን ከሁለት ሺ እስከ ሁለት ሺ 500 ብቻ እያመረቱ እንደሚገኙ አቶ ወርቅነህ ይጠቁማሉ።
የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ መከልከሉ በስራ ላይ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑንና ለመፍትሄውም በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቢነጋገሩም ምላሽ ሊያገኙ እንዳልቻሉም ያክላሉ፡፡‹‹አማራጭ መጣያ በማጣታችንም ተራራ እስኪመስል ቆሻሻ በፋብሪካችን አጠራቅመን ይዘናል››ሲሉ ያማርራሉ።ሁኔታው ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር እንዳገዳቸውና የጥሬ ቆዳ ቁርጥራጮች አንድ ላይ በመጠራቀማቸው ጠረን በመፍጠር ምቹ የስራ አካባቢ እንዳይኖር አድርጓል ይላሉ አቶ ወርቅነህ።በመሆኑም በጋራ ቆሻሻ የምናስወግድበት ስፍራ እንዲዘጋጅና መንግስት አስፈላጊውን ሊያደርግልን ይገባል ሲሉ ይጠይቃሉ።
አቤቱታ ለሞጆ ከተማ አስተዳደር
በሞጆ ከተማ አካባቢ የምንገኝ የቆዳ ፋብሪካዎች ቆዳና ሌጦ በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ እንገኛለን።ለበርካቶች የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትም ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ሚና እያበረከትን ነን።በምርት ሂደት ያለቀለት ቆዳ ስናመርት የሚወጣው ተረፈ ምርት ከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው ስፍራ እየጣልን ቆይተናል።ሆኖም በቦታው ላለፉት ጊዜያት እንዳንጥል በመታገዱ ቆሻሻ በጊቢያችን ለማከማቸት ተገድደናል።ይህም በስራችን ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል እያደረሰብን ስለሚገኝ መፍትሄ እንዲሰጠን እንጠይቃለን።
አቤቱታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት
በሉሜ ወረዳ በሞጆ ከተማ የምንገኝ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባለሀብቶች የተመሰረትን ድርጅቶች በወጪ ንግድ ላይ ተመስርተን በመስራት የውጭ ምንዛሬ እያስገባን፣ ለአካባቢው ህብረተሰብም ሰፊ የስራ ዕድል እየፈጠርን እንገኛለን።ግን ላለፉት ዓመታት ደረቅ ቆሻሻ እናስወግድበት በነበረው ስፍራ ቆሻሻ እንዳይጣል የአካባቢው ህብረተሰብ በመከልከሉ ቆሻሻ ለረጅም ጊዜ አከማችተን ይዘናል።ይህም በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ሽታና መበከል እያስከተለ ነው።
በጉዳዩ የሞጆ ከተማ አስተዳደር፣ ለቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ ለኦሮሚያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም ውይይት ተደርጎ በአምስት ቀናት ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጠን ቃል ቢገቡልንም መፍትሄ ሳይሰጡን ቆይተዋል።አሁን በጊቢያችን ያጠራቀምነው ቆሻሻ ምርት ለማምረት አስቸግሮናል።በውጤቱም አምስት ሺ የሚደርሱ ሰራተኞችን ስራ እንዲያጡ ሊያደርጋቸው የሚችል አደጋ ተጋርጧል።የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የገጠመንን ችግር አሳሳቢነት በመረዳት ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ
እንዲሰጠንና የቀድሞ የቆሻሻ መጣያ ቦታ አግባብነቱ በድጋሚ ታይቶ አካባቢውንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማይጎዳ ሁኔታ እንዲፈቀድልን እንጠይቃለን።
