ብዙውን ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች ወደ ሌላ አገር ለጉብኝት ሲሄዱ የሚሄዱበት አገርና ቀን በግልጽ ሲነገር አይታይም። ቢነገርም ባለቀ ሰዓት ለዜና ሽፋን ሲባል የሚነገርና የሚዲያ ፍጆታን ታሳቢ ያደረገ ነው።
ምናልባት ይሄ ከጸጥታና ደህንነት አንጻር ለተመለከተው ትክክል ነው ሊባል ይችላል። በዚህ ምክንያት ብቻ ነው ተብሎ ባይታመንም ግን፤ እነዚህ መሪዎች ባቀኑበት አገር ላይ ያሉ ዜጎቻቸውን በግልጽ በአደባባይም ጭምር አግኝተው ሲያወያዩ መመልከት እርም ነው።
ይህ አፍሪካዊ እውነት በኢትዮጵያ መሪዎች ዘንድ በተለይም ከሁለት አመታት ገደማ ወዲህ ብዙም ሲሰራ አይታይም። የኢትዮጵያ መሪዎች በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ደረጃ የሚደረጉ ጉብኝቶች ሳምንታት ቀድመው የሚነገሩ፤ መርሀ ግብሮቹ በሙሉ አስቀድመው የሚታወቁ፤ በዚያ አገር ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑን የሚያወያዩበት ሰዓት፣ ቦታ እና አጀንዳ ሳይቀር በግልጽ የሚነገሩ መሆን ጀምረዋል። ይህ አዲስ የመሪዎች ባህል ወደፊትም መቀጠል ያለበትና በራሱ የሚተመማን መንግስትና መሪ የሚያደርገው ድርጊት ነው።
ማንም ዜጋ አገሩ ላይ ተስፋ ካልቆረጠ አገሩን ጥሎ አይሰደድም። አሜሪካም ያለው ይሁን አውሮፓ አሊያም አረብ አገራት ስለ አገሩ ቢጠየቅ አገሩን ለአፍታም ቢሆን የማይዘነጋ በናፍቆትና በምኞት የሚንገበገብ ነው።
አገሩ ብትለማ፣ አገሩ ያለበትን አገር አይነት ምቾትና እድሎች ያሉባት ብትሆን አንድም ቀን በሰው አገር የሚያድር ዜጋ ይኖራል ተብሎ አይታመንም። የብዙዎች በስደት ላይ ያሉ ወገኖች እውነትም ይሄው ነው።
እንደዚህ አይነት ወገኖች ወደ አገር ቤት የሚመጡበትን እድል በአገር ቤት ማመቻቸት አንድ ቁምነገር ነው ተብሎ ይታመናል። ለዚህም በርትቶ መስራት በየደረጃው ያለ የመንግስት የስራ ኃላፊ ኃላፊነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ከዚህ ባሻገር ግን ለስራ በሄዱበት አገር ለአንድም ቀን ለማደር በሚያስቸግሩ እስር ቤቶች ውስጥ ያሉና ለአመታት የተዘነጉ ወገኖቻችንን አስታውሶ የተጠናከረ የዲፕሎማሲ ስራ መስራትና ካሉበት የእስር ህይወት ማውጣት ያስፈልጋል።
ይህ ስራ ለአመታት የተዘነጋ በመንግስት ደረጃም ብዙም ሲሰራበት ያልታየ የመንግስት እጥረት ነው ቢባል ከእውነታው ፈቅ ማለት አይሆንም። በተለይም ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ደረጃ የሚደረጉ ጥረቶች ምስጋና ሊቸራቸው የሚገቡ ናቸው።
አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ በርካታ ፖለቲከኞችን ለውጡ ወደ አገራቸው መልሷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ አስታዋሽ የሌላቸው ምስኪን ዜጎችን በራሳቸው (በሚጓዙበት) አውሮፕላን ይዘው በመምጣት ለአገራቸው መሬት አብቅተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ተግባራቸውም እስካሁን ከሳውዲ አረቢያ 105፣ ከግብጽ 30፣ከሱዳን 105፣እንዲሁም ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች 135 ኢትዮጵያውያን በክብር ወደ አገራቸው መልሰዋል። በዚህም የዚህን ያህል ዜጎችን እና ቤተሰቦቻቸውን እንባ አብሰዋል።
ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ማለትም ይሄው ነው። በሰው አገር በችግር ያሉ ወገኖችን አስታውሶ ለአገራቸው ማብቃት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራ ብቻ ነው ተብሎ አይታመንም፤ ተገቢም አይሆንም።ይህንን አይነቱን ተግባር በተለይም በየአገራቱ ያሉን ኤምባሲዎቻችንና አምባሳደሮቻችን ሊከተሉት ይገባል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል ጥረት ተቋማዊ መሆን አለበት። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእድሜ ልክ ጠቅላይ ሚኒስትር ስላልሆኑ ከእርሳቸው በኋላ የሚቆም ተግባር ሊሆን የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነውና በፍጥነት ተግባሩ ተቋማዊ ይሁን።
ከዚህ አንጻር በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እያደረገ ያለው ተግባር የሚያስመሰግን ነው። ኤምባሲው ከጉዞ ሰነድና ከሌሎች ጋር በተያያዘ ከሁለት አመት እስከ 40 አመት በስደት ያሉና ቀን የጨለመባቸው በስደተኛ ጣቢያ የሚገኙ ሁለት ሺ 281 ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ሁሉም ሲተጋገዝ የሚከብድ ስራ የማይወጣ ተራራ የማይታለፍ ችግር አይኖርም። ስለሆነም ይህ ተግባር የሁሉም ኤምባሲዎች ስራ በማድረግ ተቋማዊ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2012