ትወና የዓለም ቋንቋ ነው።ሰዎች ስሜታቸውን ማለትም ኀዘናቸውን፣ ደስታቸውን፣ ትዝብታቸውን፣ ቁጭትና ምሬታቸውን፣ ፍቅራቸውን ወዘተ ግልጥልጥ አድርገው ያዩበታል።ከዚያም አልፈው በገፀ ባህሪያቶቹ ውስጥ ራሳቸውን እየፈለጉ ‹‹ይህ የእኔ ታሪክ ነው›› የሚሉበት ጊዜም እልፍ ነው። በደራሲው የተጻፈው ተውኔት መድረክ ላይ ሲመጣ ‹‹እንዲህ ነበር እንዴ የፃፍኩት›› እስከማለት ደርሶ ራሱን እንዲጠይቅ ጭምር ያደርገዋል።ለዚህ ሁሉ እንደ ቅመም አሊያም ልክ እንደ ቀለበት ፈርጥ ጥበቡ ላይ ነፍስ የሚዘሩበት ተዋንያን ናቸው።
ዛሬ ከላይ ላነሳነው ወግ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነንን አንድ ተዋናይ ልናወድስ ወደናል። ለዘመናት ከሰው ልጅ ጋር መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያለ እና አብሮ የዘለቀውን የትወና ጥበብ የተረዳና ህይወቱን ሙሉ ተላብሶት የኖረ ነው። እርሱ ትልቅ የመድረክ ፈርጥ ነው። በህይወት ዘመኑ በትወና ጥበብ ላይ ባህልን፣ ሀገራዊ አንድነት፣ ደስታና ኀዘንን፣ ፍቅርና ጥላቻን ፣ ውስጣዊ ስሜትን እንዲሁም የተለያዩ መልካም ሃሳቦችን የሚያንፀባርቁ ትወናዎች ላይ ተሳትፎ ድንቅ ችሎታውን ማስመስከር ችሏል። በቻለው ሁሉ ሃሳቡን ሳይሸሽግ ለመድረክ በማብቃት ይታወቃል። የዛሬው የ “ህይወት እንዲህ ናት” አምድ እንግዳችን ያደረግነው ባሳለፍነው ሳምንት መድረኩን ተሰናብቶ ስራዎቹን ለትውስታ ትቶ የተለየንን አርቲስት ጀንበሬ በላይ ን ነው።
አርቲስት ጀምበሬ በሚሳተፍባቸው የመድረክ ቲአትሮችና የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ለሕዝብ ከመድረሳቸው በፊት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ እንዲዘጋጁ የሚለፋ ሰው ነበር። ከዚያ ሲያልፍ ከጓደኞቹ ጋር በሚገባ ተሟግቶ መድረኩ ሲያምር የሚደሰት፣ በውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፈ ሥራ ወዳድም ጭምር ነበር። በጓደኞቹ ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ‹‹መተወን እንደ ጀምበሬ›› የሚባልለት እንደሆነም ይነገርለታል።እርሱ ተወዛዋዥም፣ ሙዚቀኛም፣ የማይም ድራማ ባለሙያም፣ የሜካፕ አርቲስትም፣ የድራማቲክስ ዳንስ ጌጥም ነበር። ከእርሱ በተለይ በጥበቡ ዘርፍ እና በህይወት ክህሎት ብዙ መማር ይቻላል።አርቲስት ጀንበሬ ያልተነገረለት ግን የሁለገብ ሙያ ባለሙያ ነበር። ለሙዚቀኞች፣ ለተወዛዋዦችና ለተዋናዮች ያደረገው ነገር በቀላሉ የማይገለጽ የጥበብ ፈርጥ መሆኑን አስመስክሮለታል።ንፉግ ሳይሆን ለሙያው መምህርም ነበር። ለኢትዮጵያ ዘመናዊም ሆነ ባህላዊ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ እንዲሁም ተውኔት አሻራቸውን ካኖሩ እና ሕይወታቸውን ለዚሁ ዘርፍ ለሰጡ ከዘርፉ ተዋንያን መካከል በቀዳሚነት የሚነሳ ነው። አሁን ቀኑ ደርሶ የማይቀረውን የህይወት ስንብት አድርጓል።