የሞጆ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ
የሞጆ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ንዋይ አለሙ፤ የሞጆ ከተማ ሰፊ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ያለባት ከተማ መሆኗን ያስታውሳሉ፡፡14 የቆዳ ፋብሪካዎች፣ ሰባት ቄራዎችና የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችም እንደሚገኙ ይናገራሉ።ለአገሪቱም ለከተማውም ከፍተኛ የገቢ ምንጭና የውጭ ምንዛሬም እንደሚያስገቡ ይጠቁማሉ።
አቶ ንዋይ በተለይ የቆዳ አምራቾች የቆሻሻ መጣያ ቦታ በማጣት ከፍተኛ ችግር ተጋፍጠዋል።የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ እንዳለው እንዲሁም አደገኛ ኬሚካል ተረፈ ምርቶች እንደሚወጣበት በመጠቆም፤ በማስተር ፕላኑ መሰረት ጉርማ ፋቶሌ የገጠር ቀበሌ ማህበር ውስጥ ለረጅም ዓመታት የደረቅ ቆሻሻ ሲጣል ቢቆይም አሁን ቦታው ከሰባት ወራት በላይ እንዲዘጋ ተደርጓል ሲሉ ያመለክታሉ።
ቦታውን ለማስከፈትና ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ፣ የከተማው ስራ አስፈጻሚ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዘውት እንደነበር በማስታወስም፤ እስካሁን መፍትሄ ሊገኝለት እንዳልቻለም ይናገራሉ።በከተማው ዙሪያ ያሉ አምስት የሚደርሱ ቀበሌዎች ወደ ከተማ ተካልለዋል።ርክክብ ስላልተደረገ ከተማ አስተዳደሩ በጉዳዮ ላይ መፍትሄ ሊሰጥ አልቻለም።መፍትሄው በሉሜ ወረዳ አስተዳደር ስር ነው።ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ለምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ለኦሮሚያ ክልልም አሳውቀናል።በየፋብሪካዎቹ ከፍተኛ የቆሻሻ ክምችት አለ።ይህም በምርታቸው፣ በአካባቢው ማህበረሰብና በሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል ባይ ናቸው።
ችግሩ በሞጆ ከተማ አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ መንግስት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተቀናጅቶ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል።ከወረዳው ካቢኔ፣ ከቀበሌ ገበሬ ማህበርና ከማህበረሰቡ ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን አስታውሰው፤ የሚነሳው ችግር አካባቢው በአጥር የተከበበ አለመሆኑ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብናል፤ ስለዚህም ቆሻሻ አይጣልም ማለታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ እንደጊዜያዊ መፍትሄ ከተማ አስተዳደሩ ከብትም ሰውም እንዳይገባ ለማጠር በጀት ይዟል።አካባቢውን አረንጓዴ በማድረግ አእዋፋት አትክልት ላይ ማረፍ እንዲችሉ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።ግን ይህንንም የአካባቢው ነዋሪዎች አልተቀበሉትም።ቆሻሻ አይጣልብንም የሚል አቋም ይዘዋል።ከወረዳ አስተዳደሩ ጋር አማራጭ ቦታ እስኪገኝ ጊዜያዊ መፍትሄ እንዲሰጠው ደብዳቤ ብንጽፍም ምላሽ አልተገኘም ችግሩም ቀጥሏል ይላሉ፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ከየቤቱ ለሚሰበሰቡትም የቆሻሻ መጣያ ቦታ እጥረት አለ።ከየፋብሪካዎቹ የሚወጡት ኬሚካል የነካቸው ቆሻሻዎች ቦታ ተፈልጎ የሚቀበሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል።