እለት ከእለት በአዳዲስ መረጃዎች በምትጥለ ቀለቀው ዓለም የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን በመጠቀም የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በምርምርና በፈጠራ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ ይላል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ማህበረሰቡ የተሻለና ቀለል ያለ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተል በማድረግ ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ ያደርሳሉ።
በዚህ ረገድ፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አገራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምርና ፈጠራ ስራዎች መሬት ላይ ወርደው ፍሬ እንዲያፈሩ ለማገዝ የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች በማመቻቸት ለተመራማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች የተለያዩ የማበረታቻ ድጋፎችንና የእውቅና ሽልማቶችን እየሰጠ ይገኛል ።
በዚህ ዝግጅት የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በምርምርና በፈጠራ ስራዎቻቸው የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች መካከል አንዱን የፈጠራ ባለሙያ መምህር መዝገቡ አዳነን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ፤
መምህር መዝገቡ በምስራቅ ጎጃም ቢቸና ከተማ የበላይ ዘለቀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር ነው። የፈጠራ ፍላጎት ያደረበት ገና በልጅነቱ ነው። ያኔ ያገኘውን ሁሉ መነካካት በመውደድ በሚያደርገው ሙከራ የሚያያቸውን ነገሮች በቀላሉ ኮፒ በማድረግ መልሶ ለመስራት ጥረት ያደርግና ይሳካለትም ነበር። እንዲህ እንዲህ እያለ እያደገ የመጣ ፍላጎት በትምህርት ተደግፎ አሁን ያለበት የፈጠራ ስራ ላይ አድርሶታል።
“ለመስራት የፈለግኩት ነገር ያቅተኛል ብዬ አላውቅም። ‘ሁሉም ይቻላል!’ በሚል መንፈስ ስለምሰራ የሰራሁት ሁሉ ይሳካልኛል” የሚለው መምህር መዝገቡ፤ ከሚሰራው የፈጠራ ስራ ብዙ ነገሮች በመማሩ እውቀት ለማግኘት መቻሉን፤ እንዲሁም ከብዙ ስራዎችና ሙከራዎች በኋላ ኤሌክትሪክ እንኳን የማይዘው መሆኑን ይናገራል። የፈጠራ ስራው ባስገኘለት እውቅናም በከተማው ውስጥ “አንቱ” የተባለ የመብራት መስመር ዝርጋታ ባለሙያ ያደረገው መሆኑን ይገልጻል።
የፈጠራ ስራዎቹ ምንነት
የመምህር መዝገቡ የፈጠራ ስራዎች የድምዕ ማጉያ/ሞንታርቦ፣ የባለሶስት እግር ተሽከርካሪ/ባጃጅ ሞዴል፤ የኤሌክትሪክ ምጣድና ምድጃዎች፤ ፕሮጀክተር፤ ቴሌስኮፕ፤ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራት፤ ለሆቴሎችም፤ ለባንክ እና ለመሳሰሉት ተቋማት የሚያገለግሉ የመፈተሻ መሳሪያዎች ናቸው።
የፈጠራ ስራዎቹን ለየት የሚያደርጋቸው
የፈጠራ ስራዎቹ በገበያ ላይ ካለው የሚለየው በአካባቢ ከሚገኙ የተለያዩ ቁሳቁሶች በቀላሉ የሚሰሩ በመሆናቸው ወጪ ይቀንሳሉ፤ በቀላሉ መተካትን ይችላሉ። ለምሳሌ፤ የጽምፅ ማጉያው/ሞንታርቦው ከጃሪካን የተሰራ ሲሆን፤ በገበያ ላይ ያለው ዘመናዊ መሳሪያ የሚሰጠውን አገልግሉት በሙሉ የሚሰጥ ነው። የባለሶስት እግር ተሽከርካሪዋ/ባጃጅ ሞዴል ደግሞ የራሷ ቁልፍ ያላትና በባትሪ ተገጣጥማ የምትሰራ ሲሆን፤ ወደፊትም ወደኋላም መሄድ ትችላለች። ስትነሳም በቁልፍ ካልሆነ በጅ አትከፈትም።