ልጅነት
አርቲስት ጀምበሬ ማንጎራጎርና መተወን የጀመረው ገና ልጅ እያለ እንደነበር አብሮ አደግ ጓደኞቹ ይናገራሉ ።በአካባቢው በእነርሱ ጊዜ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ባይኖርም በተለያየ አጋጣሚ ሰፈሩ ብቅ የሚሉ ሙዚቀኞችን የማግኘት እድል ነበረው። ይህ መነሻ ሆኖት የእነርሱን ድምጽ ለማስመሰል ጥረት ያደርግ ነበር።በየሰርጉና ክርስትናው ላይም ቢሆን ጥሩ ዘፈን አውራጅና ተወዛዋዥ ነው።ያን ጊዜ ይመስላል እድሜውን ሙሉ ያሳለፈበትን ወዳጁን የትወና ሙያ የተዋወቀው። ይህን ለማዳበር ደግሞ ከብዙ ጥረት በኋላ ብሄራዊ ቴአትር መቀጠር ቻለ።ነብሱ የወደደችውን አግኝታም እስከ ህይወት ፍፃሜው ድረስ ከትወናው ጋር ላይፋቱ ተጋመዱ።
አርቲስት ጀንበሬ በትምህርት ቤትም ቢሆን ተመራጭ ተዋናይ ነበር።የተለያዩ ግጥሞችን በተማረበት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመድረክ ላይ በማቅረብ ተማሪን ያዝናናል።ህዝብ ለማዝናናትም የሚሰሩ ድራማዎች ላይ የተለያዩ ቦታዎች እየተሰጡት ይተውናል።ይህ ደግሞ በራስ መተማመኑንም ችሎታውንም እንዲያዳብር ረድቶታል።
አርቲስት ጀምበሬ በቀድሞ አጠራሩ ጎጃም ክፍለ ሀገር ሞጣ ወረዳ ቦሃ ገብርኤል በ 1933 ዓ.ም ነበር የተወለደው። የትውልድ ቀዬው ገጠራማ ስፍራ በመሆኑ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብት አግዶ ፣ ጭቃ አቡክቶ የተለያዩ ጨዋታዎችን ተጫውቶ አድጓል።
በአካባቢው ባህል ዘንድ ለታላላቅ አለመታዘዝ ነውር ነውና እርሱም እዚያ በቆየበት ጊዜ ሁሉ ለጎረቤት ይታዘዛል።ለአዛውንቶች ውሃ በመቅዳት፣ እርሻና አረም በማረም እንዲሁም ከጫካ እንጨት በማምጣት ይደግፍ እንደነበር አብሮ አደጎቹ ያስታውሳሉ፡፡
አቶ አውላቸው አንዳርጌ አብሮ አደጉ ናቸው። አርቲስት ጀምበሬ በእርሳቸው አንደበት ሲገለፅ ‹‹ፍጹም ተፈጥሮ የቸረችው ደግነት ያለው›› ይሉታል። በተለይ ካለው ላይ ማካፈል የሚወድ እንደነበር ይገልፁታል።ከልጆች ጋርም በፍቅር መጫወትን የሚያዘወትር እንደነበር ያነሳሉ።‹‹በእርግጥ የእኔና የእርሱ እድሜ አይመጣጠንም በትንሹ አስር ዓመት ይበልጠኛል›› በማለትም ከወንድማቸው እኩል ስለነበረ በአጋጣሚው ይህንን ያህል እንዳወቁት ይገልፃሉ።
የአርቲስት ጀንበሬ አብሯደግ በተለይ ከወንድሞቻቸው ጋር ጨዋታ ላይ በሚሆኑበት ሰዓት ብዙ ትዝታ እንደነበራቸው ይናገራሉ። በልጅነት ጊዜ የሚያስታውሱት በዛፍ ላይ መንጠላጠሉን ነበር።ይህ የሚፈጠረው ደን ውስጥ ገብተው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ለመመገብ በሚያደርጉት ትግል ነበር።በተለይ ሾላ፣ እንኮይ፣ አጋምና ቀጋን ከዛፎቹ ላይ እየተንጠለጠሉ አውርደው ሲሰጧቸው በጣም ይደሰቱ እንደነበር አይረሱትም።‹‹እርሱ ከሌለ ምንም ያህል አንበላም።ምክንያቱም ከዛፉ ላይ ለማውረድ ሁላችንም እንፈራ ነበር›› የሚሉት አቶ አውላቸው፤ ወንዝ ወርደው የሚያደርጓቸው ነገሮች ያስደስታቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ትምህርት
ልምድ ብዙ ነገር ያስተምራል።እናም እንግዳችንም ልምድ ያስተማራቸው አንጋፋ የተውኔት ባለሙያ ናቸው።በእርግጥ ፊደልን ከአባታቸው ዘንድ ተምረዋል።ቀጥለውም ይህንን እውቀታቸውን የበለጠ ለማዳበር በአካባቢው ዘንድ የተለመደውንና ለዘመናዊ ትምህርቱ አቅም ይፈጥራል ተብሎ ወደሚታሰብበት የቆሎ ትምህርት ቤት ገብተዋል፡፡
በገብርኤል ቤተክርስቲያንም እስከ ዳዊት ከተማሩ በኋላ ዘመናዊው ትምህርት የበለጠ እንደሚጠቅማቸው ስለተረዱ እንዲሁም በኪነጥበቡ ዘርፍ መሳተፍ ስለሚሹ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት እስከ አምስተኛ ክፍል መማራቸውን ማህደራቸው ያስረዳል።
በትምህርት ቤት ቆይታቸውም ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩና በዚህም ከክፍል ክፍል ሲዘዋወሩ አንደኛ በመውጣት እንደነበር ሰርተፍኬታቸው ያሳያል። ሆኖም ግን በተለያየ ምክንያት በቀለም ትምህርታቸው መግፋት አልቻሉም።የአገር ፍቅርና የብሄራዊ ቴአትር የትወና ሙያና መክሊታቸው በልቦናቸው ሚዛን ስላነሳ የትምህርቱ ነገር ጊዜ አጣ፡፡
የትምህርት ቤት ቆይታቸው በዘመናዊው መንገድ ብሔራዊ ቴአትር ገብተው አቶ ማቲዎስ በቀለ ከሚባሉ የቴአትር መምህር ዘንድ ተሞርዷልና በብዙ ሙያ የእውቀት ባለቤት መሆንም ችለዋል።በእርግጥ ይህ የሆነውም በምክንያት ነበር። የትምህርት ማህደራቸው እንደሚያትተው፤ እዚህ ሙያ ውስጥ እንዲገቡ የሆነው መምህራቸው ከዚህ ቀደም ያሰለጠኗቸውን ተዋንያን ፎቶ በመስታወት አድርገው ሲለጥፉና ማንነታቸውን ሲናገሩ በመስማታቸው ነበር።
አርቲስት ጀንበሬ ‹‹የእኔም ስም ዘላለም የሚቀመጥና ማንነቴን የሚነግርልኝ ያስፈልገዋል›› ሲሉ ተዋናይ ለመሆን ወስነው ተመዘገቡ። ማህደራቸው የትወና ትምህርትን ከመምህር ማቴዎስ እንደቀሰሙ ያስረዳል።ከዚያም አልፈው ከተለያዩ መምህራን ዘንድ የማይም(ድምጽ አልባ) ድራማ፣ የድራማቲክ ዳንስ፣ የሜካፕ ሥራና መሰል ትምህርቶችን ተምረዋል።
በልምዳቸውም ቢሆን የተለያዩ ስልጠናዎችን በሚሰጡበት ጊዜ የነበራቸውን ክህሎት ማዳበራቸውን ፋይል የተደረገው ማስረጃቸው ያስነብባል።
40 ዓመታትን በመድረክ