ቆሻሻ በየጊዜው የሚመረት እንደመሆኑ የሞጆ ከተማ አስተዳደር ከሉሜ ወረዳ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የኦሮሚያ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።ቆሻሻን በየአይነቱ በመለየት እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል ለመቀነስ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ይናገራሉ።በየፋብሪካዎቹ የተጠራቀሙት ቆሻሻዎች ለማህበረሰቡም የጤና ችግር እንዳይፈጥር መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ አቶ ንዋይ ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት
በኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንቫይሮሜንታል ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘርፌ መኩሪያ፤ ቆዳ ፋብሪካዎች ለምተው ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገቡና ሰፊ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ፍላጎት እንዳለ ይጠቁማሉ።ኢንስቲትዩቱም ቆዳ ፋብሪካዎች ባግባቡ ምርታቸውን እንዲያመርቱ፣ በእቅዱ መሰረት የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙና የተሟላ የሰው ሃይል እንዲቀጥሩ ያግዛል ሲሉ ያብራራሉ።
ኢንስቲትዩቱና ፋብሪካዎቹ የሚያቅዱትን አስተሳስሮ የማስቀጠል ስራዎች እንደሚተገበሩ የሚጠቁሙት ዳይሬክተሯ፤ በታቀደለት ልክ እንዳይሄድ በርካታ ችግሮች እንደተጋረጡበት ያመለክታሉ።ከምክንያቶቹ አንዱ የአካባቢ ጉዳይ አንዱ መሆኑንም ይጠቁማሉ።በአገሪቱ በወጣው መስፈርት መሰረት በተገቢው መንገድ አክመው መልቀቅ የሚያስችል ትሪትመንት ፕላንት ባለመትከላቸው በርካታ ፋብሪካዎች ተዘግተው እንደሚያውቁ፣ አሁን ፋብሪካዎች ፈሳሽ ቆሻሻ የሚያክሙበት ትሪትመንት ፕላንት በተቻላቸው መጠን አቋቁመው እየሰሩ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ወይዘሮ ዘርፌ ለፋብሪካዎቹ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሌላ ችግር ሆኖ ተጋርጦባቸዋል ይላሉ።በሞጆ ከተማ ምንም አይነት የደረቅ ቆሻሻ መጣያ ቦታ በማጣታቸው ምክንያት ላለፉት ስምንት ወራት ደረቅ ቆሻሻ በጊቢያቸው ውስጥ በማጠራቀማቸው ፋብሪካዎቹ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ባይ ናቸው።ቆዳ ፋብሪካዎች በአተገባበራቸው ብዙ ተረፈ ምርት እንደሚያመነጩ፤ በየጊዜው እያከማቹ የሚገኘው ቆሻሻ በሰራተኞች ጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል እንደሚችልና መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ያሳስባሉ።
ሂደቱ በምርታቸው ላይ ተጽእኖ እንዳለው፤ ወደ ውጭ የሚልኩትን ምርትና ሰራተኞችን እየቀነሱ ናቸው ሲሉም ይናገራሉ።በየፋብሪካዎቹ የሚታዩት በየግቢያቸው ያለው የቆሻሻ ክምር ተጽእኖው የከፋ ነው።ምርት ላይ ተጽእኖ ስላለውም ብዙዎቹ በርካታ ሰራተኞችን በመቀነስ ሂደት ላይ ይገኛሉ፣ አብዛኞቹ በእዚህ የሚቀጥል ከሆነ ፋብሪካቸውን እንደሚዘጉ እያስጠነቀቁን ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ለሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩ አስቸጋሪ መሆኑን፣ ሊመለስ የማይቻልበት ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ በየደረጃው የሚገኙ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ ማሳሰባቸውን ይጠቁማሉ።ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጽፈናል የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግሮ መፍትሄ ሊያሰጠው ይገባል ባይ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ለምስራቅ ሸዋ ሉሜ ወረዳ አስተዳደር፣ ከሞጆ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አካባቢ ጥበቃ፣ ከባለሀብቶቹ ጋር ውይይት ተደርጓል።ምንም ምላሽ ሊገኝ አልተቻለም።አሁን ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ምላሽ መሰጠት አለበት ባይ ናቸው።ከየፋብሪካዎች የሚመነጩ አደጋ የሚያስከትሉትንም ሆነ አደጋ የሌላቸው ቆሻሻዎች ማስወገጃ ጉዳይ ፈጣን እልባት እንዲሰጠው ያሳስባሉ።ኢንስቲትዩቱ ተረፈ ምርቱን ጥቅም ላይ እንዲውል እያስጠና መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።ኢንስቲትዩቱ በአቅሙ የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም ውጤት ማስገኘት እንዳልተቻለ ይጠቅሳሉ።
አደጋ የሚያስከትሉ ቆሻሻዎች ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ሊከማቹ ይገባል።ፋብሪካዎቹ ገንዘብ አዋጥተው አካባቢን እንዳይበክል በሚያስችል መንገድ ገንብተው እንዲጠቀሙ የሚጠይቁት ወይዘሮ ዘርፌ፤ ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ቆሻሻ እንዲያስወግዱ የሚደረግበት አሰራር እንዲዘረጋ ያሳስባሉ።ለወደፊቱ ከየፋብሪካዎቹ የሚመነጨው ቆሻሻ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል መርሃ ግብር ለማስተግበር በጥናት ላይ መሆኑንም ያመለክታሉ።
የሞጆ ከተማ ማዘጋጃ ቤት
የሞጆ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኢብሳ ዋቄ፤ ጣፊ አቦ ቀበሌ በቅርበት በሚገኝበት አካባቢ ኩርማ ፋቶሌ ቀበሌ ከበፊት ጀምሮ ቆሻሻ ሲጣል እንደነበረ ያስታውሳሉ።የኩርማ ፋቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች በአካባቢው ቆሻሻ እንዳይጣልባቸው አግደዋል።ልጆቻቸው ወደ ቆሻሻ ስፍራው እየገቡና ከብቶችም ከቆሻሻ ስፍራው እንደላስቲክ ያሉ ባዕድ ነገሮችን እየተመገቡ አደጋ ላይ በመውደቃቸውና ወንዝ በቅርበት በመኖሩ ክረምት ላይ ቆሻሻው እየታጠበ ወደ ወንዙ እንዳይገባ ህብረተሰቡ ለመከልከል እንደቻለ ይናገራሉ።
ከተማ አስተዳደሩ ከቀበሌና ከወረዳ አስተዳደሮች እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በርካታ ውይይቶች አካሂዶ ቦታው እንዲታጠር ጥረት ቢያደርግም አመርቂ ምላሽ ሊገኝ አልቻለም ይላሉ።የኩርማ ፋቶሌ ቀበሌና የሉሜ ወረዳ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቶ ለቀጣይ የተሻለ ቦታ እስኪዘጋጅ ለሰባት ወራት ፈቅደው ለፋብሪካዎቹ ችግር መፍትሄ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያምናሉ።
የሞጆ ከተማ ጽዳትና ውበት ዘርፍ አቋም
የሞጆ ከተማ አስተዳደር የጽዳትና ውበት የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ አደፍርስ መኮንን የቆዳ ፋብሪካንና የኢንዱስትሪ ማእከል በመሆኗን ትልቅ የውጭ ምንዛሬ የምታስገኝ መሆኗን፤ ፋብሪካዎች ተረፈ ምርታቸውን ኩርማ ፋቶሌ ቀበሌ አካባቢ ለረጅም ጊዜ ሲጥሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።
