
እውነተኛ ታሪክ ነው የምነግራችሁ። እግር ጥሎኝ ሳይሆን እግሬ እስኪነቃ ተመላልሼ ያየሁትን። በተመላለስኩበት የህዝብ “ አገልጋይ “ መሥሪያ ቤት የገጠመኝ “እውነትም የህዝብ አገልጋይ” እንድል አነሳስቶኛል። ወሬዬን ልጀምር ። ሰብሰብ ብለን የተቀመጥነው አንደኛ ፎቅ ላይ የሚገኙትን ሥራ አስኪያጅ ለማግኘት ነው። ከእርሳቸው የሥራ ሰዓት መግቢያ ቀደም ብለን በቦታው ተሰይመናል። ቀደም ብለን የመጣነው ባለጉዳዮች በኮሪደሩ ላይ ተጣብቀው በተቀመጡት የእንግዳ ማረፊያ ወንበሮች ላይ ቁጭ ብለናል። እኔም አንዷ ነኝ። በተደጋገሚ መመላለስ እና ሃላፊው እስኪመጡ ቆሞ መጠበቁ ስለሰለቸኝ በጠዋት ተገኝቼ ያችን የማትሰለች፣ የማትደክም፣ እንደሌላው ባለጉዳይ ኡ…ኡ… የማትል ወንበር ላይ ተቀምጠናል። ይሄ መብራት ሃይል ገርጂ ቅርንጫፍ ተብሎ በሚታወቀው ተቋም ውስጥ ነው።
እዛ ታዲያ ያለውን ብሶት ለሰማ፣ በየቀኑ የሚመላለሰውን ባለጉዳይ ለታዘበ አይ ሀገር ! አይ አገላጋይ የመንግሥት ሠራተኛ ! አይ አመራር! አይ ለውጥ!… ብሎ አፉን በነጠላው ይዞ ለማሽማጠጥ ያስነሳል። ግን ምን ዋጋ አለው። በየቀኑ ብሶት በየቀኑ ኡ.. ኡታ መስማት። አንቺስ ካላችሁ እኔማ ሦስት ወር በተደረገ ያላሰለሰ መመላለስ ሌላም ተጨማምሮበት በሦስት ወሩ ተሳካልኝ። ተሳካላኝ ስላችሁ ታዲያ ቀላል እንዳታደርጉት። ጠዋት ስባል ጠዋት፣ ከሰዓት ስባል በተባለው ሰዓት ከች ብዬ ፤ ሲስተም የለም፣ ባለሙያ አልገባም… የሚሉ ምክንያታችን ሁሉ አልፌ ነው። ሌላው በተለይ አቅመ ደካማው ፣ ከአለቃው በስንት መከራ ፈቃድ እየጠየቀ የመጣው ሁሉ ያለ ውጤት ተንገዋሎ ይመለሳል። እግዜር ብሎ ከሃላፊው ከተገናኘ ደግሞ ባለሙያ አለ መኪና ስለሌለ ነው። ወይ ደግሞ እኛ ምን እናድርግ ወደ በላይ ሂዱና አቤት በሉ የሚል መልስ ያገኛል። ከመብራት ሃይል አገልግሎት ማግኘት እንዲህ ቀላል አይምሰላችሁ። የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ህዝብን ማስለቀስ፣ ማበሳጨት፣ ማሰቃየት ብርቅ ነው እንዴ። አንቺ የትነበርሽ? የምትሉ ካላችሁ የአሁኑ ባሰ ብዬ እንጂ ቀድሞም ተገልጋይ ነኝ። አውቀዋለሁ በተለይ በመብራት ሃይል መስሪያ ቤት በኩል የሚማረር እንጂ የሚደሰት አልሰማሁም።
የሰማሁት ሁሉ እውነት ይመስለኛል። ማለቴ ሁሉንም ነገር እውነት ነው ብዬ ባልልም አንዳንድ ነገሮችን እውነት ናቸው ብዬ እቀበላለሁ። በተለይ በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሲነገሩ እውነት እውነት ይሸቱኝና አምናለሁ። አሁን አሁን ሳስበው ግን እውነቱ ያለው እውነት ነው ብሎ በተናገረው ሰው አንደበት ላይ ብቻ ነው ። በተግባር ግን ያው እንደተለመደው። ኧረ እንዳውም ባስ ባለ መልኩ ህዝብ እየተማረረ ነው። አገልግሎት ለማግኘት የተገለገለበትን ሂሳብ ለመክፈል፣ ለብልሽት ወይም ለሌላ ጉዳይ የመጣው ሁሉ ያዝናል! ወዴት ሄደን አቤት እንበል ሲልም ይደመጣል። በዛ ሰሞን አንድ የኢትዮጵያ ቴሌቪዝን ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል የሥራ ሃላፊን ሲያነጋግር ችግሮች እያለ ያነሳቸውን ሀሳብ ከነመረጃው እያቀረበ ሲያፋጥጥ ሳይ ምን አለ ሁሉም የሥራ ሃላፊና ባለሙያ በዚህ መልኩ የሚያጋልጠው በመጣ ስል የየዋሆች ሀሳብ አሰብኩ። ግን እንደማይሆነ አውቃለሁ። ቢሆንም ይሄ የሀገሪቱ ችግር ነው። ይሄ ከእኛ በላይ ነው። ዕቃ የለም። ዶላር ስሌለ ነው … የሚባሉ ምላሾች እንደሚበዙም እገምታለሁ ።
