
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ሆቴሎች እንደ የደረጃቸው ለደምበኞቻቸው አገልግሎቶችን ያቀርባሉ።ለአገልግሎቶቻቸውም ደምበኞቻቸውን ያስከፍላሉ።ደምበኞችም በሆቴሎቹ ቆይታቸው ከያዙት አልጋ ጀምሮ እስከተጠቀሟቸው ምግቦችና መጠጦች ድረስ ክፍያ መፈፀም ይጠበቅባቸዋል።
ይሁን እንጂ አንዳንዴ ደንበኞች በሆቴሎች ውስጥ ያሻቸውን ተጠቅመው ሲያበቁ ሂሳብ ሲጠየቁ ድንጋጤ ውስጥ የሚገቡ፤ ለመክፈልም የሚያንገራግሩ አይጠፉም።ለተጠቀሙበት አልጋ፣ ምግብ፣ መጠጥና ሌላም የአገልግሎት ክፍያ ሳይፈፅሙ እንዲሁ በነፃ ከሆቴሉ ውልቅ ብለው ለመውጣት የሚዳዱም አልፎ አልፎ አይታጡም።ኦዲቲ ሴንትራል ከሰሞኑ ይዞት የወጣው መረጃም የሆቴል አገልግሎቶችን በሚገባ ተጠቅሞ ክፍያ ሳይፈጽም ስለተገኘ አንድ ግለሰብ አስነብቧል።
የሰላሳ ሰባት አመቱ አሜሪካዊው የኡታ ግዛት ጎልማሳ ሪያን ቀልቡ ባረፈባቸው ሆቴሎች ሁሉ በመግባት ከአልጋ ጀምሮ የሚፈልገውን አገልግሎት በሙሉ ተጠቅሞ ምንም አይነት ክፍያ ሳይከፍል በተደጋጋሚ ውልቅ ብሎ ይወጣል።ሂሳብ ሳይከፍል የሚወጣው ግን ተደብቆ ወይም በስፖንሰር ተከፍሎለት አይደለም፤ በአይጦች እንጂ።እዚህ ላይ የእርሱ ከሆቴሎች በነፃ ተስተናግዶ መውጣት ከአይጦች ጋር ምን አያያዘው ሊሉ ይችላሉ።እውነታው ግን አይጦቹ ሪያንን ከከባድ ወጪ ያዳኑት መሆኑ ነው።
ነገሩ ወዲህ ነው፤ ሪያን በቅድሚያ ወደ ሆቴሎች ሰተት ብሎ ይገባል። ከዛም አልጋ ይይዛል።ጥቂት ቆይቶም ከውጭ ወደሆቴሉ በሳጥን ደብቆ የሚያስገባቸውን አይጦች በያዘው ክፍል ውስጥ ይለቃቸዋል። በመቀጠልም ከሆቴሉ ስታፍ ለአንዱ ስልክ በመደወል በሆቴሉ የንፅህና አያያዝ ዙሪያ ቅሬታውን ያቀርባል፤ ይጮሃል።
ታዲያ በዚህ ጊዜ የሆቴሉ ስራ አስኪያጆች የሆቴላቸው ስም እንዳይጠፋ ‹‹የአልጋ ሂሳብ አናስከፍልህም፤ የምግብና የመጠጥ ወጪህንም እኛ እንሸፍንልሃለን›› ይሉታል።እንዲህ አይነቱን የማታለያ ድርጊት በተደጋጋሚ በመፈፀምም ሪያን በተለያዩ ሆቴሎች በሚገኙ አልጋዎች ላይ በነፃ ተኝቷል፤ ሌሎች የምግብና የመጠጥ አገልግሎቶችን እንዳሻው ተጠቅሟል።
መቼም እንዲህ አይነቱ የማታለያ ተግባር ሁሌም አያዋ ጣምና በዚህ ድርጊት በሶስት ሆቴሎች ላይ የጠረጠረው ፖሊስ ሪያንን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገበት ይገኛል። ሪያን እንዴት በፖሊስ ሊያዝ እንደቻለ በግልፅ የተነገረ ባይኖርም በሁለት ሆቴሎች የመኝታ ክፍሎች ወስጥ አይጦቹን ስለመልቀቁ ግን ራሱ አምኗል።ሌብነትና ማጭበርበርን ጨምሮ አምስት ክሶች እንደሚጠብቁትም ተነግሯል።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012
አስናቀ ፀጋዬ