ቆሻሻው በማህበረሰቡ ላይ ተጽእኖ ያደርሳል፤ በርካታ አሞራዎች ተረፈ ምርቱን ለመለቃቀም ይሰበሰባሉ፤ ከእዚህ የተነሳ የአርሶ አደሩን ማሳ ያበላሻሉ፤ የአካባቢው ነዋሪዎችም በመጥፎ ሽታ ለዘመናት ተቸግረው ቆይተዋል፤ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ የአካባቢው ማህበረሰብ ነን የሚሉ ሰዎች በራሳቸው እርምጃ ወስደው ተረፈ ምርት እንዳይጣልም ከልክለዋል።ስፍራው ከሞጆ ከተማ አስተዳደር ውጪና በሉሜ ወረዳ የሚተዳደር በመሆኑም የከተማና የሉሜ ወረዳ አስተዳደሮች ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ለ12 ጊዜ ያክል ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
የሚነሱትን ጉዳዮች ከተማ አስተዳደሩ በአቅሙ ስፍራውን 900 ሜትር ያክል በማጠር የአርሶ አደሩ ከብቶች ወደ ስፋራው እንዳይገቡ ለማገድ ቃል ገብቷል።ለአካባቢው ነዋሪዎች የካሳ ክፍያ በመክፈል ለማጠቃለል ተሞክሯል።ግን ህብረተሰቡ ችግራችን በዚህ ብቻ አይፈታም በሚል ይህንን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።ቦታውም ተዘግቷል ይላሉ አቶ አደፍርስ።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ቦታው የቆሻሻ መጣያ ቦታ ሊያሟላቸው ከሚገቡ መስፈርቶች የሚያሟላው ጥቂቱን ነው።ከዚህ ውጭ አማራጭ አለ ማለትም አይቻልም።ለቆሻሻ መጣያ ስፍራ በቀዳሚነት የሚታየው የንፋስ እቀጣጫ ነው።በእዚህ መልኩ ከተመዘነ የተሻለ ቦታ ነው ተብሎ የሚታሰበው ይህ የተከለከለው ስፍራ ነው።
ይሁን እንጂ ባግባቡ አልተዘጋጀም።በክረምት ወቅት ከቆሻሻው ታጥቦ ወደ ወንዝ እንዳይገባ ብዙ ወጪ ፈሰስ ተደርጎ ከስር ጀምሮ መገንባት ነበረበት።መሬቱም ከስር ተገንብቶ ወደ ከርሰ ምድር ውሃ እንዳይሰርግም መደረግ ይገባው ነበር።ግን ይህ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ለመስራት አልተቻለም።ከአራት ዓመታት በፊት ይህንን ለማስተግበር 37 ሚሊዮን ብር ተገምቶ ነበር።አሁን ከዚህ በላይ ወጪ ሊጠይቅ ይችላል።ይህ በከተማዋ አቅምም አይቻልም።ከተማዋ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንደመሆኗ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል።የፌዴራል መንግስት አስተማማኝ የሆነና ህብረተሰቡን የማይጎዳ የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ መዘጋጀት አለበት የሚል አቋም ይዞ ማስተግበር አለበት ብለዋል።
የሉሜ ወረዳ አስተዳዳሪ
ቆሻሻ መጣሉ እንደታገደ መቀጠሉን የሉሜ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መንግስቱ ኩመራ ይናገራሉ።በቀበሌ ምክር ቤት ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት ቆሻሻ እንዳይጣል ተደርጎ እንደነበር ያስታውሳሉ።ቦታው ባለመከለሉ ክረምት ላይ ሽታው አርሶ አደሩን ስለሚረብሽ፣ ወንዝ የሚበክል በመሆኑ አስቸጋሪ መሆኑንም ህብረተሰቡን በማወያየት መግባባት ላይ እንዳልተደረሰና ችግሩን መፍታት እንዳልቻሉ ይጠቁማሉ።ከተማ አስተዳደሩ ሌላ አማራጭ ቢያዘጋጅ የተሻለ ይሆናል ባይ ናቸው።