ባለታሪካችን ብዙዎች ብዙ የሚነገር አለው።ከሥራ አጋሮቹ ብንነሳ «ጀንበሬ ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች መኖር የታገለ ነበር» ሲሉ ይገልፁታል።ምክንያታቸው ደግሞ ስራው ዝም ተብለው የሚተዉ አለመሆኑንና ዘመን ተሻጋሪ እንደሆነ በምክንያትነት ያነሳሉ።በተለይ ለበርካታ ጊዜ በሚታይ ቴአትር የመድረኩ ንጉስ በመሆኑ ብዙዎች ይሳብበት ነበር።በመድረክ ትወና ከ40 ዓመታት በላይ ቢያገለግልም ህይወቱ እስካለፈበት ድረስ ምንም የመሰልቸትና ጡረታ የመውጣት ሃሳብ አልነበረውም።ስለዚህም በትምህርት ሳይሆን በልምድ የቀሰመው የልዩ ተሰጦው ባለቤት እንደሆነ ማንም የሚናገርለት እንደሆነም የሙያ አጋሮቻቸው ያስረዳሉ፡፡
«ጀንበሬ የመድረክ ሥራ ከነሙሉ ክብሩ የሚታይበት፣ የተውኔቱ ህልውና የሚገለጽበት ጥበበኛ ነው፡፡» ሲሉም ይመሰክሩለታል። ለዚህም ማሳያ ብለው የሚያነሱት ደግሞ በአጋጠመው እስራት ተስፋ ይቆርጥ እንኳን ጥበብን ሳይተው በቀጥታ ‹‹ክራርና ፈትለሽ ልበሽ፣ የውሸት ተራራ›› የተሰኙት ቴአትሮች ላይ በመሳተፍ ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱ ነው።ቀጥሎ በዚያው ዓመት በዚያው ሥራውን ሀ ብሎ በጀመረበት ሀገር ፍቅር ቴአትር የምስጢር ዘበኛ፣ ኢትዮጵያ የተሰኙ ቴአትሮች ላይ መተወኑም አንቱታን አትርፎለታል።
አርቲስቱ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከ1949 እስከ 1952 ዓ.ም የሰራ ሲሆን፤ በተለያዩ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።ከዚያ ሙያውን እያሰፋ በመምጣቱና ተፈላጊነቱ በማየሉ በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ቴአትር ቤት እንዲያመራ ሆኗል።ብዙ አንጋፎችንም ያወቀውና ለሙያው ልዩ ፍቅር እንዲያድርበትም የሆነው ከዚህ በኋላ እንደነበር የታሪክ ማህደሩ ያትታል።
አንጋፋው አርቲስት ጀምበሬ በላይ ከ1953ዓ.ም እስከ 1988 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመድረክ ትወና የሰራ ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት አርቲስቱ ከተወኑባቸው ሥራዎች መካል የአዛውንቶች ክበብ፣ ኦቴሎ፣ የከተማው ባላገር፣ ሐምሌት፣ ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የእጮኛው ሚዜ፣ የልብ ፅጌሬዳ፣ አንድ ዓመት ከ አንድ ቀን፣ የፌዝ ዶክተር፣ የእግር እሳት፣ የሚስጠር ዘብ፣ የድል አጥቢያ፣ አመጽ በየገጹ፣ ያስቀመጡት ወንደላጤ፣ የበጋ ሌሊት ራዕይ፣ አበሻ በዘመኑ፣ አሉላ አባነጋ፣ እናት አለም ጠኑ፣ ሻጥር በየፈርጁ የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
እንግዳችን በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ከሰራቸውን ተውኔቶች ውጪ በየክፍለ አገሩም በመዘዋወር ያቀርብ ነበር።