አንድ በእድሜ የገፉ አዛውንት እናት ከወደ ገርጂ አካባቢ የሚመላለሱ መሆኑን ነግረውኛል። ይሄ ጭውውት እዛው በተገናኘንበት የመብራት ሃይል ግቢ ውስጥ ነው። አንድ አይነት ክንፍ ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ ይባል የለ። እኛም የጋራ የሚያደርገን እንግልት አለና በየጊዜው በመገናኘት ተግባብተን የአንቺ የአንተ ችግር ምንድነው ? ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ ? እያልን መነጋገሩ መፍትሄ ባይሆንም የውስጥን እንፋሎት ያወጣልና እንወያያለን።
እሳቸው ታዲያ እንደነገሩኝ ቆጣሪያቸውን አሁን ካለበት ተነስቶ ወደሌላ ቦታ እንዲዛወርላቸው ነው የጠየቁት። ይህንን ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት የማስነሻ ክፈይ ተብለው ከፍለዋል። ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ይነሳል የሚልም ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። ሆኖም ምላሹ የውሃ ሽታ ቢሆንባቸው በየጊዜው እየተመላለሱ ኧረ አልተሠራልኝም፤ ዝናብ ከዘነበ ቆጣሪው ከተንጠለጠለበት የጭቃ ግድግዳ ላይ ስለሚወድቅ አደጋ እንዳይደርስብኝ እባካችሁ አንሱልኝ ይላሉ። ታዲያ አንድ ቀን ሃላፊው ባለሙያ ጠርቶ እስኪ የሚቀየርበትን ቦታ ምንም ምን እንደሚያስፈልገው ተመልከት ብሎ ያዘዋል። ባለሙያውም የራሱ ስልጣን አለ አይደል “መኪና የለም” ሲል ይመልሳል። ይሄን ጊዜ ሃላፊው ይሄ ፖል የሚጭን መኪና የማያስፈልገው ሥራ ስለሆነ እንዲህ አይነቱን ባለጉዳዩ መኪና እያቀረበ ሥሩ ሲል ያዛል። እርሳቸው ይሄ ከአንደበቱ ከወጣ ብለው ኮንትራት ላዳ ታክሲ በማቅረብ ባለሙያውን ይዘው ይሄዳሉ። ባለሙያውም እቤት ድረስ ሄዶ ይመለከትና “ እማማ ይሄ ቀላል ነው ስምንት መቶ ብር ከከፈሉኝ አሁኑኑ ላንሳሎት” አለኝ። እኔ ደግሞ እንዴ ለመንግሥት ከፍያለሁ ሌላም የለኝ አልኩት። እሱም ሳይሰራው ተመለሰ። አሁን ሳስበው መንግሥት መጥቶ ይስራሎት ያለኝ ይመስላል። ይሄው ሁለት ወር ሞላኝ ማን አባ ከና ይበለኝ። እነሱም ያንገላቱኝ እኔም አልሰለች ብዬ እመላለሳለሁ። አቤት የሚባልበት የለ፤ ተቆጪ የለ ሁሉም አንድ ናቸው ። ሃላፊውም የእነሱ አይነት ሳይሆን አልቀረም ባለጉዳይን ከምንም አይቆጥርም። ሰውም አይከብደውም። ብቻ ከወዲያ ወዲህ እያመላለሱኝ ይሄው አለሁ። እያሉ የሆዳቸውን ሁሉ ዘረገፉ።
ሌላዋ ቀጠለች። ምን ሁላችን እያየን አይደል ስትል። የአገልግሎት ክፍያ ለመክፈል እንኳን የሚመጡ ባለሆቴል የመሳሰሉት ንግድ ቤቶች ክፍያቸው የሚከፈለው በውስጥ ሠራተኞች አማካይነት ነው። ሁሉ ነገር በሙስና ስትል አከለች። አሁን አጠገባችን ለአንዱ የቴክኒክ ባለሙያ በስሙ ጠርቶ ሁለት የታሰረ ባለ መቶ ብሮች ሰጥቶ ክፈልና ቀሪው የቁርስ ነው ሲለው በጆሮዬ ሰምቻለሁ፤ በአይኔ አይቻለሁ እያለች የታዘበችውን አከለች። ሁላችንም ብሶታችንን ብናወጣው ነገር በአህያ አይጫንም እንደሚባለው ይሆንብናልና እንዳው ብቻ ኧረ የተሰጣችሁን ሃላፊነት በአግባቡ ህዝብን አገልግሉበት ልንል ወደድን።
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር