ጃርዲያ (Giardia) በዓይን የማይታይ ጥገኛ ተውሳክ ሲሆን የሚያስከትለው የተቅማጥ በሽታ ደግሞ ጃርዲያሲሰ ተብሎ ይጠራል። ይህ ተውሳክ በየቦታው ሊገኝ ይችላል። ማለትም በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች አይነ ምድር ወይም ሠገራ በተነካካ ቦታ አፈር ላይ፣ ምግብ፣ ውኃ ሊኖር ይችላል። ይህ ተውሳክ በተፈጥሮው ራሱን የሚከልልበት ሽፋን ስላለው ሳይጎዳ ለረጅም ጊዜ በአንድ ቦታ መቆየት ከመቻሉም በላይ ክሎሪንና ሌሎችም ማፅጃ ኬሚካሎችን የመቋቋም ችሎታ አለው።
ጃርዲያ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰት በሽታ ነው። በታዳጊ አገሮች ብዙ ሰዎችን የሚለክፍ ሲሆን በልጆች ላይ ደግሞ የልክፍቱ መጠን ከፍ ያለ ነው። በታዳጊ አገሮች ከጠቅላላው ሕዝብ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው በጃርዲያ በሽታ ተለክፎ ያውቃል ተብሎ የሚገመት ሲሆን በሽታው በታዳጊ አገሮች ብቻ ግን ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር ሰዎችን በማጥቃት ከሚታወቁ የአንጀት ጥገኛ ተውሳክ ጃርዲያ የመጀመሪያ ደረጃን እንደያዘ መዛግብቶች ያሳያሉ።
ሰዎች በጃርዲያ የሚለከፉት በተበከለ ውኃና ምግብ ውስጥ የሚገኘውን በራሱ ሽፋን ውስጥ የተደበቀውን ተውሳክ በሚውጡበት ጊዜ ነው። ይህ ተውሳክ በማይክሮስኮፕ ካልሆነ በስተቀር በዓይን በቀጥታ ሊታይ አይችልም። የሚገርመው ነገር ደግሞ በዚህ በሽታ ለመለከፍ ከአስር ያልበለጡ በሽፋን ውስጥ ያሉ ተውሳኮች በአፍ በኩል መግባት በቂ መሆኑ ነው። በበሽታው የተለከፈ ሰው ደግሞ በዓይነ ምድር አማካኝነት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተውሳኮችን ሊፀዳዳ እንደሚችል ሁኔታውም ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ማወቅ ያስፈልጋል። እንግዲህ ተውሳኩ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከእንስሳት ወደ ሰው እንደሚተላለፍም ይታወቃል።
የበሽታው ስሜቶችና ምልክቶች
በተውሳኩ ከተለከፍን በኋላ ስሜቶችና ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት ከአንድ እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ማንኛውም ሰው በጃርዲያ መለክፍ የሚችል ሲሆን በተለይ በዚህ ተውሳክ ለመለከፍ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የሚከተሉት ናቸው።፡
1. ጃርዲያ በብዛት ወደሚገኝባቸው የዓለም ክፍሎች የሚጓዙ መንገደኞች፣
2. መዋዕለ ሕፃናት ቅጥር ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች፣
3. በጃርዲያ ከተከለፈ ሰው ጋራ በቅርበት ወይም አብረው የሚኖሩ ሰዎች፣
4. በጃርዲያ የተለከፈን ውኃ የሚጠጡ ሰዎች፣
5. ካምፕና ጫካ መውጣት የሚወዱ ሰዎች ከወንዝ ወይም ከኩሬ ወይም ከሀይቅ ውኃ የሚጠጡ ሰዎች፣
6. በበሽታው ከተለከፉ እንስሳት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ናቸው።
ከድመትና ከውሾች ወደ ሰው የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ የሚባል ነው፤ ምክንያቱም ድመትና ውሾችን የሚያጠቃው የጃርዲያ ዝርያ የተለየ በመሆኑ ነው። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በተውሳኩ ቢለከፉም የበሽታውን ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። አብዛኞች ሰዎች ግን እንደተለከፉ በትኩሱ የሚያሳይዋቸው ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።
• ተቅማጥ፣
• ጋዝ (ሆድ መጮህና በአየር መሞላትና ማስተንፈስ)፣
• ቅባትነት ያለው ሠገራ ማለትም በመፀዳጃው ገንዳ ውስጥ የመንሳፈፍ ሁኔታ የሚያሳይ ሰገራ፣
• ከፍተኛ የሆድ ቁርጠት፣
• የአንጀት መታወክ ማለትም እንደማቅለሽለሽና ማስታወክ ያሉ ስሜቶች፣
• በተቅማጡ ምክንያት የሰውነት ድርቀት መከሰት ናቸው።
ሌሎች መጠነኛ ምልክቶች ደግሞ ቆዳ ላይ ሽፍ ማለትና ማሳከክ፣ በዓይን አካባቢ እብጠት መፈጠርና የመገጣጠሚያዎች እብጠትን ይጨምራል። አንዳንድ ጊዜ የበሽታው ስሜቶችና ምልክቶች ረገብ ያሉ ይመስላሉ ሆኖም ከሳምንታት በኋላ ተመልሶ የመምጣት ሁኔታ ያሳያሉ። ይህ በሽታ በተቅማጡ ምክንያት የክብደት መቀነስ ከዚህም ተያይዞ አንጀት ጠቃሚ የምግብ ክፍሎች እንደ ቫይታሚን ኤ እና ቢ12፤ ጮማና ላክቶስ ወደሰውነት እንዳይገቡ ያደርጋል። በልጆች ደግሞ ይህ በሽታ ሲከፋ የሰውነትና የአእምሮ እድገት መግታትን ያስከትላል።
ምርመራ
ሐኪሞች በሽታው በብዛት ባለበት አካባቢ በሽተኞች በሚነግሯቸው ምልክቶችና ስሜቶች በመነሳት በሽተኛው በጃርዲያ መለከፉን መጠርጠር ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን የሠገራ ምርመራ በማድረግ በዓይነምድር ውስጥ ተውሳኩን በማየት ወይም በማግኘት ሲሆን በተጠናከረ መንገድ ተውሳኩን ለማየት በተለያዩ ቀናት ዓይነምድርን መመርመር ይረዳል። ይህም በሽተኞች አንዳንድ ጊዜ ተውሳኩን በዓይነምድራቸው አልፎ አልፎ ስለሚያስወጡ ነው። ተውሳኩን በማይክሮስኮፕ ከማየት የተሻለ መንገድ ደግሞ ዓይነምድሩ ላይ ኢሚዩኖአሴይ የተባሉ ምርመራዎችን ማድረግ ነው። በአደጉ አገሮች ከዚህ በተጨማሪ በደም በኩል የሚደረግ ምርመራም አለ።
ሕክምና
የተለያዩ መድኃኒቶች ለዚህ በሽታ ይታዘዛሉ። ከነዚህም ውስጥ በአገር ቤት ስሙ ሚዝል ተብሎ የሚጠራው ሜትሮናይዳዞል ( metronidazole) ጨምሮ ቲኒዳዞል (tinidazole) ፤ ኒታዞክሳናይድ( nitazoxanide) ይገኙበታል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በሽታውን በደንብ የማከም ችሎታ አላቸው። ከነዚህ በተጨማሪ ፓሮሞማይሲን፤ ኩዊናክሪን እና ፉራዞሊዶን (paromomycin, quinacrine, and furazolidone) የተባሉ በተቀያሪነት አገልግሎት ላይ ይውላሉ። መድኃኒቶች እንደየሀገሩ ሁኔታ ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ። ለማንኛውም እነዚህ መድኃኒቶች ከሀኪም ጋር በመመካከር የሚታዘዙ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል።
በሽታውን መከላከል
እንግዲህ ወደ አፍ የሚገባ መጠጥና ምግብ በበሽታው ከተለከፉ ሰዎች በሚወጣው ዓይነምድር አማካኝነት መበከል የሚችል ስለሆነ በመፀዳጃ ቤቶች አካባቢ የሚኖር ንፅህና ከፍተኛ ሚና አለው። ከዚህ በተጨማሪ በግል ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር የግል ንፅሕናችንን በደንብ መጠበቅ፣ ያልተጣራን ውኃን አለመጠጣት፣በተውሳኩ ሊለከፉ የሚችሉ ምግቦች አለመመገብ፣ እጅን በሳሙና በደንብ አድርጎ ቢያንስ ለሃያ ሰከንዶች መታጠብ። ይህም ምግብ ከማዘጋጀት በፊትና ምግብ ከማቅረብ በፊት መሆን አለበት። ከመመገብዎ አስቀድሞ፣ የታመመን ሰው ከመንካትዎ በፊትና ከነኩ በኋላ፣ ከተፀዳዱ በኋላ፣ የተፀዳዳ ሕፃንን ከነኩ ወይም ልብስ ከቀየሩ በኋላ፣ የሚጣሉ ቆሻሻዎችን ከነኩ በኋላ ፅዳት መከተል አለበት። ልጆችዎንም ሆነ ሌሎች ልጆችን እንዲታጠቡ ማስተማርና ማገዝ አስፈላጊ ነው።
በአጠቃላይ እርስዎ ወይ ልጅዎ በበሽታው ከተለከፈ መዋኛ ቦታዎችን ኩሬና ወንዞች ውስጥ ከመዋኘት መቆጠብ ሌሎች እንዳይያዙ ይረዳል። የታመመ ልጅ ካለም እስከሚድን ድረስ ትምህርት ቤት እንዳይሄድ ማድረግ ተገቢ ነው። መዋኛ ቦታዎችና ኩሬ ወይም ወንዞች ከዋኙ ውኃውን ላለመጠጣት ይሞክሩ። ከላይ እንደተጠቀሰው በሽታው በብዛት ወደሚገኝባቸው ክፍለ ዓለማት ኢትዮጵያን ጨምሮ የሚጓዙ ከሆነ የሚጠጡትን ውኃ በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብዎታል። ሌሎች ጥንቃቄ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች ቢኖሩ በበሽታው የተለከፈ ሰው ወይም ሕፃን ዓይነምድር ያረፈባቸውን ዕቃዎች፣ መጫወቻዎችን ጨምሮ ጓንት በመልበስ በተገቢ ማጠቢያ ማጠብ ያስፈልጋል። ማንም ሰው መያዝ ስለሚችል ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ በግልዎ ማድረግ የሚገባዎትን የጥንቃቄ እርምጃዎች ማድረግ አይዘንጉ። ደጋግመን ማስታወስ የሚገባን ነገር ቢኖር ተላላፊ በሽታዎች የግለሰብ ችግር ብቻ አለመሆናቸውንና በአጭር ጊዜ ማኅበረሰብን ማዳረስ እንደሚችሉ ነው።
References: ሐኪም በሌለበት (በጠና አበረ)፣ www.goshhealth.org፣
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012