ከተማ አስተዳደሩ ሽታን ለማጥፋትና አስፈላጊውን ሁኔታ ለማስተካከል አልሞከሩም።በፊት አጥፍተዋል ለዘጠኝ ዓመታት ያህል መፍትሄ ሳይሰጥ ቆይተዋል፣ እዛ ቦታ ከተማ አስተዳደሩ ምንም አይነት ስራ አልሰሩም።ለአርሶ አደሮችም ካሳ አልተከፈለም፣ ዝም ብሎ ቆሻሻ መጣል ብቻ ነበር።ስራዎች ከተሰሩ ሕብረተሰቡን ማሳመን ይቻላል።ይህ ከሆነ ከህብረተሰቡ ጋር ተወያይተን ሌላ አማራጭ እስኪገኝ ድረስ ከስድስት እስከ ስምንት ወራት ድረስ እንዲጣልበት ይደረጋል።ሰሞኑንም ከዞን አመራሮች መጥተው ተወያይተናል።ይህንን እንኳን ባይቀበሉ ከከተማ አስተዳደሩና ከዞን ጋር ተወያይተን የህግ የበላይነትን እናስከብራለን ብለዋል።በአዲሱ ፕላን መሰረት አካባቢው ወደ ሞጆ ከተማ መካለሉንም አቶ መንግስቱ ነግረውናል።
የሞጆ ከተማ ከንቲባ
የሞጆ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ እንደሚሉት፤ የቆሻሻውን መጣያ ያለበትን ቀበሌ ጨምሮ በከተማው ዙሪያ ያሉ ገጠር ቀበሌዎች ወደ ፊት ወደ ከተማው እንዲካለሉ አዲስ ፕላን ወጥቷል።ግን አሁን ለገጠመው ችግር አይደርስም።ከተማ አስተዳደሩ ከወረዳው በህጋዊ መንገድ ቦታውን ጠይቆ ቆሻሻ ይጣልበት በነበረበት ስፍራ ላሉ አርሶ አደሮች ካሳ ከፍሎ መሬቱን መረከቡን ይናገራሉ።
የወረዳው ችግር እችላለሁ፣ እፈጽማለሁ እያለ ነው እስካሁን እያጓተተው ያለው።የሉሜ ወረዳ አልችልም፣ ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ወደ ዞን አልያም ወደ ክልል ቢያስተላልፍ የሚቀጥለው አካል እስካሁን መፍትሄ ይሰጠን ነበር፡፡‹‹ የህግ የበላይነትን አስከብሬ ትደፋላችሁ፣ ቦታው የራሳችሁ ነው፣ ካሳ ከፍላችሁ የተሰጠጣችሁ ቦታ ነው›› ይለናል።ቀበሌዋ ባለችበት ምክር ቤት ቆሻሻ እንዳይጣል ይወስናሉ።ይህ ልክ አይደለም በሚል አርሶ አደሩን ሰባት ጊዜ አወያይተናል።ከተማው እንዳያወያየን ተጠሪነታችን ለከተማ አስተዳደር አይደለም ብለው እምቢ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትዩት፣ የክልል አካባቢ ጥበቃ፣ የሉሜ ወረዳው አመራሮች ባሉበት ተወያይተን ነበር።‹‹በአንድ ሳምንት ውስጥ የህግ የበላይነት አስከብሬ ቆሻሻ ትጥላላችሁ አለን›› ግን አልሆነም።በየጊዜው የሚጠይቁን ስለአዋጅ፣ ስለህግ ነው።ቦታ እያስጠናን በመሆኑ ለጊዜያዊ መፍትሄ እስከ ስምንትና እስከ አስር ወራት ያህል ቆሻሻ ለመጣል ጠይቀን አልፈቀዱልንም፡፡
ሌላ ቅሬታ የማያስነሳ መሬት በምትክነት እንዲሰጡን ጠይቀን ይህንንም አርሶ አደሩ እምቢ አይልም ብለውን ነበር።የዞንና የክልል አመራሮች ባሉበት ጉዳዮን አንስቼዋለሁ።ችግር ያመጣል የተባለውን አርሶ አደሩ ማሳ ላይ አሞራዎች ያርፉበታል የተባለውን ካሳ ለመክፈል ካሳውን ገምቱና እንክፈል ብለን ጠይቀን ነበር፡፡ግን ይህንን ማድረግ አልቻሉም።አሁን ቀሪ ሰባት ወራትን ቆሻሻ እንዲጣል ሊፈቀድ ይገባል።ከሐምሌ ወር በኋላ ግን አዲስ በጀት እንይዛለን።እስከዚያው ጥናቱ ይጠናቀቃል፣ ተለዋጭ የቆሻሻ መጣያ ቦታ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ዝግጅት ክፍሉ
ችግሩ በሞጆ ከተማ አቅም ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን ለመገንዘብ ችሏል።የሉሜ ወረዳ አስተዳደርም‹‹የህግ የበላይነትን አስከብሬ ቆሻሻው እንዲደፋ አደርጋለሁ ቢልም እስካሁን መፍትሄ አልሰጠም።መፍትሄው በሉሜ ወረዳ አስተዳደር ስር ቢሆንም ወረዳው ዕልባት ሊሰጥበት የፈቀደ አይመስልም።በመሆኑም የተሻለ ቦታ እስኪገኝ የምስራቅ ሸዋ ዞንና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የባለሀብቶቹን ችግር አሳሳቢነት በመገንዘብ በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው አፋጣኝ ውሳኔ እንዲያስተላልፉበት ለማሳሰብ እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
ዘላለም ግዛው