ከእነዚህ መካከልም ሞረሽ፣ የፍቅር መጨረሻ፣ ትግላችን፣ የድል አጥቢያ አርበኛ፣ ምኞቴ፣ በልግ፣ ጎንደሬው ገብረማርያም፣ አቶ ተማቹ፣
ሰላም በምድር፣ እኝ ብዬ መጣሁ፣ ለሰው ሞት አነሰው የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸው።
አርቲስት ጀንበሬ ሥራዎች ከመድረክ ትወናም ያለፉ ናቸው።ለምሳሌ በሜካፕ ሥራ የሰለጠነ በመሆኑ ለተውኔቱ ብቁ ሰዎችን በመስራት ተውኔቱ በመድረክ ላይ ሙሉ ሆኖ እንዲታይም ያደርጋል።በተመሳሳይ የድራማቲክስ ዳንስ ባለሙያም ነበር።ከዚያ ሻገር ሲልም የቴሌቪዥን ድራማዎችም በመስራት ይታወቃል። እርሱ የሚተውንበት ድራማ እያለ ሌላ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የሚከፍት እንደማይኖር በልበሙሉነት የሥራ ባልደረቦቹ ይመሰክሩለታል።
አርቲስት ጀንበሬ ከሰራቸው የቴሌቪዥን ድራማዎች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት የዘመቻው ጥሪ፣ አመልአለብኝ፣ ግራ የገባው ግራ፣ ያልተከፈለው እዳ የተሰኙት ሲሆኑ፤ በእነዚህም ድንቅ ስራዎቹ በተመልካች ልብ ውስጥ ቦታ አግኝቷል።
ባለታሪካችን ይህንን ድንቅ የጥበብ ባለሙያነቱን በአገር ውስጥ ብቻ የገደበው አልነበረም።ይልቁንም ከአፍሪካ አልፎ አውሮፓ ድረስ ተሻግሮ ስራዎቹን አቅርቧል።ለአብነትም ከአፍሪካ በሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ የመሳሰሉት አገራት በመሄድ አንቱታን ያተረፉለትን ሥራዎች ሰርቷል። ወደ አውሮፓ አገራት ደግሞ ስንሻገር ካናዳና ሜክሲኮ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በአገር ባህልና በውዝዋዜ ዘርፍ ከ1948 እስከ 1964ዓ.ም በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ቴአትር
እንደሰራ የሚነገርለት አርቲስት ጀንበሬ በላይ፤ በሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ በሴኔጋል፣ በናይጀሪያ በሰራቸው ስራዎች የማይዘነጋ ትውስታን ጥሎ አልፏል።በተለይም የአገር ገጽታ ግንባታ ላይ አሻራውን አሳርፏል።በተጨማሪም በአልጀርስ፣ ሌጎስና የመን ላይ በሰራው ትወናም ይታወሳል።
እንግዳችን በሚሰራቸው ተውኔቶችና በሌሎች ተግባራቱ ውስጥ ኢትዮጵያን ሳያስተዋውቅ ቀርቶ እንደማያውቅ ይነገርለታል።አገር ወዳድነቱ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።ለዚህም ደግሞ ከታሪክ ማህደሩ የተገኘው ማስረጃ እንደሚያመለክተው ከኬንያና ሴኔጋል ልዩ ሽልማት ተበርክቶለታል።በተመሳሳይ በትወና ከእነዚህ አገራት የተለያዩ የምስጋና ወረቀቶች ተሰጥተውታል።
