የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት «የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት»ን የሚከለክለውን አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል። አዋጁ እንዲረቀቅም ሆነ እንዲጸድቅ ሲደረግ ከምንም መነሻ ሳይሆን ትልልቅ መግፍኤ ምክንያቶች አሉ።
ከእነዚህም መካከል በዋና በዋና መገናኛ ብዙኃንም ይሁን በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ሲለቀቁ የተስተዋሉ ያልተገቡ ሀሳቦችና አስተያየቶች፤ እነሱም ያስከተሏቸው ጥቃትና ጉዳቶች ናቸው።
በተለይ ሁለተኛ ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ጊዜ የቀረውንና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የተፈጠረው የነፃነት አውድ ላልተገባ ድርጊት የሚጠቀሙበት ወገኖች እየበረከቱ መጥተዋል።
እነዚህ ወገኖችና ግለሰቦች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት ሽፋን በማድረግ ሁከት የሚቀሰቅሱና ግጭት የሚፈጥሩ ሀሰተኛ ወሬዎችን በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት በማሰራጨት በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮች፤ ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለወደመው የሕዝብና የአገር ንብረት ምክንያት ሆነዋል።
ከሁሉም የከፋው ደግሞ እነዚህ ሀሰተኛና የጥላቻ ወሬ አሰራጮች ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ከመጠቀም ባለፈ ሆን ብለውና አቅደው ብሔርን ከብሔር፤ የአንድን ሃይማኖት ተከታይ ከሌላው እምነት አማኝ ጋር የሚያጋጩ ንግግሮችን እና ጸያፍ ሀሳቦች በማሰራጨት በፈጠሩት ሁከት ግለሰቦች ዱላ ተማዝዘዋል፤ ማህበረሰብ ከማህበረሰብ ተጋጭቷል።
በርካታ ሕዝብም ለትውልዶች ከኖረበት ቀዬ ተፈናቅሏል። ይህ ሁሉ ሲሆን ሀይ ባይ ወገን መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን፤ ድርጊቱ ከመከሰቱ በፊት የሚያግድ፤ ከተከሰተ በኋላም የሚያርቅ ሕግ በአገሪቱ ባለመኖሩ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ከዚህ በኋላ ይህ መቀጠል የለበትም፤ ሊቆምም ይገባል። ምክንያቱም እንዲህ ያለው ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ብሔርን ከብሔር፤ ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ተግባር የጥቂቶች፤ በተለይም በድርጊቱ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ ወገኖች ብቻ ድርጊት በመሆኑ ነው። እንጂ ሕዝቡማ ቀድሞውንም አብሮና ተሳስቦ የኖረ፤ ወደፊትም በዚሁ መስመር ተቻችሎ የሚኖር ነው።
አሁን የጸደቀው ይህ አዋጅ የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፤ በህትመት፤ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ በጽሑፍ፤ በምስል፤ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ እንደሆነ ደንግጓል። ይህ እንደ ሕግ መታወጅ ያለበት ነው። ምናልባትም ከጊዜ አንጻር የዘገየ ይባል እንደሁ እንጂ ተገቢም ነው።
ሕጉ ለሕዝብ ውይይት በቀረበበት ወቅት በርካታ ወገኖች በሕገመንግሥቱ የተቀመጠውን ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ይገድባል፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተገለጹትን ይሽራል፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ያለፈውን የጸረ ሽብር ሕግ ይመልሳል በሚል ስጋታቸውን ገልጸው ነበር። በተደጋጋሚ በተደረገው ምክክርም እነዚህን ስጋቶች ጨምሮ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረቡ አስተያየቶችን ያገናዘበ ርምጃ ተወስዶ በርካታ ማስተካከያዎች ተደርገውበት የጸደቀ ነው። እናም አዋጁ ስጋቶችን የቀነሰ ችግሮችንም ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ማለት ይቻላል።
በተለይም ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት፤ የአንዱን እምነት ተከታይ በሌላኛው ላይ እንዲነሳ የማድረግና ግለሰቦችን በአካላዊ ማንነታቸው የበታችነት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ንግግሮችና የሚሰራጩ ዜናዎች ከጅምሩ መቆም ያለባቸው በራስ ነው። በህሊና ተቆጭነት፤ እናም ግለሰቦች እራሳቸውን ከእንዲህ ዓይነት ንግግር እና ተግባር ሊያርቁ ይገባል። ማህበረሰቡም በውስጡ ያሉትን እንዲህ ዓይነት ሀሳብ የያዙ አካላት ሀይ ሊላቸው፤ ወጥተውም ቢገኙ እምቢኝ አልቀበልም ሊላቸው የግድ ነው። ይህ ከሆነ በኋላ ነው የሕግ እና የተጠያቂነት ጉዳይ የሚመጣው።
በዚህ ረገድ የአዋጁ መውጣት አንድና ዋነኛ ጉዳይ ነው። አዋጁን ማስተግበር ደግሞ ትልቁ የሕጉ ፋይዳ ነውና መንግሥት የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል እንላለን። ማህበረሰቡም የሕጉ መውጣት አጋዥ ጉልበት መሆኑን ተገንዝቦ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ሊያርማቸው፤ ሲያልፍም አልቀበልም ሊላቸው ይገባል። ግለሰቦችም ዳኝነት የሚጀምረው ከራስ ነውና በህሊና ዳኝነት ተገዝተው ከእንዲህ ያለ ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2012