ሌላው፤ ፕሮጀክተሩ ለማስተማሪያ የሚያገለግሉ የትምህርት መረጃ መሳሪያዎችን በማጉላት የሚያሳይ ነው። ይህም ተማሪዎቹ ጥቃቅን የማይታዩ ነገሮች በቀላሉ እያዩ እንዲማሩ ለማድረግ ያግዛል። በተለይ፤ ብርሀን አስተላላፊ/ትራንስፖርንት በሆኑ ወረቀቶች ላይ የተጻፉ ፅሁፎችን አጉልቶ ያሳያል። ቴሌስኮፑ እንዲሁ ለፊዚክስ ትምህርት ማስተማሪያነት በእጅጉ ይጠቅማል።
የፈጠራ ስራዎች ጠቀሜታ
እንደ መምህር መዝገቡ ማብራሪያ፤ አብዛኛዎቹን የፈጠራ ስራዎቹን በትምህርት ቤት ውስጥ እርሱና ባልደረቦቹ በትምህርት መርጃ መሳሪያነት እየተጠቀሙባቸው ሲሆን፤ በፕላዝማ የሚሰጡትን ትምህርቶች በማውረድ ለተማሪዎች ገለጻ ለማድረግ እንደሚጠቀሙበትም ይናገራል።
መምህሩ የፈጠራ ስራዎቹን ስራ ላይ በማዋል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ከመገኘቱ ባሻገር የክልል የላብራቶሪ ተጠሪ በመሆንም እያገለገለ ይገኛል። በምስራቅ ጎጃም በቢቡኝ ወረዳ ለሚገኙ ሁለት ተቋማት ሞንታርቦ ሰርቶ በመስጠት እየተጠቀሙበት መሆኑንም ይናገራሉ።
የኤሌክትሪክ ምጣድ፤ ምድጃዎችና የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራት በደንብ ተሰርቷል ። ነገር ግን ጥቅም ላይ በማዋል ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ለማስተላለፍ አልተቻለም ። ምክንያቱም የፋይናንስ እጥረት ስለገጠመው እንደሆነ ጠቁሟል።
የፈጠራ ስራው ያስገኘው እውቅና እና ሽልማት
መምህር መዝገቡ በፈጠራ ስራው በሀገር አቀፍ፤ በክልልና በዞን ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶች ያገኘ ሲሆን፤ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች ውድድር ላይ ቀርቦ የእውቅና ሰርተፍኬትና የነሃስ ሜዳሊያ ሽልማት አግኝቷል።
በስራ ላይ ያጋጠሙ ፈተናዎች
የፈጠራ ስራዎች ተግባራዊ ሆነው ህብረተሰቡ ዘንድ እንዲደረሱ በማድረግ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በዚህም የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ማበረታቻ ማድረግ እንዳለባቸው ይታመናል። መምህር መዝገቡም ለፈጠራ ስራዎቹን በሚፈልገው መንገድ ለማስኬድ የሚያወጣው ወጪና ስራው የሚያስገኘው ትርፍ የማይጣጣም መሆኑን ይጠቁማል። በዚህ ረገድ ለፈጠራ ስራዎች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ስራውን ችላ እንዲለው እንዳደረገውም ይናገራል።
እንደ መምህር መዝገቡ ገለጻ፤ የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ስልጠና በመስጠት እገዛ አድርጎለታል። ይህ የሚመሰገን ቢሆንም፤ የሚመለከታቸው አካላት ግን ለማበረታታት ችላ ማለት የለባቸውም። በዚህ በኩል የግል ተቋማትም የፈጠራ ባለሙያችንን ቢያግዙትና ቢያበረታቱት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
ወደፊት ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች እያዘጋጀ ለማቅረብ በትጋት እየሰራ መሆኑን የሚገልጸው መምህር መዝገቡ፤ ሽልማትና ማበረታቻ የሚያስገኙ ዝግጅቶች በትምህርት ቤት መዝጊያ ወቅት ባይደረጉና ይልቁንም በመክፈቻ አካባቢ ቢሆን መልካም ነው። ምክንያቱም፤ በዓመቱ የትምህርት ማብቂያ አካባቢ የሚደረገው ሽልማት የመረሳት እጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል፤ አስታዋሽም ያጣሉ ይላል።
የመምህር መዝገቡ የፈጠራ ስራዎች በከፊልም ቢሆን ህብረተሰቡ ዘንድ ደርሰው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛል። እኛም የፈጠራ ባለሙያዎችን ከማበረታታትና ከመሸለም በዘለለ ለማህበረሰቡ ጥቅም ላይ ለማዋል መስራት እንደሚያስፈልግ ለመጠቆም እንወዳለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/ 2012 ዓ.ም
ወርቅነሽ ደምሰው