በአገር ውስጥም በሰራው ሥራ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የምስጉን ሰራተኝነት ሽልማት ተበርክቶለታል።ይህ የምስጉን ሰራተኝነት የምስክር ወረቀት በሚሰራቸው የጥበብ ሥራዎችም የተበረከተለት እንደሆነ የህይወት ታሪኩ ላይ የተጻፈው ማስረጃ ያትታል።
ማህበራዊ ተሳትፎ
በየክፍለ አገሩና ጦር ግንባር በመሄድ ሰዎች ተዝናንተው የፈለጉት ስኬት ላይ እንዲደርሱ ያደረገው አርቲስቱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ለህዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለመስራት ሲያስብ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ይወጣል።ከዚያ አለፍ ሲባል ደግሞ ሙሉ ጊዜውን የሚያሳልፈው ከጥበብ አጋሮቹ ጋር በመሆኑ ለእነርሱም እስከሞት ድረስ መታገልና ለስኬታቸው የሚጥር መሆኑን ከባልደረቦቹ ሰምተናል።
አርቲስት ጀንበሬ ለሙያው ልዩ ፍቅር ያለው በመሆኑም በተለይም ከ 1948 እስከ 1949 ዓ.ም በተለያዩ ክፍለ አገር ሄደው በሚሰሩበት ጊዜ ከሌሎቹ አጋሮቹ ይልቅ ቅድሚያ ሃላፊነቱን በመውሰድ ተጠያቂነቱን ተወጥቷል።
ብሔራዊ ቴአትር ባዘጋጀው የህይወት ታሪክ ላይ እንደተቀመጠው፤ አርቲስቱ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የመጡ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን ወደ ፊት ያመጣ እና የጥበብ ሥራዎቻቸው ከፍ ያለ ማማ ላይ እንዲቀመጥ ያደረገ ነው።ከዚያ ባሻገር አርቲስቶቹ በራሳቸው ቆመው ለራሳቸው እንዲኖሩና እችላለሁ ብለው እንዲያምኑ ያደረገም ነው።አገራቸውን እያሰቡና ለህዝባቸው እንዲኖሩ በማድረጉም ዙሪያ ትልቅ ሥራ ሰርቷል።
አንጋፋ እና ታታሪ የመድረክ ንጉስ ነው እያሉ የሚጠሩት አይነት በመሆኑም እንደ ሀገር ታላቅ የጥበብ ሰው ታጥቷል።እንዲህ ዓይነቱ ሙሉ የሆነ አርቲስት ማጣት እጅግ በጣም ልብ ሰባሪ ነው።ምክንያቱም ስለእርሱ የነገረለት፣ የተረከለት፣ የደገፈው ወይም የጠቀመው የለም።
አርቲስት ጀንበሬ በቀይ ኮኮብ ጥሪ ሳይቀር የተሳተፈ ነው። ብዙዎችንም አሰልጥኖ የሙያ ባለቤት አድርጓል።ዘማቾች ደስተኛ እንዲሆኑ በሙያው ያበረታ እንደነበርም የሥራ ባልደረቦቹ ይናገራሉ። በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሕብረ ዝማሬዎችን ከማቅረብ ባለፈ በየትምህርት ቤቱ እየሄደ ያሰለጥንም እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም።ይህ ደግሞ ማህበራዊ ተሳትፎውን የሚያጎላለት ነው ይላሉ።
በትወና ሙያ ውስጥ የኖረና የሞተ ነው የሚሉት ደግሞ ቤተሰቦቹ ሲሆኑ፤ ጀንበሬ ሰርቶ ሳይጠቀም ያለፈ ሰው ነው።በህክምና ሲረዳም ብዙዎች ሊደርሱለት የቻሉት ሥራዎቹ ሰው ወዳድነትን ስላተረፉለት ነው።ግን ይህም ቢሆን ለእርሱ ሥራ በቂ ክፍያ እንዳልነበረ ይናገራሉ።
የመንበረ ጸሐይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ካህንና ማህበርተኛቸው በበኩላቸው፤ ጀንበሬ ሰው ማስታረቅ የሚወድ፣ ጥፋትን ሁሉ በመልካም አስተሳሰቡ የሚረታ፣ ሁሌ ለመልካም ነገር የሚሸነፍና የተቸገረ ሲያይ የሚያመው ሰው ነው። በዚህም ብዙ ጊዜ ከሰው ተበድሮ ሳይቀር ሰዎችን ለመርዳት ይሞክራል።በተመሳሳይ እርቅ ሲፈጸም እንኳን እርሱ ከሌለ ይሳካል ተብሎ ስለማይታሰብ ለሰዓታት ይጠበቃል።ማህበራዊ ተሳትፎውን በቀላሉ ይህ ነው ተብሎ የሚገለፅ እንዳልሆነ ይነገራል። ቤተሰቦቹ አምላክ ስለፈለገው ነው የወሰደውና ብዙ ማዘን አይገባም ብለዋል መልካምነቱን ሲገልጹ።
ከሥራ ባልደረቦች አንደበት
አርቲስት ፍቅርተ ደሳለኝ ‹‹የፍቅር ሰው ነው፣ ሥራዎቹም ከዚህ ይመነጫሉ።ሙያውን በጣም ይወዳል:: ጀንበሬ እንደስሙ ለሰዎች ብርሃን ሲሆን የቆየ ነው። ባለበት ቦታ ሁሉ ሳቅና ደስታ የሚፈጥር፤ ከትንሹ ጋር ትንሽ፣ ከትልቁ ጋር ደግሞ ትልቅ በመሆን ቁም ነገርም ሆነ ጨዋታን የሚከውን ነው።የደግነት ምሳሌ እንደእርሱ አይቼ አላውቅም።ምክንያቱም ያለውን ሁሉ ለሰዎች ማካፈል የሚወድ ነው።እንደውም እርሱ ገንዘቡን ለሰው አድሎ እርሱ ባዶጁን በመሆን ሲራብም አስታውሳለሁ።›› ትላለች ለብዙ ዓመታት ከእርሱ ጋር እንደሰራች እየገለፀች።
ቀጥላም እንባ እየተናነቃትም ቢሆን ‹‹ጀንበሬ ለተተኪ ትውልድ ብዙ አርኣያ የሚሆን ተግባር የፈጸመ ነው።በእርሱ የሙያ ፍቅር ሁሉም ተዋናዮች ተሰርተዋል። ተወዛዋዥና ድምጻውያም እንዱ በእርሱ መርህ የሚሄዱ ናቸው።ምክንያቱም በጎነት መገለጫው ስለሆነ ክፉ ያደርግብኛል ብሎ የሚያስብ ሰው የለምና›› ትላለች። ሲመክራቸው ከገንዘብ በላይ ሙያና ሰው ውደዱ እያለ መሆኑን የምታነሳው ፍቅርተ፤ ምክሩና ጨዋታ ወዳድነቱ ዘላለም ከህሊናዋ እንደማይጠፋ ትናገራለች።እንደውም እርሷም ሳቂታና ተጨዋች የሆነችው ከእርሱ ጋር ብዙ በመስራቷ እንደሆነም ታስረዳለች፡፡
‹‹እኔን አሳድጎኛል፤ ከእኛ በፊትም ሆነ በኋላ ያሉ የቴአትር ቤቱ ተዋናዮችን አሰልጥኖ የሙያ ባለሙያ እንድንሆን ረድቶናል።በተለይም በሥራ ወዳድነቱ ሁልጊዜ የምቀናበት ሰው ነበር።እናም እርሱን እያየሁ ለሥራ ሰዓቴ ትኩረት እንድሰጥ ሆኛለሁ›› የሚለው ደግሞ ደራሲ፣ ተዋናይና ገጣሚ ጌትነት እንየው ነው።አርአያ መሆኑን ሲያስረዳም ‹‹ከእርሱ ጋር ብዙ ሥራዎች ብሰራ እድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር።ሆኖም ሁለት ቴአትሮችን ብቻ ነው የሰራሁት።በዚህ ቆይታዬ ግን ዘላለም የማይጠፋ ትምህርት ተምሬያለሁ።ሲቆጣኝ ፣ በፍቅር አይኑ ሲያየኝና ለእኔ ሙያውን ሲያጋራኝ ደስተኝነቴ በየቀኑ ይጨምር ነበር፡፡›› ይላል።
ከተውኔቱ ባሻገር ብዙ የውዝዋዜ ሥራዎችን አብራው እንደሰራች የምትገልጸው አንጋፋዋ የመድረክ ተወዛዋዥና ተዋናይት አልጋነሽ ተካ በበኩሏ፤ ከጀንበሬ ባህሪ ሁሉ አብልጬ የምወደው አገር ወዳድነቱን ነው ትላለች።ለዚህ ደግሞ በአብነት የምታነሳው በተለያዩ የአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገራት ተዘዋውረው ሲሰሩ የሚያደርገው ተግባራት ናቸው።አገሩን የሚያስተዋውቅበት ልዩ ተሰጥኦው በጣም ያስገርማት እንደነበርም ትናገራለች።
አርቲስቷ እንደምትለው፤ ተዋናይ ጀንበሬን ማጣት ብዙ ወርቆችን እንደመነጠቅ ነው።ምክንያቱም ደግነት ቁሞ ሲሄድ ማየት ከተፈለገ እርሱ ማሳያ ነው።የመድረክ ንጉስ ለመሆኑም መስካሪ አያሻውም።ግን ህመምና ሞት ተረባርበው ወሰዱት።እናም ስራዎቹን ከማስታወስ በስተቀር ምንም በእጃችን አይኖረንም ትላለች።ነብሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን ብቻ በማለትም ንግግሯን ትቋጫለች።
ቤተሰብ
አርቲስት ጀንበሬ ቤተሰቡን አጥብቆ የሚወድ፤ በማህበራዊ ህይወቱ ከሁሉ ጋር በፍቅር የሚኖር፣ ማህበር፣ እድርና እቁብ ላይ ትልቅ ተሳትፎ ያለው ለተቸገረም ደራሽ ነበር።በዚህም ለሰው እንጂ ለራሱ ያልኖረ ሰው እንደሆነ ይነገርለታል።‹‹በሰጠሁ ቁጥር ይሰጠኛልና ያለኝን ማካፈል ልምዴ መሆን አለበት›› ብሎ የሚያምንም እንደሆነ ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።በዚህም በሰራው ልክ ያልተጠቀመና ለቤተሰቡ መኖር ያልቻለ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ለቤተሰቡ ትክክለኛ አባወራ ነበር።የቤተሰቡ ኑሮ የተቃናና መልክ የያዘ እንዲሆን ለማድረግ የማይቆፍረው ድንጋይ አልነበረም።ያገኘውን ገንዘብ ጥቂት ቢሆንም ለባለቤቱ በመስጠት ጓዳ ጎድጓዳውን መሙላት የሚወድ እንደነበርም ባለቤቱ ይናገራሉ።ልጆቹም ቢሆኑ መልከ መልካምና ለብዙ ሰው አርኣያ የሆነ አባት እንደሆነ ይገልጻሉ።በዚህ ጉዞው ሁሉ ብዙ ነገሮች እንደተሳኩላቸውም ያነሳሉ።ግን ያሰበው ጥግ ላይ ሳይደርስ ጉልበቱ እንዲደክም፣ በተለያዩ ነገሮች እንዳይደግፈን ህመም የአልጋ ቁራኛ አደረገው ይላሉ።ይህም ቢሆን ግን ድጋፉ ሳይለየን አራት ወንድና ሁለት ሴት ልጆቹን አስተምሮ ለቁም ነገር አብቅቶናል።
ሞትን መጋፈጥ የሚቻለው አንድም አካል አይኖርምና ህመሙ በርትቶበት ነብሱን ወሰዳት።በዚህም ጥልቅ ኀዘን ውስጥ ጣለን።እናም ነብስ ይማር ከማለት ውጪ አማራጭ የለንምና ነብሱን በአጸደ ገነት ያኑርልን ሲሉ የመጨረሻ የስንብት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የዝግጅት ክፍልም ለቤተሰቡ ለወዳጅ ዘመድ እንዲሁም ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ተመኘን። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው